የሽግግር ፍትሕ ሒደቱ ጊዜ እንደሚያስፈልገው ቢያምኑም የተጠያቂነትና የፍትሕ ሒደቱ በትክክለኛ መንገድ እየሄደ መሆኑን፣ በኢትዮጵያ በኩልም ተጠያቂነትን ለማስፈን እውነተኛ የፖለቲካ ፈቃደኝነት መኖሩን ማየት እንደሚሹ በኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር አስታወቁ፡፡
የኅብረቱ የኢትዮጵያ ጽሕፈት ቤት ዋና ተወካይ ሮናልድ ኮቢያ (አምባሳደር) እንደገለጹት፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረውን ጦርነት አስመልክቶ የፌዴራል መንግሥትና የሕወሓት ተወካዮች ግጭት ለማቆም ባደረጉት ስምምነት መሠረት፣ ሦስተኛውና ዋናው የስምምነቱ አካል ተጠያቂነትና ፍትሕን የማስፈን ሒደቱ ከሌሎቹ የበለጠ ሰፋ ያለ ጊዜ ይወስዳል፡፡
‹‹ፍትሕና ተጠያቂነትን በጥቂት ቀናት ማስፈን አይቻልም፡፡ ፍትሕ የሚሰፍነውም በዚህ መንገድ አይደለም፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ፍትሕን ማስፈን እንዲሁም የሕግ ሥርዓቶች እንዲኖሩ ለማድረግ ጊዜ እንደሚያስፈልግና የአውሮፓ ኅብረትም ይህን እንደሚረዳ አስረድተዋል፡፡
በጦርነቱ ወቅት የአውሮፓ ኅብረትና የኢትዮጵያ ግንኙነት መንገጫገጭ ገጥሞት እንደነበረ፣ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ግንኙነቱን ለማሻሻል እየተሠራ መሆኑን አምባሳደሩ ገልጸዋል፡፡
አምባሳደሩ ይህንን የገለጹት የአውሮፓ ኅብረት ከተመሠረተ 72 ዓመታት መሆኑን በማስመልከት ስለኅብረቱ አመሠራረትና ከኢትዮጵያ ጋር ስላለው ከአራት አሠርት ዓመታት በላይ ስላስቆጠረው ግንኙነት፣ ሰኞ ሚያዝያ 30 ቀን 2015 ዓ.ም. አዲስ አበባ በሚገኘው የኅብረቱ ዋና መሥሪያ ቤት መግለጫ በሰጡበት ወቅት ነው፡፡
በኢትዮጵያ ሊጀመር በሒደት ላይ ያለው የሽግግር ፍትሕ ጊዜ እንደሚወስድ፣ ይህም ሒደት የተጀመረው ግንኙነት ለማሻሻል እንቅፋት እንደማይሆን ተናግረዋል፡፡
የፍትሕና የተጠያቂነት ሒደቱን በሚመለከት ሪፖርተር ላቀረበላቸው ጥያቄ ማብራሪያ የሰጡት አምባሳደሩ፣ ነገሮች ወደ ትክክለኛ አቅጣጫ እየሄዱ መሆናቸውን የሚያረጋግጥ አዝማሚያ ማየት እንደቻሉ ተናግረዋል፡፡ የሽግግር ፍትሕ ረቂቅ መዘጋጀቱንና አሁንም በምክክር ላይ መሆኑን፣ ኅብረቱም ገለጻ እየተደረገለት እንደሆነና በመልካም ሁኔታ እንደሚያዩት (አምባሳደር) ሮናልድ ተናግረዋል፡፡
‹‹የፍትሕ ሒደት ግልጽ ካልሆነ ፍትሕም አይባልም፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ ግልጽነትና ከአድልኦ የፀዳ የተጠያቂነት ፍትሕ ሒደት እንዲኖር እንደሚያስፈልግ፣ ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ብቻም ሳይሆን ለኢትዮጵያ ሕዝብም ግልጽ ሆኖ መካሄድ እንዳለበት አሳስበዋል፡፡
የትግራይ ክልል ጊዜያዊ አስተዳደር ኃላፊዎች ከዚህ በፊት በፍትሕ ሒደቱ ላይ የዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ መካተት እንዳለበት ፍላጎታቸው እንደሆነ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ፕሬዚዳንት አቶ ጌታቸው ረዳ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
ይህን በሚመለከት ሪፖርተር አስተያየታቸውን የጠየቃቸው የአውሮፓ ኅብረት አምባሳደር፣ የፍትሕ ሒደቱ እንዴት መሆን እንዳለበት መወሰን የኢትዮጵያ ኃላፊነት እንደሚሆንና ባለድርሻ አካላትም በራሳቸው ውሳኔ ፍትሕን በኢትዮጵያ መደገፍ እንዳለበት ገልጸዋል፡፡ ‹‹የእኛ ድጋፍ ሒደቱን ማጀብ ነው፣ የአንድ ጊዜ ድጋፍ አይደለም፤›› ሲሉ የተናገሩት ሮናልድ (አምባሳደር)፣ ‹‹ማንኛውም የውጭ አካል በሒደቱ መካተትን ሲፈልግ ከኢትዮጵያ ጋር ተስማምቶ ነው መሆን ያለበት፤›› ብለዋል፡፡
በአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪነት የተካሄደውን የሰላም ድርድር በሚመለከት የአውሮፓ ኅብረት ለማገዝ ዝግጁ ቢሆንም ባለመጋበዙ እንዳልተሳተፈ ገልጸዋል፡፡ ‹‹ኢትዮጵያ የአውሮፓ ኅብረት የሰላም ድርድሩ አካል እንዲሆን ጋብዛ ቢሆን ኖሮ አካል እንሆን ነበር፤›› ያሉት አምባሳደሩ፣ የአውሮፓ ኅብረት በድርድር ውስጥ ባይገኝም ተደራዳሪዎቹ ለድርድር እንዲቀመጡ ድጋፍ ማድረጉን ገልጸዋል፡፡