ኢትዮ ቴሌኮም የሙዚቃ ሥርጭትን (ስትሪሚንግን) ጨምሮ ሌሎች የዲጂታል መዝናኛ አገልግሎቶችን ከተለያዩ አጋሮች በመተባበር ይፋ አደረገ፡፡
የቀረቡት የዲጂታል መዝናኛ አገልግሎቶች የኪነ ጥበብና የፈጠራ ባለሙያዎች የሚያበረታቱና የኪነ ጥበብ ሥራዎች ለማኅበረሰቡ በቀጥታ ተደራሽ በማድረግ፣ ባለሙያዎች የድካማቸውን ፍሬ እንዲያገኙ የሚያስችልና ለደንበኞች ምቹ የክፍያና የአገልግሎት አሰጣጥ ሁኔታዎችን የሚፈጥር መሆኑን ኩባንያው አስታውቋል፡፡
በኢትዮ ቴሌኮምና በአጋሮቹ ይፋ ከተደረጉት አራት አገልግሎቶች መካከል በሐበሻ ቪው የሚቀርበው አይፒቲቪ ወይም ቪዲዮ ስትሪሚንግ አንዱ ሲሆን፣ ይህም ደንበኞች የቀጥታ የቴሌቪዥን ፕሮግራሞችን፣ ድራማዎችን፣ ፊልሞችንና ሌሎች የተመረጡ በርካታ አገልግሎቶችን ኢንተርኔትን በመጠቀም በሞባይል ስልካቸው፣ በቴሌቪዥናቸውና በኮምፒዩተራቸው ለመመልከት ያስችላቸዋል ተብሏል፡፡
ሰዋሰው የሙዚቃ ስትሪሚንግ ሁለተኛው የመዝናኛው ዘርፍ የዲጂታል አገልግሎት ሲሆን፣ የሙዚቃ ወዳጆችና አድናቂዎች የአገር ውስጥና የውጭ ሙዚቃዎችን በአንድ ቦታ የሚያገኙበትና የሚያደምጡበት አማራጭ አገልግሎት መሆኑ ተነግሯል፡፡
በቴክኖላቭና አይኮኔክት ዲጂታል ሰርቪስ በተባሉ ኩባንያዎች የቀረቡት ቴሌጌም እና ቴሌ ዊን የተሰኙት የሞባይል ጌሞች፣ ሌላኞቹ አገልግሎቶች ሲሆኑ፣ በተለያየ ዕድሜ ክልል የሚገኙ ደንበኞች የተመረጡ የሞባይል ጌሞችን በአነስተኛ ክፍያ አውርደው መጠቀም የሚያስችሉ መሆኑን፣ ኩባንያው አገልግሎቶቹን ሚያዚያ 26 ቀን 2015 ዓ.ም. በኃይሌ ግራንድ ሆቴል ይፋ ሲያደርግ አስታውቋል፡፡