- የኬንያው ኤልዶሬት ማራቶን ተሳታፊዎች ተጋብዘዋል
የበርካታ አትሌቶች መፍለቂያ በሆነችው በቆጂ ከተማ ሁለተኛው ታላቁ ሩጫ እሑድ ግንቦት 6 ቀን 2015 ዓ.ም. እንደሚከናወን ታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ አስታውቀ፡፡ የቱሪዝም ሚኒስቴር ከታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ጋር በመተባበር ‹‹ልወቅሽ ኢትዮጵያ›› በሚል መሪ ቃል ውድድሩ እንደሚከናወን ለሁለት ቀናት ከሌሎች ዝግጅቶች ጋር በከተማዋ እንደሚሰናዳ ተገልጿል፡፡
ከተማዋ ከምትታወቅበት አትሌቲክስ ባሻገር፣የቱሪስት መዳረሻ ከተማ እንድትሆን ከሩጫ ውድድሩ ጎን ለጎን በበቆጂ ሰንሰለታማ ተራሮች ላይ የእግርና የብስክሌት ጉዞ እንደሚደረግ ተገልጻል፡፡ አገሪቱ ከምትታወቅባቸው መልካም ዕድሎች መካከል አትሌቲክስን አንደኛው ሲሆን፣ ይህም የስፖርት ቱሪዝም ለማስፋፋት መልካም ዕድል እንደሆነና ዝግጅቱን አገር አቀፍ ለማድረግ በቆጂን ማዕከል ያደረገ ውድድር እንደሆነ ተብራርቷል፡፡
በከተማዋ በርካታ የውጭ ቱሪስቶች አማካይነት የምትጎበኝ በመሆኗ ከስፖርቱ ቱሪዝም ባሻገር ከአስጎብኚ ድርጅቶች ጋር ለመሥራት የሚያስችል አጋጣሚን ይፈጥራል ተብሏል፡፡በቆጂ በቂና የተሟላ መሠረተ ልማት የሌላት መሆኗ የዞን ውድድሮችን እንኳን ሳታስተናግድ መቆየቷ ተነስቷል፡፡
በአርሲ ዞን ከምትገኘው በቆጂ፣ ካፈራቻቸው አትሌቶች መካከል ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለና ጥሩነሽ ዲባባን ይገኙበታል።
በመርሐ ግብሩ እንደተገለጸው፣ በጥሩነሽ ዲባባ የተሰየመ ዕድሜያቸው ከ15 ዓመት በታች በሆኑ ታዳጊ አትሌቶች መካከል ውድድር ይደረጋል።
በታዋቂ አትሌቶች፣የበቆጂና አካባቢው ኗሪዎችና ከአዲስ አበባ የሚጓዙ የጤና ሯጮችን ጨምሮ 1,200 ተካፋዮች በዘንድሮ ውድድር እንደሚሳተፉ ታውቋል፡፡
በተጨማሪ በዓለም አቀፍ ደረጃ ውጤት እያስመዘገቡ ያሉ የረዥም ርቀት አሸናፊዎችን በማፍራት የሚታወቀው የኬንያዊ ኤልዳሬት ከተማ ኤልዶሬት ሲቲ ማራቶን፣ የ2015 ዓ.ም. ኢትዮ ቴሌኮም ታላቁ ሩጫ በበቆጂ አሸናፊ የሚሆኑ አትሌቶች በሚቀጥለው ዙር በኤልዶሬት ከተማ ተገኝተው የውድድሩ ተጋባዥ እንደሚሆኑ አዘጋጁ አስታውቋል፡፡
‹‹ይህ ዕድል በተለይ ለታዳጊ አትሌቶች የተሻለ ልምድ እንዲቀስሙ ከመርዳቱም በላይ ለዓለም አቀፍ የውድድር መድረኮች የመወዳደር ልምድ እንዲያካብቱ ይረዳል።የሁለቱን ከተሞች እህትማማችነትን በማጠናከር የቱሪዝም ፍሰትን እንደሚጨምር ይጠበቃል፤›› በማለት የታላቁ ሩጫ በኢትዮጵያ ሥራ አስፈጻሚ ዳግማዊት አማረ ገልጻለች፡፡