Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ከታክስ 200 ቢሊዮን ብር የማመንጨት አቅም ይዛ ግቧን ማሳካት ያልቻለችው አዲስ አበባ ከተማ

ተዛማጅ ፅሁፎች

በአዲስ አበባ ከተማ ብቻ 452‚000 ዜጎች ግብር ይከፍላሉ፡፡ ከእነዚህም ዜጎች በአምስቱ የግብር ከፋይ መደቦች ውስጥ የሚገኙ ናቸው፡፡ በከተማ አስተዳደሩ ደረጃ “ሀ” ምድብ ሥር የሚገኙ የግብር ከፋዮች ብዛት 71‚879 ሲሆን፣ ከእነዚህም ከተማዋ የምታገኘው ገቢ የአንበሳውን ድርሻ ይይዛል።

በደረጃ “ለ” ምድብ የተመዘገቡት ግብር ከፋዮች ብዛት 48‚116 ሲሆን፣ በደረጃ “ሐ” ምድብ የተመዘገቡት ደግሞ 332‚153 መሆናቸውን ከከተማ አስተዳደሩ ገቢዎች ቢሮ የተገኘ መረጃ ያመለክታል።

በመረጃው መሠረት አብዛኞቹ ግብር ከፋዮች የሚገኙት በደረጃ “ሐ” ምድብ ሥር ነው። የከተማዋ የግብር ከፋዮች ቁጥር ከ2010 ዓ.ም. ጀምሮ ከፍ እያለ መምጣቱንና በ2015 በጀት ዓመት ብቻ ዘጠኝ በመቶ ዕድገት ማሳየቱን መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡ በዚህ ረገድ ምንም እንኳን የግብር ከፋዮች ዕድገት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ ቢሆንም፣ ከተማዋ ካላት አቅም አንፃር የምታገኘው ዓመታዊ የግብር ገቢ ዝቅተኛ መሆኑ ይነገራል፡፡

ቢሆንም የከተማዋ ዓመታዊ የግብር ገቢ ከዓመት ዓመት ዕድገት እየታየበት ሲሆን፣ ለአብነትም እስከዚህ ወር ያለው የ2015 የበጀት ዓመት የ23.5 በመቶ ዕድገት መመዝገቡን ከገቢዎች ቢሮ የተገኘው መረጃ ያሳያል፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካዊና ኢኮኖሚያዊ ሁነቶች መናኸሪያ፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት መቀመጫና የዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ ከተማ በሆነችው አዲስ አበባ የሚዘዋወረው ኢኮኖሚ ከፍተኛ እንደሆነ ቢነገርም፣ ያለው ሀብትና ከግብር የሚሰበሰበው ገቢ ግን ዝቅተኛ መሆኑ ዕሙን ነው፡፡

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ገቢዎች ቢሮ ሚያዝያ 16 ቀን 2015 ዓ.ም. ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር “የግብር አሰባሰብ ተግዳሮቶችና መውጫ መንገዶች” በሚል የፓናል ውይይት አካሂዷል፡፡

በፓናል ውይይቱ ከተገኙት መካከል የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር የፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ አብዱል ቃድር ሬድዋን ይገኙበታል፡፡ እንደ አቶ አብዱልቃድር ገለጻ፣ የከተማ አስተዳደሩ በታክስ ብቻ ብዙ ወጪዎቿን ይሸፍናል፡፡

አሁንም ድረስ የከተማ አስተዳደሩ ወጪ የሚሸፍነው በውስጥ ገቢ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ የከተማዋ የልማት ጥያቄዎች 98 በመቶ የሚሸፍነው በውስጥ ገቢ መሆኑን፣ ሁለት በመቶ ብቻ በብድርና በዕርዳታ በሚገኝ ገቢ ላይ የተመሠረተ መሆኑን አስረድተዋል፡፡

በሌላ በኩል ከታክስ የሚገኘው ገቢ ጉድለት ቢኖረውም፣ በየዓመቱ የሚሰበሰበው እየጨመረ እንደሆነ፣ ይህም በ2010 በጀት ዓመት 33‚4 ቢሊዮን፣ ሲሆን የ2015 ዓ.ም. በዘጠኝ ወራት ብቻ 73 ቢሊዮን ብር በላይ መሰብሰቡን በመጥቀስ የከተማዋ ገቢ ዕድገት እያሳየ መሆኑን ያብራራሉ፡፡

እንደ ኃላፊው ገለጻ፣ ከተማዋ ከታክስ የምታገኘው ገቢ በሚፈለገው (በሚጠበቀው) ደረጃ ባይሆንም፣ አስተዳደሩ ያሉበትን ቁልፍ ችግሮች ለመፍታት እያገዘው ነው፡፡

