የኢትዮጵያ ቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በ90 ሚሊዮን ብር በጀት አንድም ዓለም አቀፍ ቅርሶችን መጠገን እንደማይቻል አስታወቀ፡፡
ባለሥልጣኑ ይህንን ያስታወቀው ሚያዝያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የንግድና ቱሪዝም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ግምገማ ባካሄደበት ወቅት ነው፡፡
ቋሚ ኮሚቴው በዘጠኝ ወራት በቀረበው ሪፖርት አነስተኛ አፈጻጸም የነበረው ‹‹የቅርስ ጥገና›› መሆኑን በመግለጽ፣ በዓለም ቅርስነት የተመዘገቡ ቅርሶች ተገቢው ጥገና ተደርጎላቸው ለቱሪስት ክፍት መደረግ አለባቸው ብሏል፡፡
በዚህም ጅማ አባጅፋር፣ ጎንደርና ሌሎችም ቅርሶች በታሰበላቸው የጊዜ ገደብ ጥገናቸው አለመከናወኑን ቋሚ ኮሚቴው በመግለጽ፣ አደጋ የተጋረጠባቸው ቅርሶች መኖራቸውም ተገልጿል፡፡
የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አበባው አያሌው (ረዳት ፕሮፌሰር)፣ ባለሥልጣኑ በተመደበለት 90 ሚሊዮን ብር በጀት አንድ ቅርስን መጠገን አይችልም ብለዋል፡፡
የቅርስ ጥገና ከፍተኛ ወጪ የሚጠይቅ መሆኑን ቋሚ ኮሚቴው መገንዘብ እንዳለበት ጠቁመው፣ ተገቢውን በጀት ለጥገና ብቻ ማግኘት እንደሚያስፈልግ ዋና ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
መንግሥት የቅርስ ጥገና ከፍተኛ ገንዘብ የሚያስወጣ መሆኑን መገንዘቡ ጥሩ ጅማሮ ቢሆንም፣ አሁን ካለው የጥገና ፍላጎት አንፃር በጀቱ ትንሽ ነው ሲሉ አክለዋል፡፡
ከበጀት በተጨማሪ ሌሎች ችግሮች መኖራቸውን የጠቆሙት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለይ ከእምነት ተቋማት ጋር የሚያያዙ ቅርሶች ላይ ፍላጎት ያላቸው ቡድኖች በመኖራቸው ችግሮቹ አስቸጋሪ ሆነዋል ብለዋል፡፡
ችግሮቹ ማኅበረሰቡንና ፍላጎት ያላቸውን ቡድኖች አሳምኖ ወደ ሥራ ለመግባት ጊዜ የሚወስዱ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡ በዓለም አቀፍ ቅርስነት የተመዘገቡ በተለይ ጎንደር የሚገኙ ቅርሶችን ጨምሮ በ1972 ዓ.ም. በወርልድ ሞንመንት ፈንድ አማካይነት ጥገና እንደተደረገላቸው አስታውሰዋል፡፡ በወቅቱ ጥገና የተደረገላቸው ዘጠኝ ያህል ዓለም አቀፍ ቅርሶች መሆናቸውን ተናግረው፣ ከዚያ ወዲህ ወጥ የሆነ ተገቢ ጥገና እንዳልተደረገላቸው አስረድተዋል፡፡
ይሁን እንጂ ባለሥልጣኑና ቱሪዝም ሚኒስቴር ቅርሶች ለመጠገን በቂ ጥናትና የማልማት ሥራ ማከናወን እንደሚገባ መተማመን ላይ በመድረሳቸው፣ የጎንደር ቅርሶችን ጥገና በተመለከተ አምና ሰፊ ጥናት መደረጉን ገልጸዋል፡፡
ወቅቱ የጦርነት በመሆኑ መንግሥት ተገቢውን በጀት አለመያዙን ገልጸው፣ ለአራት ዓመታት የሚተገበር ፕሮግራም መሰናዳቱን ተናግረዋል፡፡
ዓለም አቀፍ ቅርሶችን በተመለከተ ባለሥልጣኑ ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን በመግለጽ፣ ጥገና በሚያስፈልጋቸው ቦታዎች ጽሕፈት ቤት ተከፍቶ ክትትል እየተደረገ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
በተለይ የበጀት አጠቃቀምን በተመለከተ ከቋሚ ኮሚቴው ለተነሳው ጥያቄ ምላሽ የሰጡት ዋና ዳይሬክተሩ፣ በተለያዩ ምክንያቶች በጀት ጥቅም ላይ ላይውል እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ለቅርስ ጥናት የሚያስፈልገውን በጀት በተመለከተ ከገንዘብ ሚኒስቴር ጋር ያለው ጉዳይ የተሰጠውን (የተለቀቀውን) በጀት ሥራ ላይ ሳታውሉ፣ ለምን ከፍ ያለ በጀት ትጠይቃላችሁ የሚል መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ለቅርስ ጥገና የሚያስፈልገው በጀት ከፍተኛ መሆኑንና የቅርስ ጥገና የሚያከናውኑ ተቋራጮች በበቂ ሁኔታ አለመኖርም እንቅፋት መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ባለሥልጣኑ በእነዚህ ሁሉ ችግሮች ውስጥ እንኳን ሆኖ፣ አሁንም ቅርሶች ይዞታቸውን ሳይለቁ ዕድሳት ለማድረግ እየሠራ መሆኑን አስረድተዋል፡፡