Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ተሟገት‹‹ወዝ አደሩ ያሸንፋል!››

‹‹ወዝ አደሩ ያሸንፋል!››

ቀን:

በአብዱ ዓሊ

ሃምሳ ዓመት ሊሞላው ከአንድ ዓመት በታች ብቻ በቀረው የኢትዮጵያ የጠላትነት ፖለቲካ ውስጥ (አሁንም ከሃምሳ ዓመት በኋላ ጨርሰን ድነን፣ ተፈውሰን፣ ከበሽታውም ነፃ ስለመሆናችን ማስረጃ ባልያዝንበት በዚህ ዓይነት የጠላትነትና የእኔ ብቻ ልክ ፖለቲካ ውስጥ) ለዚህ ጽሑፍ የመረጥኩት አርዕስት ራሱ ‹‹ጤነኛ›› አይደለም፡፡ ‹‹ነገር ፈላጊ››ነቱ ገና ጨርሶ አልቀረም፡፡ ወዝ አደር ነው? ላብ አደር? ያሸንፋል ነው? ያቸንፋል? ገና ጉዱን፣ ነውሩን፣ መሳቂያና ማፈሪያ ታሪኩን ተርኮ ጨርሶ ሒሳብ አወራርዶ፣ ገና ሙዚየም አልገባም፣ የሙዚየም ዕቃ አልሆነም፡፡ ሰኞ ሚያዝያ 23 ቀን የዋለው የሕዝብ በዓል ዕለቱን የሕዝብ በዓል አድርጎ በደነገገው የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ ቁጥር 16/1967 አንቀጽ 3 (1) (ቸ) ድንጋጌ የኦፌሴል ስያሜ/መጠሪያ መሠረት የዓለም ሠራተኞች የወዝ አደር ቀን (ሜይ ፩) ነው፡፡

አሁን ሥራ ላይ ያለው የአገራችን የአሠሪና ሠራተኛ ጉዳይ ሕግ አዋጅ ቁጥር 1156/2011 ነው፡፡ በዚህ የሠራተኛ ሕግ መሠረትም የሕዝብ በዓላት ጉዳይ ተደንግጓል፡፡ ስለዚህም አግባብ ባለው ሕግ መሠረት የሚከበሩ የሕዝብ በዓላት ደመወዝ የሚከፈልባቸው ናቸው፡፡ እንደተጠቆመው በዚህ የሥራ ሰዓትን፣ የሳምንት ዕረፍት ጊዜና በተለይም የሕዝብ በዓላትን በሚገዛው በኢትዮጵያ የአሠሪና ሠራተኛ ሕግ መሠረት አግባብ ያለው ሕግ ቢባል ከላይ የተጠቀሰው የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ ቁጥር 16/1967 (እንደተሻሻለ) ነው፡፡   

