በሀብተ ገብርኤል አዳነ፣ በታጠቅ የኔሁንና በብሩክ የኔሁን
የግንባታ ፕሮጀክቶች ከጽንሰ ሐሳብ ጀምሮ ተገንብተው ለአገልግሎት እስኪበቁ ድረስ በርካታ ሒደቶችን እንደማለፋቸው መጠን በእያንዳንዱ ሒደት ውስብስብ ችግሮች ሊገጥሙ ይችላሉ። ፕሮጀክቱ እንዲያሳካ የታለመለትን አገልግሎት በአግባቡ መስጠት ይችል ዘንድ ከአርክቴክቸራል ንድፍ ሥራው ጀምሮ በጥንቃቄ እየተሠራና በባለሙያዎች እየተተቸ የዲዛይን ሥራው የሚቀጥል ሲሆን፣ የሥነ መዋቅር ዲዛይን (Structural Design)፣ የኤሌክትሪካል ዲዛይን፣ የሳኒተሪ ዲዛይንና የኤሌክትሮ ሜካኒካል ዲዛይን የአርክቴክቸራል ዲዛይኑን ተከትለው ይሠራሉ። በሁሉም ሙያዎች ዘርፍ የሚደረገው ዲዛይን በአግባቡ እየተገመገመና እየተተቸ ሲሠራ የፕሮጀክቱን ዓላማና አገልግሎት ከግንባታ በኋላ ሙሉ በሙሉ ለማከናወን የሚያገለግል ዲዛይን ይዘጋጃል።
የዲዛይኑን መጠናቀቅ ተከትሎ ፕሮጀክቱን ወደ መሬት ለማውረድ የሚያስፈልገውን የገንዘብና የጊዜ በጀት፣ ፕሮጀክቱ የሚሠራበትን የግብዓት ዓይነትና የሚሠራበትን መንገድ የያዘ የሥራ ዝርዝር መግለጫ (Technical Specification)፣ ፕሮጀክቱን የሚሠራውን ተቋራጭ መለየት የሚያስችል የጨረታ ሰነድ ይዘጋጃል። ጨረታውን ተከትሎ አሸናፊውን በመለየት ውል የሚያዝ ሲሆን ውሉን በጥንቃቄ ማዘጋጀት በግንባታ ወቅት የሚነሱ ጭቅጭቆችንና አለመግባባቶችን ለማስቀረት ይረዳል። በግንባታ ወቅት ዲዛይኑን በውል አግባብ መሬት ላይ መውረድ ሲጀመር ችግሮች መከሰት ይጀምራሉ። የእነዚህ ችግሮች ምንጭ ዲዛይኑ፣ የግንባታ ማቴሪያሎች፣ የሥራ ዓይነቶች ዝርዝር መግለጫ (Specification)፣ ውሉ፣ የአቅርቦት እጥረት፣ የፋይናንስ እጥረት፣ አገራዊ ሁኔታና ሌሎችም ሊሆኑ ይችላሉ።
በመሆኑም እንደ አጠቃላይ ሲታይ የግንባታ ፕሮጀክቶች ባህሪ ከሐሳብ ማመንጨት ጀምሮ ገንብቶ እስከማስረከብ ድረስ ያለው ሒደት ውስብስብ ችግሮችን ያስተናግዳል። በዚህ ጽሑፍ የሚዳሰሰው አንዱ ውስብስብ ችግር የዋጋ ንረት በሚከሰት ጊዜ፣ ለግንባታ ፕሮጀክቶች ስለሚፈጸመው የዋጋ ማስተካከያ ነው።
በአገራችን ካለፉት ሦስት ዓመታት ጀምሮ ከፍተኛ የሆነ የዋጋ ግሽበት ያጋጠመ ሲሆን፣ ይህም የግንባታ ግብዓቶች ዋጋ በእጅጉ እንዲጨምር አድርጓል። በዚህም የተነሳ በርካታ የመንግሥትና የግል የግንባታ ፕሮጀክቶች የግንባታ ሁኔታ በአዝጋሚ ሁኔታ ከመከናወን እስከ መቆም ደርሷል። ይህን ግንዛቤ ውስጥ በማስገባት መንግሥት በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚገኙ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ ግንባታዎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው ፈቅዷል። ይሁን እንጂ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች፣ ተቋራጮችና አማካሪዎች የዋጋ ማስተካከያውን የሚሠሩበት መንገድ ግልጽ በሆነ የአሠራር ሒደትና መመርያ በአግባቡ ያልታሰረ በመሆኑ፣ በባለድርሻ አካላቱ የተለያየ አረዳድና አመለካከት ይንፀባረቃል። ይህም የተቋራጮችን ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስቸግር ሲሆን፣ መንግሥትንም አላስፈላጊ ጫና ውስጥ ሊከተው ይችላል። ከዚህም ባሻገር በችግር ውስጥ ያለውን የአገራችንን የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ከድጡ ወደ ማጡ ሊወስደው ይችላል።
ስለሆነም በዚህ ጽሑፍ በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች ፕሮጀክቶች ላይ የግንባታ ዋጋ ማስተካከያ ጉዳይን በጥልቀት እንመረምራለን፣ ችግሮችንና የችግሮችን ተፅዕኖ እናሳያለን፣ ችግሮችን በጋራ ፈትቶ ፕሮጀክቶች የተሻለ አፈጻጸም ኖሯቸው የሚጠናቀቁበትን የመፍትሔ ሐሳብም እናቀርባለን። አንባቢያንም ከዚህ አንገብጋቢ ጉዳይ ጀርባ ያለውን እውነት በመግለጽ ወደ መፍትሔ ሐሳቡ በምናደርገው ጉዞ ይቀላቀሉንና በዋጋ ማስተካከያ ሒደት ላይ ያለውን ችግር የጋራ መፍትሔ እናብጅለት።
የግንባታ ዋጋ ማስተካከያና የአሠራር ሒደት
በግንባታ ሒደት ውስጥ በተለያዩ ምክንያቶች የግንባታ ዕቃዎች፣ የሰው ኃይልና የማሽነሪ ኪራይ ዋጋ ከጊዜ ወደ ጊዜ ስለሚለዋወጥ፣ የአቅርቦት ሰንሰለት ሊዛባና የዋጋ መናር ሊከሰት ስለሚችል የግንባታ ዋጋ ማካካሻ በግንባታ ውሎች ውስጥ እንዲኖር ይደረጋል። በግንባታ ውል ውስጥ የዋጋ ማስተካከያ አንቀጽ በማካተት፣ ሁለቱም ወገኖች (ውል ሰጪ ማለትም ባለቤትና ውል ተቀባይ ማለትም ተቋራጭ) በግብዓት ዋጋ ለውጥ የሚመጣን የፕሮጀክት ወጪ መጨመር ወይም መቀነስ አደጋ በመጋራት፣ ፕሮጀክቱ በበጀት የተረጋጋ ሆኖ እንዲያልቅ ማድረግ ይችላሉ። ይህም በዋጋ ለውጥ ምክንያት የሚፈጠሩ አለመግባባቶችንና የግንባታ መዘግየቶችን በመቀነስ ውጤታማ የግንባታ ሒደት እንዲኖር ያስችላል።
መንግሥት በአገሪቱ የተከሰተውን የዋጋ ንረት ተከትሎ፣ በሁሉም የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የተጀመሩና የቆሙ ግንባታዎች የዋጋ ማስተካከያ ተደርጎላቸው እንዲያልቁ አቅጣጫ ሰጥቷል። ይህ አቅጣጫ ያስፈለገበት ዋነኛ ምክንያትም፣ ሁሉም የዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች በዋጋ ማስተካከያ ላይ ተመሳሳይ አረዳድ ስላልነበራችው ነው። የግንባታ ጊዜያቸው ከ18 ወራት በላይ ለሚጠይቁ ፕሮጀክቶች የዋጋ ማስተካከያ መፍቀድ የሚቻል ቢሆንም፣ ብዙ የዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች ከ18 ወራት በላይ የውለታ ጊዜ ቢኖራቸውም የዋጋ ማስተካከያ እንደሌላቸው ተደርጎ ውል ተይዟል። በውል ውስጥ የዋጋ ማስተካከያ የፈቀዱ ፕሮጀክቶችም የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግላቸው ግብዓቶች ተለይተው ሲሚንቶ፣ የአርማታ ብረት፣ የነዳጅ፣ የሴራሚክ፣ የአልሙኒየምና የመሳሰሉትን ብቻ እንደሚሆኑ ይገልጻሉ።
የዋጋ ማስተካከያ በሚፈቅዱ ውሎች ማስተካከያው በሚከተለው አግባብ ይፈጸማል።
- የውልስምምነቱከፀናበትጊዜጀምሮከ12 ወራትበኋላለሚሠሩሥራዎችየዋጋማስተካከያይደረጋል።የዋጋማስተካከያየሚደረግላቸውየግብዓትዓይነቶች በውሉላይበግልጽስለሚቀመጡየግብዓቶችየዋጋመጠን (Weigting) ከአጠቃላይየፕሮጀክቱየውልመጠንአንፃርበመቶኛይሰላል።
- የግብዓቶችየዋጋመጠን (Weigting) በአንድላይይደመራል፣የድምሩፐርሰንትየዋጋማስተካከያየሚደረግበትመጠን (Adjustable Portion) ተብሎይጠራል።የዋጋማስተካከያየሚደረግበትመጠንከ100 ላይተቀንሶየሚቀረውመጠንየዋጋማስተካከያየማይደረግበትመጠን (Non-Adjustable Portion) ተብሎይወሰዳል።
- የዋጋማስተካከያስሌትአብዥ (Pn) በአጠቃላይየውልሁኔታዎችአንቀጽ 62 ውስጥበተሰጠውቀመርመሠረትይሰላል።
- የዋጋማስተካከያማድረግከሚቻልበትጊዜጀምሮለተሠሩሥራዎችጊዜያዊክፍያ (Interim Payment) በየወሩበመፈጸምየዋጋማስተካከያውአብሮይሰላል።የቅድመክፍያተመላሽናሌሎችተቀናናሽክፍያዎችተቀንሰውየሚቀረውክፍያበዋጋማስተካከያስሌትአብዥተባዝቶለተቋራጩየዋጋማስተካከያክፍያተፈጻሚይሆናል።
ግልጽ ያልሆነው ተቋራጮች፣ አማካሪዎችና የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የዋጋ ማስተካከያን የተረጎሙበት የተለያየ መንገድ ነው፡፡
ዋናው የችግሩ ምንጭ የዋጋ ንረት ነው
ባለፉት ሁለትና ሦስት ተከታታይ ዓመታት የግንባታ ዕቃዎች፣ የሠራተኛ ደመወዝና የማሽነሪ ኪራይ ዋጋ በከፍተኛ ደረጃ ጨምሯል። ለምሳሌ ከመጋቢት 2013 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 2014 ዓ.ም. ባለው ጊዜ ውስጥ የሲሚንቶ ዋጋ በ77.54 በመቶ ሲጨምር፣ የአርማታ ብረት ዋጋ ደግሞ በ92.01 በመቶ ጨምሯል ሲል የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ሪፖርት ያመለክታል። የግንባታው ዘርፍ በኢትዮጵያ ከግብርና ቀጥሎ ሁለተኛው ትልቁ የሥራ ዕድል መፍጠሪያ በመሆኑ፣ የተፈጠረው የዋጋ ግሽበት በሚሊዮን በሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን ኑሮ ላይ ከፍተኛ ጫና እየፈጠረ ነው።
በግንባታ ዕቃዎች ዋጋ መናር የተነሳ በኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶች ሳይጠናቀቁ ለመቆም ተዳርገዋል። በርካታ ፕሮጀክቶች ውላቸው የዋጋ ማስተካከያ ባለመፍቀዱ የቆሙ ሲሆን፣ የዋጋ ማስተካከያ የሚፈቅድ ውል ያላቸው ፕሮጀክቶችም የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግባቸው የግንባታ ግብዓቶች ውስን በመሆናቸው፣ የዋጋ ንረት የተከሰተው በሁሉም ግብዓቶች በመሆኑ ግንባታቸውን ማስቀጠል አልቻሉም።
