Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ለኮምቦልቻ ወደብ የተያዘ በጀት ለጂማ አለመዛወሩን አስተባበለ

ተዛማጅ ፅሁፎች

  • የመቀሌ ደረቅ ወደብና ተርሚናልን ለማስጀመር ዝግጅት ማጠናቀቁን ገልጿል

የኢትዮጵያ የባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት፣ በአማራ ክልል ደቡብ ወሎ ዞን ኮምቦልቻ ከተማ አዲስ ደረቅ ወደብ ለመገንባት የያዘውን በጀት ወደ ጂማ የደረቅ ወደብ ግንባታ አዘዋውሯል በሚል የሚናፈሳው መረጃ የተዛባ ነው ሲል አስተባበለ፡፡

ከኮምቦልቻ ደረቅ ወደብ ጋር ተያይዞ ከሰሞኑ ሲናፈስ የነበረው ጉዳይ ዓላመውን ስቶ በሌላ መልኩ ሲገለጽ የቆየ መሆኑን የተቋሙ አመራሮች፣ የድርጅቱን የዘጠኝ ወራት የዕቅድ አፈጻጸም አስመልክቶ በሰጡት የጋዜጣዊ መግለጫ አስረድተዋል፡፡

በኢባትሎአድ የፖርት ተርሚናል አገልግሎቶች ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ምሕረተዓብ ተክሉ እንዳስረዱት፣ ተቋሙ ኮምቦልቻ ላይ ያለው ተርሚናል ቦታ በጣም ጠባብ በመሆኑ ተጨማሪ የማስፋፊያ ቦታ ከተጠየቀ ከአምስት ዓመታት በላይ እንደሆነ አስታውሰው፣ በተለያየ ጊዜ የጠየቃቸው ቦታዎች ሲቀያየሩ ቆይቶ በስተመጨረሻ መገኘቱን ተናግረዋል፡፡

የተመረጠው ቦታ ከኢንዱስትሪ ፓርክና አየር ማረፊያ፣ ከባቡር ሃዲድ በጣም የቀረበ ሆኖ የተገኘና የክልሉ መንግሥት ተስማምቶ የከተማ አስተዳደሩም አምኖ ኢባትሎአድ በጀት በጅቶ ሲንቀሳቀስ አንድ ችግር ማጋጠሙን ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገልጸዋል፡፡

ኢባትሎአድ ለማስፋፊያው ቦታ ከግማሽ ቢሊዮን ብር በላይ ካሳ እንዲከፍል መጠየቁን ያስታወቀ ሲሆን፣ ነገር ግን በዚህ ዙሪያ ጥያቄ እንደነበረውና ይህም ‹‹የመሬት ታሪፍ ስሌቱ ልክ አይደለም፣ በድጋሚ ይታይ›› የሚል እንደነበር ተጠቅሷል፡፡

ከድርጅቱ በተጨማሪ የትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ ሚኒስቴር፣ የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን እንዲሁም የአማራ ክልል መስተዳደር በጉዳዩ ላይ እንዲሳተፉ ከማድረግ በተጨማሪ፣ በተለያየ ጊዜ የተሾሙ የከተማው ከንቲባዎችን ለማሳመን የተለያዩ ሥራዎችና ጥረቶች እንዳልተሳኩ ያስረዱት አቶ ምሕረተዓብ፣ ይህ ባለመሆኑ ምክንያት ግንባታው ሳይጀመር እንደቀረ ተናግረዋል፡፡

‹‹ከዚያ ውጭ በጀቱ ወደ ጂማ ሄዷል የሚባለው የሐሰት ፕሮፓጋንዳ ነው፤›› ሲሉ ያስረዱት ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚው፣ መሥሪያ ቤቱ በዕቅድ የሚንቀሳቀስ፣ አስካሁን ስምንት ወደቦች ያሉትና ሁለት የማስፋፊያ ሥራዎች ወደ ፊት ለመሥራት በዕቅድ እንደያዘ በመግለጽ፣ እያንዳንዱ ፕሮጀክት በተያዘለት በጀት የሚሠራና ከአንዱ ወደ ሌላኛው የሚወሰድበት አግባብ እንደሌለ አስታውቀዋል፡፡

