Thursday, June 1, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ከፍተኛ ገንዘብ እየተጠየቁ መሆናቸውን ተናገሩ

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚገቡ ስደተኞች ከፍተኛ ገንዘብ እየተጠየቁ መሆናቸውን ተናገሩ

ቀን:

  • የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የስደተኞች ቁጥር እየጨመረ ነው ብሏል

በሱዳን ብሔራዊ ጦርና በፈጥኖ ደራሽ ታጣቂዎች መካከል እየተካሄደ ባለው ጦርነት ሕይወታቸውን ከአደጋ ለማዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚሸሹ ስደተኞች በኢትዮጵያና ሱዳን አዋሳኝ ድንበር አካባቢ በሚገኙ ሕገወጥ ታጣቂዎች ከፍተኛ ገንዘብ እየተጠየቁ መሆኑን ለሪፖርተር ገለጹ፡፡

ከጦርነት ሸሽተው ከሱዳን 450 ኪሎ ሜትር ርቀት የሚገኘው አማራ ክልል ምዕራብ ጎንደር ዞን የገቡ ስደተኞች፣ ድንበር በሚገኙ በሕገወጥ ታጣቂዎች ከፍተኛ መጠን ያለው ገንዘብ እየተጠየቁ መሆኑን በስልክ አስረድተዋል፡፡

ምን ያህል ገንዘብ እንደተጠየቁ ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ ‹‹አሻጋሪዎች ነን›› በሚሉት ድንበር ላይ በማድፈጥ እስከ 200 ሺሕ ብር እንደሚጠይቋቸው፣ የተጠየቁትን ገንዘብ ካልሰጡ ወደ ኢትዮጵያ እንይሻገሩ እንደሚከለክሏቸው፣ የሚጠይቁትን ገንዘብ እንዲከፍሉ የተጠየቁና አቅም የሌላቸው በርካታ ስደተኞች ወደ ሱዳን ለመመለስ እየተገደዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ የሚመለከተው አካል ጉዳዩን ተከታትሎ በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲሰጣቸውም ጠይቀዋል፡፡

የስደተኞቹን ቅሬታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የምዕራብ ጎንደር ዞን የኮሙዩኒኬሽን መምርያ ኃላፊ አቶ ፋንታሁን ቢሆነኝ፣ ‹‹እስካሁን እንዲህ ዓይነት መረጃ አልደረሰንም፣ የተዘጋ መንገድም የለም፡፡ አለመዘጋቱን የሚያመለክተውም በየቀኑ እየጨመረ ያለው የሰዎች ፍልሰት ነው፡፡ በመንገድ ላይ እክል ቢኖር ወደ ዞኑ የሚገቡት የስደተኞች ቁጥር ይቀንስ ነበር፤›› ብለው፣ ‹‹ምናልባት ሁኔታውን እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም ያላግባብ ገንዘብ የሚጠይቁ አካላት አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡ እንዲህ ዓይነት ችግር የሚገጥማቸው ሰዎች ችግራቸውን ማሳወቅ ይችላሉ፤›› የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

ቤት ንብረታችንን ትተን ነፍሳችንን ለማዳን ለመሸሽ ተገደናል ያሉት ስደተኞቹ፣ ግጭት የሚሸሽ ሰው ገንዘቡን ትቶ ነው የሚመጣ በመሆኑ፣ በዚህ ሁኔታ በመቶ ሺዎች የሚቆጠር ገንዘብ የት ሊያገኝ ይችላል ሲሉ ጠይቀዋል፡፡ ድርጊቱ ለስደተኞች በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ነው ሲሉም አማረዋል፡፡

ከሱዳን የሚመጡ ስደተኞችን ለማስተባበር ከሚያዚያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የሎጂስቲክስ፣ የፀጥታ፣ የምግብና ምግብ ነክ ግብረ ኃይል ተቋቁሞ ሥራ እንደተጀመረ፣ በመተማ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች ከ10 በላይ የጤና ባለሙያዎች እንደተመደቡ፣ እስከ ሰኞ ሚያዚያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ 260 ስደተኞች የሕክምና አገልግሎት እንደተሰጠቸው፣ ነፍሰጡር ሆነው የተሰደዱ እናቶች በሕክምና እንደወለዱ፣ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ዘርፍ 433 ተሽከርካሪዎችን ለስደተኞች ማመላለሻ እንደመደበ አቶ ፋንታሁን ገልጸዋል፡፡ ለጋሽ ድርጅቶች ዕርዳታ እንዲያደርጉም ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል፡፡

ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ የሚመጡ የስደተኞች ቁጥር በየቀኑ እየጨመረ መሆኑን፣ እስካሁን ግን ክልሉ ከአቅሙ በላይ ስላልሆነበት ዕርዳታ እንዲደረግለት እንዳልጠየቀና ምን ያህል ስደተኞች እንደገቡ የሚያጣራ ኮሚቴ ተቋቁሞ ወደ መተማ መላኩን የብሔራዊ አደጋ ሥጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን የሕዝብ ግንኙነት ኃላፊ አታለል ፍረንስ ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

በጦርነቱ ሳቢያ ከሱዳን ወደ ኢትዮጵያ ምን ያህል ስደተኞች እንደተሰደዱ ከሪፖርተር ጥያቄ የቀረበላቸው የኮሙዩኒኬሽን መምርያ ኃላፊው፣ በግጭቱ ሳቢያ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሱዳን የሚገኙ የ67 አገር ዜጎች በድንበር በኩል ወደ ኢትዮጵያ መሰደዳቸውን እንዳላቆሙ፣ እስካሁን ከ17 ሺሕ በላይ ስደተኞች ምዕራብ ጎንደር ዞን እንደገቡ፣ ከእነዚህም መካከል 7044 የሚሆኑት ኢትዮጵያውያን፣ ቀሪዎቹ 10,437 የሌሎች 67 አገሮች ስደተኞች መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡

በሱዳን ብሔራዊ ጦርና ፈጥኖ ደራሽ ታጣቂ መካከል ሚያዚያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ግጭት እንደተቀሰቀሰ፣ በዚህም በመቶዎች የሚቀጠሩ ሰዎች እንደሞቱ፣ ኢትዮጵያውያንን ጨምሮ በሱዳን የሚኖሩ ከ67 በላይ አገር ዜጎች ግጭቱን ለመሸሽ እንደተገደዱ፣ በቤትና ንብረት ላይ ከፍተኛ ውድመት መድረሱ እየተገለጸ ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...