በኢትዮጵያ ውስጥ የባንክ ተደራሽነት ወደ 45 በመቶ ከፍ ማለቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ መረጃ ያመለክታል፡፡ ይሁን እንጂ ከብድር ተደራሽነት አንፃር ሲታይ የኢትዮጵያ ያለችበት ደረጃ እዚህ ግባ የሚባል አይደለም፡፡ የአገሪቱ ባንኮች ካቀረቡት ብድር ተጠቃሚ የሆኑት ቁጥር ከ350 ሺሕ ያልበለጡ መሆናቸውን የብሔራዊ ባንክ መረጃ ይገልጻል። ይህም ብድር እየቀረበ ያለው ለጥቂቶች እንደሆነ ግልጽ ማሳያ ነው፡፡
ችግሩ የተበዳሪዎቹ ቁጥር ማነሱ ብቻ ሳይሆን የብድር ተጠቃሚዎች ትልልቅ ተቋማት መሆናቸው ነው፡፡ የአገሪቱ ባንኮች ለአነስተኛና ለጥቃቅን ለሚባሉ ተቋማት በራቸው ክፍት አለመሆኑ አነስተኛና መካከለኛ ተቋማት ቢዝነሳቸውን ለማሳለጥ እንዳልቻሉ በተደጋጋሚ ሲነገር ቆይቷል፡፡ የክፍያ ፋይናንሻል ቴክኖሎጂ መሥራችና ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ሙኒር ዱሪም፣ በኢትየጵያ ያለው የብድር አቅርቦት አነስተኛና ጥቃቅን ቢዝነሶችን ያላገነዘበ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡ የአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሌላው ችግር፣ ከባንኮች ብድር ለማግኘት ቢሹ የግድ ማስያዣ መጠየቃቸው ፋይናንስ አግኝተው ቢዝነሳቸውን ለማቀላጠፍና ለማሳደግ በእጅጉ የሚቸገሩ ሆነው ቆይተዋል፡፡
ሰሞኑን ‹‹ለጥቃቅን፣ ለአነስተኛና ለመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች በመረጃ የተደገፈ የዲጂታል ብድር ለአካታች ኢኮኖሚ›› በሚል ርዕሰ በተካሄደው ኮንፈረንስ ላይ ይኼው የአነስተኛ ተቋማት የፋይናንስ ተደራሽነት ችግሮችና የዲጂታል የፋይናንስ አቅርቦት ሊያስገኝ የሚችለውን ዕድል በተመለከተ ውይይት ተደርጓል።
ጥቃቅን አነስተኛና መካለኛ ኢንተርፕራይዞች ለኢኮኖሚ ዕድገት፣ እንዲሁም ለሥራ ፈጠራ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያላቸው ቢሆንም፣ የፋይናንስ አቅርቦት ተጠቃሚ አለመሆናቸው ለዕድገታቸው ከፍተኛ እንቅፋት ነውም ተብሏል፡፡
በኢትዮጵያ ጥቃቅን፣ አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ወደ 4.9 ቢሊዮን ዶላር የሚሆን ያልተሟላ የፋይናንስ አቅርቦት ፍላጎት እንዳላቸው የአይኤፍሲ ጥናት ያሳያል፡፡ ከዚህ ውስጥ 91 በመቶ የሚሆነው ክፍተት አነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚገጥማቸው ነው፡፡ ይህ ትልቅ ክፍተትና ፍላጎት የካፒታል ኢንቨስትመንትን ማሽን ግዥ፣ የውጭ ምንዛሪና ሥራ ማስኬጃ የፋይናንስ ፍላጎቶችን ያካተተ እንደሆነ በመድረኩ የቀረበው መረጃ ያሳያል፡፡
