Friday, June 2, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ስፖርትለኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና መዘጋጃ የሆነው የእንጦጦ የአትሌቶች መለማመጃ መታጠሩ ቅሬታን አስነሳ

ለኦሊምፒክና የዓለም ሻምፒዮና መዘጋጃ የሆነው የእንጦጦ የአትሌቶች መለማመጃ መታጠሩ ቅሬታን አስነሳ

ቀን:

የበርካታ አንጋፋ አትሌቶች የልምምድ ሥፍራ የነበረው የእንጦጦ ሜዳ መታጠር ቅሬታን አስነሳ፡፡

ከቀድሞ አሠልጣኝ ወልደ መስቀል ኮስትሬ (ዶ/ር) ዘመን አንስቶ ኃይሌ ገብረ ሥላሴ፣ ደራርቱ ቱሉ፣ ቀነኒሳ በቀለ፣ እንዲሁም በርካታ አንጋፋ አትሌቶች ልምምድ ሠርተው ያለፉበት የእንጦጦ ሜዳ ለሌላ ግንባታ ለማዋል ተላልፎ መሰጠቱ ተሰምቷል፡፡

የበርካታ አትሌቶች የልምምድ ሥፍራ የሆነው እንጦጦ ሜዳ ወይም በተለምዶ ‹‹ብሔራዊ ቡድን ሜዳ›› በመባል የሚታወቀው የልምምድ ሥፍራ መታጠሩ እንዳሳሰባቸው አሠልጣኞች ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

የተለመደው የዕለት ተዕለት ልምምድ ለማድረግ ወደ ሜዳው አትሌቶቻቸውን ይዘው ወደ ሥፍራው ያቀኑ አሠልጣኞች ሥፍራው ለልማት በመፈለጉ እንደታጠረ እንደተገለጸላቸው የረዥምና የመካከለኛ ርቀት አሠልጣኝ ብርሃኑ መኮንን ለሪፖርተር አስረድተዋል፡፡

የአብዛኛዎቹ አትሌቶች መዋያ መሆኑ የተነገረለት የእንጦጦ የአትሌቲክስ ሜዳ በአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ወ/ሮ አዳነች አቤቤ አማካይነት ግንባታ ለማከናወን ከወራት በፊት የመሠረት ድንጋይ መቀመጡ ተገልጿል፡፡

‹‹በከተማዋ አማራጭ የአትሌቲክስ የማዘውተሪያ ሥፍራ አለመኖሩ እየታወቀ ‹አንድ ለእናቱ› የሆነው የአትሌቶቹን የልምምድ ሜዳ መቀማት አግባብ አይደለም፤›› በማለት አሠልጣኝ ብርሃኑ ለሪፖርተር አስተያየታቸውን ስጥተዋል፡፡

እንደ አሠልጣኙ አስተያየት ከሆነ ሥፍራው ለልማት የመፈለጉ ወሬ ከተሰማበት ጊዜ አንስቶ ጉዳዩ ስላለሳሰባቸው ‹‹ሜዳውን አድኑልን›› ብለው ለኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽንና የአትሌቶች ማኅበር ቅሬታ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡

በየዕለቱ ከ100 አትሌቶች በላይ በሥፍራው ላይ ልምምድ እንደሚያደርጉ የተገለጸ ሲሆን፣ በተለይ አትሌቶች የዳገት ልምምድ፣ የፍጥነት ማዳበሪያ ልምምድ እንዲሁም የአካል ብቃት እንቅስቃሴ ልምምዶች ተመራጭ መሆኑን ይነገራል፡፡

በአንፃሩ ሥፍራው ለአቅመ ደካማ እናቶችና ሴቶች የሥራ ፈጠራ የሚውል ማምረቻ እንዲሁም የመኖሪያ ቤት ግንባታ ፍጆታነት ለማዋል ታቅዶ መታጠሩ ተጠቅሷል፡፡  

በጉለሌ ክፍለ ከተማ ሥር የሚገኘውና ከ20 ዓመታት በላይ የአትሌቶች ልምምድ የማድረጊያ ሥፍራ የሆነው እንጦጦ ሜዳ የተለያዩ የሥልጠና ዓይነቶች ሲሰጡበት እንደነበር፣ የረዥም ርቀት አሠልጣኙ ሁሴን ሼቦ (ኮማንደር) አስተያየታቸውን ለሪፖርተር ሰንዝረዋል፡፡

እንደ አሠልጣኙ አስተየያት ከሆነ ሥፍራው ኢትዮጵያውያን አትሌቶች ለከፍታ ልምምድ ካላቸው ቦታዎች አንዱ መሆኑን ጠቅሰው፣ በተለይ ብሔራዊ ቡድን ለሚያደርገው ዝግጅት ተመራጭ መሆኑን ያስታውሳሉ፡፡ የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ብሔራዊ ቡድን ለዓለም አቀፍ ሻምፒዮናዎች ዝግጅት ሲያደርግ ለአቅም ግንባታ፣ ለአገር አቋራጭ ውድድሮች እንዲሁም የመም (ትራክ) ዝግጀት ይጠቀሙበት እንደነበር አሠልጣኝ ሁሴን ለሪፖርተር አብራርተዋል፡፡

‹‹በአገሪቱ በማዘውተሪያ ሥፍራ ዕጦት እየተፈተነ ያለው አትሌቲክሱ በመንግሥት መፍትሔ ሊበጅለት ይገባል፡፡ አትሌቲክሱ ለአገሪቱ እያበረከተ ያለው አስተዋጽኦ መንግሥት የተገነዘበው አይመስለኝም፤›› በማለት ሁሴን (ኮማንደር) ያስረዳሉ፡፡

አሠልጣኙ ሲያክሉም አትሌቲክሱ ለአገሪቱ የውጭ ምንዛሪ ከማስገኘት አንፃርና የዘመኑ አንዱ የቢዝነስ መንገድ መሆኑን መንግሥት መዘንጋቱን ጠቅሰው፣ በተለይ ለእግር ኳሱ የሚሰጠውን ትኩረት ያህል ሊሰጠው አለመቻሉ እንደሚያስቆጫቸው ለሪፖርተር ተናግረዋል፡፡

በእንጦጦ አካባቢ ማርያምን አለፍ ብሎ በሚገኘው ሥፍራ ሌላው የአትሌቶች በተለምዶ ‹‹አራት ሺሕ ጫማ›› የሚጠራው የልምምድ ስፍራ እንደነበር የሚገልጹት አሠልጣኝ ሁሴን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ለግንባታ እየተሰናዳ መሆኑን አክለዋል፡፡

ዋና ኢንስፔክተር ወንድዬ ደሳለኝ የፌዴራል ማረሚያ ቤት የመካከለኛ ርቀት ዋና አሠልጣኝ ሲሆኑ፣ ኢትዮጵያ በዓለም ሻምፒዮና እንዲሁም በኦሊምፒክ ያላት ታሪክ መነሻው የእንጦጦ ሜዳ መሆኑን ያወሳሉ፡፡

ሥፍራው፣ የአየር ንብረቱ እንዲሁም ከፍታው አመቺነት አንፃር ለአትሌቲክሱ ትክክለኛ ቦታ እንደሆነ ለሪፖርተር ያስረዳሉ፡፡

እንደ አሠልጣኙ አስተያየት ከሆነ ሥፍራውን ያላግባብ ተላልፎ መሰጠቱን ጠቅሰው፣ አትሌቲክስን በአግባቡ የተረዳ ባለሙያ ከተማ አስተዳደሩን ማማከር ቢቻል ውሳኔው ሊቀለበስ እንደሚችል እምነት እንዳላቸው አንስተዋል፡፡

‹‹አትሌቲክስን የተረዱ ግለሰቦች ለአመራሮች የልምምድ ቦታው ያለውን ጠቀሜታ ማስረዳት ቢችሉ እንዲህ ዓይነት ውሳኔ ይወሰናል የሚል ግምት የለኝም፤›› በማለት አሠልጣኝ ወንድዬ አስተያየታቸውን ለሪፖርተር አክለዋል፡፡  

የአዲስ አበባ ከተማ ወጣቶች ስፖርት ቢሮ የማዕከላትና ስፖርት ማዘውተሪያ ሥፍራዎች ልማት አስተዳደር በበኩሉ፣ በከተማዋ በስፖርት ማዘውሪያ ሥፍራነት ተመዝግበው ያሉት ሥፍራዎች ላይ ምንም ዓይነት ግንባታ እንዳልተከናወነ ገልጾ፣ ከተጠቀሰው ሥፍራ ጋር በተያያዘ ማጣራት እንደሚያደርግ ለሪፖርተር ገልጿል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በአዲስ አበባ በድምቀት ተከበረ

የአዛርባጃን ኤምባሲ  የአዛርባጃንን ብሄራዊ ቀን በትላንትናው ዕለት አከበረ። ሰኞ...

የመንግሥትና የሃይማኖት ልዩነት መርህ በኢትዮጵያ

እንደ ኢትዮጵያ ባሉ አገሮች የሃይማኖት ተቋማት አዎንታዊ ሚና የጎላ...

ሐበሻ ቢራ ባለፈው በጀት ዓመት 310 ሚሊዮን ብር የተጣራ ትርፍ ማግኘቱን አስታወቀ

የአንድ አክሲዮን ሽያጭ ዋጋ 2,900 ብር እንዲሆን ተወስኗል የሐበሻ ቢራ...