ሰላም! ሰላም! ወከባና ሩጫው እንዴት ይዟችኋል? አንዳንዴ ሀሞት ያፈሳል አይደል? ይህች ዓለም ያለ ድካም አትሞከርም፡፡ ማለቴ ካልደከመው የሚበረታ፣ ካልታከተው የሚጠነክር ያለ አይመስልም። እንኳን ሩጠን ቁጭ ብለን የሚደክመን እኮ እየበዛን ነን፡፡ ታዲያ ይኼን ጊዜ ሰው ማለት ስስ ጎኑ የበዛ ፍጡር መሆኑ ይገባናል። በተለይ እኛ አዳሞች በስስ ጎንና በጎን አጥንት በኩል ጉድለታችን ብዙ ነው። ምን ለማለት እንደፈለግኩ ገብቷችኋል። በዚህ ጥድፊያና ኹካታ በበዛበት ዘመን ሔዋንን ሳይዙ ጉዞ አደጋው ከፍ ያለ ነው። እውነቴን እኮ ነው፡፡ ‹‹መልካም ሴት ለባልዋ ዘውድ ናት›› የተባለውን አላነበባችሁም? ቆይ እስቲ የማንበብ ባህል ያላዳበረ ኅብረተሰብ ሲሠለጥን የታየው የት ነው? ማንበብ የሚሉት ወሳኝ ጉዳይ ብዙውን ሰው ለምን ያንገሸግሸዋል? እንደ ባሻዬ አስተያየት ያለ እንስቶች የሚደረግ የሕይወት ጉዞ እንኳን ለሥጋ ለነፍስም አይረባም። ታዲያ ሁሌም የሚገርመኝ ሴቶች እንዲህ ዓይነቱ ማሰሪያ አንቀጽ ላይ ሚናቸው መጉላቱ ብቻ አይደለም። ከእነሱ ውጪ ሕይወት የሚባለው ነገር አሰልቺ መሆኑን ማን ይክዳል? በበኩሌ ዕድሜ ለውዷ ባለቤቴ ለማንጠግቦሽ ሐሳብ አይገባኝም። አንዳንዱ ግን ትዳርን በሚያህል ትልቅ ቁምነገር ላይ ‘ኮንትሮባንድ’ ይሠራል ይባላል። ይወሰልታል ለማለት ነው። ‘ትዳር ጣፋጭ ነው እንደ ማር’ ባለበት አፉ ሌላ ይስማል። ‹‹ዓይን ያወጣ ዘመን›› አሉ ባሻዬ፡፡ እውነታቸውን እኮ ነው!
ማንጠግቦሽና ምሁሩ የባሻዬ ልጅ የፍቅርን ነገር ካነሱ ሳይተራረቡ አይላቀቁም። ‹‹አይ የሴቶች ነገር?›› ይላታል። ‹‹አይ የወንዶች ነገር?›› ትለዋለች። ‹‹ደግሞ ወንዶች ምን አደረጉ?›› ሲላት፣ ‹‹ሴቶችስ ምን ኃጢያት ተገኘባቸው?›› ትለዋለች። ጎራ ለይተው አንዳቸው የአንዳቸውን ፆታ ገመና ሲዘከዝኩ ይኼ ሁሉ ድርጊት ድራማ ነው? ወይስ በዕውኑ ዓለም የተፈጸመ ነው? እላለሁ፡፡ እናም መሀል እሆንና የሁለቱንም ‹‹ጠቅልለህ ውቃ›› ወግ በትዝብት አዳምጣለሁ። ምነው የዘንድሮ ወግ ሁሉ የጅምላ ብቻ ሆነ? ፈረንጆቹ ‹‹ጄኔራላይዜሽን›› የሚሉት የጅምላ ፍረጃ ትክት ሲለኝ ብቸኝነት ያምረኛል፡፡ ይኼ የጅምላ ፍረጃ ከላይ እስከ ታች ይወርድና አዳሜን በፆታ፣ በሃይማኖት፣ በብሔር፣ በቋንቋና በመሳሰሉት ሲያባላ የዴሞክራሲ ዳር ድንበሩ ይጠፋብኛል፡፡ ማንጠግቦሽና የባሻዬ ልጅ ቀልዱን ትተው ከልባቸው ሲጫወቱ ማንጠግቦሽ፣ ‹‹የሴቶች ጥቅምና አስተዋጽኦ ብዙ ሆኖ ሳለ ለእኩልነታቸው የሚሉ አስመሳዮች ደግሞ በስማቸው ይሸቅላሉ፡፡ እስቲ ማን ነው ወይም ማን ናት በሴቶች እኩልነት ስም እየሸቀለ ወይም እየሸቀለች ለጭቁኗ ሴት ጥብቅና የምትቆመው…›› ብላ ትኮሳተራለች። ‹‹እኔምለው ግን ማንጠግቦሽ እናንተ ራሳችሁ እያላችሁ ለምን ወኪል ፍለጋ ትለፋላችሁ? ምነው ለራሳችሁ እናንተው ብትታገሉ?›› ሲላት ዓይን ዓይኗን እያየ፣ ‹‹እኛ ብቻ እናውቅላችኋለን የሚሉ አገር ምድሩን ሞልተውት እንጂ መቼ መተባበሩን ጠላን?›› ትለዋለች። ታዲያ ምን እንደሚነካኝ አላውቅም እንዲህ ዓይን ዓይኗን ሲያይብኝ ቅናት ነገር ይጀማምረኛል። መቼም የባሻዬ ልጅ ባይሆን ልቤ ሌላ ይጠረጥር ነበር። ምን ነካችሁ? ‘ሰውን ማመን ቀብሮ ነው’ አይደለም እንዴ የተባለው!
ታዲያ ጨዋታ ነውና የሰሙትን ማሰማት መልካም ነገር ይመስለኛል። ባለፈው ሳምንት አንድ ልጅ እግር ደላላ በእግር በፈረስ አስፈልጎ አገኘኝ። ‹‹ምነው በሰላም ነው?›› አልኩት። ‹‹ኧረ ጋሼ አንበርብር ሰው ሁሉ ሊበላኝ ነው…›› አለኝና ሰላምታውን በቅጡ ሳይጨርስ። ‹‹ምን ብሎ?›› አልኩት ደንገጥ ብዬ። ለሥራው አዲስ ስለሆነ ምን ተግዳሮት ገጠመው እያልኩ አብሰለስላለሁ። የእኛን አገር ነገር ታውቁታላችሁ። አዲስ የሥራ ቅጥር ማስታወቂያ ይወጣና በአምስትና በአሥር ዓመት የሥራ ልምድ ጥያቄ ይጨናነቃል፡፡ ‹‹የእዚህ አገር ነገር እንደ ገብስ ቆሎ መታሸት ነው…›› ያለኝ አንድ ሥራ ፈላጊ ወጣት አስታውሳለሁ። ‹‹እንዴት?›› ስለው፣ ‹‹የትምህርቱ መመዘኛ ተሟልቶ የልምዱ ጥያቄ ሲነሳ ለዓመታት ያሻል። ያ በልምድ የታሸው በተራው ቀጣሪ ሲሆን፣ ማን ታሽቶ ማን ይቀራል ዓይነት የእልህ የሚያስመስል መመዘኛ ያወጣል…›› ብሎኛል። ሁሉም ተማሪ ሁሉም ለማጅ ሆኖ ባያልፍ ግን ምን ይውጠን ነበር ወገኖቼ? አንዳንዱ ከእናቱ ሆድ ይዞት የወጣ ይመስል ያለ እኔ ማን አለ እያለ ከተማ ይበጠብጣል። ይኼ ወጣት ደላላ፣ ‹‹ወንዱ ሚስት፣ ሴቱ ባል ፈልግልኝ እያሉ አስቸገሩኝ…›› አይለኝ መሰላችሁ? እናማ ጨዋታ የያዘ ስለመሰለኝ ከት ብዬ ሳቅኩበት። ፍቅር በድለላ፣ ትዳር በፎርሙላ ከቶ የት አገር ታይቶ ይሆን? መቼም እኛ ከውጭ አገር ልምድ በመቅሰም፣ ቀስመንም የሚረባውን ከማይረባው ባለመለየት በአፍሪካ የመጀመርያዎቹ ሳንሆን አንቀርም። ይህች ‹‹አንደኛ›› እና ‹‹የመጀመርያ›› ሳትሆን ትቀራለች መጨረሻ ላይ የወረወረችን? ማን ያውቃል!
