Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊኢሰማኮ በሰላማዊ ሠልፍ ለመንግሥት ጥያቄ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ኢሰማኮ በሰላማዊ ሠልፍ ለመንግሥት ጥያቄ እንደሚያቀርብ አስታወቀ

ቀን:

በኑሮ ውድነት ምክንያት በሠራተኞች ላይ እየደረሰ ያለው ጫና መፍትሔ እንዲያገኝና ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል ምጣኔ እንዲሻሻል፣ በሰላማዊ ሠልፍ ጥያቄ ለመንግሥት እንደሚያቀርብ የኢትዮጵያ ሠራተኛ ማኅበራት ኮንፌዴሬሽን (ኢሰማኮ) አስታወቀ፡፡

‹‹ለሠራተኛው መሠረታዊ ጥያቄዎች አፋጣኝ መፍትሔ›› በሚል መሪ ቃል የዘንድሮውን ሜይዴይ በዓል ለማክበር የተነሳው ኢሰማኮ፣ ሊመለሱ የሚገባቸው አንገብጋቢ የሠራተኛው ጥያቄዎች በመደራረባቸው እንደሆነም ተገልጿል፡፡

‹‹በዘንድሮው የሜይዴይ በዓል በዋናነት የሚነሳው ጥያቄ የኑሮ ውድነት ነው፡፡ በሁለተኛ ደረጃ ደግሞ ያስቀመጥነው ዝቅተኛ የደመወዝ ወለል እንዲስተካከል ነው፤›› ያሉት የኢሰማኮ ፕሬዚዳንት አቶ ካሳሁን ፎሎ፣ ‹‹እነዚህ ወቅታዊ ጥያቄዎች በአስቸኳይ መፍትሔ እንዲያገኙ ይፈለጋል፤›› ብለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት እየጎላ የመጣውን የሠራተኞች የመደራጀት መብት ጥሰት እንዲቆም ጭምር ጥያቄ ይቀርባል ሲሉም አስረድተዋል፡፡

የሠራተኛው በነፃ የመደራጀትና የመደራደር መብት በሕጉ መሠረት እየተተገበረ ባለመሆኑ፣ ሕግ እንዲከበር በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች በአደባባይ በሚካሄዱ ሠልፎችና በፓናል ውይይቶች ለመንግሥት እንዲደርስ እንደሚደረግ አቶ ካሳሁን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

‹‹ኢሰማኮ ሊመለስልን ይገባል ብሎ የሚያቀርበው ሌላው ጥያቄ በቀድሞ የሠራተኛና ማኅበራዊ ሚኒስቴር፣ አሁን የሥራና ክህሎት ሚኒስቴር የወጣውን የሥራና ሠራተኛ አገናኝ ኤጀንሲዎች የ20/80 መመርያን የሚመለከት ነው፤›› ብለዋል፡፡

በዚህ መመርያ መሠረት ኤጀንሲዎች ለሚያስቀጥሩት ሠራተኛ ከኩባንያዎች ከሚያገኙት ገቢ 20 በመቶውን ለአስተዳደራዊ ወጪ በማስቀረት፣ 80 በመቶውን ለሠራተኞች መክፈል አለባቸው የሚለው ድንጋጌ እየተከበረ ባለመሆኑ፣ ይህም በሕጉ መሠረት ተፈጻሚ እንዲሆን ኢሰማኮ ጥያቄ ያቀርባል ብለዋል፡፡ ይህ መመርያ በአግባቡ ሊተገበር ባለመቻሉ ሠራተኞች በከፍተኛ ሁኔታ ችግር ውስጥ መሆናቸውን አቶ ካሳሁን ገልጸው፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኩረት ሰጥቶ የማስተካከያ ዕርምጃ መውሰድ ይኖርበታል ሲሉ አክለዋል፡፡

‹‹በተለይ ከኑሮ ውድነት ጫና ጋር የተያያዘውን ጉዳይ አጠናክረን የምናቀርብበት ነው፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ከሠራተኛው ደመወዝ ላይ የሚቆረጠው የሥራ ግብር ጊዜውን የዋጀና የብር የመግዛት አቅምን ያላገናዘበ በመሆኑ በአስቸኳይ ይስተካከል ዘንድ ጥያቄ እንደሚቀርብ አስታውቀዋል፡፡

የሥራ ግብር ይቀነስ ብቻ ሳይሆን በትራንስፖርት ክፍያ፣ በውሎ አበልና በመሰል ክፍያዎች ላይ የሚጣሉ ፍትሐዊ ያልሆኑ ታክሶች በሠራተኛው ላይ ከፍተኛ ጫና በማሳደራቸው ሊስተካከሉ ይገባል ብለዋል፡፡

‹‹እስካሁን ሥራ ላይ ባለው ሕግ የሥራ ግብር የማይከፈልበት ከ600 ብር በታች ሲሆን፣ ከ600 ብር በላይ ያለው ግብር ይከፈልበታል፤›› ያሉት አቶ ካሳሁን፣ ይህ ሕግ የወጣው የገንዘብ የመግዛት አቅም ጠንካራ በነበረበት ወቅት ስለነበር እስካሁን መቆየት አልነበረበትም ሲሉ ሞግተዋል፡፡

‹‹ከውሎ አበል ክፍያ ጋር በተያያዘም አንድ ሠራተኛ ሲወጣ የሚከፈለው አበል ከ500 ብር በላይ ከሆነ ግብር ይጠይቅበታል፡፡ 500 ብር ለአልጋ፣ ለቁርስ፣ ለምሳና ለእራት ይበቃል ተብሎ ሕጉ የወጣ ቢሆንም፣ አሁን ካለው የኑሮ ውድነት አንፃር በቂ ስላልሆነ፣ መሻሻል ስለሚኖርበት በነገው ሠልፍ ላይ ለመንግሥት ጥያቄው ይቀርባል፤›› ብለዋል፡፡

በአንዳንድ ድርጅቶች ውስጥ ያሉ ሠራተኞች ለትራንስፖርት ተብሎ የሚከፈላቸው ገንዘብ ከ600 ብር በላይ ከሆነ ግብር ይከፈልበት መባሉ አግባብ ባለመሆኑ ይህም እንዲስተካከል ኢሰማኮ ይፈልጋል፡፡

የነዳጅ ዋጋ ዝቅተኛ በነበረበት ጊዜ የወጣ አሠራር የነዳጅ ዋጋ እጅግ በጨመረበት በዚህ ወቅት፣ የቀድሞውን ሕግ ይዞ መጓዝ ፍትሐዊ አይደለም የሚል አቋም ያለው ኢሰማኮ፣ ጥያቄዎቹ እስኪመለሱ ድረስ በሰላማዊ መንገድ ትግሉን እንደሚቀጥል አቶ ካሳሁን ገልጸዋል፡፡

በመሆኑም በዘንድሮው የሜይዴይ በዓል እነዚህን ጥያቄዎች በመያዝ በአዲስ አበባ በመስቀል አደባባይ፣ የኢሰማኮ ቅርንጫፎች በሚገኙባቸው በአዳማ፣ በጅማ፣ በሐዋሳ፣ በድሬዳዋ በሰላማዊ ሠልፍ ይከበራል ተብሏል፡፡

በባህር ዳርና በኮምቦልቻ ግን ከፀጥታ ችግር አኳያ በፓናል ውይይት የሚካሄድ መሆኑን የገለጹት አቶ ካሳሁን፣ በእነዚህ ክንውኖች ላይ ዋነኞቹ የሠራተኞች ጥያቄዎች እንደሚቀርቡ ጠቅሰዋል፡፡ ሜይዴይ በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ134ኛ ጊዜ የሚከበር ሲሆን፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ48ኛ ጊዜ ይከበራል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...