መንግሥትም የችግሩን አሳሳቢነት በመረዳት ከሚያዚያ 25 ቀን 2013 ዓ.ም. በፊት ለተያዙ ውሎች የዋጋ ማስተካከያ እንዲኖራቸውና ሁሉም የግንባታ ግብዓቶች የዋጋ ማስተካከያ እንዲደረግላቸው፣ በአራት ወካይ ግብዓቶች ሥር (ሲሚንቶ፣ የአርማታ ብረት፣ ሴራሚክና ናፍታ) እንዲወከሉ ማድረጉ ይታወቃል። ሁሉም የግንባታ ግብዓቶች በአራቱ ወካይ ግብዓቶች ሥር የሚከፋፈሉ ሲሆን የእያንዳንዱ ወካይ ግብዓቶች መጠን በመቶኛ ከዋናው የውል መጠን አንፃር ይሰላል።
65/35 የዋጋ ማስተካከያ መጠን አይደለም
በአንዳንድ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤቶች የተያዘው ግንዛቤ ከዋናው ውል ውስጥ የዋጋ ማስተካከያ የሚያስፈልገው 65 በመቶ ሲሆን፣ ማስተካከያ የማይደረግበት ደግሞ 35 በመቶ ነው የሚል ነው። በመሠረታዊነት 35 በመቶኛ ማለት የሥራ ማስኬጃ ወጪ (20 በመቶ) እና ትርፍ (15 በመቶ) ሲሆን፣ ከ100 ፐርሰንት ላይ ይህ ተቀንሶ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግበት 65 በመቶ እንደሆነ ተደርጎ ይወሰዳል። የሥራ ማስኬጃ ወጪና ትርፍ 35 በመቶኛ መሆኑን የሚያስረዳ መመርያ መንግሥትም ሆነ ተቋራጮች የሌላቸው ሲሆን፣ ቁጥሩ የተወሰደውም ተቋራጮች አዲስ የሥራ ትዕዛዝ ሲሰጣቸው አዲስ ዋጋ ለማፀደቅ በሚያቀርቡት የዋጋ ዝርዝር መግለጫ ላይ የሥራ ማስኬጃና ትርፍ ድምር 35 በመቶ ስለሚል ነው። እንደ አገር ግን የድርጅቶችን ዕድገት ታሳቢ ያደረገ ወጥ የሥራ ማስኬጃና ትርፍ መጠን ቢቀመጥ መልካም ነው። ወይም ደግሞ ተቋራጮች ደረጃቸውንና የድርጅታቸውን አቅም ታሳቢ በማድረግ የሥራ ማስኬጃና የትርፋቸውን መጠን ቢያስቀምጡ መልካም ይሆናል።
ከላይ የተገለጸው እንዳለ ሆኖ 35 መቶኛው የሥራ ማስኬጃና ትርፍ በመሆኑ፣ የዋጋ ማስተካከያ አይደረግበትም ማለት የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግበት ከ100 ላይ 35 መቶኛን ቀንሶ 65 መቶኛው ነው ማለት አይደለም። ይህ የተሳሳተ ግንዛቤ የመጣው ለአንድ የሥራ ዓይነት የዋጋ ተመን እንዴት እንደሚሠራ ባለመገንዘብ ነው።
የአንድን የሥራ ዓይነት የዋጋ መጠን (Unit Price) ለማስላት ቀጥተኛ ዋጋ የሚወሰነው የቁሳቁስ ወጪን፣ የጉልበት ወጪንና ሥራውን ለመሥራት የሚያገለግሉትን መሣሪያዎች ወይም ማሽኖች ዋጋ በመጨመር ነው። ለምሳሌ የአንድ ሥራ ዓይነት ቀጥተኛ ዋጋ (Direct Cost) 5,000 ብር ነው ብለን ካሰብን፣ የትርፍና የሥራ ማስኬጃ ወጭን (Overhead Cost and Profit Marigin) የቀጥተኛ ዋጋውን 35 በመቶ ሲደመርበት ማለትም 5000+0.35*5000= 6750 ብር ይሆናል። ይህ ማለት አጠቃላይ ዋጋው የቀጥተኛ ዋጋው 135 በመቶ ይሆናል።
በመሆኑም 65 በመቶ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግበትና 35 በመቶ ዋጋ ማስተካከያ የማይደረግበት ብለን ካሰብን፣ የ6,750 ብር 65 በመቶ ሲሰላ የሚሰጠን ቀጥተኛ ዋጋውን 5,000 ብር ሳይሆን 4,387.5 ብር ነው። ይህ የስሌት ስህተት የሚስተካከለው አጠቃላይ ዋጋውን በ1.35 በማካፈል ሲሆን 6,750/1.35 = 5,000 ይሆናል ማለት ነው። ይሁን እንጂ አጠቃላይ የሥራው ዋጋ 100 በመቶ ነው ተብሎ ከታሰበ በ1.35 ሲካፈል 74.07 በመቶ የሚመጣ ሲሆን፣ ይህም የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግበት (Adjustable portion)፣ ቀሪው 25.93 በመቶ ደግሞ የዋጋ ማስተካከያ የማይደረግበት (Non Adjustable portion) ይሆናል ማለት ነው።
አንዳንድ ተቋራጮች ስሌቱን በትክክል ያልተገነዘቡ ሲሆን ሌሎች ትክክለኛውን የአሠራር ሒደት ቢገነዘቡም ከአሰሪ መሥሪያ ቤቶች ጋር ያላቸውን መልካም ግንኙነት ላለማሻከርና አንዳንድ ኃላፊዎች ላይረዱት ይችላሉ በሚል ምክንያት፣ 65 በመቶ የዋጋ ማስተካከያ ይደረግበታል የሚለውን ተቀብለውታል። ስለሆነም ሁሉም አካላት ግልጽ ግንዛቤ እንዲኖራቸውና በመረጃ ላይ የተመሠረተ ውሳኔ እንዲወስኑ ተቋራጮችና አስፈጻሚ ኃላፊዎች ተግባብተው በግልጽ የአሠራር ሒደቱን ማወቅና መከተል ይኖርባቸዋል።
74.07 በመቶ የዋጋ ማስተካከያ ከፍተኛ ነውን?
ቁጥሩን ብቻ ዓይቶ 74.07 በመቶ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ ከፍተኛ ነው ብሎ መደምደም አይቻልም። በአንድ በኩል ተቋራጮች አብዛኞቹን የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግባቸውን ማቴሪያሎች፣ ማሽነሪና የሰው ኃይልን በከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ባለው ወካይ ግብዓት እንዲመደብ ካደረጉ የዋጋ ማስተካከያው ከዋናው ገንዘብ 300 ፐርሰንት በላይ ከፍ ሊል ይችላል። ይህ መንግሥት ለተቋራጮች አግባብ ያልሆነ ክፍያ በመክፈል በጣም ከፍተኛ ወጭ ሊያወጣ ይችላል። ምክንያቱም ሁሉም ዕቃዎች፣ የጉልበት ዋጋና ማሽነሪዎች የዋጋ አጨማመራቸው በተመደቡበት ወካይ ግብዓት ልክ ላይሆን ይችላል።
በሌላ በኩል ደግሞ የዋጋ ግሽበቱ የተጋነነ መሆኑን ልብ ማለት ያስፈልጋል። ባልታሰበ የዋጋ ንረት ምክንያት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ውስጥ ያለ እያንዳንዱ ምርትና አገልግሎት ተቋራጮች ሊቋቋሙት ከሚችሉት በላይ ጨምሯል። በዚህ ምክንያት በርካታ የግንባታ ፕሮጀክቶች ከታቀደው ጊዜ እጅግ በጣም ዘግይተዋል፣ ይህም በተራዘመ ጊዜና በዋጋ ንረት ምክንያት ተጨማሪ ወጪዎችን አስከትሏል። 74.07 በመቶ ከፍተኛ ቁጥር ቢመስልም የዋጋ ማስተካከያው አሁን ያለውን የኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ የዋጋ ንረት በአግባቡ መረዳት አስፈላጊ ይሆናል።
የዋጋ ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸውና የማያስፈልጋቸው ግብዓቶች ምንድናቸው?
በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ ያለው ተካታታይና ከፍተኛ የዋጋ ንረት በሁሉም የቁሳቁስ፣ የጉልበትና የማሽነሪ የዋጋ ንረት ላይ ተፅዕኖ እንደሚያሳድር በስፋት ስለታየ የዋጋ ማስተካከያ የማያስፈልጋቸው ግብዓቶች አሉ ወይ የሚለው ጥያቄ አሻሚ አይደለም። ሁሉም ግብዓቶች በዋጋ ንረቱ ሳቢያ ዋጋቸው በጣም ንሯል። አንዳንድ ኃላፊዎችና ባለሥልጣናት ተቋራጮች የሥራ ማስኬጃ ወጪያቸውንና ትርፋቸውን መቆጣጠር እንዳለባቸው ሐሳብ ያቀርባሉ። ይሁን እንጂ ተቋራጮች በዋጋ ንረት ምክንያት የሥራ ማስኬጃ ወጪያቸውን መቀነስ የሚችሉበትን መንገድ በጥናት ተመሥርቶ ስለማይቀርብ በተቋራጮች ዘንድ ለመተግበር ያስቸግራል። የፕሮጀክቶች መዘግየት በራሱ ለተቋራጮች ያልታቀዱ የፕሮጀክት ሥራ ማስኬጃ ወጪዎችን ያመጣል። በመሆኑም ዋጋቸው ያልጨመረ የግንባታ ዕቃዎች፣ የሰው ኃይል፣ የማሽነሪዎችና የሥራ ማስኬጃ ወጪ ባላመኖሩ ሁሉም የግንባታ ግብዓት የዋጋ ማስተካከያ ሊደረግለት ይገባል።
በወካይ ግብዓቶች ሥር መመደብና ችግሮቹ
ሁሉም የግንባታ ግብዓቶች በአራት ወካይ ግብዓቶች ማለትም በሲሚንቶ፣ በአርማታ ብረት፣ በሴራሚክና በነዳጅ እንዲወከሉ መንግሥት መወሰኑና አቅጣጫ መስጠቱ ይታወቃል። ይሁን እንጂ ብዙ ባለሙያዎች በግንባታ ውስጥ ጥቅም ላይ የሚውሉትን እጅግ በጣም ብዙ ግብዓቶችን በመጥቀስ፣ ከቁፋሮ እስከ ማጠናቀቂያ ሥራዎች ላሉ የግብዓት ዓይነቶች በአራት ወካዮች ብቻ መወከል አግባብነት እንደሌለው ይገልጻሉ።
እንደ መንግሥት የተሰጠው አቅጣጫ የግብዓት ዓይነቶች ቅድሚያ በሥራና በተዛማጅ ባህሪያቸው እየታየ በሚቀርቡት ወካይ ግብዓት ሥር እንዲወከሉ ነው። ነገር ግን ይህ አካሄድ ችግር የሚፈጥረው ዕቃዎች በባህሪያቸው ተመሳሳይ ሆነው፣ የዋጋ አጨማመራቸው በጣም የተለያየ ሲሆን ነው። እንደ አማራጭ፣ አንዳንድ የመንግሥት አስፈጻሚ መሥሪያ ቤት ባለሙያዎች በዋጋ ጭማሪ ተመሳሳይነት ላይ ተመሥርተው እንዲመደቡ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ይህም በባህሪም ሆነ በዋጋ የማይመሳሰሉ ዕቃዎችን በአንድ ላይ መመደብን ያመጣል።
በዋጋ ጭማሪ ተመሳሳይነት ላይ የተመሠረተው የመመደብ አካሄድ ከተወሰደ፣ ትልቅ ፈተና የሚሆነው የግብዓቶች ዋጋ መለዋወጥ ነው። የእያንዳንዱ የግንባታ ዕቃዎች የዋጋ ጭማሪ ቋሚ አይደለም። ይህም ማለት በየወሩ ተመሳሳይ ጭማሪ ያላሳዩ ግብዓቶችን እንደ አዲስ መመደብ ያስፈልጋል። ይህ ደግሞ ወጥነት ባለው ምደባ መሄድን ስለማያስችል አስቸጋሪ ነው። በመሆኑም ለተቋራጮችና ለአማካሪዎች የዋጋ ማስተካከያ ሁኔታን ለመገመት አስቸጋሪ ከማድረጉ ባሻገር፣ በፕሮጀክት የገንዘብ ፍሰት ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ ይፈጥራል።
የአመዳደብ ሒደቱ ተግዳሮቶች እንዳሉ ሆኖ በኢትዮጵያ የኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪ ትልቁ ችግር የግንባታ ዕቃዎችን ትክክለኛ የዋጋ መረጃ አለማግኘት ነው። የመንግሥት ውል ዋጋን ከኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት ወይም ከታወቁ የቁሳቁስ አቅራቢዎች መጠቀምን ያዛል። ይሁን እንጂ የስታትስቲክስ አገልግሎትም ሆነ ዕውቅና ያለው ኩባንያ የግንባታ ቁሳቁሶችን ዋጋ በየወሩ አያወጣም። ይህም ለተቋራጮች ወጪዎችን ለመገመትና የፕሮጀክት መሪዎች የፕሮጀክቶችን የፋይናንስ ፍላጎት በትክክል ለማቀድ አስቸጋሪ ያደርገዋል።
ወካይ ግብዓቶች በቁጥር ትንሽ በመሆናቸው የሚነሳው ሌላው ጉዳይ፣ አንዳንድ ተቋራጮች በርካታ የግንባታ ቁሳቁሶችን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ባሳዩ ወካዮች ምድብ ውስጥ ለመመደብ ፍላጎት ማሳየታቸው ነው። የዚህ ዓላማ በርካታ ግብዓቶችን ከፍተኛ የዋጋ ጭማሪ ባለው ወካይ ግብዓት ሥር በመመደብ ከፍተኛ የዋጋ ማስተካከያ ማግኘት ነው። ይሁን እንጂ ይህ አካሄድ ትክክለኛ ያልሆነ የዋጋ ተመንን በማስከተል መንግሥት ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ የሚያደርገውን ጥረት ሊያደናቅፍ ይችላል። በተቋራጮች መካከል ያለው የሥራ ማስኬጃ ወጪና የትርፍ መጠን ተመሳሳይ አለመሆን፣ በነፃ ገበያ ኢኮኖሚ ውስጥ መንግሥት የሥራ ተቋራጮችን የሥራ ማስኬጃ ወጪና የትርፍ ኅዳግ የመወሰን ሥልጣን የለውም። ይሁን እንጂ በተቋራጮች መካከል የእነዚህ ወጭዎች ወጥ አለመሆን መንግሥት በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ውስጥ የዋጋ ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸውንና የማያስፈልጋቸውን ግብዓቶች በመቶኛ ለመወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የችግሩ ምንጭ በጨረታ ወቅት ተቋራጮች የእያንዳንዱን የሥራ ዓይነት ነጠላ ዋጋ የሒሳብ ስሌት ከሥራ ማስኬጃና የትርፍ ኅዳግ ጋር አለማስገባታቸው ነው። ያለዚህ መረጃ ደግሞ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግለትንና የማይደረግለትን የውል መጠን መወሰን አስቸጋሪ ያደርገዋል።
የኮንስትራክሽን ባለሥልጣን ጥናትና ውጤቱ ሲገመገም
