Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

የሜትር ታክሲ ኩባንያዎች ሕገወጥ ተግባራትን የሚከላከል አሠራር ማበጀት የግድ ይላቸዋል!

የትራንስፖርት ዘርፉን ከማዘመን አንፃር እንደ ራይድ፣ ፈረስ፣ ዛይራይድና የመሳሰሉ የሜትር ታክሲ ኩባንያዎች ይዘውት የመጡት ቴክኖሎጂ ቀመስ አገልግሎት ጥሩ ምሳሌ በመሆን ይጠቀሳሉ፡፡

አብዛኛው የኅብረተሰብ ክፍል አቅም ኖሮት በእነዚህ የሜትር ታክሲዎች እየተጠቀመ ነው ባይባልም፣ አቅሙ ለሚፈቅድላቸው ተገልጋዮች ግን አማራጭ መሆን ችለዋል፡፡ በትራንስፖርቱ ዘርፍ ያለውን ችግር በማቃለሉ ረገድ የራሳቸውን አስተዋጽኦ ማበርከታቸው አይካድም፡፡ ከዚህ ቀደም በግምትና በድርድር ‹‹ኮንትራት›› በሚል ይካሄድ የነበረውን ኋላቀር የአገልግሎት አሰጣጥ በዘመናዊ መንገድ እንዲካሄድ አስችለዋል፡፡ በሞባይል መተግበሪያዎች በመታገዝ በጉዞ ርቀት የሚሰላ ቋሚ የክፍያ ሥርዓትን መትከል ተችሏል፡፡ ተገልጋዩም ሆነ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች የዋጋ ክርክር ውስጥ ሳይገቡ በሞባይል ላይ በተጫነው መተግበሪያ በሚሰጠው መረጃ ላይ ተመሥርተው በመተማመን የአገልግሎት ግብይት የሚያካሂዱበት አሠራር እንዲሰፍን ሆኗል፡፡ 

የሜትር ታክሲዎች የጉዞ የመነሻ ዋጋና በአንድ ኪሎ ሜትር የሚጠይቁት ታሪፍ የተጋነነ ነው የሚለው አስተያየት እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዘመናዊ የትራንስፖርት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ ዘርፉን አዘምነዋል፡፡

የሜትር ታክሲዎች በዚህ አገልግሎት መሰማራት ሌላው በጎ መገለጫቸው ለብዙዎች የሥራ ዕድል መፍጠራቸው ነው፡፡ ዛሬ በአሥር ሺዎች የሚቆጠሩ ተሽከርካሪዎች በዚህ ቢዝነስ ውስጥ እንዲገቡ መፈቀዱ በአሥር ሺዎች ለሚቆጠሩ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል፡፡ ለአንዳንድ ቋሚ ሥራ ላላቸው የድርጅት ተቀጣሪዎችም የተጨማሪ ገቢ ምንጭ በመሆን ከፍተኛ ፋይዳ ማበርከት ችሏል። ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታንም አስገኝቷል፡፡ 

ሕጋዊ የክፍያ ሥርዓትን ከማስፈንና ዘመናዊ የክፍያ ዘዴን ከማላመድ አንፃርም ቢሆን የሜትር ታክሲዎች የትራንስፖርት ዘርፉን አንድ ዕርምጃ ወደፊት አራምደዋል፡፡ እስካሁን ድረስ በትራንስፖርት ዘርፍ ገቢና ወጪን በማቀናነስ ታክስ የመክፈል አሠራር መፍጠር ማስቻላቸውንም የሚጠቀስ ነው፡፡ በዘርፉ በቁርጥ ግብር ብቻ ግብር ይከፍሉ የነበሩ የታክሲ አገልግሎት አቅራቢዎች አሁን ላይ ገቢን መሠረት ያደረገ ግብር እንዲከፍሉ በማድረግ ሥርዓት ያበጀ ሲሆን፣ መንግሥት ከዚህ ዘርፍ የሚያገኘው የግብር ገቢም ከፍ እንዲል አስችሏል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ግን ከሜትር ታክሲዎች አገልግሎት አሰጣጥ ጋር በተያያዘ እየታዩ ያሉትና ብቅ ብቅ ማለት የጀመሩ ግድፈቶች ለመልካም የታሰበውን አሠራር እያጎደፉት ነው፡፡ ችግሩ ወደ ሜትር ታክሲው ኩባንያ ማዕከል ሳይደውሉ ተገልጋዮች መንገድ ላይ ያገኙትን ሜትር ታክሲ ከመጠቀም ጋር የሚገናኝ ነው፡፡ 

ሳይደውሉ በቅርብ ያገኙትን ሜትር ታክሲዎችን ለመጠቀም የሚወጡ ተገልጋዮች አገልግሎቱን ከሞባይል መተግበሪያው ውጪ በድርድርና በኪሎ ሜትር በሚሠላ ዋጋ ክፍያ እንዲፈጽሙ መጠየቃቸው አገልግሎቱን እየበረዘ ነው፡፡ 

ጥቂት የማይባሉ ተጠቃሚዎች ወደ ማዕከል ሳይደውሉ፣ ካሉበት ቦታ በሚያገኙት ሜትር ታክሲ የሚጠቀሙበት አንዱ ምክንያት፣ ወደ ማዕከል በመደወል የሚላክላቸውን ተሽከርካሪ ለማግኘት ጊዜ እየወሰደ በመምጣቱ ነው፡፡ ስለዚህ ተጓዞች ያለ ጥሪ  ያገኙትን ሜትር ታክሲ እንዲጠቀሙ ሲያስገድዳቸው ደግሞ አሽከርካሪዎች አገልግሎቱን ለመስጠት የሚፈቅዱት ከሞባይል መተግበሪያው ውጪ እየሆነ ነው፡፡ 

አንዳንድ የሜትር ታክሲ አሽከርካሪዎች አጋጣሚውን ባልተገባ መንገድ እየተጠቀሙበት ነው፡፡ የሞባይል መተግበሪያውን በመጠቀም የተገልጋዮችን የስልክ ሞልተው መሥራት ሲገባቸው፣ ዋጋ ተደራድረን እንሂድ ወይም ከመተግበሪያው ውጪ በኪሎ ሜትር ይዘን ሒሳብ እንተሳሰብ እያሉ ነው፡፡   

የባሰባቸው አሽከርካሪዎች ደግሞ መተግበሪያውን ከተጠቀሙ ይህንን የሜትር ታክሲው ኩባንያ ኮሚሽን ይቆርጥብናል ብለው ደፍረው ይናገራሉ፡፡ መተግበሪያውን ላለመጠቀም የሚሰጡት ሌላው ምክንያት ደግሞ ለመንግሥት የሚከፍሉትን ግብር ይጨምርብናል በሚል እንደሆነ ሳይፈሩ የሚናገሩም በርክተዋል፡፡ እንዲያውም ከሞባይል መተግበሪያው ውጪ የሚጠቀሙ ከሆነ ለተገልጋዩ ዋጋ ይቀንሳል በሚል ማግባቢያ፣ በኪሎ ሜትር እንሂድ በማለት በግልጽ እየተናገሩ እሺ የሚላቸውን ይጭናሉ፡፡  

ከሞባይል መተግበሪያው ውጪ በኪሎ ሜትር በሚሠላ ዋጋ መጠቀም ያልፈለጉ ተጓዦችን ለማስተናገድ ፈቃደኛ የማይሆኑ የሜትር ታክሲ ሾፌሮች ቁጥር እየጨመረ ነው፡፡ በተለይ ምሽት ላይ ችግሩ እየጎላ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ ያልተገቡና ሕገወጥ ሊባሉ የሚችሉ ተግባራት አሁን አሁን እየተበራከቱ መምጣታቸው ደግሞ ለበጎ የታሰበው የሜትር ታክሲዎች ዘመናዊ አሠራር ችግር ውስጥ እንዲገባ ያደርጋል፡፡ 

ይህ ደግሞ ከታለመለት ግብ ውጪ ሆኖ ለሌላም ወንጀል በር የሚከፍት ስለሚሆን ድርጊቱ ከወዲሁ ዕርምት ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ስለዚህ ዲጂታል የግብይት ሥርዓትን ለማስረጽ እንደ ምሳሌ የሚቆጠረው የእነዚህ ታክሲዎች አሠራር በምንም መልኩ ከሞባይል መተግበሪያው ውጪ አገልግሎት መስጠት እንደማይችሉ ማሳወቅ ያስፈልጋል፡፡ 

በተለይ በሞባይል መተግበሪያውን ላለመጠቀም በግልጽ ከአንዳንድ አሽከርካሪዎች የሚሰጠው ምክንያት በራሱ ወንጀል መሆኑን ማሳወቅም ተገቢ ይሆናል፡፡ ምክንያቱም  መተግበሪያውን ከተጠቀምን የሜትር ታክሲ ኩባንያው ይህንን ያህል ኮሚሽን ይቆጥርብኛል፣ መንግሥትም የሚያስከፍለን ግብር ይጨምርብናል፣ የሚለው ምልከታቸው ከግብር ሥራው ጋር በተያያዘ ሊያስጠይቃቸው መቻሉን አውቀው መታረም ይኖርባቸዋል፡፡ 

በመሆኑም በምንም ሁኔታ መለመድ የሌለበትን ይህንን ሕገወጥ ተግባር በእንጭጩ መቅጨት የሁሉም ባለድርሻ አካላት ኃላፊነት ነው፡፡ እንዲህ ያለው ችግር ዋነኛ መፍትሔ ያለው ግን በተገልጋዮች እጅ ነው፡፡ ‹‹ያለ ሞባይል መተግበሪያው አንጓዝም›› በማለት የሚወስዱት ዕርምጃ ሕገወጥ አሠራሩን ለመቀነስ ይረዳል፡፡ 

የተጓዦች መብታቸውን ከማስከበር በላይ ሕገወጥ አሠራርን በመከላከል ኃላፊነታቸውን የሚወጡት እንቢ በማለት ጭምር ነው፡፡ ማንነቱን ሊያሳውቅ ባልፈለገና ሕጋዊውን አሠራር ወደ ጎን በመተው አገልግሎቱን ለመስጠት የሚፈልግ አሽከርካሪ ደግሞ ወንጀል ላለመሥራቱ ማረጋገጫ ስለሌለ ለራስ ደኅንነትም ሲባል ሕጋዊነትን መከተል ጠቀሜታው የበዛ ነው፡፡ 

የሜትር ታክሲ ኩባንያዎችም በአንዳንድ አሽከርካዎች የሚፈጸመውን ሕገወጥ ተግባር የሚከላከሉበት አሠራር ማበጀት የግድ ይላቸዋል፡፡ በእነሱ ስም የሚንቀሳቀሱ አሽከርካሪዎች ለኩባንያዎቻቸው ስም መጉደፍ ምክንያት ስለሚሆኑ ሊያስቡበት ይገባል፡፡ 

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት