በአበበ ፍቅር
በወርኃ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. የፋሺስት ጣሊያን ኃይሎች አዲስ አበባ ደረሱ፡፡ በዚህም ወቅት ሁለት ነገሮች አሳሳቢ ሆነው ከፊታቸው ወገግ አሉ፡፡ ቀዳሚው ‹‹ጣሊያን በኢትዮጵያ ላይ ልትዘረጋ ያሰበችው አስተዳደር የክልል መንግሥት እንዳይሆን ምን እናድርግ›› የሚለው ሲሆን ጁሴፔ ፈብሪካ የተባለ የፋሺስት ፓርቲ አባል ሮም ውስጥ የሚታተም ‹‹ኢትዮፔያ›› በተሰኘ ጋዜጣ ላይ ያወጣው ጽሑፍ የሞሶሎኒ ሥርዓት ምን ያስብ እንደነበር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡
‹‹እኝህ ጥቁሮች ከእኛ ጋር የሥራ ግንኙነት በሚያደርጉበት ጊዜ ህሊና የሌላቸው በመሆናቸው ከእኛ ሰው ጋር እኩል የሆኑ ይመስላቸዋል፡፡ እንዲህ ያለው ግንኙነት ከቀጠለ አገራችን በበሽታ (በጀርም) መበከሏ አይቀርም፡፡ የነጮች ቢሮ ከጥቁሮች ቢሮ በጣም የራቀ መሆን አለበት፡፡ ጥቁሮች ለነጮች ፋይሎችን በሚያቀርቡበት ጊዜም እጃቸው ፋይሉን እንዳይነካው በሌላ ንፁህ ወረቀት መያዝ አለባቸው፡፡››
የፋሺስት ኃይሎች ለወታደሮቻቸው ከኢትዮጵያውያን ጋር መገናኘት መርከስ እንደሆነ ቢለፍፉም ሮም ግን ተወዳጅ በነበረው ‹‹ፋቼታ ኔራ›› ሙዚቃ ከመደነሷ አልቦዘነችም ነበር፡፡
‹‹ፋቼታ ኔራ በጦርነቱ ወቅት የወጣ የፍቅር ዜማ ነው፡፡ ትርጉሙም አንድ የጣሊያን ወታደር በአካል የሚያውቀውን ውብ የሐባሻ ሴት መናፈቁን ይገልጻል፡፡ ስጦታ ይዤ መጣሁልሽ ይላታል፡፡››
አንቺ ጥቁር ፊት
የሐበሻ ውበት
ጠብቂኝ በጉጉት
ደርሷል ያ ሰዓት
ስቀርብ ስጠጋሽ
አለ የምሰጥሽ
ይህ ዜማ ወታደሩ በሰሜንና በምሥራቅ ወደ አዲስ አበባ ሲገፋ በሠራዊቱ ውስጥ የተለመደ የድል ዜማ ፋሺስት የአገሪቱን መዲና በተቆጣጠረ በ15 ቀናት ውስጥ ግን በአዋጅ ታገደ፡፡ ፋቼታ ኔራ ብቻ ሳይሆን በሮም ሱቆች ውስጥ የተሰቀሉ ወጣቱን ያነሳሳሉ የተባሉ የሐበሻ ሴቶች ውብ ምሥሎችም እንዲወርዱ ተደረገ፡፡
የሞሶሎኒ ሥርዓት እንዲሁም ሆኖ የቅኝ ግዛት አስተዳደሩ የክልስ መንግሥት ይሆንብኛል የሚለው ሥጋቱ አልነበረም፡፡ በመሆኑም አዲስ አበባና ሮም ላይ ሙዚቃን ከማገድ ባለፈ ተጨማሪ ሕጎችን አወጣ፡፡
ማንኛውም ካለ መንግሥት ፈቃድ ወደ ጥቁሮች መንደር እንዳይገባ ከለከለ፡፡ ገብቶ የተገኘ እስከ አንድ ዓመት እስር እንደሚጠብቀው አወጀ፡፡
የፋሺስት ኃይሎች አዲስ አበባ ላይ የተደላደሉ መስሏቸው ክልስ መንግሥት እንዳይፈጠር ሲሰጉ፣ የአገሬው አርበኛ ግን በዱር በገደሉ መፋለሙን አላቆመም፡፡ ሞሶሎኒም ኢትዮጵያውያን የነጮችን የበላይነት እንዲቀበሉ የማድረጉ እንቅስቃሴ ገፋበት፡፡
የአገሬው ሰው ለሥርዓቴ እንዳይገዙልኝ ያደርጋሉ ብሎ ያመነበትን ሁሉ ከማስወገድ የማይቦዝነው የፋሺስት ሥርዓት አዝማሪዎች ዋነኛ ትኩረቱ ነበሩ፡፡ በዚህም ፋሺስት በወረራ በነበረባቸው አምስት ዓመታት መሰንቆ እንደ ጦር መሣሪያ ተቆጥሮ ማንገት ተከልክሎ ነበር፡፡ ይሁን እንጂ አዝማሪው የአገሩን ነገር በፍርሃት ችላ አላለውም፡፡ እንዲያውም በአማርኛ ሙዚቃ ታሪክ ውስጥ ከግጥም መልዕክት አንፃር ቅኔያዊ ጠባይ ጎልቶ ይስተዋል መጀመሩን ታሪክን መርማሪዎች በማስረጃ አስደግፈው ያብራራሉ፡፡
ጠመንጃና ሙዚቃ
ለመሆኑ ‹‹ጠመንጃና ሙዚቃ››ን ምን አገናኛቸው የሚለውን ሐሳብ ለመዳሰስ፣ ‹‹የጦር አምላክ ያውቃል›› የሚለው ብሒል፣ አገር አለኝታዬ የምትለውና ዋነኛው ነገር ጥይት እንደሆነ አመላካች ነው፡፡
‹‹የአገሬ ህልውና ያለው ታሪክና ጥይት ውስጥ ነው›› ይላል ደራሲ አዳም ረታ፣ ይህ በጦርነት ጉሰማ ውስጥ የኖረ ታሪክ በሌሎች የሕይወት ሰበዞች ጭምር የታጀበ ነው፡፡
ሙዚቃ ደግሞ በእነዚህ ታሪኮች ውስጥ የስሜት አድማስ የሕይወት ጣዕም ሆኖ፣ ዘመን ስትሞሸር ብትኖርም በውል የመረመሯትና ያስታወሷት ጥቂቶች ናቸው፡፡
‹‹ያሸለቡ ታሪኮች መቀስቀሻ ድርሰት ነው›› የተባለለት ‹‹ጠመንጃና ሙዚቃ›› የተሰኘው መጽሐፍ በይነገር ጌታቸው ተሰንዶ ለአንባብያን ቀርቧል፡፡ አምሮቴ በፖለቲካ የታጠረውን የአገሬው ትዝታ በማኅረበሰብ፣ በባህልና በታሪክ ውስጥ መተረክ ነው፤›› የሚለው ጸሐፊው በዚህ ደግሞ ሙዚቃ ታሪክና ፖለቲካ ድንበራቸው ፈርሶ ዘፈን ከፓርቲ የላቀ ርዕዮት ያረግዛል፡፡ ዘፋኝም ፖለቲካን ሙጥኝ ይላል ሙዚቃም ማሳሰቢያ መንገድ ሆኖ አገር ይቀኛል፡፡
‹‹ጠመንጃና ሙዚቃ›› የኢትዮጵያን የወርቃማ ዘመን ሙዚቃዎች በጥናት ከመተንተኑም ባሻገር፣ የዘመን ምልክት የሆኑ ከ40 በላይ የሙዚቃ ባለሙያዎች ሥራዎችና የሕይወት ጉዞ ይተነትናል፡፡ አንድ ሺሕ የሚጠጉ መረጃዎችንም አካቷል፡፡
መጽሐፉ በፖለቲካ የተሸመነ፣ በደም የቀለመና በአርነት የፈካ የኢትዮጵያውያን የሙዚቃ ሰዎች ድርሳን ነው፡፡ እዚህ ውስጥ ጊዜ ሥልጣን አለው፡፡ የአገር መውደቅ መነሳት፣ የሕዝብ መራብ መጠማት፣ ዘመንን እየመሰለ ይግተለተላል፡፡ ባህልና ጥበብም ወቅትን ተከናንቦ ያልፋል፡፡ የአገሬውን ሙዚቃ ዋና ሚና ዘመኑ ምን ያሰበ እንደነበር ወገግ አድርጎ ማሳየቱ ነው ሲል በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ያትታል፡፡
‹‹አንጋች ቀዳሽ፣ አሊያም አራሽ›› የሆነው የትናንቱ ማኅበረሰብ የወል ግዛቱ ይኼ ግዛቱ ነው፡፡ እንዲህ ያለው ሰምና ወርቅ ደግሞ ‹‹ጠመንጃና ሙዚቃ›› እስከ ማጎራበት ይደርሳል ሲል በስፋት ያብራራል፡፡
‹‹የኢትዮጵያ ሙዚቃ የሚዘወረው በአንጋቹ ወይም በጠመንጃ ነው፡፡ ነፍጥ ነፃነትን ይሰጣል፣ አሊያም ይነፍጋል፤›› የሚለው ጽሐፊው፣ የኢትዮጵያ የሦስት ሺሕ ዓመት ታሪክ የአልደፈር ባይነት ጉዞ ያለ ሙዚቃ ማሰብ አዳጋች ነው ይላል፡፡
የማኅበረሰቡ የወል ማንነት በወጉ ከተቃኘ ደግሞ የኪን አዕማድ ሆኖ ብቅ ይላል ሲል በመጽሐፉ መግቢያ ላይ ተቀምጧል፡፡
‹‹ጠመንጃና ሙዚቃ›› አንድም የኢትዮጵያን ታሪክ በሙዚቃ ውስጥ ለመቃኘት የሚሞክር ድርሳን ሲሆን፣ በሌላ በኩል ከአርባ በላይ የሙዚቃ ሰዎችና የሕይወት ታሪክ የተሰነደበት መጽሐፍ ነው፡፡
በውጭው ዓለም የተለመደው ነገር ግን በእኛ በኩል ወደኋላ የቀረው የሙዚቃዎች የመረጃ ክፍተትን ለመሙላት ከ700 በላይ ዜማዎች በማን ተቀነቀኑ? እንዲሁም በማን ተቀናበሩ? ግጥምና ዜማቸውስ በማን ተጻፈ? የሚሉትን ጥያቄዎች በወጉና በመረጃ ተደግፈው እንዲመልሱ ለማድረግ ሞክሯል፡፡
‹‹ለቅዱስ ያሬድ ይህ ዓለም በመላ አንድ ትልቅ ማኅሌት ነው›› በማለት የሚጀምረው መጽሐፍ፣ በኢትዮጵያ ሙዚቃ ውስጥ ሰፊ ሥፍራን ስለሚይዘው አዝማሪ በስፋት ይዳስሳል፡፡ ‹‹አዝማሪ ወፖለቲካ›› በማለት በተለይ ደግሞ በንጉሡ ዘመን አዝማሪዎች የነበራቸውን የፖለቲካ ተሳትፎ ይጠቅሳል፡፡
ለዓድዋ ድል መገኘት ጠመንጃ አንግተው ከተፋለሙት ባልተናነሰ ሁኔታ፣ አዝማሪዎች ታላቅ አበርክቶት አድርገዋል፡፡ በዳግም የጣሊያን ወረራም (1928 – 1933) ቢሆን ኪነ ጥበብን ተጠቅመው ከአርበኞች ጋር በዱር በገደል ተሠልፈው ኢትዮጵያን ለድል ማብቃታቸውን በስፋት ያሳያል፡፡
በያኔው የሀገር ፍቅር ማኅበር ሥር ተሰባስበው አሻራቸውን ላስቀመጡና አሁን ላለው ትውልድ አርዓያ የሆኑ ዘፋኞች ትውልድና ዕድገታቸውን እንዲሁም ሥራዎቻቸውን የሰነደው መጽሐፉ ተፈራ ካሳ፣ ብዙነሽ በቀለ፣ ተዘራ ኃይለ ሚካኤል፣ ጥላሁን ገሠሠ፣ መሐሙድ አህመድ፣ አሰፋ አባተ፣ እሳቱ ተሰማና የሌሎች በርካታ ዘፋኞች በክብር ዘበኛ ኦርኬስትራ ከ1960 እስከ 1965 ዓ.ም. ያቀረቡትን ሙዚቃ እንዲሁም የግጥምና የዜማ ደራሲዎችን ስም ዝርዝር አሳይቷል፡፡
መጽሐፉ በሕይወት ስላሉና እንዲሁም በሕይወት ስለሌሉ አርበኞችና ዘፋኞች ከውልደት እስከ ሞት በተለይ ደግሞ አሁን ላይ ለተደረሰበት የሙዚቃ ኢንዱስትሪ የያኔዎቹ እንጋፋዎች ምን ያህል አስተዋጽኦ እንዳደረጉና ከሔደና ከመጣው አገዛዝ ጋር ያደረጉትን እልህ አስጨራሽ ትግል ይዳስሳል፡፡