በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት ከባድ ጉዳት ከደረሰባቸው መሠረተ ልማቶች አንዱ የሆነውና ለሁለት ዓመታት ያለ አገልግሎት የቆየው የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያን መልሶ ለመገንባት፣ በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያስፈልግ የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ አስታወቀ፡፡
የአውሮፕላን ማረፊያው መንደርደርያ (Ranway) ተቆፍሮ ሙሉ በሙሉ መበላሸቱንና ተርሚናሉም ከባድ ውድመት እንደደረሰበት፣ በተደረገው የመጀመሪያ ደረጃ ፍተሻ (Preliminary Assessment) መታወቁን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ መስፍን ጣሰው ገልጸዋል፡፡
‹‹ለመልሶ ግንባታው የሚያስፈልገውን ትክክለኛ ወጪ ለማወቅ ዝርዝር ጥናት እያደረግን ነው፡፡ ከዚህ ቀደም የተሠራው ግምታዊ ወጪ ነው፡፡ ዝርዝር ጥናቱን የሚያከናውን ቡድን አቋቁመን ወደ ሥራ ገብቷል፤›› ሲሉ አቶ መስፍን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ የጥናት ቡድኑ ከአየር መንገዱ፣ ከሲቪል አቪዬሽን ባለሥልጣን፣ ከኤርፖርቶች ድርጅትና ከባለድርሻ አካላት የተውጣጣ መሆኑን አስረድተዋል፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው ከባድ ጉዳት እንደደረሰበትና በብዙ መቶ ሚሊዮኖች የሚቆጠር ገንዘብ እንደሚያስፈልግ አቶ መስፍን ተናግረዋል፡፡
ይሁን እንጂ የአውሮፕላን ማረፊያውን መልሶ ግንባታ ለማስጀመር በዚህ ዓመት በጀት እንዳልተያዘ አቶ መስፍን አብራርተዋል፡፡ ‹‹የዚህ ዓመት በጀት ካላንደር በሰኔ ያልቃል፡፡ ከዚያ በፊት የመልሶ ግንባታ ዋጋ ግምቱን ካወቅን ለሚቀጥለው ዓመት በጀት እንጠይቃል፤›› ብለዋል አቶ መስፍን፡፡
በዕቅዱ መሠረት ከተሳካ በ2016 ዓ.ም. የመጀመርያዎቹ ሩብ ዓመታት የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ ወደ አገልግሎት ሊመለስ ይችላል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ ይሁን እንጂ የግንባታ ዕቃዎችን ወደ ቦታው ለማጓጓዝ፣ የየብስ ትራንስፖርት ወደ አክሱም መጀመር እንዳለበትና የኮንትራክተሮች ደኅንነትም መረጋገጥ እንዳለበት ተጠቁሟል፡፡
የአክሱም አውሮፕላን ማረፊያ በተለይ ቆሞ የነበረውን የዓለም አቀፍና የአገር ውስጥ ቱሪዝም ፍሰት ያነቃቃል ተብሎ ይጠበቃል፡፡ አውሮፕላን ማረፊያው በግማሽ ቢሊዮን ብር የተገነባ ሲሆን፣ ጦርነቱ በተጀመረ በመጀመርያዎቹ ወራት ሆን ተብሎ ጉዳት እንደደረሰበት ተዘግቧል፡፡ አውሮፕላን ማረፊያውን መልሶ ለመገንባት ከመጀመርያው ወጪ ያልተናነሰ ገንዘብ እንደሚያስፈልግ ተጠቁሟል፡፡
በሌላ በኩል በመቀሌ ምክትል ከንቲባ አቶ ኤልያስ ካህሳይ የተመራው ልዑክ በአዲግራት አዲስ አውሮፕላን ማረፊያ እንዲገነባ ጥያቄ አቅርቧል፡፡ ልዑኩ ከአየር መንገዱ ዋና ሥራ አስፈጻሚና ከአዲስ አበባ መስተዳደር ጋር ቆይታ በማድረግ በትብብር መስኮች ላይ መመካከራቸው ታውቋል፡፡ ይሁንና የኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ በዚህ ዓመትና በሚቀጥለው ዓመት አዲስ ኤርፖርት ግንባታ የመጀመር ዕቅድ እንደሌለው አቶ መስፍን ምላሽ ሰጥተዋል፡፡ አየር መንገዱ በአሁኑ ጊዜ በ11 ቢሊዮን ብር አጠቃላይ በጀት አምስት መንደርደሪያዎችንና ስምንት ተርሚናሎችን እየገነባ መሆኑን፣ እነዚህ ሳያልቁ ሌላ አዲስ ግንባታ እንደማይጀምር ተገልጿል፡፡
በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት የቀጠለው ግጭት ከስድስት ወራት ወዲህ መቋጫ ካገኘ በኋላ፣ ወደ መቀሌ የሚደረገው መደበኛ በረራ በቀን ሰባት የደረሰ ሲሆን ሽሬ ደግሞ ሁለት ደርሷል፡፡ ከጦርነቱ በፊት ወደ መቀሌ በየቀኑ እስከ አሥራ አራት በረራዎች ይደረጉ ነበር፡፡ በረራዎቹን ቀድሞ ወደ ነበሩበት ለማድረስ በተለይ የነዳጅ አቅራቢ ድርጅቶች በትግራይ ክልል ሥራ መጀመር እንዳለባቸው ተጠይቋል፡፡