አርሶና አርብቶ አደሩን ከአስተማማኝ ገዥዎች ጋር በማገናኘትና ጠንካራ የገበያ ትስስር በመፍጠር፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን የጥሬ ዕቃ አቅርቦት ችግር በመቅረፍ ከውጭ የሚገቡ ምርቶችን በመተካት፣ ትልቅ ሚና ይጫወታል የተባለለት የግብርና ምርት አምራችና አስመራች ግንኙነትን ለመወሰን የወጣው የግብርና ምርት ውል (Contract Farming) አዋጅ በፓርላማ ፀደቀ፡፡
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ትናንትና ማክሰኞ ግንቦት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባ የፀደቀው ይህ አዋጅ፣ አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶና አርብቶ አደሮችን ከትልልቅ ገዥዎች ጋር እኩል የሆነ የመደራደር አቅም ይፈጥራቸዋል ተብሏል፡፡ በተጨማሪም ከዚህ ቀድሞ የነበረውን የተዘበራረቀ፣ ወጥነት የሌለውና ለአፈጻጸም አስቸጋሪ፣ እንዲሁም ላለመግባባት በር ሲከፍት የነበረውን አሠራር በማስቀረት፣ ራሱን የቻለ ግልጽ አሠራርን የሚዘረጋ የውል አዋጅ ስለመሆኑ ተብራርቷል፡፡
አርሶ አደሩና ፍላጎት ያላቸው የግብርና አቀነባባሪ ኩባንያዎች በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርተው እንዲተሳሰሩ ምቹ ሁኔታዎችን በመፍጠር፣ ባለሀብቱ ጥራትና ብዛት ያለው ምርት ለማግኘት አርሶና አርብቶ አደሩን ተጠቃሚ ሊያደርጉ የሚያስችሉ አሠራሮችን በቴክኖሎጂ፣ በሥልጠና፣ በግብዓት አቅርቦት በተቀላጠፈ ሁኔታ ተደራሽ የሚደርግበት አሠራር የሚዘረጋ መሆኑም ተገልጿል፡፡
በዚህም ግብርናው አገራዊ የምግብ ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆኑ የኤክስፖርት ምርቶችን በብዛትና በጥራት በማቅረብ፣ ለኢንዱስትሪው ዘርፍ ጥሬ ዕቃ በማቅረብና ለኢንዱስትሪ ምርቶች ገበያን በመፍጠር ቁልፍ ሚና እንዲጫወት የሚያደርግ መሆኑን አዋጁ ያስረዳል፡፡
በዚህ አዋጅ የግብርና ምርት ውል ዓይነቶች ሁለት መሆናቸው የተብራራ ሲሆን፣ የመጀመሪያው አስመራች ከአምራቹ ጋር የሚዋዋለው የልማትና ምርት ግብይት ውል ነው፡፡ በዚህ ውል አስመራቹ ለአምራቹ ተፈላጊውን ግብዓት የማቅረብና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት ግዴታ ይገባል፡፡ ሁለተኛው የምርት ተጠቃሚ ኢንዱስትሪዎች፣ አገልግሎት ሰጪዎችና ጅምላ ነጋዴዎች ከግብርና ምርት አምራቾች ጋር የሚያደርጉት የምርት ግብይት ውል ሲሆን፣ አስመራቹ ለአምራቹ ተፈላጊውን ግብዓት የማቅረብና የቴክኒክ ድጋፍ መስጠት በተዋዋይ ወገኖች ስምምነት ብቻ የሚወሰንበት መሆኑ በአዋጁ ተደንግጓል፡፡
ፓርላማው በተጨማሪ የዕፅዋት ዘር ለመደንገግ የወጣ አዋጅ በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡ አዋጁ በኢትዮጵያ የዕፅዋት ዘር ዘርፍ፣ የግብርና ምጣኔ ሀብት ዕድገትን፣ የምግብ፣ የሥነ ምግብና የመኖ፣ እንዲሁም የደን ውጤቶችን ዋስትና የሚያረጋግጥ፣ ዘላቂ የዕፅዋት ዘር ሥርዓት በመዘርጋት የዝርያና ዘር በብዛትና በጥራት ለአምራቾች እንዲቀርብ፣ ሥርዓተ ምኅዳር ላይ አስተዋጽኦ የሚያደረግ መሆኑ ተብራርቷል፡፡
በተጨማሪም የግልና የመንግሥትን የዕፅዋት ዘር ኩባንያዎች በማሳተፍና ዓለም አቀፋዊ ተወዳዳሪነትን በማረጋገጥ ለምርምር፣ ለቴክኖሎጂ ሽግግርና ሥርፀት፣ ለምርትና ምርታማነት ዕድገትና ለምርት ጥራት አስተዋጽኦ ያደርጋል ተብሏል፡፡