በሚያዝያ 2014 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን፣ ለዘገዩ የዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክቶች የዋጋ ማስተካከያ ሒደቶችና አማራጭ የበጀት አመላካች ጥናት ማውጣቱ ይታወሳል። ጥናቱ በአጠቃላይ በ40 ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ 451 ፕሮጀክቶች መኖራቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፣ የመጀመሪያው የውለታ መጠናቸው 62,320,092,362.39 ብር ሲሆን ቀሪው ያልተሠራው የሥራ መጠን 27,266,710,769.22 ብር መሆኑን ይጠቁማል።
ጥናቱ የፕሮጀክቶችን ያልተሠራ ሥራ በዋጋ ማስተካከያ ለማሠራት ሁለት የአማራጭ መፍትሔዎችን አቅርቧል። የመጀመሪያው መፍትሔ በዶላር ምንዛሪ ለውጥ ላይ የተመሠረተ ሲሆን፣ ሁለተኛው ደግሞ ፕሮጀክቶች ሲጀመሩ ከነበሩበት መነሻ ዋጋ (Base Price) ወደ አሁኑ ዋጋ (Current Price) በመቀየር ላይ የተመሠረተ ነው። ይሁን እንጂ የጥናቱ ስሌቶች እንዴት እንደተሣሉ የሰጠው መረጃ የለም።
በጥናቱ መሠረት ቀሪ ፕሮጀክቶችን ለማጠናቀቅ መንግሥት ከ78,685,926,986.50 ብር እስከ 90,674,105,596.31 ብር ወጪ ማድረግ ይኖርበታል። ይሁን እንጂ በጥናቱ ሒደትና ውጤት ላይ በርካታ የሚነሱ ጉዳዮች አሉ።
ከችግሮቹ ውስጥ አንዱ በዶላር ምንዛሪ ለውጥ ላይ የተመሠረተው ማስተካከያ የውጭ ምንዛሪ የማይጠይቁ እንደ የአገር ውስጥ ቁሳቁስና ጉልበት ያሉ ግብዓቶችን በትክክል አለመወከሉ ነው። በተጨማሪም ጥናቱ የውጭ ምንዛሪ ለውጡን የወሰደው ከብሔራዊ ባንክ መረጃ መሆኑን ይገልጻል። ይሁን እንጂ መሬት ላይ ያለው ሀቅ የግንባታ ዕቃዎች ከውጭ ወደ አገር ውስጥ የሚገቡት በስፋት በጥቁር ገበያ የውጭ ምንዛሪ አማካይነት ነው።
ሌላው ጉዳይ ጥናቱ ለዋጋ ማስተካከያ ስሌቶች ወሳኝ የሆነውን የወካይ ግብዓቶችን ይዘት በመቶኛ አለመጥቀሱ ነው። ጥናቱ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግባቸውና የማይደረግባቸው ግብዓቶች መጠን እንዴት እንደሚሰላም አያብራራም። በመሆኑም ጥናቱ በትክክል ስለመሠራቱና ውጤቱም ትክክል ስለመሆኑ ጥያቄ ሊያስነሳ ይችላል።
የጥናቱ ውጤት ሲጠቃለል በባለድርሻ አካላት በተለይም በሚመለከታቸው የመንግሥት ባለሥልጣናትና አስፈጻሚዎች፣ ለዩኒቨርሲቲ ፕሮጀክቶች ቀሪ ግንባታ አስፈላጊውን የዋጋ ማስተካከያ ወጪ በትክክል ማወቅ እንዳልተቻለ ነው።
የዋጋ ማስተካከያን በአግባቡ አለመረዳትና መዘዞቹ
የዋጋ ማስተካከያ ሒደቶችን በተመለከተ ያለው ግልጽ ያልሆነ አረዳድ በዚሁ ከቀጠለ በተጓተቱ የዩኒቨርሲቲ ግንባታ ፕሮጀክቶች፣ እንዲሁም በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪው ላይ የሚኖረው ተፅዕኖ አስከፊ ሊሆን ይችላል። አንዳንድ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ተቋራጮች የፕሮጀክት ባለቤቶችንና የአማካሪዎችን በዋጋ ማስተካከያ ሒደት ውስጥ ያለውን የአረዳድ ክፍተት ተጠቅመው፣ ፍትሐዊ ያልሆነ ጥቅማ ጥቅሞችን ሊያገኙና ከአገሪቱ የኢኮኖሚ ቀውስ ውስጥ ሀብት ሊያካብቱ ይችላሉ። በተቃራኒው ግራ የተጋቡ አማካሪዎች የክፍያ ማስተካከያዎችን ለማፅደቅ ሊያመነቱ ይችላሉ፡፡ ይህም ክፍያ እንዲዘገይ በማድረግ ተቋራጮች ለባሰ የገንዘብ ፍሰት ችግር ሊዳረጉ ይችላሉ።
የዋጋ ማስተካከያ ምን ያህል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ በምሳሌ ለማየት 100,000,000 ብር ቀሪ ውል ያለውን ፕሮጀክት እንመልከት። የዋጋ ማስተካከያ ስሌት (Pn) አሁን ባለው የአረዳድ ችግር ምክኒያት በ0.1 ቢጨምር፣ መንግሥት ተጨማሪ 10,000,000 ብር ያወጣል (0.1 *100,000,000= 10,000,000 ብር)። ይህ የሚያሳየን የዋጋ ማስተካከያ ስሌት ምን ያክል ጥንቃቄ የሚፈልግ ሥራ እንደሆነ ነው። አሁን ካለው የአረዳድ ዝንፈትና ከፕሮጀክቶቹ ብዛት አንፃር ሲታይ በትንሹ 451 ያህል ስህተቶች ሊኖሩ ቢችሉ፣ አንድ ጊዜ በስህተት አረዳድ ከተሠራ የመንግሥትን ካዝና ምን ያህል ሊያመነምን እንደሚችልና ለማስተካከልም ምን ያህል ፈታኝ እንደሚሆን መገመት አይከብድም። ከዋጋ መናር በተጨማሪ በተፈጠረው የአረዳድ ችግር ምክንያት ብቻ መንግሥት በአሥር ቢሊዮኖች የሚቆጠር ብር እንዲያጣ ሊያደርገው ይችላል።