በመሆኑም በማደግ ላይ ላሉ አገሮች የጥቃቅን፣ የአነስተኛና የመካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ችግር መፍታት ለኢኮኖሚ ዕድገትና ድህነት ቅነሳ ወሳኝ ሚና ስለሚጫወት በዚህ ላይ አበክሮ መሥራት እንደሚገባም በውይይት መድረኩ ላይ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ ያለው ልምድ ሰፋፊ ብድሮችን መስጠት በመሆኑ፣ ይህ መለወጥ እንዳለበት አቶ ሙኒር ገልጸው፣ የብድር አሰጣጥ አነስተኛና ጥቃቅን ቢዝነሶችን ያገናዘበ መሆን እንዳለበትም አክለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ በዲጂታል መንገድ የሚቀርብ አነስተኛ ብድር አሰጣጥ ቀዳሚው አማራጭ መሆኑ ጎልቶ ተንፀባርቋል፡፡
በአፍሪካ በአነስተኛና ጥቃቅን አቅርቦት ረገድ እንደ ምሳሌ ከሚጠቀሱት ውስጥ ጋና፣ ናይጄሪያና ኬንያ ናቸው፡፡ ለምሳሌ በኬንያ ያለ ዋስትና የሚቀርብ ብድር ተጠቃሚዎች ቁጥር 30 ሚሊዮን ደርሷል፡፡
እንድ ጉሊት ነጋዴ በኬንያ ሌሊት ላይ ብድር ወስዳ፣ አትክልት ገዝታ፣ ከሰዓት በኋላ አትክልቱን ሸጣ ትርፍ አግኝታ ብድሩን የምትመልስበት ሥርዓት መፈጠሩን አቶ ሙኒር አውስተዋል፡፡ እንዲህ ያለው ዕድል ኢትዮጵያ ውስጥ እየመጣ ስለመሆኑ በተጨባጭ የታዩ ልምዶች እንዳሉም ጠቅሰዋል፡፡ ከእነዚህ መካከል የኦሮሚያ የኅብረት ሥራ ባንክ ከስድስት ወር በፊት የዲጂታል የማክሮ ብድር ከጀመረ በኋላ ሰማንያ ሺሕ ለሚሆኑ አነስተኛ ተበዳሪዎች ያለ ዋስትና ብድር አቅርቧል፡፡ ሌላው እንደ ምሳሌ የተጠቀሰውና በውይይት መድረኩ ላይ ተሞክሮውን ያካፈለው ኢትዮ ቴሌኮም ነው፡፡ ኢትዮ ቴሌኮም ከዳሸን ባንክ ጋር በመተባበር ለአንድ ሚሊዮን የሚደርሱ አነስተኛ ተበዳሪዎች ተጠቃሚ ማድረግ የቻለበትን ዕድል ፈጥሯል፡፡ እነዚህ ተሞክሮዎች ሌላው የሚማርበት ከመሆኑም በላይ የዲጂታል መንገድ አነስተኛ ብድሮችንና የፋይናንስ አገልግሎቶችን በቀላሉ ማቅረብ የሚቻል መሆኑን ነው፡፡
እንደ አቶ ሙኒር ዱሪ ገለጻ፣ ዲጂታል የፋይናንስ አገልግሎት ብዙ ጠቀሜታ አለው ቀልጣፋና አሳላጭ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ግን በተፈለገው መጠን እያቀረበ አይደለም፡፡
‹‹በኢትዮጵያ በፋይናንስ ዘርፉና በዲጂታል ሥርዓት መካከል ከእርስ በርስ መማማርና ዕውቀት ማጋራት የለም ብዬ አምናለሁ፤›› ያሉት አቶ ሙኒር፣ ‹‹በአሁኑ ዘመን ዕውቀት በትንሽ ሰዎች የተወሰነ ሳይሆን፣ ማንም ለመማር የሚፈልግ ሰው ሊያገኘው የሚችል ነው፤›› ይላሉ፡፡ ዕውቀትን ዲሞክራታይዝድ ማድረግ የመጫወቻ ሜዳውን ለሁሉም ተዋናዮች እኩል ለማድረግና በአጠቃላይ ዘርፉን በማሳደግ ለደንበኞች ጥራት ያለው አገልግሎት ለመስጠት እንደሚቻል አስረድተዋል፡፡
የዓለም አቀፍ ፋይናንስ ኮርፖሬሽን የሌሎች አፍሪካ አገሮች ተሞክሮዎችን ከኢትዮጵያ ሁኔታዎች ጋር በማነፃፀር ጥቃቅንና አነስተኛና መካከለኛ ተቋማትን፣ እንዲሁም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎችን በዲጂታል ፋይናንስ አገልግሎት ተጠቃሚ ማድረግ ሁነኛ መፍትሔ ነው ብሏል፡፡
የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ምክትል ገዥ አቶ ሰለሞን በበኩላቸው፣ የዲጂታል የብድር አቅርቦት ሰፊ ጠቀሜታ እንዳለው ጠቅሰው፣ በኢትዮጵያ የብድር አቅርቦትን ለማስፋት ብዙ ሥራዎች እየተሠሩና እየተተገበሩ መሆኑን ገልጸዋል፡፡ ለዚህም በብሔራዊ ባንክ በኩል አነስተኛና የተንቀሳቃሽ ዋስትና ሥርዓት ተግባራዊ ማድረጋቸውን በምሳሌነት አንስተዋል፡፡ በዚህ አሠራር ሶፋ ያለው እሱን አስይዞ የመበደር ዕድል ይሰጣል፣ በግና ፍየል ያለውም እሱን አስይዞ መበደር ይችላል፣ የመሬት የመጠቀም መብት ያለውም የመጠቀም መብቱን አስይዞ መበደር የሚችልበት አሠራር መኖሩን ጠቁመዋል፡፡ የመጋዘን ደረሰኝንም በማስያዝም ብድር ማግኘት የሚቻልበት አሠራር መኖሩን ገልጸዋል።
ሌላው ክሬዲት ጋራንቲ ስኪም (ለተበዳሪ ብድር ዋስትና የሚሰጥበት ሥርዓት) ሲሆን፣ ይህ አሠራር ከዲጂታል የብድር አቅርቦት አሠራር ጋር በማቀናጀት በተለይ አነስተኛ ተበዳሪዎችን ለመድረስ ሰፊ ዕድል እንዳለው አመልክተዋል፡፡ የተለያዩ አካላት በጋራ በመሆን የብድር አቅርቦትን መስጠት የሚያስችለውን ይህንን ሥርዓት ተግባራዊ ለማድረግ እየተሠሩ መሆኑን ገልጸዋል። ‹‹ለምሳሌ አንድ ሰው መቶ ብር ተበድሮ ባይመልስ አሥሩን እኔ እችላለሁ፣ ይህንን ያህል የእኔ ዋስትና እሰጣለሁ በሚሉ እንደ መንግሥትና የልማት አጋሮች ያሉ ተቋማት ድጋፍ ዜጎች ብድር የሚያገኙበት አሠራር ነው። ተከፋፍለው ዋስትና የሚጡበት አሠራር በመሆኑ፣ ይህም አሠራር የብድር ሽፋን በማሳደግ ረገድ ብቃት አለው፤›› ብለዋል፡፡ ይህንን ዓይነቱን አሠራር ለማስፋትም ከሚመለከታቸው አካላት ጋር በመሆን እየሠሩበት መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሌላው የብድር ሽፋንን ለማሳደግ የብድር መረጃ ሥርዓት አስፈላጊ በመሆኑ፣ በባንኮች እየተተገበረ ያለውን የብድር የመረጃ ሥርዓት አነስተኛ የብድር ተቋማት እንዲተገብሩት ማድረግ ነው፡፡ በመሆኑም ዲጂታል የታገዘ የብድር አቅርቦት ጠቀሜታው ታውቆ እንዲሰፋ የሚያደረግ ስለመሆኑ የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ ያለ ዋስትና ብድር እንዲቀርብ የሚያስችሉ አሠራሮችም እንዲተገበሩ የሚያደርግ ስለመሆኑ ሳይገልጹ አላለፉም፡፡
የውይይት መድረኩ ላይ በጉልህ እንደተንፀባረቀው፣ ለአነስተኛ ተበዳሪዎች ብድር መስጠት ተገቢ መሆኑንና ባንኮችም በዚህ መሳተፍ እንደሚገባቸው የተገለጸ ቢሆንም፣ በኢትዮጵያ የሚንቀሳቀሱ ባንኮችና ማክሮ ፋይናንስ ተቋማት የብድር የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ መሆኑን ነው፡፡ ለዋጋ ንረት መንስዔ አይሆንም ወይ የሚል ጥያቄ ተነስቷል፡፡ በዚህ ጥያቄ ዙሪያ ብሔራዊ ባንክ ምን ዓይነት ምልክታ እንዳለው ከሪፖርተር ለቀረበለት ጥያቄ አቶ ሰለሞን፣ ‹‹ይህ በገበያ ዋጋ የሚወሰን ነው፤›› ብለዋል፡፡ በጥያቄው ላይ በሰጡት ተጨማሪ ማብራሪያም የብድር ወለድ ምጣኔ ለገበያው የተተወ ስለመሆኑም አስረድተዋል፡፡
ከዚህ ቀደም የብድር ወለድ ምጣኔም ሆነ የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ ምጣኔ በመንግሥት ይወሰን እንደነበር ያስታወሱት አቶ ሰለሞን፣ አሁን ላይ ግን ሊብራላይዝ እያደረግን ስንሄድ ዝቅተኛውን የተቀማጭ ገንዘብ ወለድ ምጣኔን መንግሥት ሰባት በመቶ እንዲሆን ሲወስን የማበደሪያ የወለድ ግን በሙሉ ለገበያው እንዲተው ተደርጓል ብለዋል፡፡
ስለዚህ የብድር የወለድ ምጣኔ በአቅርቦትና ፍላጎት የሚወሰን እንደሆነ በመግለጽ፣ የብድር ወለድ ምጣኔው በብሔራዊ ባንክ በኩል በጣም ሄዷል ተብሎ አይታመንም የሚል ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ እንዲህም ሆኖ ግን የብድር ወለድ ምጣኔያቸው ወጣ ያሉ ነገሮች መኖራቸው የጠቀሱት አቶ ሰለሞን፣ እነዚህንም ቢሆን ገበያው ራሱ ሊመልሳቸው ይችላል የሚል አመለካከት እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡
በአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት ቴክኖሎጂን ተጠቅሞ ያለ ዋስትና የሚሰጥ ብድር ጠቀሜታ ያለው ቢሆንም፣ የወለድ ምጣኔ ከፍተኛ መሆን፣ እንዲሁም ያለ ዋስትና ብድር መስጠት አደጋ አይሆንም ወይ? የሚል መጠይቅ የቀረበላቸው አቶ ሙኒር ደግሞ የራሳቸው ምልከታ አላቸው፡፡
የወለድ ምጣኔው አድጓል አላደገም የሚለው በባንኮች የሚመለስ ነው የሚሉት አቶ ሙኒር፣ ነገር ግን እንደ አንድ የዘርፉ ተዋንያን ያላቸው ምልከታ ለታችኛው ኅብረተሰብ ክፍል የሚቀርበው ብድር አቅማቸውን ያገናዘበ ሊሆን ይገባል ይላሉ፡፡ በተለይ በዲጂታል የተደገፈ ብድር ሲጀመር የወለድ መጠኑ ይቀንሳል ብለው እንደሚጠቁሙም ገልጸዋል፡፡
እስካሁንም ለአነስተኛና ጥቃቅን ተቋማት የፋይናንስ አቅርቦት ተግዳሮት አንዱ ምክንያት የሚሰጠው ብድር ዲጂታል ላይ የተመሠረተ ያለመሆኑ ነው፡፡ የአንዱን ተበዳሪ የብድር ታሪክ የሚታይበት ዕድል ስለሌለ የወለድ ምጣኔ ከፍ ሊል ችሏል ብለው ያምናሉ፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ ተጨማሪ ማብራሪያ የሰጡት አቶ ሙኒር፣ እስካሁን በተለምዶ ኢትዮጵያ ውስጥ ያለውን ሪስክ በዋስትና ላይ መሠረት አድርጎ ነው የሚከላከለው፡፡ አፍሪካና ኤዝያ ላይ ግን ይህንን ሪስክ መመዘን የሚችል መመዘኛዎች እየተፈጠሩ ነው፡፡
በተለይም አርተፊሻል ኢንተለጀንስ ቴክኖሎጂ በጣም ዕድገት እያሳየ ስለመጣ ሪስክ ሜዠር የሚደረግበት አማራጮች ሰፊ እየሆኑ በመምጣታቸው ይህንን መሠረት አድርጎ መሥራት ሥጋቱን እንደሚቀንሰው ያምናሉ፡፡
በተለይ ዳታን የተመሠረተ የብድር አገልግሎት መስጠት ሲጀመር ግን በመሠረታዊ ደረጃ ለውጥ ይመጣል ብለው እንደሚያምኑ የገለጹት ሙኒር፣ የብድር ወለድ ላይ ትልቅ ለውጥ የሚጠብቁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡ በዕለቱ ከዚሁ ጋር በተያያዘ ልምዳቸውን ያቀረቡ ባለሙያዎችም በዚህ ሐሳብ ከመስማማታቸው በላይ ለአነስተኛና መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች የሚሰጠው ብድር ዳታን መሠረት ያደረገ መሆኑ ጠቀሜታው የጎላ ነው ብለዋል፡፡