በቀጣይ በኮምቦልቻ ከመሬት ስሌት አከፋፈሉ ጋር በተያያዘ በገለልተኛ አካል ተጠንቶ መስተካከል የሚችልበት ዕድል ካለ በማግሥቱ መገንባት እንደሚቻልና የበጀት ችግር እንደሌለ፣ ወደ ጂማም የሄደ ፕሮጀክት አለመኖሩን ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ድርጅት አስታውቋል፡፡

የጂማ ፕሮጀክት በተያዘው ዓመት የማስተር ፕላን፣ የቢዝነስ ፕላን የማስጠናትና አጠቃላይ አጥር የማጠር ሥራ የሚመለከትና ለዚህም 150 ሚሊዮን ብር የተመደበለትና ይህም በተያዘው ልክ እየሄደ እንደሚገኝ ተነግሯል፡፡

የኢባትሎአድ ዋና ሥራ አስፈጻሚ በመሆኑን በቅርቡ የተሾመት በሪሶ አመሎ (ዶ/ር) በበኩላቸው፣ ድርጅቱ ሥራውን የሚሠራው ዓለም አቀፍ ተደራሽነት ያለው እንደሆነና በድርጅቱ የሚደረግ ልማት ከአንድ አካባቢ ተነጥቆ ወደ ሌላ አከባቢ የሚሄድበት አግባብ እንደሌለ አረጋግጠዋል፡፡

በሌላ በኩል ከመቀሌ ወደብና ተርሚናል ጋር ተያይዞ የሰላም ስምምነቱ ከተፈረመ በኋላ ተቋሙ ያደራጀው አንድ ቡድን ሄዶ ቅድመ ዝግጅት እንደተደረገና በሰው ኃይል፣ በአይቲ፣ በመሣሪያዎች (ሁለት ዓመት የቆሙ) ጠግኖ የማስተካከል ሙሉ ዝግጅት የተጠናቀቀ በመሆኑ ከተያዘው ሳምንት ጀምሮ ወደ ሥራ የሚገባበት በቂ ዝግጅት መጠናቀቁ ታውቋል፡፡

ድርጅቱ ባለፉት ዘጠኝ ወራት አጠቃላይ የኦፕሬሽን አገልግሎቱ መጠን 4.1 ሚሊዮን ቶን ማድረሱን ያስታወቀ ሲሆን፣ ከዚህም የድርጅቱን መርከቦች፣ የኪራይ (Slot Carrier and Charter)  መርከቦችን በመጠቀም 2.9 ቶን በማጓጓዝ ከዕቅድ በላይ አፈጻጸም የተመዘገበበት መሆኑ ተገልጿል፡፡

ኢባትሎአድ በዘጠኝ ወራት ከሚሰጠው አገልግሎቶችና ከሌሎች የገቢ ምንጮች  34.8 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ አቅዶ 30.8 ቢሊየን ብር ገቢ ማግኘቱ ታውቋል፡፡ በሌላ በኩል በዚህ ጊዜ ድርጅቱ ለሚያከናውናቸው ሥራዎች  31.09  ቢሊዮን ብር ወጪ ለማድረግ አቅዶ 26.71 ቢሊዮን ብር ወጪ እንዳደረገ በዚህም በተጠቀሰው ጊዜ 3.80 ቢሊየን ብር  ትርፍ ከታክስ በፊት ለማግኘት አቅዶ 4.09 ቢሊዮን ብር ማግኘቱ አስታውቋል፡፡

በሌላ በኩል ባህር ትራንስፖርትና ሎጂስቲክስ አገልግሎት ያሉትን ሁለት የነዳጅ ጫኝ መርከቦቹን ወደ ዕቃ ጫኝ መርከብ ለመቀየር ሲያደርግ የነበረው ድርድር ተሳክቶ፣ መርከቦቹን በአንድ አልትራማክስ  ትልቅ የደረቅ ጭነት መቀየሩን ይፋ አድርጓል፡፡

የድርጅቱ የሺፒንግ አገልግሎት ዘርፍ ምክትል ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድወሰን ካሳ እንደተናገሩት፣ አዲሷ ግዙፍ መርከብ በሻንጋይ የምትገኝ ሲሆን፣ ድርጅቱ መርከቧን እንደተረከበና በቅርቡ ወደ ሥራ እንደምትገባ አስታውቀዋል፡፡ በቅያሬ የመጣችው መርከብ ኤም ቪ አባይ 2 የሚል ስያሜ የተሰጣት ሲሆን፣ ከፍተኛ የመጫን አቅም ያላት ግዙፍ መርከብ እንደሆነች ታውቋል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች