ደጋማውን የአንኮበር አካባቢ እየተንዘፈዘፉ አልፈው እምዬ ሚኒሊክ ከከተሙባት የአንኮበር ተራራ ቁልቁል ወደ አርጎባዎቹ ቆላማ መንደር ሲወርዱ አንድ አስደናቂ መስኸብ ያገኛሉ፡፡ በ1,620 ሜትር ገደማ ከባህር ወለል በላይ በሰፈረ ወይና ደጋማ አካባቢ ከአንቦር ሰንሰለታማ ተራራ ግርጌ ከአረፈ ረባዳ ቦታ ላይ የሚያገኙት ይህ ድንቅ ስፍራ አብዱል ረሱል ይባላል፡፡ ከታሪካዊቷ የአልዩ አምባ ከተማ ስምንት ኪሎ ሜትር ገደማ ርቀት ላይ በክረምቱ ወቅት ብርቱ ከሚሆነውና ከምዕራብ ወደ ምሥራቅ ከሚፈሰው የደረቄ ወንዝ ከሚያልፍበት ጉብታ ላይ የሚገኘው አብዱል ረሱል ቀደም ባለው ጊዜ ሰዎች ወንዙን ተገን ያደረጉ ኑሮ ይኖሩ እንደነበር ማሳያ ነው፡፡
የአካባቢው መጠሪያ የተገኘው ይህንን ሥፍራ ካቀናው አብዱል ናስር ከተባለ አንድ ግለሰብ መጠሪያ እንደሆነ ይነገራል፡፡ በጊዜ ብዛት ግን ከግለሰቡ ስም የተነሳ የተሰጠው ይህ መጠሪያ ወደ አበዱል ረሱል እንደተቀየረ ነው የአካባቢወ ነዋሪዎች የሚያስረዱት፡፡ የአልዩ አምባ ከተማ ጥንታዊ ትሁን እንጂ ከአልዩ አምባ በፊት እንደተቆረቆረች የሚነገርላት አበዱል ረሱል በትክክል የተቆረቆረችበት ዘመን አይታወቅም፡፡ ነገር ግን ከ1258 እስከ 1415 ዓ.ም. የይፋት ሱልጣኔት በነበረበት ዘመን የተቆረቆረች ከተማ ስለመሆኗ መዛግብት ያስረዳሉ፡፡
የአብድል ረሱል ጥንታዊ ከተማ በዚያን ወቅት ከ4,000 በላይ የሚደርሱ ነዋሪዎች እንደነበሩባት ዛሬ ላይ ከሚታዩት የመንደሯ ፍርስራሽ ቅሪቶች በመነሳት አጥኚዎች ግምታቸውን ያስቀምጣሉ ይኸ ደግሞ በዚያን ወቅት ሌሎች የአገራችን ከተሞች ሊኖራቸው ከሚችለው የሕዝብ ብዛት አንፃር ሲተያይ አብዱል ረሱል ሞቅ ያለች ከተማ እንደነበረች ለመረዳት ይቻላል፡፡
በአካባቢው ሰዳድ ተብሎ የሚጠራው ሥፍራ ለከተማዋ የመቃብር ቦታ እንደነበር አጥኚዎች ይናገራሉ፡፡ በዚህ ሥፍራም 3,000 የሚገመቱ የመቃብር ጡሉሎች (ድንጋዮች) ይገኛሉ፡፡ ይህ ሥፍራ ከአብዱል ረሱል በስተምሥራቅ ከአንድ እስከ ሁለት ኪሎ ሜትር ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ከእነዚህ መቃብሮች ውስጥ አንዱ የከተማዋ መሥራች የአብዱል ናስር መቃብር ነው፡፡ የጣሊያን ወረራ ወቅት ቀስ በቀስ ስትዳከም ለመጣችዋ የአብዱል ረሱል ከተማ መጥፋት ምክንያት ሆና መስሕባዊ ቅሪትም ሆና ቀረች፡፡
– ሀገሬ ሚዲያ ‹‹ቱባ›› (2002)