በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማትን ለመቆጣጠር የሚያስችል መመርያ፣ ለከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት ሊቀርብ መሆኑን የትራፊክ ማኔጅመንት ኤጀንሲ አስታወቀ፡፡
ለከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት የሚቀርበው መመርያ በቂ የሆነ ጥናት የተደረገበትና የፍትሕ ቢሮው የመመርያውን ሰነድ ሙሉ ለሙሉ ገምግሞ ያሳለፈው መሆኑን፣ ኤጀንሲው የዘንድሮ ዓመት የስድስት ወራት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርቱን ለመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት ባቀረበበት ወቅት አስታውቋል፡፡
የአጀንሲው ምክትል ዋና ዳይሬከተር አቶ አማረ ታረቀኝ ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ አገልግሎት የሚሰጡ የተሽከርካሪ ማቆሚያ ተቋማት ለመቆጣጠር በበላይነት ኤጀንሲው እየሠራ ቢሆንም እስካሁን የራሱ የሆነ መመርያ የለውም፡፡
በዚህ መሠረት በግሉ ዘርፍ የተሰማሩ ባለሀብቶች ወይም የሕንፃ ባለቤቶች፣ በሕንፃቸው ሥር ያለውን የተሽከርካሪ ማቆሚያ (ፓርኪንግ) የሚጠቀሙት፣ ከታለመለት ዓላማ ውጪ መሆኑን በተደረገው የዳሰሳ ጥናት ለማየት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
እነዚህንም ግለሰቦች ሆኑ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት የሚሰጡ ተቋማትን ለመቆጣጠር፣ መመርያው ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው የገለጹት አቶ አማረ፣ መመርያውን በቅርቡ በማፀደቅ ወደ ሥራ ይገባል ብለዋል፡፡
በሌላ በኩል በአዲስ አበባ ከተማ የሚታየውን የትራፊክ አደጋ ለመቀነስና በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመፈተሽ፣ የመንገድ ደኅንነት ምክር ቤት መቋቋሙን ምክትል ዋና ዳይሬከተሩ ገልጸዋል፡፡
በዚህ መሠረት በ2015 ዓ.ም. በጀት ዓመት የስድስት ወራት ሪፖርት ላይ የተወሰኑ የምክር ቤት አባል ተቋማት ሚናቸውን በአግባቡ መወጣት ላይ ውስንነት እንደሚታይባቸው፣ ወደፊት ችግሩን እንዲቀርፉ ምክር ቤቱ ውሳኔ ማስተላለፉን አብራርተዋል፡፡
በአጠቃላይ በከተማዋ የተሽከርካሪ ማቆሚያ አገልግሎት እየሰጡ ያሉ ተቋማት፣ በከተማ አስተዳደሩ የካቢኔ አባላት በኩል ፀድቆ ተግባራዊ የሚደረገውን መመርያ በመከተል ሥራቸውን እንዲሠሩ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ከዚህ በተጨማሪም የፓርኪንግ ሥርዓቱን ለማሻሻል 71 የሕንፃ ባለቤቶች ፈቃድ እንዲያወጡ የተደረገ መሆኑን፣ 41 ለሚሆኑ የሕንፃ ባለቤቶች ደግሞ ፈቃዳቸው መታደሱን ሪፖርቱ በቀረበበት ሚያዝ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. ተገልጿል፡፡