ኢትዮጵያ በወራሪው የፋሺስት ጣሊያን ሠራዊት ላይ ድል የተቀዳጀችበት 82ኛ ዓመት ሚያዝያ 27 ቀን 2015 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከተማ አራት ኪሎ በሚገኘው የሚያዝያ 27 ቀን አደባባይና የድል ሐውልት ሥር የአበባ ጉንጉን በማስቀመጥ ተከብሯል፡፡
ኢትዮጵያ ዓርብ ሚያዝያ 27 ቀን ያከበረችው የድል በዓል መንሥኤ፣ ፋሺስት ኢጣሊያ በመስከረም 1928 ዓ.ም. በወልወል በኩል የጀመረችው ወረራ አጠናክራ ለአምስት ዓመታት አገሪቱ በወረራ ከያዘችበት በኢትዮጵያውያን ተጋድሎና እርመኛነት በድል የተጠናቀቀበት መሆኑ ነበር፡፡
የወቅቱ ንጉሠ ነገሥት (1923-1967) ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ በስደትና በዲፕሎማሲያዊ ትግል ከቆዩበት የእንግሊዟ ባዝ ከተማ በሱዳን በኩል በምዕራብ ኢትዮጵያ ኦሜድላ ላይ ጥር 12 ቀን 1933 ዓ.ም. የኢትዮጵያን ሰንደቅ ዓላማ ያውለበለቡበት ከወራት ቆይታ በኋላም ከአርበኞች ጋር የዘለቁበትና በዕለተ ቀኑ ሚያዝያ 27 አዲስ አበባ የደረሱበት ነበር፡፡
የፋሺስቶች ወረራና ለጊዜውም ቢሆን ኢትዮጵያን መያዛቸው፣ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት የተጀመረው በአውሮፓ ውስጥ ነው ከሚለው አተያይ በተቃራኒው፣ በአፍሪካ ኢትዮጵያ ውስጥ መስከረም 22 ቀን 1928 ዓ.ም. በተፈጸመው ወረራ ሁለተኛው የዓለም ጦርነት መጀመሩን የሚሞግቱ ምሁራን (ዶ/ር ንጉሤ አየለ፣ ዶ/ር ዓለሜ እሸቴ ፕሮፌሰር ሪቻርድ ፓንክረስት) አሉ፡፡ እንዲያውም የአፍሪካ ቀንድ (1928 እስከ 1933 ዓ.ም.) የዘለቀ የጦርነት ጎራ ሆኖ መዝለቁም ታውቆለታል፡፡
ከድል ሐውልት ማዕቀፍ ውስጥ በተናጠል ኪነ ቅርፆች ላይ ከተጻፉት መታሰቢያዎች መካከል ቀዳሚው፣ ለአገራቸው ነፃነት አምስት ዓመት ሙሉ በዱር በገደል እየተንከራተቱ ደማቸውን ላፈሰሱና አጽማቸውን ለከሰከሱ ለስመ ጥሩ አርበኞች የቆመ የዘላለም መታሰቢያ ነው፡፡
ሌሎቹ አምስት ዓመት ሙሉ በጠላት የጭቆና ቀንበር ውስጥ ተቀምጠው የሞት ጥላ በራሳቸው ላይ እያንዣበበ ሐሳባቸውን ከአርበኞችና ከስደተኞች ሳይለቁ አገራቸውን በስውር ላገለገሉ የውስጥ አርበኞች የቆመ መታሰቢያ፡፡ ያለ አገር ክብርና ነፃነት አለመኖሩን ተረድተውት የጠላት መሣርያ ከመሆን መከራና ስደትን መርጠው አምስት ዓመት ሙሉ ተስፋ ባለመቁረጥ ሲንገላቱና ሲንከራተቱ ለኖሩ ስደተኞች የቆመ መታሰቢያ የሚሉ ናቸው፡፡
አፍሪካዊ አውሮፓዊን ድል ለማድረግ የቻለበት ከዓድዋው ድል ቀጥሎ ሁለተኛው የድል ቀን ሚያዝያ 27 መሆኑ በአፍሪካውያንም ሆነ በሌላው ዓለም እንደሚታወቅ ይወሳል፡፡
ከስድስት አሠርታት በፊት፣ በታተመ የማስታወቂያ ሚኒስቴር የታሪክ ድርሳን ላይ እንደተመለከተው፣ በነገሥታቱ መሪነት ኢትዮጵያን የድል አክሊል እንደተቀዳጀች እንድትኖር ያደረጓት ሕይወታቸውን ስለ ሠዉላትና የማትናድ ሕንፃና የማትፈርስ ግንብ አድርገው ስለ ገነቧት ነው፡፡
‹‹ትንሣኤና ሕይወት ሚያዝያ ፳፯ት›› የተሰኘው የ1956 ዓ.ም. ድርሳን እንደሚያወሳው፡- የታሪክ ሥፍራዎችና ሜዳዎች፣ የነፃነት ቀኖችና ወሮች ከነዘመናቸው የማይረሱ ናቸው፡፡ ለምሳሌ ዓድዋና የካቲት ሐያ ሦስት ቀን በመቼውም ዘመን በማናቸውም ወርና ቀን ቢሆን ሲታወሱ ትዝ የሚለው፣ በ1888 ዓ.ም. ከኢጣሊያኖች ጋር ተደርጎ በነበረው ጦርነት የተገኘው ድልና በዚህ ምክንያት በዓለም ላይ ጮራውን የፈነጠቀው የኢትዮጵያ የመታወቅ ዝና ነው፡፡ ድሉም ሲታሰብ አብረው ከሚታሰቡት ከንጉሠ ነገሥቱ ከአፄ ምኒልክ ጀምሮ ከሠራዊት እስከ መኳንንት የነበሩት የጦር ጀግኖች ናቸው፡፡
‹‹ለአፄ ምኒልክና ለአፄ ኃይለ ሥላሴ ካሉዋቸው የድል ቀኖች ዋናዎቹ የካቲት 23 ቀን (1888 ዓ.ም.) እና ሚያዝያ 27 ቀን (1933 ዓ.ም.) ናቸው፡፡ ከዚህም አስቀድሞ ለነበሩት ለአፄ ቴዎድሮስና ለአፄ ዮሐንስ የድል ቀኖችና ሜዳዎች ነበሯቸው፤ እነ ጉንደት፣ እነጉራዕ፣ እነ ሰሐጢና እነ ዶግዓሊ የየራሳቸው የድል ቀኖች አሏቸው፡፡
ከሰማንያ ሁለት ዓመት በፊት የተገኘው የሚያዝያ 27ቱ ድል ለመላው ለአፍሪካ አህጉር ነፃ አወጣጥ መንገድ ጠራጊ መሆኑንም ያመሠጥራሉ፡፡ ለኢትዮጵያ ድጋፍ በሰጠችው የእንግሊዝ ጦር ሠራዊት ውስጥ ከቅኝ ግዛቶቿ የአፍሪካ አገሮች የተመለሱት አፍሪካውያን ወታደሮች ኅሊና ውስጥ ‹‹እኛም ነፃ መውጣት አለብን!›› የሚለው መነሣሣት የታየው በሚያዝያው ድልና ስኬት መሆኑም ተመልክቷል፡፡
እንደ ታሪካዊው ድርሳን አዘጋገብ፣ ‹‹ኢትዮጵያ ከ1928 ዓ.ም. ከሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በፋሺስት ኢጣሊያ የተያዘችበት) እስከ 1933 ሚያዝያ 27 ቀን (አዲስ አበባ በድል የተያዘችበት) ድረስ የጠላት ኰቴ በመስኮቿ ላይ ቢዘዋወርም ገዢነቱን አላወቀችለትም፡፡ ጫካው ሁሉ የጃርት ወስፌ ስለሆነበትና ሜዳውም ቢሆን አቃቅማ ብቻ ሆኖ ስላስቸገረው ምን ያህል ጭንቀት እንዳደረበት አምስት ዓመት ያልሞላው የሥቃዩ ዘመን ምስክር ነው፡፡››
በኢትዮጵያ ታሪክ ምርምር በማድረግ ብዙ ድርሳናት የጻፉት የቴልአቪቭ ዩኒቨርሲቲ ፕሮፌሰር የታሪክ ምሁሩ ሀጋይ ኤርሊህ (ፕሮፌሰር) እንደጻፉት፣ የአርበኞች ድል በዘመኑ የነበሩ የዓለም ኃያላን የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ተቀብለው፣ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት መሥራች አባል እንድትሆን አድርጓል፡፡
በጦርነቱ መባቻ በፋሺስት መሪ ሙሶሎኒ ትዕዛዝ ሚያዝያ 27 ቀን 1928 ዓ.ም. የጣሊያን ጦር በወረራ አዲስ አበባ የገባ ሲሆን፣ ከአምስት ዓመታት በኋላ በአርበኞች ትግል በተገኘው ድል በዚሁ ቀን ቀዳማዊ አፄ ኃይለ ሥላሴ ተመልሰው አዲስ አበባ በመግባታቸው በዓሉ ለኢትዮጵያ ሁለተኛ የድል በዓል ሆኗል።