በዚህ ሕግ እንደተወሰነው፣ ሲወርድ ሲዋረድ የአገር ፖሊሲና ሕግ ሆኖ በዘለቀ እንግዳ ድንጋጌ መሠረት፣ ‹‹አንድ የሕዝብ በዓል ከሌላ የሕዝብ በዓል ጋር ቢደረብ ወይም በሕግ በተወሰነ የዕረፍት ቀን ላይ ቢውል፣ በዚያ ቀን የሠራ ሠራተኛ ክፍያ የሚደረግለት በአንዱ የሕዝብ በዓል ብቻ ይሆናል›› (አንቀጽ 75/2)፡፡ ይህ ምን ማለት ነው? ምርመራም ማብራሪያም የማያስፈልገው ጥሩ ምሳሌና ማስረጃ ትንሳዔ ነው፡፡ ትንሳዔ ሁልጊዜ እሑድ እንደሚውል (በሕግ አውጪውም ጭምር) የሚታወቅ የሕዝብ በዓል ነው፡፡ እሑድ ደግሞ በየሳምንቱ የሕዝብ የዕረፍት ቀን ነው፣ በሕግ፡፡ በሌላ አገር የሕዝብ በዓላት ሕጎች በተለይም የእነዚህ ሕጎች አፈጻጸም ኢትዮጵያ ውስጥ ጭምር ሲተገበር እንደሚታየው፣ አንድ የሕዝብ በዓል ከሌላ የሕዝብ በዓል ጋር ቢደረብ፣ ወይም በሕግ በተወሰነ የዕረፍት ቀን ላይ ቢውል (ለምሳሌ ፋሲካ) ሰኞ ወይም ተከታዩ ቀን የዕረፍት ቀን ነው፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች፣ መንግሥታዊ ያልሆኑ ድርጅቶች፣ ወይም የውጭ አገር መንግሥታት ተቋማት ውስጥ የሚሠሩ ሠራተኞች ይህንን ‹‹ዕድል›› እንቁልጭልጭ ሲሉን እናውቃለን፡፡ ሜይ ዴይ፣ ወይም መግቢያ ላይ በጠቀስኩት የሕዝብ በዓላትና የዕረፍት ቀን አዋጅ፣ እንዲሁም የሕዝብ በዓላት አከባበር አዋጅ ቁጥር 28/67 ‹‹የዓለም ሠራተኞች የወዝ አደር ቀን›› ተብሎ የተሰየመው የሕዝብ በዓል በሚከበርባቸው አገሮች ውስጥ በአብዛኛው በዕለተ ቀኑ ሜይ አንድ ላይ ሲከበር፣ በሌሎች የማይናቅ ቁጥር ባላቸው አገሮች ደግሞ ሜይ ወር ሲገባ በመጀመርያው ሰኞ ይከበራል፡፡ ይህ ኢትዮጵያ የሠራተኛና አሠሪ ሕግ፣ በተለይም የሕዝብ በዓላት ድንጋጌዎች ውስጥ ለምን ተፈልጎ ይታጣል ብሎ መጠየቅ አጉል መሞላቀቅ ባይሆንም፣ አስቀድመው መሠራት የሚገባቸው የሠራተኛውን መሠረታዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች መሠረት ማስያዝ የሚገባቸው ዋና ዋና ጉዳዮችን መጀመርያ መረባረቢያ ማድረግ የተባለውን መብት በሙሉ አስከትሎና አግተልትሎ የሚያመጣ ይመስለኛል፡፡

ከእነዚህ መብቶች አንዱና ዋነኛው የአገር የሠራተኛው ሕዝብ ሆድ ቁርጠት ሆኖ የኖረው የመደራጀት መብት ነው፡፡

‹‹ሰላማዊ ስብሰባ የማድረግና ማኅበር የማቋቋም የነፃነት መብት›› ከሌሎች መሠረታዊ መብቶችና ነፃነቶች ጋር የኢትዮጵያ የበላይ ሕግ አካል የሆኑት የኤርትራ ግዛት፣ ኢትዮጵያ መንግሥት ግዛት ጋር መቀላቀልን ከወሰነው ከፌዴራል ሕግ መስከረም 1 ቀን 1945 ዓ.ም. ጀምሮ ነው፡፡ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በአምስተኛው የስብሰባ ወራት ኅዳር 22 ቀን 1943 ዓ.ም. በዋናው ጉባዔ ስለኤርትራ ጉዳይ በቁጥር 390 (5) የሰጠው ውሳኔ የመጀመርያዎቹ ሰባት አንቀጾች (ፓራግራፎች) ናቸው መስከረም 1 ቀን 1945 ዓ.ም. ጀምሮ የፌዴራል አክት/ሕግ ተብለው የታወጁት፡፡ በትዕዛዝ ቁጥር 6/1945 ደግሞ የፌዴራል አዋጅና የ1923 ዓ.ም. ሕገ መንግሥት የአገሪቱ የበላይ ሕግ ሆኑ፡፡

ከ1945 ዓ.ም. ወደ 1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ተምዘግዝገን እንድረስ፡፡ ከሌሎች መካከል የ1987 ዓ.ም. የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት በአንቀጽ 42 የሠራተኞች መብትን  ይደነግጋል፡፡ እንዳለ ልጥቀሰው፡፡

አንቀጽ 42 የሠራተኞች መብት

ሀ. የፋብሪካና የአገልግሎት ሠራተኞች፣ ገበሬዎች፣ የእርሻ ሠራተኞች፣ ሌሎች የገጠር ሠራተኞች፣ ከተወሰነ የኃላፊነት ደረጃ በታች ያሉና የሥራ ፀባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች የሥራና የኢኮኖሚ  ሁኔታዎችን ለማሻሻል በማኅበር የመደራጀት መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት የሠራተኛ ማኅበራትንና የሌሎች ማኅበራትን የማደራጀት፣ ከአሠሪዎችና ጥቅማቸውን ከሚነኩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የመደራደር መብትን ያካትታል፡፡

ለ. በንዑስ አንቀጽ (ሀ) የተመለከቱ የሠራተኛ ክፍሎች ሥራ ማቆምን ጨምሮ ቅሬታቸውን የማሰማት መብት አላቸው፣

ሐ. በንዑስ አንቀጽ (ሀ) እና (ለ) መሠረት ዕውቅና ባገኙት መብቶች ለመጠቀም የሚችሉት የመንግሥት ሠራተኞች በሕግ ይወስናሉ፣

መ. ሴቶች ሠራተኞች ለተመሳሳይ ሥራ ተመሳሳይ ክፍያ የማግኘት መብታቸው የተጠበቀ ነው፣

  1. ሠራተኞች በአግባቡ የተወሰነ የሥራ ሰዓት፣ ዕረፍት፣ የመዝናኛ ጊዜ፣ በየጊዜው ከክፍያ ጋር የሚሰጡ የዕረፍት ቀኖች ደመወዝ የሚከፈልባቸው የሕዝብ በዓላት፣ እንዲሁም ጤናማና አደጋ የሚያደርስ የሥራ አካባቢ የማግኘት መብት አላቸው፡፡
  2. እነዚህን መብቶች ተግባራዊ ለማድረግ የሚወጡ ሐጎች፣ በዚህ አንቀጽ ንዑስ አንቀጽ 1 መሠረት ዕውቅና ያገኙትን መብቶች ሳይቀንሱ የተጠቀሱት ዓይነት የሠራተኛ ማኅበራት ስለሚቋቋሙበትና የጋራ ድርድር ስለሚካሄድበት ሥርዓት ይደነግጋሉ፡፡

በማኅበር የመደራጀትን መብት ሕገ መንግሥቱ በአንቀጽ 31 (በማናቸውም ሰው ለማንኛውም ዓላማ በማኅበር የመደራት መብት ላይ ብቻ) አደራውን ትቶ አላለፈም፡፡ ከላይ በተጠቀሰው የአንቀጽ 42 ድንጋጌ በግልጽ እንደተወሰነው በታወቀው የአሠሪና ሠራተኛ ‹‹ሠራተኛ›› ትርጉም ውስጥ ከሚሸፈኑ የሠራተኛ ዓይነት ላይ ብቻ አልተገደበም፡፡ ሌሎችም ‹‹ከተወሰኑ ኃላፊነት ደረጃ በታች ያሉና የሥራ ፀባያቸው የሚፈቅድላቸው የመንግሥት ሠራተኞች…›› ጭምር በማኅበር የመደራጀት መብት አላቸው፡፡ ይህ መብት ትርጉም፣ ፋይዳና አገልግሎት አለው፡፡ ‹‹የሥራና የኢኮኖሚ ሁኔታዎችን ለማሻሻል›› መሣሪያ ነው፡፡ ከአሠሪዎችና ጥቅማቸውን ከሚነኩ ሌሎች ድርጅቶች ጋር የመደራደሪያ መሣሪያ ነው፡፡ የሠራተኞች ቅሬታ የማሰማት መብት በሕገ መንግሥቱ፣ በራሱ በዚህ ድንጋጌ እንደተመለከተውና ሕግም በሚገዛው መሠረት ሥራ ማቆምን ይጨምራል፡፡ ከነሐሴ 15 ቀን 1987 ዓ.ም. ጀምሮ ‹‹ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ውሏል›› ተብሎ የታወጀው ይህ ሕገ መንግሥት (የዚህ ሕገ መንግሥት አንቀጽ 42 ድንጋጌ ግን) ዛሬም ድረስ የአንቀጽ 42 (1) (ሐ) እና 42 (3) ዝርዝር በሕግ አልተወሰነም፡፡

ጎዶሏችን ግን ይህንን የቤት ሥራ (ዝርዝሩ በሕግ ይወሰናል) አለመውጣታችን ብቻ አይደለም፡፡ ሕግ ያላቸው፣ ዝርዝር ሕግ የወጣላቸው፣ የሕግ ችግር የሌለባቸው፣ የሠራተኛ መብቶችና ነፃነቶች የአገር መኗኗሪያ መሆን ያልቻሉት እነዚህ ሕግ ያላቸው፣ ሕግ የወጣላቸው መብቶችና ነፃነቶች በተግባርና በተጨባጭ ሕይወትና ኑሯችን ውስጥ የሚታዩ፣ ከገዥዎች የቁርጠኝነት መሃላ ውጪ የሚኖሩ ማድረግ ባለመቻላችን ነው፡፡ መብቶቻችንና ነፃነቶቻችን የምር መኗኗሪያችን ይሆኑ ዘንድ በሥልጣን ላይ ያለ አካልም ሆነ ሌላ ማንኛውም ጉልበተኛ ሲያሻው ሊነጥቀን በማይችልበት ማኅበራዊ ልማት ውስጥ መግባትና ይህንንም መደላድል መገንባት አለብን፡፡ የኢትዮጵያን የዴሞክራሲ ግንባታ ለዘመናት ሲታገለውና ሲያሰናክለውም የኖረው የመንግሥት አውታራት ገለልተኝነት አለመኖሩ ነው፡፡ በየትኛውም ደረጃ ማለትም በፌዴራልም ሆነ በክልል ወይም ከዚያ በታች የሚገኙ መንግሥታዊ ዓምዶች ገለልተኛ ሆነው መታነፅ ይጎድላቸዋል፡፡ መንግሥት በጠቅላላና የሥልጣን አካላቱ፣ እንዲሁም በሲቪልና ወታደራዊ ቢሮክራሲው በመላ ሰብዓዊ ክብርንና መሠረታዊ መብቶችንና ነፃነቶች የሚያከብር፣ የሚያስከብር፣ ለዚህም ሲባል ሁሉንም ዓይነት መንዕስ ሁኔታዎች በሥፍራቸውና በቦታቸው የሚያደላድል፣ ከእምነቶች፣ ከወገንተኛነት፣ ወገን ለይቶ ከመሠለፍ የተከለከለ ሆኖ መታመፅ ይጎድለዋል፡፡ እንደ ዳኛ የወል፣ እንደ ምሰሶ የመሀል ይባላል፡፡ ገለልተኝነትን ወይም ኢአድሏዊነትን ለመመሰል ዓይኗን በጨርቅ የተጋረደች ሴት ለፓርቲያዊ መሆን ወይም ለብሔርተኛ ወይም ለሌላ እምነት አድልኦ ዓይናቸው የተጋረደ ሆኖ፣ የሁላችንም የጋራ አለኝታ ተደርገው ለመታየት የበቁ መንግሥታዊ አውታራት ያልተገነቡበት፣ ዘላቂነታቸውም መተማመኛ ያላገኘበት አገር ‹‹ማንም ስለማይሰጠው፣ ማንም ስለማይከለክለው›› (ማንም ስለማይነጥቀው) መብትና ነፃነት ሊናገር አይችልም፡፡

የሠራተኛው መብቶች የሚረጋገጡት እርግጠኛና ዘላቂ መተማመኛና ዋስትና የሚያገኙት መንግሥታዊ አውታራት ከቡድን ታማኝነት ሲላቀቁ፣ ገዥው በሕዝብ ድምፅ የሚወጣና የሚወርድበት ሥርዓት ሲዘረጋ ነው፡፡ የአንድ ፓርቲ ገዥነት በነፃና በፍትሐዊ ምርጫ ላይ ብቻ የተንጠለጠለ ሲሆን ነው፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ላብ አደሮችም ሆነ ወዝ አደሮች፣ እንዲሁም የኢትዮጵያ ሕዝቦች መብቶቻቸውንና ነፃነቶቻቸውን መኗኗሪያ ለማድረግ፣ እነዚህንም ማንም የማይሰጣቸው ማንም የማይነጥቃቸው የተፈጥሮ መብቶች ናቸው ለማለት የአገሪቱን የመንግሥት አውታራት ገለልተኛ አድርጎ ማቋቋም ይኖርበታል፡፡

ይህ የትግል ምዕራፍ፣ ተጠናዋች ቢያጋጥመውም፣ ጦርነት ያህል ፈተና ቢገጥመውም ከአምስት ዓመታት በፊት ተጀምሯል፡፡ የኢትዮጵያ ሠራተኞች ይህንን አሁንም ብዙ ፈተና ያጋጠመውን የትግል ፈር፣ አስቀድሞ ዴሞክራሲን የማደላደል የትግል መስመር መከተል አለበት፡፡ ወዝ አደሩ ማሸነፉን የምናረጋግጠው በዚህ መንገድ በኩል ስንጓዝ ነው፡፡

ወደ ዓለም አቀፋዊ የሠራተኞች ቀን ክብረ በዓል መለስ እንበል፡፡ ‹‹የዓለም ሠራተኞች የወዝ አደር ቀን›› በዚህ ስያሜ በሚታወቀበት አዋጅ ቁጥር 17/1967 የሕዝብ በዓል ሆኖ እንዲከበር ከተደነገገበት ጊዜ ጀምሮ (ይህ አዋጅ የፀናው በነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ከጥር 9 ቀን 1967 ዓ.ም. ጀምሮ) ነው፡፡ ስለዚህም ከሚያዝያ 1967 ዓ.ም. አንስቶ በሕዝብ በዓልነት ሲከበር ኖሯል፡፡ ሲከበር ኖሯል ማለት ብዙ፣ ልዩ ልዩነት ያለው ታሪክ ያለው ነው፡፡ በዚያ ደመኛና በአመዛኙ የጠላትነት ፖለቲካ በነገሠበት ፖለቲካ ውስጥ ሜይ ዴይ ደም ፈሶበታል፣ ዕልቂት ተፈጽሞበታል፡፡ ሰላማዊ ትግል በተጨናገፈበትና ምናልባትም እርም በተባለበት ማዕቀፍ ዳራ ውስጥ ተቃውሞና ቅሬታ ተስተጋብቶበታል፡፡ በአመዛኙ ግን ‹‹አብዮታችን የደረሰበት የዕድገት ደረጃ›› የሚያሳይ/ሪፖርት የሚያደርግ የፍሎት ወይም ‹‹Flot›› ትርዒት ታይቶበታል፡፡ በአብዛኛው ከገዥው ፓርተ ቁጥጥር ባልወጣ፣ እንዲያውም የእሱ ፈቃዶች፣ ምኞትና ቴአትር የሚከወንበት የ‹‹ግዳጅ›› የዕረፍት ቀን ሆኖ ኖሯል፡፡ የሕዝብ በዓላት አከባበር አዋጅ ቁጥር 28/1967 እንደሚደነግገውም (ይህ አዋጅ በአብዛኛው ከሌሎች የተዘረዘሩ የሕዝብ በዓላት አከባበር ጋር በተያያዘ ሥራ ላይ ባለመዋሉ፣ ባለመለመዱ፣ ወይም ባለመዘውተሩ፣ ወዘተ ምክንያት ሳይሻር ከአገልግሎት ውጪ የወጣ ወይም ያረጀ ያፈጀ ሕግ የሚባል ነው፡፡

ፈረንጆች (‹‹Desuetude›› ዴስቲዊድ ይሉታል) የአከባበር ሥርዓት ተዘርግቶለት ነበር፡፡ በተጠቀሰው ብዙ ጊዜም ሥራ ላይ ውሎ በሚያውቀው በዚህ ሕግ መሠረት ‹‹እ.ኤ.አ. ግንቦት 1 ቀን የዓለም አቀፍ የወዝ አደር ቀን በመሆኑ እንደሚከተለው ይከበራል፣

  • ወዝ አደሩ ሠራተኛ የሠራተኞችና የገበሬዎች ማኅበሮች፣ ምሁሮችና ተማሪዎች ሰፊው የኢትዮጵያ ሕዝብ ተካፋይ በሚሆንበት ከፍ ባለ ሥርዓት ይከበራል፣
  • ርዕሰ ብሔሩ ወይም ርዕሰ መንግሥቱ በበዓሉ ላይ በመገኘት ለሰፊው ሕዝብ ስለወዝ አደሩ ሠራተኛ አቋምና ዓላማ ንግግር ያደርጋል፣ እንዲሁም
  • የሠራተኞች ማኅበር መሪ ስለበዓሉ ታሪካዊነት ለሰፊው ሕዝብ ንግግር ያደርጋል ይላል›› ወይም ይል ነበር የአከባበር ሕጉ፡፡

የዘንድሮው ሜይ ዴይ (ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ወይም ሜይ ዴይ 2023) እንዴት እንደሚከበር በዋዜማው ቀናት/አካባቢ የነገሩን በሪፖርተር የሚያዝያ 22 ቀን ዘገባ መሠረት የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ፕሬዚዳንት ናቸው፡፡ የሪፖርተር ዘገባ አርዕስት ‹‹ኢሠማኮ በሰላማዊ ሠልፍ ለመንግሥት ጥያቄ እንደሚያቀርብ አስታወቀ›› ይላል፡፡ ከዜናው እንደተረዳነው፣ ‹‹ለሠራተኛው መሠረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሔ›› የሚል መሪ ቃል አለው የተባለው፣ ለመንግሥት በአደባባይ ሠልፍና ፓናል ውይይት የሚቀርበው ጥያቄ በግንባር ቀደምትነት የኑሮ ውድትን ችግር የመጀመርያው አድርጓል፡፡ የዝቅተኛው መነሻ ደመወዝ ሕግ ጥያቄ ሌላው አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡ የሠራተኞች የመደራጀት መብት ጥሰት ከፍተኛ ምናልባትም አደገኛ ደረጃ ላይ ደርሷል ተብሎ የተገለጸ ጉዳይ ነው፡፡ ሌላው የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር ያወጣው የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የ20/80 የተባለ መመርያ አለመከበር የሚመለከተው ነው፡፡ ከሠራተኞች ደመወዝ፣ የትራንስፖርትና የውሎ አበል ላይ የሚከፈለው ግብር ጉዳይ ከጥያቄዎች መካከል ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዞ ጭምር የሚቀርብ ጥያቄ ነው፡፡  

ሚያዝያ 23 ቀን ዋዜማ ላይ ይህንን ሰምተን፣ በዓሉ እየተቃረበ መጥቶ ነገ ሰኞ ነው ሲባል እሑድ ምሽት ላይ አዲስ አበባ ፖሊስ የፌስቡክ ገጽ ላይ፣

‹‹ነገ በአዲስ አበባ ከተማ ምንም ዓይነት የአደባባይ ኩነት ወይም ሠልፍ አለመኖሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታወቀ፡፡ ሕግን የማስከበር ተግባሩንም አጠናክሮ እንደሚቀጥል ፖሊስ አሳስቧል፡፡

‹‹ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. የላብ አደር ቀን ይከበራል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ በፀጥታና ደኅንነት ግብረ ኃይል ስም ለመላው የአገራችን ላብ አደሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን አስተላልፏል፡፡ የላብ አደር ቀንን አስመልክቶ በአዲስ አበባ ከተማ ምንም ዓይነት የአደባባይ ኩነቶች፣ ሠልፍ፣ እንዲሁም ፖሊስም ሆነ የአስተዳደር አካላት የሚያውቁት ምንም ዓይነት ስብሰባ አለመኖሩ የአዲስ አበባ ፖሊስ አስታውቋል፡፡ ማኅበረሰቡ ከፀጥታው አካል ጎን በመቆም ለፀጥታ ሥራው ስኬታማነት እያደረገ ላለው ድጋፍ ምሥጋናውን ያቀረበው ፖሊስ ኅብረተሰቡ የተለመደው ቀና ትብብሩን አጠናክሮ እንዲቀጥል ጥሪውን አስተላልፏል፡፡››

ወዲያውኑ ይህ መግለጫ በተሰጠበት በዚያው ዕለት ሚያዝያ 22 ቀን 2015 ዓ.ም. በኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የተፈረመው አድራሻውን ‹‹‹ለሁሉም የመገናኛ ብዙኃን›› ያደረገው ደብዳቤ በዲጂታል ሚዲያው ተሠራጨ፡፡ ‹‹የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ በዓል መሰረዙን›› አስታወቀ፡፡

የደብዳቤው ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ይነበባል፡፡

‹‹የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በየዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን የዓለም የሠራተኞች ቀን (ሜይ ዴይ) በዓል በተለያዩ ዝግጅቶች ሲያከብር መቆየቱ ይታወቃል፡፡ በዘንድሮ 48ኛው የሜይ ዴይ በዓልን በአዲስ አበባና ቅርጫፍ ጽሕፈት ቤቶች በሚገኙበት በሰላማዊ ሠልፍ ለማክበር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ የበዓሉን አከባበርና አጠቃላይ መርሐ ግብር አስመልክቶ ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ በመገናኛ ብዙኃን ማስተላለፉ ይታወሳል፡፡

‹‹ነገር ግን ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በዓሉን ለማክበር የተያዘው ፕሮግራም የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ቢሮ ስለከለከለን ፕሮግራሙን ለመሰረዝ የተገደድን መሆኑን እየገለጽን፣ ይህንኑ መልዕክት ለኢትዮጵያ ሠራተኞች በሚዲያችሁ አማካይነት እንድታስተላልፉልን የተለመደ ትብብራችሁን እንጠይቃን፡፡››

ይህ ይፋ እንደሆነ በዚያው በእሑዱና በሰኞ መካከል ባለ አጭር ጊዜ ውስጥ በአንዳንድ የመገናኛ ብዙኃን የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት የሰጡትን የቃል/የቃለ ምልልስ ማብራሪያ አሰሙን፡፡ ዝርዝሩ የኮንፌዴሬሽኑ ፕሬዚዳንት እንዳነጋገራቸው ሚዲያ፣ ‹‹ፕሮግራም›› የተለያየና ብዙ ወይም ዘርዘር ያለ ነው፡፡ በአጠቃላይ ዋናው ቁምነገር ግን ከልካዩ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ፀጥታ ቢሮ መሆኑን ሰምተናል፡፡ በሁለቱ መሥሪያ ቤቶች ማለትም በኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን ኃላፊ/ተወካይና በአዲስ አባባ ከተማ አስተዳደር የፀጥታ ቢሮ ተወካይ መካከል የፖሊስ የክልከላ መግለጫ/ማስታወቂያ ከተሰጠ በኋላ የተደረገው ንግግር የስልክ እንደሆነም ይታወቃል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግም ይህ የስልክ ንግግር ኮርዲያል/Cordial (ማለትም በወዳጅነትና በፍቅር፣ በጨዋታነት ስሜት ውስጥ የታጠረ) እንዳልነበረ ጠቋሚ መግለጫዎች/ምልክቶች ሰምተናል፡፡

ነገ ‹‹የላብ አደር ቀን ይከበራል፡፡ የአዲስ አበባ ፖሊስ በፀጥታ ደኅንነት ግብረ ኃይል ስም ለመላው የአገራችን ላብ አደሮች የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክቱን›› ያስተላልፋል ማለት ድረስ እጁን የዘረጋው፣ እዚሁ የመልካም ምኞት መግለጫ ያስተላለፈው፣ የደስታው ተካፋይ መሆኑን የገለጸው ፖሊስ ሕግና ፀጥታ የማስከበር ኮንሰርን/ሥጋት/ጭንቀትና ደንታ ወይም አደጋ የመከላከል ዝግጅነት/ቅድመ ዝግጅነትና መጨነቅ መጠበብ የገዛ ራስን የሕግ አክባሪነት የውኃ ልክ ማስገመት ብቻ ሳይሆን፣ አንድ የአገር የሕዝብ በዓል ሳይከበር እንዲቀር ማድረጉ ተሰምቶታል?

‹‹ነገ [ሚያዝያ 23 ቀን ወይም በየዓለም ሠራተኞች የወዝ አደር ቀን] በአዲስ አበባ ከተማ ምንም ዓይነት የአደባባይ ኩነት ወይም ሠልፍ አለመኖሩ [ን]…›› አስታውቃለሁ ሲል ለሕጋዊነት ወግ እንኳን አለመጨነቁ አያሳስብም?  

ማኅበሩ/ኮንፌዴሬሽኑ ያለው፣ ለማለትም የፈለገው የተናገረው ነው፡፡ ‹‹ለሠራተኛው መሠረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሔ›› እንፈልጋለን አለ፡፡ እግዜር ይስጠውና ከዚያ በላይ የሚያስፈራራና የሚያስደነግጥ አልቲመተም አልሰጠም፡፡ ዋ! በዚህ ቀን ውስጥ ወይም ሱሪ በአንገት አውጡ አላለም፡፡

እነዚህን ጥያቄዎች በአዲስ አበባ፣ በአዳማ፣ በጅማ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ በአደባባይ ሠልፍና በፓናል ውይይት ላይ አነሳለሁ፣ በባህር ዳርና በኮምቦልቻ ደግም ይህንን ማድረግ የሚያስችል አመቺ ነገር ስለሌለ እሱን ትቻለሁ ነው ያለው፡፡ ይህንን የመሰለ ‹‹የሕዝብ በዓል›› ማክበርን በመሰለ ማዕቀፍ ውስጥ አንድ አገር አቀፍ ማኅበር፣ ለመብቶች ትግል መታገል የቆመ ማኅበር ከሞላ ጎደል በዋነኛነት ዓመቱን በሙሉ ሲዘጋጅለት የቆየውን የዓለም ሠራተኞችን ቀን በዓል ዝም ብሎ ያለ አማራጭ፣ ያለ ሌላ መላና ብልኃት ሲዘጋና ዝጋ ሲል… ከዚያም በኋላ የሚያዝያ የመጨረሻ ሳምንት ያላንዳች አደጋ ‹‹ቀኑ መሽቶ ሲነጋ›› ያየነው ‹‹በኪነ ጥበቡ››፣ በ‹‹መለኮታዊ ኃይል›› ምክንያት ነው ወይስ በእኛ ‹‹ጥበብ›› እና ችሎታ ነው?

የሚያዝያ 23 ፋይዳ ከሠራተኛው ሕይወት፣ ህልውና፣ መብትና ነፃነት አኳያ ይቅር አይነሳ፣ የሌላ ጊዜ ጉዳያችን ይሁን ቢባል እንኳን፣ የፖሊስ በዕለት ተዕለት ሥራው ሲጋፈጠው እንደሚያውቀው ሌላው ቢቀር ዕለቱ በወንጀል ሕጉ አንቀጽ 817 እንደተደነገገው ‹‹የግዴታ እንዲከበር በሕግ የተወሰነ በዓል›› ነው፡፡ ከዚህ በላይ ደግሞ  መንግሥት በተለይም በአዲስ አበባ ፖሊስ አማይነት፣ መንግሥት የራሱን ውስን አስተሳሰብና ተግባራት፣ እንዲሁም ፍላጎትና ትዕዛዝ ከውይይት በላይ አድርጎ፣ ሌላው ወገን ሰሚና ጆሮ ብቻ እንዲሆን በማድረጉ ከአደጋ የተረፍነው ድንገት፣ በአጋጣሚና ዕድለኛ ሆነን እንጂ ፍጥርጥራችን በዘረጋውና ባበጀው መከላከያ አለመሆኑን ከድንጋጤ ጋር መረዳት አለብን፡፡ ‹‹የዓለም ሠራተኞች የወዝ አደር ቀን›› የሕዝብ በዓል ነው፡፡    

ከአዘጋጁ፡- ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...