ይህ ቢሆንም የከተማዋን ሁለንተናዊ የልማትና የአገልግሎት ጥያቄ ለማሟላት የከተማ አስተዳደሩ የገቢ ፋይናንስ ችግሮች እንዳሉበት፣ የወጪ የልማት ጥያቄዎችን በበጀት ለመመለስ የሚያስችል ገቢ በማመንጨት ረገድ ችግሮች መኖራቸውን አቶ አብዱል ቀድር ያስረዳሉ፡፡ “የመካከለኛ ጊዜ ወጪ” የሚባል የሦስት ዓመት የገቢ ትንበያና የወጪ ምደባ መሠራቱን የጠቆሙት ኃላፊው፣ በዚህ ትንበያ መሠረት ከተማ አስተዳደሩ ሀብትና የሚያስፈልገው የልማት ጥያቄ ያልተመጣጠነ መሆኑ በግልጽ መለየቱን አስረድተዋል፡፡

በከተማዋ የሚሰበሰበው ታክስ ለአገሪቱ አጠቃላይ ዓመታዊ ምርት (ጂዲፒ) የሚያበረክተው ድርሻ ከ13 እስከ 15 በመቶ ብቻ እንደሆነና ይህም ከሰሃራ በታች የሚገኙ አገሮች ከዋና ከተሞቻቸው የሚሰበስቡት ገቢ ከሚያበረክተው የ18 በመቶ ድርሻ አንጻር የአዲስ አበባ በእጅጉ ዝቅተኛ እንደሚባል ኃላፊው አውስተዋል፡፡

በሦስተኛ ወገን የተሠራ ጥናትን ዋቢ አድርገው እንደተናገሩትም፣ አዲስ አበባ ከተማ በዓመት ከ200 ቢሊዮን ብር በላይ ከታክስ ብቻ ገቢ የመሰብሰብ ዕምቅ ሀብት አላት፡፡

ይህ ዕምቅ ሀብት ከ2015 ዓ.ም. በታክስ ይገኛል ከተባለው ዕቅድ ጋር ሲነፃፀር ዝቅተኛ መሆኑን ያስረዳሉ፡፡ በሦስተኛ ወገን የተጠናው ጥናት ከተማዋ በዓመት 200 ቢሊዮን ብር የግብር ገቢ መሰብሰብ የሚያስችል ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴ የሚካሄድባት ቢያመለክትም፣ ዘንድሮ ለመሰብሰብ የታቀደው 120 ቢሊዮን ብር መሆኑ ከዕቅዱ ጀምሮ ያለውን ክፍተት እንደሚያሳይ ጠቁመዋል፡፡

ዘንድሮ ለመሰብሰብ የታቀደው የግብር ገቢ 120 ቢሊዮን ብር ቢሆንም ባለፉት ዘጠኝ ወራት የተሰበሰበው 73 ቢሊዮን ብር ነው። ይህ ገቢም ከተማዋ ካላት ሀብት አንፃር እጅግ በጣም ዝቅተኛ መሆኑን ያሳያል ሲሉ አስረድተዋል።

የገቢ ስብጥርን በተመለከተ አስተያየት የሰጡት አቶ አብዱልቃድር 80 በመቶ ከታክስ ገቢዎች የሚገኝ መሆኑን፣ ከታክስ ውጪ የሚገኝ ገቢ ደግሞ ከ5.9 በመቶ አይበልጥም ብለዋል፡፡ የተቀሩት ከአገልግሎቶች የሚሰበሰብ ገቢ መሆኑን አስረድተዋል።

እነዚህ የታክስ ዓይነቶች ለሌሎች አገሮች ዋና የፋይናንስ ምንጫቸው እንደሆኑ የሚገልጹት ኃላፊው፣ በኢትዮጵያ ግን እያበረከቱ ያለው ድርሻ ዝቅተኛ ነው ብለዋል፡፡

የዚህ የታክስ ዓይነት በየዓመቱ መጨመር የነበረበት ቢሆንም በአምስት ዓመታት ውስጥ ያለበት ደረጃ ሲቃኝ ድርሻው እየቀነሰ እንደሚገኝ አቶ አብዱልቃድር ተናግረዋል፡፡

በዚህ ጉዳይ ግብር ሰብሳቢውና ከፋዩ ዘንድ ብዙ ችግሮች መኖራቸውን በመጠቆም፣ ክፍተቱን በዘላቂነት መፍታት እንደሚገባ ምክረ ሐሳብ ያቀርባሉ፡፡ ከተማ አስተዳደሩ በጀት አጠቃቀሙ አሉታዊ ተፅዕኖ እንዳለው፣ በጀትን ሙሉ በሙሉ አሟጦ መጠቀም ላይ ትኩረት መሰጠት እንዳለበት ይገልጻሉ፡፡ በጀት አጠቃቀምን ከሁለት ዓመት በፊት ሲታይ 80 በመቶ እንደነበር አስታውሰው፣ የዘንድሮ ዓመት ደግሞ 100 በመቶ እንደሆነ ገልጸዋል፡፡

በዘርፉ የሚገኘውን አቅም በሥርዓቱ መጠቀምና ገቢን ሙሉ በሙሉ አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባ፣ በተለይም የገቢ ዘርፉ ዕምቅ ሀብት ስላለው የከተማዋን የገቢ ምንጭ በማስፋት መደበኛ ካልሆኑ ሴክተሮች ግብር መሰብሰብ እንደሚያስፈልግ ጠቁመዋል፡፡

በዘርፉ የሚስተዋሉ ብልሹ አሠራር ምክንያት ወደ ግለሰቦች ኪስ የሚገባው ገንዘብ መኖሩን ጠቁመው፣ ችግሩን ለመፍታት የተለያዩ ቴክኖሎጂዎችን መጠቀምና ሁሉም ዜጋ ትኩረት መሰጠት አለበት ብለዋል፡፡

ከግብር ከፋዩ ዜጋም መክፈልን አንዳንዶች ለአገር ዕድገት የተቀሩት ደግሞ እንደ ተጨማሪ ጫና የሚለው ዕሳቤ መፈተሽ እንደሚገባ አስረድተዋል፡፡ የልማትና ሌሎች ሥራዎች የሚሸፍንበት መሆኑን የሁሉም ዜጎችን ግንዛቤ ማሳደግ ላይ ከፍተኛ ሥራ መሥራት እንደሚገባ ገልጸዋል፡፡

ከተማ አስተዳደሩ አሁን ባለው የታክስ አሰባሰብ ሁኔታ ሲቃኝ የንብረት፣ ሌሎች የታክስ ዓይነት ገቢ እየተሰበሰበ ነው ለማለት እንደሚያስደፍር ጠቁመው፣ ችግሩን በዘላቂነት መፍታት እንደማያስፈልግ ገልጸዋል፡፡

የተለያዩ የግብር ዓይነቶች የሚሰበሰበውን ገንዘብ ለማሳደግ በጥልቀትና በትኩረት የሚሹ ግብር ዓይነቶች ላይ ማየት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ የአዲስ አበባ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ አቶ አደም ኑር እንደተናገሩት፣ እንደ አገር የተጀመረው ‹‹ግብር ለአገር ክብር›› የሚለው ንቅናቄ ከተጀመረ በኋላ የገቢ አሰባሰብ 1.084 ወይም አንድ ቢሊዮን ብር በላይ በመጋቢት ወር ተሰብስቧል፡፡

በዚህ ንቅናቄ የሕግ ማስከበር ሥራውም ከፍ ማለቱን፣ ገቢን ከመጨመርና ከማሳደግ አንፃርም ከፍተኛ ውጤት እየታየ ነው ብለዋል፡፡ በአንድ ወር ውስጥ የገቢና የግብር አሰባሰብ ባለፈው ዘጠኝ ወራት ከተገኘው 73 ቢሊዮን በአንድ ቢሊዮን ብር መጨመሩን ጠቁመዋል፡፡

ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ ሲደረግ የነበረው ንቅናቄ በአዲስ አበባ ከተማም በሰፊው በመተግበሩ የመጣ ውጤት እንደሆነ አስረድተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በአዲስ አበባ ከተማ በግብር አሰባሰብ የገጠሙ ችግሮች ዙሪያ ገለጻ የተደረገ መሆኑን፣ ውስጥ ከግብር ከፋዩ በኩል ያጋጠሙ ችግሮች ተጠቅሷል፡፡

ከግብር ከፋዩ በኩል የሚታዩ ክፍተቶች ማስረጃ ያለማቅረብ፣ ግብር መሰወር፣ ሐሰተኛ ደረሰኝ ማሳተምና ሌሎችም ችግሮች በገለጻው ተዘርዝሯል፡፡

ከግብር ሰብሳቢው በኩል የታዩ ችግር ተከሎ ከተዘረዘሩት ውስጥ የተሰጣቸውን መመርያ ኃላፊነት ያለመተግበር ችግርና ግብር ከፋዩን በአግባቡ ያለማስተናገድ ችግሮችና የሙስና በሥራቸው ላይ የአቅም ውስንነት ችግሮች እንዳሉ በገለጻው ተነስቷል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች