Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ብሔራዊ መታወቂያ አለመኖር እንቅፋት እንደሆነበት ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

የወንጀል ተጠርጣሪዎችን ለመያዝ ብሔራዊ መታወቂያ አለመኖር እንቅፋት እንደሆነበት ፌዴራል ፖሊስ አስታወቀ

ቀን:

  • በቤልጂየምናሆላንድ የሠለጠኑ አነፍናፊ ውሾችን ገዝቻለሁ ብሏል

የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ተጠርጣሪዎች ይዞ ፍርድ ቤት ለማቅረብ፣ በአገር አቀፍ ደረጃ የብሔራዊ መታወቂያ አለመኖር ማነቆ እንደሆነበት አስታወቀ፡፡

ፖሊስ ይህን ያስታወቀው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕግና ፍትሕ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ፣ የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽንና ተጠሪ ተቋማትን የ2015 በጀት ዓመት የዘጠኝ ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት በገመገመበት ወቅት ነው፡፡

ቋሚ ኮሚቴው የፍርድ ቤት ትዕዛዝ አለመከበርን በተመለከተ በቀረበው ጥያቄ፣ በበጀት ዓመቱ ፍርድ ቤት እንዲቀርቡ ያዘዘው 2,945 ተከሳሾችን ቢሆኑም፣ የቀረቡት 1,169 (39.6 በመቶ)፣ እንዲሁም ማስረጃ እንዲቀርብባቸው ከታዘዘው 4,775 መዛግብት ውስጥ ማቅረብ የተቻለው 3,298 (69 በመቶ) መሆኑን በሪፖርቱ መገለጹን አስታውቋል፡፡

በተመሳሳይ በርካታ ተከሳሾችና ማስረጃዎች ባለመቅረባቸው የሚዘገዩ በርካታ መዛግብት መኖራቸውን በዘጠኝ ወር ሪፖርቱ መጥቀሱን ቋሚ ኮሚቴው ገልጾ፣ ለዚህም እንደ ምክንያት ከተቀመጡ ነጥቦች አንዱ ተጠርጣሪዎችና ተከሳሾች ከአገር መውጣታቸውን ከኢሚግሬሽንና ዜግነት ጉዳይ ዋና መመርያ ማረጋገጫ ማቅረብ መቻሉ እንደሆነ አስረድቷል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ምክትል ኮሚሽነር ዘለዓለም መንግሥቴ ለቀረበው አስተያየት በሰጡት ማብራሪያ፣ ‹‹የተከበረው ምክር ቤት እንዲረዳን የምፈልገው፣ ብሔራዊ መታወቂያ የለንም፣ እንግዲህ በአምስት ብርና በአሥር ብር ወይም በ15 እና 20 ብር የሚወጣ መታወቂያ ላይ የተመዘገበ ሰው ፈልጎ ማግኘት ራሱን የቻለ ትልቅ ሥራ ነው፣ ምክር ቤቱ እንዲረዳን የምፈልገው ጉዳዩ በጣም ትልቅ ሥራ መሆኑን ነው፤›› ብለዋል፡፡

‹‹ያለው መታወቂያ ሲታይ አንድ ሰው ስድስትና ስምንት በተለያየ አካባቢና በተለያየ ስም አውጥቶ እናገኘዋለን፡፡ በመሆኑም ይህን ወንጀለኛ ከዚህ ሁሉ ውስጥ ፈልጎ ማግኘት የራሱ የሆነ ውስንነት አለው፤›› ብለው፣ ይህ የሆነው ደግሞ ብሔራዊ መታወቂያና ዳታቤዝ ባለመኖሩ እንደሆነ አስረድተዋል፡፡

ፖሊስ በአሁኑ ወቅት የወንጀል ተጠርጣሪዎችን በቁጥጥር ሥር እያዋለ ያለው በሌሎች ቴክኒካዊ ጉዳዮችና ከሌሎች አካላት ጋር በመቀናጀት መሆኑን ጠቅሰው፣ ለአብነትም ከብሔራዊ መረጃና ኢንሳ ጋር በመተባበር እንጂ፣ ‹‹በትክክለኛው የቀበሌ መታወቂያ ተጠርጣሪን ማግኘት በጣም ከባድ ነው፤›› ብለዋል፡፡

መንግሥት የብሔራዊ መታወቂያ ፕሮጀክት በሙከራ ደረጃ በተለያዩ የፌዴራል የመንግሥት ተቋማት ላይ እየተተገበረ ሲሆን፣ ይህ መታወቂያ የነዋሪነት ወይም አድራሻ ለማረጋገጥ የሚሠራበት እንዳልሆነ ይነገራል፡፡

ምክትል ኮሚሽነሩ ከአባላቱ የተነሱትን የፍርድ ቤት ውሳኔ አለመከበርን ጥያቄ አስመልከተው ሲያብራሩ፣ ‹‹የፍርድ ቤት ውሳኔ በጣም ነው የምናከብረው፣ በተለይ ደግሞ ይህ ተቋማዊ ሪፎርም ከመጣ ወዲህ ፍርድ ቤት በእኛ ላይ በየትኛውም ጊዜ አቤቱታና ደብዳቤ አቅርቦ ወይም ጽፎልን አያውቅም፣ ነገር ግን ፍርድ ቤት አካባቢ የቴክኒክ ችግሮች አሉ፤›› ብለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ ዋና ኮሚሽነር ጄኔራል ደመላሽ ገብረ ሚካኤል በበኩላቸው የተቋማቸውን የዘጠኝ ወራት ሪፖርት ሲያቀርቡ፣ የፖሊስን ሥራ ዘመናዊ ቴክኖሎጂ የሚያላብስ አዲስ ሶፍትዌር በአርቲፊሻል ኢንተለጀንስና በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ በጋራ እያበለፀጉ መሆናቸውን አውስተዋል፡፡ ይህ ሶፍትዌር በጥቂት ወራት ይፋ እንደሚደረግ ገልጸው፣ በዚህ አፕሊኬሽን አማካይነት ማንኛውም ዜጋ ወይም ቱሪስት አደጋዎች ሲያጋጥሙት በአፕሊኬሽኑ አማካይነት ሪፖርት ማድረግ ያስችለዋል፡፡

የፌዴራል ፖሊስ በቤልጂየምና በሆላንድ የሠለጠኑ ኬ19 የተሰኙ አነፍናፊ ውሾችን በመግዛት፣ ወደ አገር ቤት ማስገባቱን ኮሚሽነር ጄኔራሉ አስታውቀዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...