ለማንኛውም በዚህ ወከባው ፋታ አልሰጥ ባለበት ሰዓት አንዳንዴ ቆም እያሉ እርስ በእርስ መገማገምና ራስንም መገምገም ቢለምድብን ጥሩ ነበር። በተለይ የራስን አካሄድ ከማወቅና ከመገምገም በፊት ሌላው ባይቀድም እንዴት ሸጋ ነበር መሰላችሁ? አዛውንቱ ባሻዬን፣ ‹‹ዘንድሮ እኮ ሰው መጠቋቆሙን አበዛው…›› አልኳቸው። ፊታቸው በሐሳብ ጉም መስሎ፣ ‹‹እንደ መፍረድ ምን ቀላል ነገር አለ ብለህ ነው ልጅ አንበርብር? እንግዲያማ መጽሐፉ ይል የነበረው የራስህን ጉድፍ ሳታጠራ የጓደኛህን ማጥራት አይቻልህም ነው። አይ እኛ? አሁንም ራሳችን ግራ እየገባን ሌላውን ግራ ማጋባት መደበኛ ሙያ አደረግነው መሰለኝ?›› አሉኝ በሐዘን ተውጠው። ምሁሩ የባሻዬ ልጅም፣ ‹‹የዴሞክራሲ አንዱ ጥቅም የተለያዩ አመለካከቶችን ወይም አስተያየቶችን ሰምቶ የሚጠቅመውን መውሰድ ነው፡፡ ሌሎችም መደመጥ ስላለባቸው ይህንን ዕድል እንዲያገኙ ማድረግ የዴሞክራሲ ግቡ ነው…›› ብሎኝ ነበር። ታዲያ ይኼ ራስን ሳይገመግሙና ሳይመዝኑ እንዴት ይሆናል? የእኛ ትልቁና ዋናው በሽታ እኮ ስለራሳችን መስማት የማንፈልጋቸው እውነታዎች ብዙ መሆናቸው ነው። እውነቴን እኮ ነው ለምን ብዬ እዋሻለሁ? እናም በዚህ ዘመን ዕድሉን ተጠቅመን ቁጭ ብለን የነበረውን ተረት፣ አባባል፣ ወግና ልምድ ስንከልስ ከምንውል አኗኗራችንና ስለራሳችን ያለንን አመለካከት ብንቀይር ምን ይለናል? ‹‹የተለየ አስተያየትና ሐሳብ መስማት የማይወዱ ወገኖቻችን በአንድ ማርሽ ብቻ የትም እንደማይደረስ ብንጠቁማቸው ለአገር ትልቅ ነገር እንዳበረከትን ይቆጠራል…›› የሚል ምክር የለገሰኝ የባሻዬ ልጅ ነው፡፡ ሳይጠቅመኝ አይቀርም!
አንድ ወዳጄ ባለፈው ሰሞን ለአንዲት ተራ ጉዳይ ሦስት ሺሕ ብር በጥሬው መሸጎጥ ግድ ሆነበትና ጉዳዩን ማስጨረሱን ሰማሁ። ከመስጠቱ በፊት ግን የተጨቃጨቀውን ሲነግረኝ ውሸቱን መስሎኝ ነበር። ወዳጄ ጉዳይ አስፈጻሚውን፣ ‹‹እባክህ ጉዳዬን ቶሎ ፈጽምልኝ?›› ይለዋል። ‹‹ነገርኩህ እኮ በዚህ የኑሮ ውድነት እንዴት እንዲህ እንጨካከናለን?›› ካለው በኋላ ጉዳይ ፈጻሚው፣ ‹‹እንዲህ ስትጨቃጨቅ ግሽበቱ ኪስህ ውስጥ ያለውን ገንዘብ ያተንልህና ታርፈዋለህ…›› እንዳለው አጫወተኝ። ‹‹አንዳንዶቹ እኮ ጉቦ ሲጠይቁ የቫት ደረሰኝ አምጡ ቢባሉ ከመስጠት አይመለሱም…›› ሲለኝ ደነገጥኩ፡፡ ነገሩ ሙስናን የሚያጋልጡ ከለላ ባጡበት በዚህ ዘመን መስጠት እንዴት ወንጀል ይሆናል? ወይ አገርና ጉቦ? ወይ ታሪክና እውነታ? በእኔ ሞት ዕውን ኢትዮጵያ የትጉኃን መናኸሪያ ናት? ወይስ የዘረፋ ሰብሳቢዎች? ኧረ ግራ ገባን? ‹‹ከሠራን ላይቀር ከደከምን ላይቀር ለፍሬ እንድከም እንጂ፣ ለይምሰል ለይምሰሉ ከሆነ ከአብዮት ተነስተን እስከ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ድረስ ምን አደከመን?›› ይለኛል ምሁሩ የባሻዬ ልጅ። እውነቱን እኮ ነው!
መቼም ትልቅ ሰው ልቡ ተራራ ነው። የባሻዬን ልጅ በሚመጣው አዲስ ተረካቢ ትውልድ ውስጥ ትልቅ አስተዋጽኦ ሲያበረክት እንደማየው አልጠራጠርም። ከሥር ያሉትም ታዳጊዎች ተቺዎቻቸው ወደ አስተማሪነት፣ የሚረግሙዋቸው ወደ መራቂነት ከተሸጋገሩላቸው ባለ ራዕይ መሆን ይችላሉ። የአገር የዕድገት ጉዞ የሚሳካው ትዕግሥትና አቅም ባለው ትውልድ ነው። አይደለም እንዴ? እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በዚህች የደላላ ጭንቅላቴ እንዲህ የማስብ ከሆነ ብዙ ከሚጠበቅባቸው ታላላቅ ምሁራኖቻችን በርካታ የሐሳብ መዋጮ ይጠበቃል። ሳንነጋገር እንዴት ልንራመድ ኖሯል? የባሻዬ ልጅ በምሁር አንደበቱ እንደነገረኝ ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ ነፃነት የሚያስፈልገው የወደፊቱ ትውልድ ለአገሩ የሚጠቅም ተግባር ለማከናወን ስለሚረዳው ጭምር ነው፡፡ ይህን ሁሉ እንዳስብ የምትረዳኝ ይህችው የተከበረች ሥራዬ ብቻ ነች። ለነገሩ እሷም ውስጥ ትዝብቱ አይቀርም። የደላላነት ሙያ በልምድ ብቻ ሳይሆን በሁለመናዬ እንደተሠራጨ የምረዳው ከምደልላቸው ቁሳዊ ነገሮች ባሻገር የአካባቢዬን፣ የአገርንና የዓለምን ውሎ ሳውጠነጥን በመዋሌ ነው። ድለላን ከገዥና ከሻጭ ግንኙነት በላይ የማየው ማኅበራዊ ኃላፊነት ስላለበት ጭምር ነው፡፡ እውነት ነው!
ሰሞኑን አንድ ተዘግቶ የኖረ ኮንዶሚኒየም ቤት ለማከራየት ስባዝን አንዲት ወጣት አገኘሁ። ከከፍተኛ የትምህርት ተቋም በቅርቡ በማስተርስ ዲግሪ ተመርቃ ሥራ መያዟ ነበር። አሁን ራስዋን ችላ ለመኖር ቤት ስትፈልግ አጋጣሚ ይኼው አገናኘን። ‹‹በይ ያገኘሁልሽ ጥሩ ቤት ነው። ስታይው አመሥግነሽኝ አትጠግቢም…›› ስላት እየሳቀች፣ ‹‹አይ ምን አሪፍ ቢሆን ኪራይ መሆኑን ረሳኸው? ፈጣሪ ፈቅዶልን መንግሥት የሠራውን ቤት በፍትሐዊ መንገድ ሲያከፋፍለን ያኔ ነው እውነተኛ ደስታ…›› አለችኝ። ከአነጋገሯ የተረዳሁት 40/60ን ማለቷ ነው። አሁንም ቤት ያላቸው ለዚህ መርሐ ግብር ይጋፋሉ ሲባል ሰማሁ ልበል? ‹‹ታውቃለህ?