_ፓሊስ የደረሰኝም ሆነ የሰማሁት ነገር የለም ብሏል
የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሠማኮ) በየዓመቱ ሚያዝያ 23 ቀን የሚከበረውን የዓለም የሠራተኞች ቀን (ሜይዴይ)፣ ነገ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓም በሰላማዊ ሰልፍ በመስቀል አደባባይ እንደሚከበር የተነገረና ሪፖርተር ጋዜጣም በዛሬው እትሙ የዘገበ ቢሆንም፣ ዛሬ ሚያዚያ 22 ቀን 2015 ዓም ምሽት ላይ መሰረዙ ተነግሯል።
በኢሠማኮ ፕሬዚደንት አቶ ካሣሁን ፎሎ ፊርማ ተረጋግጦ ለሪፖርተር የተላከው መግለጫ እንደሚገልጸው፣ በዓሉ በተለያዩ ዝግጅቶች ሲከበር መቆየቱ ይታወቃል። በዘንድሮው 48ኛው የሜይዴይ በዓልን በአዲስ አበባና ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤቶቹ በሚገኙበት በሰላማዊ ሰልፍ ለማክበር | አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ሲያደርግ ቆይቶ፣ የበዓሉን አከባበርና አጠቃላይ መርሀ-ግብር አስመልክቶ ሚያዝያ 21 ቀን 2015 ዓ.ም. ጋዜጣዊ መግለጫ በመገናኛ ብዙሀን ማስተላለፉ አስታውሷል፡፡
ነገር ግን ሚያዝያ 23 ቀን 2015 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በዓሉን ለማክበር የተያዘው ፕሮግራም “የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ጸጥታ ቢሮ ስለከለከለን” ፕሮግራሙን ለመሰረዝ የተገደድን መሆኑን እየገለጽን፤ ይህንኑ መልዕክት የኢትዮጵያ ሠራተኞች እንዲያውቁት ብሏል።
የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽንም ነገ ሚያዚያ 23 ቀን 2015 ዓም ምንም የሚያውቃቸው ኩነቶችና ሰልፍ እንደሌለም አስታውቋል።