የጣሊያን ጦር ዓድዋ ላይ በኢትዮጵያ ጀግኖች ከተሸነፈ ከአርባ ዓመታት በኋላ እንደገና ለበቀል ሲመጣ በተደራጀ የጦር መሣሪያ በአየር ኃይል መርዛማ ኬሚካል በመጠቀም ንፁሃን ዜጎችን ቢፈጅም፣ የኢትዮጵያ አርበኞች ለወራሪው ኃይል ሳይበገሩ ለአምስት ዓመታት ታግለው ማሸነፋቸው ይወሳል።
እንደ ሀጋይ ኤርሊህ (ፕሮፌሰር) ማብራርያ፣ በወረራው መጀመሪያ ንጉሠ ነገሥቱ ከጣሊያን ጋር ውጊያ መግጠማቸው፣ ፍልሚያው እየተጠናከረ ሲሄድ ጣሊያን በናፓል የመርዝ ጋዝ ሕዝቡን ፈጅቷል፡፡ አፄ ኃይለ ሥላሴ ወደ መንግሥታቱ ማኅበር (ሊግ ኦፍ ኔሽንስ) መሄዳቸውን፣ አርበኞቹ ውስጥ ለውስጥ እየተገናኙ በዱር በገደሉ የሽምቅ ጦርነት ከፍተው የትጥቅ ትግላቸውን አጠናክረው መቀጠላቸውን፣ ከአምስት ዓመታት ፍልሚያ በኋላ ለድል መብቃታቸውን ጠቅሰዋል፡፡
በስደት የነበሩት ንጉሠ ነገሥቱ ከአጋር መንግሥታት ግንኙነት ሲያደርጉ ቆይተው በእንግሊዝ ድጋፍ የተመለሱ ሲሆን፣ ይህ በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ወቅት የተደረገው ፍልሚያ ብዙ ጀግኖች መስዋዕትነት የከፈሉበትና በኢትዮጵያ ታሪክ ጉልህ ሥፍራ እንዳለው ይወሳል፡፡
የኢትዮጵያ የጦር መሪዎች የጣሊያንን ጦር ለመግጠም ሲነሱ በወቅቱ በቂ ትጥቅና ስንቅ ባይኖራቸውም፣ ንጉሡ በስደት ቢሄዱም ኢትዮጵያውያን ምንም ዓይነት ልዩነት ቢኖራቸውም በአገራቸው ጉዳይ አንድ ሆነው የሚቆሙ መሆኑን ታሪክ ያረጋግጣል ያሉት ፕሮፌሰር ሀጋይ፣ ቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ከኢትዮጵያ ሲወጡ ወደ እስራኤል መምጣታቸውን፣ ቤተሰባቸውን ኢየሩሳሌም በማሳረፍ፣ በሃይፋ ወደብ ወደ ጄኔቭ መሄዳቸውን፣ በእንግሊዝ ለዓመታት ቆይተው በሱዳን በኩል መመለሳቸውን አስታውሰዋል፡፡
በወቅቱ የእስራኤል የነፃነት ትግል መሪዎች አንዱ የነበሩት ጌዲዮን ኦዴድ ከኢትዮጵያ ትግል ትምህርት የቀሰሙ መሆኑን፣ በሁለቱ አገሮች ሕዝቦች መካከል የነበረው ታሪካዊ ግንኙነት ጥብቅ መሆኑንም ሀጋይ ገልጸዋል።
የዘንድሮውን በዓል አስመልከተው በዋዜማው መግለጫ የሰጡት፣ የጥንታዊ ኢትዮጵያ ጀግኖች አርበኞች ማኅበር ፕሬዝዳንት ልጅ ዳንኤል ጆቴ መስፍን፣ በዓሉ የአገርን ኅብረ ብሔራዊ አንድነት የሚጎለብትና የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት የሚያጠናክር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመን ከ1934 ዓ.ም. እስከ 1966 ዓ.ም. ድረስ የድሉ በዓል ይከበር የነበረው ሚያዝያ 27 ቀን ሲሆን፣ ከደርግ መንግሥት መምጣት በኋላ በዓሉን ወደ ‹‹መጋቢት 28›› ለውጦት ከወደቀም በኋላ እስከ 1987 ዓ.ም. ሲከበር ኖሯል፡፡
ኢሕአዴግ ሥልጣን ላይ በወጣ በአምስተኛ ዓመቱ በነባር አርበኞቹና በኅብረተሰቡ ጥያቄ፣ በታሪክ ምሁራንም አረጋጋጭነት በዓሉ በ1988 ዓ.ም. ወደ መሠረታዊ ቀኑ ሚያዝያ 27 ቀን ተመልሶ በመከበር ላይ ይገኛል፡፡