በዚህ መድረክ ጥቃቅን፣ አነስተኛ መካከለኛ ተቋማትን እንዲሁም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው ገበሬዎችን በዲጂታል ፋይናንሻል አገልግሎት ተደራሽ ማድረግ ያለው ጠቀሜና ተግዳሮት ከተሞክሮዎች ጋር የተዳሰሰበትም ነበር፡፡
የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ካንትሪ ዳይሬክተር አቶ ሳሙኤል ያለው በበኩላቸው፣ የማስተር ካርድ ፋውንዴሽን ተመጣጣኝ የፋይናንስ አገልግሎት ለኢንተርፕራይዞች ተደራሽ እንዲሆኑ በማድረግ ሥራ ፈጠራን በከፍተኛ ደረጃ ለመጨመር ቁርጠኛ ነው፡፡ አገሪቱ ትኩረት ያደረገችባቸውን ጉዳዮችን በማገናዘብ ከግል ዘርፍ፣ ከተወከሉ ተቋማት፣ የሲቪል ማኅበረሰብ ተቋማትና ወጣቶች ጋር ኢንቨስት ሊደረግባቸው የሚችሉና በወጣቶች የሚመሩ ኢንተርፕራይዞች በበቂ ሁኔታ እንዲፈጠሩ እየሠራንም ነው ብለዋል፡፡ ‹‹የፋይናንሻል አገልግሎቶች ጥቃቅን አነስተኛ መካከለኛ ኢንተርፕራይዞች ሥራቸውን ለመሥራት የሚያስፈልጋቸውን ካፒታል መሸፈን አለባቸው ብለን እናምናለን፤›› ያሉት አቶ ሳሙኤል፣ ቴክኖሎጂንና ዘመናዊ አሠራርን መጠቅሞ የፋይናንሻል አገልግሎቶች ለሁሉም ተደራሽ እንዲሆኑ ለማስቻል ቁልፍ ሚና አላቸው፤›› ብለዋል፡፡
ለአነስተኛና ኢንተርፕራይዞች የሚቀርበው ብድር በማሳደጉ ረገድ ከዚህ በኋላ መልካምን ዕድል መኖሩን የሚጠቁሙት አቶ ሙኒር፣ ቴሌና የኦሮሚያ ኅብረት ባንክ ያስገኙትን ውጤት በምሳሌነት ጠቅሰዋል፡፡
የዲጂታል ኢኮኖሚው ያለ ዋስትና እነዚህን በመቶ ሺዎች ለሚቆጠሩ ጥቃቅንና አነስተኛ ተቋማት ከባንክ ሲስተሙ ብድር እንዲያገኙ አስችሏል፡፡ ስለዚህ እነዚህ ውጤቶች ምናልባት ኢትዮጵያ ከዚህ በኋላ ትልቅ የፋይናንስ ዘርፉ ዕድገት የምታሳየው ይሆናል ይላሉ፡፡
አሁን እየታየ ያለውን መልካም ጅምር ለማሳደግ ግን ሁሉም የፋይናንስ ተቋማት ውስጣዊ አሠራራቸውንና አመለካከታቸውን መለወጥና ጊዜውን የዋጀ መሆን እንደሚገባው ጠቅሰዋል፡፡ በአጠቃላይ የዲጂታል ሥርዓቱን ወደፊት ለመግፋት እንደ ትልቅ ሥራ የሚቆጠረውም ይህ ነው ብለዋል፡፡
ኢትዮጵያ ውስጥ በአብዛኛው የሚሰጠው ብድር ከፍተኛ መጠን ለሚፈልጉ ነው፡፡ የአነስተኛ ጥቃቅን ቢዝነሶች ለሥራቸው የሚፈልጉት ከ5 ሺሕ እስከ 150 ሺሕ ብር ሆኖ ሳለ፣ ይህንን ያህል ገንዘብ ቢሆንም ይህን ለማግኘት ይቸገራሉ፡፡
በዕለቱ የተደረገው ኮንፈረንስ ማጠቃላያ ላይ እንደተገለጸው፣ ፖሊሲ አውጪዎች፣ የፋይናንስ ተቋማት፣ የልማት አጋሮች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማትና ሌሎች የዘርፉ ተዋናዮች እንዲሁም ለዲጂታል ብድር ተደራሽነትና አካታችነት ላይ የሚሠሩ አካላት በኢትዮጵያ ሙሉ በሙሉ ወይም በበቂ ሁኔታ ተደራሽ ላልሆኑ አካላት ብድር እንዲያቀርቡ አጋጣሚ የሚፈጥር ነው፡፡