›› አለችኝ ድንገት ጮክ ብላ። ‹‹እስከ ዛሬ ሲያንከራትተን የነበረው በመልካም አስተዳደር አማካይነት ምላሽ ማግኘት የሚችል ችግር ነበር። አሁን ደግሞ ችግራችን በሀቀኝነትና በታማኝነት ለሥርዓቱ ተገዥ የሚያደርገን ሆነ። ከሕግ የበላይነት ይልቅ የሥልጣን የበላይነት ነገሠ። እናም በኪራይ ቤት የመንከራተታችን ጉዳይ በውል አልታወቅ አለ…›› ስትለኝ የወጣቷ ስሜት አንጀቴን አላወሰው። የመልካም አስተዳደር ዕጦት የሚያስከትለው ዘርፈ ብዙ ችግር ስንቱን እንደሚያንገበግበው የድለላ ሙያዬ ያሳየኛል፡፡ ወጣቷ ተከራይ ድርሻዬን ቆርጣልኝ ከእሷ በተጨማሪ ደግሞ ሌሎች አንድ ሦስት ሥራዎች ሠራራሁና እንደ ጨረስኩ የባሻዬን ልጅ በስልክ አገኘሁት። ገና ቀትር ስለነበር ግሮሰሪ የምንሄድበትን ጥሩ ምሳ በላንበትና ቡና ልንጠጣ አንድ ባህላዊ ቡና የሚፈላበት ቤት ገባን። የባሻዬ ልጅ በሐዘን አንገቱን ግራ ቀኝ ነቅንቆ አንድ ጨዋታ አጫወተኝ። ወግ መልካም ነው!
‹‹ፋሽስት ኢጣሊያ አገራችንን በግፍ ወርሮ በመርዝ ጋዝ ሲጨፈጭፍ እንዲህ ሆነ። አንድ ቀን አንድ የእኛ ሰው ንፋስ እየተቀበለ ሳለ የጣሊያን ወታደሮች ያገኙታል፡፡ ባዶ እጁን መሆኑን ካረጋገጡ በኋላ ያነጋግሩታል፡፡ የሠፈሩ ነዋሪ መሆኑን ሲነግራቸው ወደ ጦር ሠፈራቸው ይወስዱታል። እዚያም ምሳውን ካበሉ በኋላ ቡና አጠጥተው ይለቁታል። ሲመለስ ያጋጠመውን ለአካባቢው ሰዎች ቢያጫውታቸው ቡና መጠጣት ያምራቸውና ሃምሳ ያህል ሆነው ባዶ እጃቸውን ወደ ጣሊያኖች ሠፈር ይጓዛሉ። የጣሊያን ወታደሮች ግን በመትረየስ ፈጁዋቸው…›› ካለኝ በኋላ፣ ‹‹አንበርብር አይገርምህም የሕዝባችንን የዋህነት?›› አለኝ። ያጫወተኝ ታሪክ ልቤን እጅግ ሰበረው። ይህ የፍቅር ሕዝብ ለምን ይሆን በፋሽስቶች በመርዝ ጋዝ እንዲያልቅ የታዘዘበት ስልም ተብሰለሰልኩ። የባሻዬ ልጅ በተጨማሪ ከዓመታት በፊት ለግራዚያኒ ማስታወሻ ሙዚየምና መናፈሻ በአገሩ ተሠርቶ መመረቁን ቢነግረኝ እንደተከዝኩ ዋልኩ። ‹‹ታሪክ ፋሽስቶችን ይፋረድ›› የሚል መጽሐፍ መጻፍ አማረኝ። ግና አሁንም ክፉዎች ከደጎች በላይ የሚሞገሱበት ጊዜ ላይ መሆናችንን ሳስታውስ ሐሳቤን ሰረዝኩት፡፡ ምናለበት ብዙ ከንቱ ድርጊቶችን ከአዕምሮዬ መሰረዝ ብችል!
ከባሻዬ ልጅ ጋር እንደተለያየን ለቅሶ ለመድረስ አንድ ወዳጄ ዘንድ ሄድኩ፡፡ የአያቱን ሞት ተረድቶ አንድ ሳምንት ሐዘን የተቀመጠው ወዳጄ እንዳያኮርፈኝ በማለት ነው ሳልወድ የሄድኩት፡፡ ‹‹ሰልስት አትድረሱ›› በሚባልበት በዚህ የሠለጠነ ጊዜ ወዳጄ ከቢጤዎቹ ጋር ካርታ እየተጫወተ ነበር፡፡ ጠራራ ፀሐይ በፈጠረችው ሙቀት አንዳች የሚያህል ጋቢ ተከናንቦ ላቡ ጠብ እያለ የአያቱን ሐዘን በካርታ ቁማር የሚያረሳሳው ወዳጄ ኮስተር ቢልብኝም፣ ‹‹እግዜር ያጥናህ›› ማለቴ ግን አልቀረም፡፡ ይኼው ወዳጄ ዘግቶኝ ካርታው ላይ ቢያተኩርም እንደ እኔ በመገረም ከሚመለከተው ሰው ጋር በሹክሹክታ ወግ ያዝን፡፡ እንደ እኔ የዚህን ሰው ኩርፊያ ፈርቶ የመጣው ሰውዬ፣ ‹‹ለቅሶ ከተቀመጠ ይኼው ሰባት ቀኑ፡፡ ከዚህ ሁሉ ቀን በኋላም ተቀምጦ ይቆምራል፡፡ ሰው ለምን ለቅሶ አልደረሰኝም ብሎ ያኮርፋል ሲሉ መጣሁ እንጂ ድርሽ አልልም ነበር…›› አለኝ ተንገፍግፎ፡፡ እኔም የእሱን ሐሳብ እንደምጋራ ስነግረው ሰውየው ደስ ብሎት ወግ ጀመረ፡፡
‹‹ይኼን እንኳ ተወው የልማድ እስረኛ ስለሆነ ነው፡፡ አሉ እንጂ ተምረዋል፣ ብዙ ልምድ አካብተዋል፣ ሌሎችን ማስተማር ይችላሉ የሚባሉት ታጥቦ ጭቃ የሚሆኑት…›› አለኝ፡፡ ወሬውን ፈልጌያለሁና፣ ‹‹ለምሳሌ?›› አልኩት፡፡ ‹‹ምን ሩቅ አስኬደህ ዙሪያህን አትመለከትም? ከጎረቤትህ ጀምር፣ መሥርያ ቤትህ ድረስ፣ ትልልቅ የመንግሥት ተቋማትን አስስ፣ አንቱ የተባሉ ሰዎችን ተመልከት፣ አንድ ዓይነት አመለካከት፣ ፍላጎትና ስሜት ታነባለህ፡፡ ኧረ ጎበዝ ለየት ያለ ነገር አስተዋውቁን ይኼ ሰለቸን እኮ ስትል አንድ ታርጋ ይለጠፍብህና ትፈረጃለህ፡፡ ልማዳዊ ድርጊት ሠልጥኖ የተሻለ አመለካከት ወይም ለውጥ ሲመጣ ሊገነድስ የሚነሳው ይበዛል፡፡ ነገራችን ሁሉ አድሮ ቃሪያ ሆኗል…›› ሲለኝ ይኼስ በደንብ ገብቶታል አልኩ፡፡ ከለቅሶው ቤት ተሰናብተን ስንወጣ ይኼ የተባረከ ሰው ጎጂ ልምዶች ምን ያህል እየተጫወቱብን እንዳለ በሚገባ ነገረኝ፡፡ አዲሱን ትውልድ ከእንዲህ ዓይነቶቹ ጎጂ ድርጊቶች የመጠበቅ ሞራላዊ ኃላፊነት እንዳለብን አስገነዘበኝ፡፡ መንታ መንገድ ላይ ደርሰን ስንሰነባበት፣ ‹‹ወንድሜ እዚህ አገር ከመጠን በላይ ያስቸገረው የጅምላ ፍረጃ ነው፡፡ በጅምላ ተፈርጀህ ትጠላለህ፣ በጅምላ ተፈርጀህ ትወነጀላለህ፣ በጅምላ ተፈርጀህ መብትን ትቀማለህ፣ በጅምላ ተፈርጀህ ትሰደዳለህ…›› እያለ ተብሰለሰለ፡፡ መልካም ሰንበት!