Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊበሕክምና ስሕተት ምክንያት በስቃይ የምትኖር ነፍስ

በሕክምና ስሕተት ምክንያት በስቃይ የምትኖር ነፍስ

ቀን:

ግርማ ሞገስ ያለው የወጣትነት ፎቷቸው በቤታቸው ግድግዳ ላይ ተሰቅሏል፡፡ በሰዎች ዕጦት ቤቱ ጭር ቢልም የተሰቀለው ፎቶ ከበራፍ ጀምሮ ሰውን ይጋብዛል፡፡

በሕክምና ስሕተት ምክንያት ካቲተር (የመሽኛ ትቦ) ያልተለያቸው አባት ዕንባ ልብን ይሰብራል፡፡ ጤናማ ሳሉ ለሥራቸው ትጉ በጎረቤቶቻቸው ምሥጉን እንደነበሩ፣ በአሁኑ  ወቅት ከስቃያቸው ጋር ብቻቸውን የሚቆዝሙ ሆነዋል፡፡

በዕንባ የተሞሉ ዓይኖቻቸውን እያበሱ ከስቃያቸው ብዛት ‹‹ከዚህስ ሞት ይሻለኛል›› እንዲሉ አድርጓቸዋል፡፡ ነፍሳቸው በፈጣሪ እጅ ሆና ስቃይና ፍዳቸውን ዕለት ዕለት ሳይወዱ በግዳቸው ያደምጣሉ፣ አብረውት ይኖራሉ፡፡ አሁንማ ሕመሙ አገርሽቶባቸው ለኢንፌክሽን የተጋለጡት እኚህ አባት የመንግሥትና የማኅበረሰቡን ጆሮ ይሻሉ፡፡ ፍትሕን የተጠሙት እኚህ አባት ስቃያቸውን የሚጋራላቸው፣ ማረፊያ ያጡ አካላቸውን የሚጠግንላቸውን፣ ከዕንባ ያልተለየ ዓይናቸው የሚያብስላቸው ለማግኘት ይናፍቃሉ፡፡

የዚህ ሁሉ መከራ ገፈት ቀማሽ የሆኑት የ75 ዓመት አረጋዊና በሕክምና ስሕተት ምክንያት ስቃይ ውስጥ የሚገኙት አቶ ብርሃኔ በላይ ናቸው፡፡

ሕመሙ ከአቅማቸው በላይ በመሆኑ እንደ እኩዮቻቸው መዝናናት፣ ማኅበራዊ ሕይወትና ሌሎች ተግባራትን ከማከናወን ታቅበዋል፡፡ የዕድሜ እኩዮቻቸው ለቤተሰቦቻቸውና ለማኅበራዊ ሕይወታቸው ታች ላይ ሲሉ አቶ ብርሃኔ ግን ሕመማቸውና ስቃያቸው ከዚህ አግቷቸዋል፡፡

አቶ ብርሃኔ ስለተፈጸመባቸው በደል እንዲህ ያስረዳሉ፡፡ በ2012 ዓ.ም. መስከረም ወር ላይ አልፎ አልፎ የሸንት መቆራረጥ ችግር አጋጥሟቸው ሕክምና ለማግኘት ወደ ቅዱስ ጴጥሮስ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል አቅንተዋል፡፡ የሽንት መቆራረጥ የፈጠረባቸው ፕሮስቴት የተባለ ዕጢ በቀዶ ሕክምና መልክ የሚወጣ በመሆኑ አልጋ ይዘው ሕክምና ለማድረግ መገደዳቸውን ተናግረዋል፡፡ በወቅቱ የቀዶ ሕክምና ያደረገላቸው የሕክምና ባለሙያ ‹‹በተገቢውና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ስላልሠራቸው፣ ለከፋ ችግር መጋለጣቸውን›› በሐዘኔታ ያስረዳሉ፡፡ ስቃያቸው በዚሁ ያላበቃው አቶ ብርሃኔ ለአምስት ጊዜያት በተደጋጋሚ ቀዶ ሕክምና ማድረጋቸውን አስታውሰዋል፡፡  

በሆስፒታሉ ቀዶ ሕክምና ያደረጉላቸው ዳዊት ሰዓረ (ዶ/ር) ናቸው፡፡ ዳዊት (ዶ/ር) በተደጋጋሚ ያደረጉት የቀዶ ሕክምና ችግሩ ሥር የሰደደ በመሆኑ የተሻለ ሕክምና ማግኘት እንዳለባቸው በመግለጽ፣ ሜክሲኮ ሜቴክ አጠገብ በሚገኘው ሸበሌ መለስተኛ ቀዶ ሕክምና ክሊኒክ እንዲታከሙ እንደመከሯቸው አስታውሰዋል፡፡ በክሊኒኩ ትንሽ ነገር ያስተካክሉልሃል የተባሉት አቶ ብርሃኔ፣ ከዚህ ቀደም በሐኪሙ የተሠራው ሰርጀሪ ምክንያት ጠቅላላ የሽንት መተላለፊያ ቱቦ መዘጋቱ እንደተነገራቸው ይናገራሉ፡፡

ከዚህ በኋላ ዓለም የተደፋባቸውና ሕይወታቸው እንዳልነበረ የሆነባቸው አቶ ብርሃኔ፣ በቂ ሕክምና ሳያገኙ ዓመቱን ሙሉ መንከራተታቸውን በዕንባ በታጀበ ድምፃቸው ተናግረዋል፡፡ በብሩክ የግል ሆስፒታል የራጅ ምርመራ ማድረጋቸውን አስታውሰው፣ ዝርዝር የምርመራ ውጤቱን ካዩ በኋላ ወደ ጥቁር አንበሳ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል መሄድ እንዳለባቸው እንደተነገራቸው ይገልጻሉ፡፡

በቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል ቀዶ ሕክምና ካደረጉላቸው ሐኪም የሪፈራል ወረቀት በማጻፍ ወደ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ያመሩት አቶ ብርሃኔ፣ ‹‹ቀዶ ሕክምና ያደረጉት ፊኛቸው አካባቢ የተረሳ መርፌ እንዳለ፣ የሽንት ማስተላለፊያ ቱቦ መስመር ጠቅላላ ተዘግቷል፤›› ብለው ነገሯቸው፡፡

በጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አልጋ ይዘው ለመታከም ሲጠባበቁ ቆይተው፣ ባላወቁት ጉዳይ መታከም እንደማይችሉ ተነገራቸው፡፡ ታማሚውን ሲያስታምሙ የቆዩት ባለቤታቸውም በዚሁ ምክንያት ድንገት በሞት እንዳጧቸው፣ ይህም የእግር እሳት እንደሆነባቸው በዕንባ ያስረዳሉ፡፡ ይህ ሁሉ ‹‹ጴጥሮስ ሆስፒታል በሕይወቴ ላይ በመፍረድ ወደር የሌለው ግፍ ፈጽሞብኛል፣ አካሌን አጉድሎብኛል፣ ቀዶ ሕክምና ያደረገልኝ ዶክተር መርፌ በአካሌ ውስጥ ለምን ተውክ?›› ብዬ ብጠይቅ፣ ‹‹ተማሪዎች ናቸው የረሱት፤›› የሚል ምላሽ እንደሰጣቸው ያስረዳሉ፡፡

በዚህ ሁሉ ጊዜያት ለደረሰባቸው ግፍ ትልቅ ጠባሳና ሐዘን መዳረጋቸውን፣ መንግሥት በሕግ አግባብ በቂ ሕክምና እንዲያገኙና በቤተሰባቸው ለደረሰው የሞራል ስብራት፣ ጊዜና ገንዘባቸውን ሁሉ ያጡበትን ቅሬታ ለማሰማትና በሕግ ለመጠየቅ ለጤና ሚኒስቴር የጤና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ኮሚቴ ጥቅምት 6 ቀን 2013 ዓ.ም. ቅሬታ እንዳሰሙ ተናግረዋል፡፡

ቅሬታውን ባቀረቡ ከዓመት በኋላ ውሳኔ ተሰጥቷቸዋል፡፡ ኮሚቴው በሙያ ሥነ ምግባር ከባለሙያዎች የሙያ ብቃት መጓደልና የሥነ ምግባር፣ ግድፈት ጋር ተያይዞ የሚቀርቡ ቅሬታዎችና ደረጃቸውን ያልጠበቁ የጤና አገልግሎት አሰጣጥ ችግር ሲገጥም አስተዳደራዊ ዕርምጃ የመውሰድ ሥልጣን አለው፡፡

በዚህም ኮሚቴውም በመስከረም 26 ቀን 2014 ዓ.ም. ባደረገው ስብሰባ  የአመልካችን የቅሬታ ማመልከቻ፣ አቶ ብርሃኔ ቀርበው ስለጉዳዩ የሰጡትን የቃል ማብራሪያ፣ ሕክምናውን የሰጡት የሕክምና ባለሙያ የተከሳሽነት ቃልና ሕክምናው ከተሰጠበት ቅዱስ ጴጥሮስ ሆስፒታል፣ ከጥቁር አንበሳ ሆስፒታልና ከሸበሌ መለስተኛ የቀዶ ሕክምና ክሊኒክ የአመልካችን የሕክምና ማኅደር በጥሞና ከመረመረ በኋላ ያሳለፈውን ውሳኔ ሰነዱ ያስረዳል፡፡

የኮሚቴው የውሳኔ ሐሳብ ቃል በቃል እንደሚከተለው ተቀምጧል፡፡ ‹‹ምንም እንኳን ለተፈጠረው ችግር ቀጥተኛ ምክንያት ባይሆንም፣ በታካሚው ሰውነት ውስጥ የቀዶ ሕክምና በተደረገለት የሰውነት ክፍል ውስጥ መስፊያ መርፌ መርሳት እንደ ግድፈት ታይቷል፡፡ ሌላው አማራጭ የሕክምና ሒደት ባለበት ከተማ በተደጋጋሚ የጠበበውን የሽንት ቱቦ ለማስፋት የተደረገው የሕክምና ሒደት ትክክል አለመሆኑን ኮሚቴው እንደ ስሕተት ማየቱን›› ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ስለሆነም ሕክምናውን የሰጠው ሐኪም የሰጠው ሕክምና ያላግባብ በተደጋጋሚ በመስጠቱና በጊዜው ወደ ተሻለ ሕክምና ባለመላኩ ለሐኪሙ ‹‹ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ›› እንዲሰጠው ቦርዱ መወሰኑን ሪፖርቱ ያሳያል፡፡

ለቀዶ ሕክምናው ዕቃ ያቀረቡትንም ነርስ በተመለከተ ሕክምናው ከተጠናቀቀ በኋላ ዕቃ ቆጥረው መረከብ የነበረባቸው ቢሆንም፣ ይህንን ባለማድረጋቸውና መርፌው መረሳቱን ባለማሳወቃቸው ምክንያት ‹‹ፍፁም ከባድ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ይሰጥ›› በማለት ኮሚቴው ስለምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደር ቁጥጥር በወጣው የሚኒስቴሮች ምክር ቤት ደንብ ቁጥር 299/2006 አንቀጽ 72(1) መሠረት፣ ይህን የውሳኔ ሐሳብ ይፀድቅ ዘንድ ለመጨረሻ ውሳኔ ተልኮ የበላይ አካላት አምነውበት ውሳኔውን አፅድቋል፡፡ ይህንንን ውሳኔ የጤና ሚኒስትሯን ጨምሮ የኮሚቴ አባላት በፊርማ አፅድቀውታል፡፡

አቶ ብርሃኔ ሽንት የሚሸኑት በካቲተር በመሆኑ፣ አሁንም ስቃያቸው አለማብቃቱን በዕንባ እየገለጹ፣ ውሳኔው ከሕመማቸውና ከስቃያቸው እንዳላዳናቸው ይናገራሉ፡፡ ‹‹አሁንም ፍትሕ እሻለሁ›› የሚሉት እኚህ ታካሚ የኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ይፍረደኝ በማለት ይማፀናሉ፡፡

በየጊዜው ለካቲተር የሚያወጡት ወጪ በጡረታ ከሥራ ለተሰናበተ ሰው ከኑሮ ውድነት ጋር አስቸጋሪ ሕይወት እንዲኖሩ አድርጓቸዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ሪፖርተር ያነጋገራቸው ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ በጤና ሚኒስቴር የጤና ባለሙያዎች ሥነ ምግባር ኮሚቴ አባል፣ ኮሚቴው በዋናነት ጉዳዮችን የሚያየው ከባለሙያ ጋር የተያያዘ እንደሆነ በመግለጽ፣ ውሳኔ የተሰጠባቸው ጉዳዮችን በድጋሚ ማየት እንደማይችሉ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ የአቶ ብርሃኔ ጉዳይ ላይ ሰፊ ውይይትና ምክክር ተደርጎበት እንደተወሰነ ጠቁመዋል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹ታካሚው በኮሚቴው ውሳኔ ቅሬታ ካለባቸው ሕግ ቦታ መሄድ እንጂ፣ ወደ ሚዲያ መሄድ የለባቸውም፤›› ብለዋል፡፡

 በዚህ ጉዳይ በድጋሚ አቶ ብርሃኔ እንደተናገሩት፣ የሕክምና ስህተቱ እንዳለ ሆኖ ኮሚቴው የተሻለ ሕክምና እንዲያገኙ የሚያደርግ ውሳኔ አልሰጠም፡፡ ‹‹ውሳኔው ለአንድ ወገን ያደላና በሰው ሕይወት ዕድሜ ልክ ስቃይን የሚያባብስ ውሳኔ ነው፤›› ይላሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ኮሚቴው ከችግሩ ግዝፈት አንፃር አሁንም በድጋሚ ማየትና ተገቢውን ውሳኔ እንዲሰጣቸው ጠይቀዋል፡፡ ለዓመታት ጤናቸውን፣ ገንዘባቸውን፣ ጊዜያቸውን እንዳልነበር ያደረጉ ግለሰቦችና ተቋም ጭምር ኃላፊነት መውሰድ እንደነበረባቸው በቁጭት ተናግረዋል፡፡

ከዚያ ውጪ የሞራል ስብራት የሚጠግንላቸውንና የተሻለ ሕክምና የሚያገኙበትን ዓይነት ውሳኔ መወሰን እንዳለበት በመግለጽ፣ አሁንም በስቃይ ላይ የሚገኙ በመሆናቸው የሕዝብንና የመንግሥትን ዕገዛና ድጋፍ ተማጽነዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...