ስለሆነም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት በተለይም የመንግሥት ተቆጣጣሪ መሥሪያ ቤቶች፣ በዋጋ ማስተካከያ ሒደቱና ውጤት ላይ የሚሰትዋሉ ችግሮችን ከሥር ከሥር ተከታታይ ውይይቶችንና ጥናቶችን በማድረግ መፍታት ይጠበቅባቸዋል። ይህን አለማድረግ በኮንስትራክሽን ኢንዱስትሪና በአገሪቱ ኢኮኖሚ ላይ አስከፊ መዘዝ ሊያስከትል ይችላል።
መውጫ
የመፍትሔ ሐሳቦች፡- በኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲዎች የግንባታ የዋጋ ማስተካከያ ፍትሃዊነትን እና ግልጽነትን እንዴት ማረጋገጥ ይቻላል? የዚህ ጽሑፍ አቅራቢዎች በዋጋ ማስተካከያ ላይ የራሳቸውን ጥናት ካደረጉና ለተለያዩ ፕሮጀክቶች የዋጋ ማስተካከያ ሥራዎችን ከሠሩ በኋላ ካገኙት ልምድ ተነስተው የሚከተሉትን የመፍትሔ ሐሳቦች አቅርበዋል።
የወካዮችን ቁጥር መጨመር፡ የወካይ ግብዓቶች ቁጥር መጨመር እያንዳንዱን ግብዓት በወካዮች ሥር በአግባቡ ለመመደብ ያስችላል። ይህን ማድረግ የትኞቹ ግብዓቶች በየትኞቹ ወካዮች ሥር ይመደቡ የሚለውን ጭቅጭቅ በአግባቡ ይቀንሰዋል። እስከ አሥር የሚደርሱ ወካይ ግብዓቶች ቢኖሩ የተሻለ የዋጋ ማስተካከያ ማድረግ እንደሚቻል ጸሐፊዎች ያምናሉ።
የግንባታ ግብዓቶችን ዋጋ በማጥናት በየወሩ ማሳወቅ፡ የኢትዮጵያ ስታትስቲክስ አገልግሎት የግንባታ ግብዓቶችን ዋጋ ተአማኒና ተጨባጭ ከሆኑ የገበያ ምንጮች መረጃዎችን በማጠናቀር ሰብስቦ ማሳተም ቢችል የተሻለ የዋጋ ማስተካከያ መሥራት ያቻላል። ይህን ማድረግ ወርሐዊ የዋጋ ማስተካከያ ስሌት ሒደትን ከማፋጠኑ ባሻገር፣ አማካሪዎችና ተቋራጮች ተአማኒ ወርኃዊ ዋጋ በመውሰድ ተቋራጮች የዋጋ ማስተካከያ ክፍያቸውን በየወሩ እንዲከፈሉ ያስችላል።
የክፍያ የምስክር ወረቀቶችንና የዋጋ የማስተካከያ ክፍያዎችን በየወሩ ማዘጋጀት፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ በየወሩ የሚሠሩ ሥራዎች መጠን ዝቅተኛ ቢሆንም፣ በየወሩ ለተሠሩ ሥራዎች ክፍያ ማዘጋጀት ተገቢ ይሆናል። የዋጋ ማስተካከያ ክፍያ ሥሌት (Pn) የሚሰላው ሥራው በተሠራበት ወር ያለውን የግብዓቶች ዋጋ መሠረት አድርጎ ስለሆነ በየወሩ የዋጋ ማስተካከያ መሥራት ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ አሁን ላይ ባለው ነባራዊ ሁኔታ በየወሩ የግብዓቶች ዋጋ እየጨመረ ስለሚሄድ የዋጋ ማስተካከያው ሥራው በተሠራበት ወር ካልተሠራ የዋጋ ማስተካከያ ሥሌቱ ከፍ ይላል። ይህም መንግሥትን አግባብ ላልሆነ ተጨማሪ ወጭ ይዳርጋል። አንዳንድ ጊዜም ከፍ ያለ የዋጋ ማስተካከያ ሥሌት ለማግኘት ሆን ብለው የክፍያ ሰርተፊኬት ለማዘጋጀት የሚያዘገዩ ሥነ ምግባር የጎደላቸው ተቋራጮችና አማካሪዎች ሊኖሩ ይችላሉ።
ግልጽ መመርያዎችን ማዘጋጀት፣ የኢትዮጵያ ኮንስትራክሽን ባለሥልጣን በሁሉም ዩኒቨርሲቲዎች ወጥ የሆነ የዋጋ ማስተካከያ ሒደት እንዲኖር ከሁሉም ጋር በተከታታይ ተቀራርቦ በመሥራት ወጥ የሆነ መመርያ ቢያዘጋጅ መልካም አፈጻጸም እንዲኖር ማድረግ ይችላል። መመርያውም የዋጋ ማስተካከያ የሚያስፈልጋቸውንና የማያስፈልጋቸውን ግብዓቶች በግልጽ የሚያስቀምጥ፣ የዋጋ አወሳሰድን የሚያሳይ፣ እንደ ፕሮጀክቶቹ ባህሪ በጥንቃቄ መታየት ያለባቸውን ነገሮች የሚተነትን፣ የዋጋ ማስተካከያ የሚደረግባቸውን ግብዓቶች መጠን አሰላል ላይ መጠቀም የሚገባውን ማባዣዎች (Conversion Factor) እና የመሳሰሉትን በአግባቡ ማሳየት ይኖርበታል።
ለአዲስ የሥራ ትዕዛዝ አዲስ ዋጋ መትከል፡ አዲስ የሥራ ትዕዛዝ ለተቋራጩ በሚሰጥበት ወቅት የሥራው ዓይነት በውሉ ላይ ከነበረ በውሉ መሠረት እንዲሠራ ተቋራጩ የሚገደድ ቢሆንም፣ አሁን ባለው የዋጋ ንረት ምክንያት ይህን ማድረግ ተቋራጩን ለተጨማሪ ችግር መዳረግ በመሆኑ፣ የወቅቱን ዋጋ መሠረት ያደረገ አዲስ ነጠላ ዋጋ በመትከል ተቋራጮችን ከተጨማሪ ጫና መታደግ ይቻላል።
የሥራ ማስኬጃና የትርፍ መጠን መወሰን፡ አሁን ባለው ነባራዊ ሁኔታ ተቋራጮች የተለያየ የሥራ ማስኬጃና የትርፍ መጠን ያላቸው ሲሆን፣ ይህን ለማስተካከል ለዚህ የዋጋ ማስተካከያ ብቻ መንግሥት የተቋራጮችን የሥራ ማስኬጃና የትርፍ መጠን አጥንቶ መወሰን ይኖርበታል። ይህ ሁሉንም ተቋራጮች ላይወክል ቢችልም፣ ወጥነት ያለውና ግልጽነትን ያመጣል።
የተጠናከረ የአማካሪዎችና የተቋራጮች መድረክ መፍጠር፡ ከአማካሪ አማካሪና ከተቋራጭ ተቋራጭ የተለያየ ግንዛቤ ስላለና ተመሳሳይ አሠራር በሁሉም ዘንድ መፍጠር እንዲቻል የአማካሪዎችና ተቋራጮች ፎረም ተፈጥሮ የሐሳብ ውይይት እየተደረገ ወጥ በሆነ መንገድ የዋጋ ማስተካከያው መሠራት ይኖርበታል። ይህም በመላ አገሪቱ ባሉ ዩኒቨርሲቲዎች ወጥነት ያለውና ፍትሐዊ የሆነ የዋጋ ማስተካከያ ሒደት ይኖራል።
የዋጋ ማስተካከያ የሚጀምርበትን ጊዜ ማስተካከል፡ የዋጋ ማስተካከያ የሚጀምረው ውሉ ከፀናበት ቀን ጀምሮ ከአሥራ ሁለት ወራት በኋላ ነው። ውሉ የሚፀናው ደግሞ የውል ሰነድ ከተፈረመበት ጊዜ ጀምሮ ነው። ይሁን እንጂ አሠሪ መሥሪያ ቤቶች ጨረታ ካወጡ በኋላ በተለያዩ ምክንያቶች የውል መፈራረም ቀንን በጣም ሊያዘገዩት ይችላሉ። በዚህም ምክንያት ተቋራጩ ውል ሳይዝ ብዙ ጊዜ ሊቆይ ይችላል። ይህም የዋጋ ግሽበቱን ከታሰበው በላይ ያደርገዋል። ስለሆነም በጨረታ መዝጊያ ቀንና በውል ቀን መካከል ሰፊ ጊዜ ሲባክን ተቋራጩን በጣም ተጎጂ ያደርገዋል። ስለሆነም እንዲህ ዓይነት ችግር ለገጠማቸው ፕሮጀክቶች የዋጋ ማስተካከያ የሚጀምርበትን ቀን ከአሥራ ሁለት ወራት በኋላ የሚለውን መቀየር ያስፈልጋል። ከዚህ በተጨማሪ አንዳንድ ተቋራጮች ውል ወስደው ሥራ ሳይጀምሩ ለረዥም ጊዜ በመቆየት የውል ማስተካከያ ጊዜው ሲጀምር ብቻ ሥራ ይጀምራሉ። አንዳንድ ተቋራጮች ደግሞ ያለውን ጫና ተቋቁመው ውል ከወሰዱበት ጊዜ ጀምሮ የዋጋ ማስተካከያ የሚጀምርበት ጊዜ ሳይገቡ በርካታ ሥራዎችን በዕቅዳቸው መሠረት ያስኬዳሉ። በዚህ ውስጥ ሥራቸውን በአግባቡ የሠሩ ተቋራጮች ተጎጂ ሲሆኑ፣ ሥራውን ሳይሠሩ ቆይተው የዋጋ ማስተካከያ ሲገቡ የሚጀምሩት ደግሞ የተሻለ ተጠቃሚ ይሆናሉ። ይህም ምስጉን ተቋራጮችን ስለሚጎዳ መንግሥት ለእንደዚህ ዓይነት ተቋራጮች የዋጋ ማስተካከያው ጊዜ ቀደም ብሎ እንዲጀምር ማድረግ ቢችል መልካም ነው። በቀጣይ ጽሑፍ እስክንገናኝ መልካም ጊዜ!
ከአዘጋጁ፡- ጸሐፊዎቹ በቅደም ተከተል በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምሕንድስና መምህርና በቢአይቲ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ የኮንትራት መሐንዲስ፣ በባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ የሲቪል ምሕንድስና መምህርና በቢአይቲ ትሬዲንግ ኃላፊነቱ የተወሰነ ኩባንያ ፕሮጀክት አስተባባሪ ሲሆኑ፣ ጽሑፉ የእነሱን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