Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ውስብስብ!

እነሆ ዛሬ የምንጓዘው ከሳሪስ አቦ ወደ ቦሌ ነው። ተማሪው፣ የግልና የመንግሥት ሠራተኛው፣ ራስ ገዙ፣ ነጋዴው፣ ወዘተ ትሩፋት ልታመጣልኝ ትችላለች ያሏትን ነገን ተስፋ በማድረግ ጎዳናው ላይ ናቸው። ከነገ ውጪ ማንም ለምንም የተስፋ ጉልበት ያለው አይመስልም። ከዕለት ዕለት የሚደቁሰው ክርን እየበዛ መሄዱን ለማስተዋል መንገዱን የሞላውን መንገደኛ የፊት ገጽታ መመልከት በቂ ነው። ‹‹‘ይኼም ቀን ያልፍና…’ አለ ዘፋኙ…›› ይላል አንዱ መንገደኛ ለራሱ ተናግሮ እየሳቀ። አንዳንዱን ብሶቱ እንዲህ ከውስጡ እያመለጠ በአደባባይ ሲያጋልጠው ማየት ተለምዷል። የቻለው ግና አፍኖት ወደ ውስጥ እየተነፈሰ ገጹ ጠቁሮ ይራመዳል። የሚታየውና የሚወራው አልገጥም ሲል ይሆናል ተብሎ የሚጠበቀው ነገር ሁሉ ዕድሜው ሲራዘም አንገት መድፋት መቼ ይቀራል? ‘ቆይ ኧረ ለምንድነው የምኖረው?’ የሚል ጠያቂ ቢበረክት ምን ይደንቃል? ወይ ነገር ዓለሙን እርግፍ አድርገው ትተው በራስ ዛቢያ ላይ ብቻ እየተሽከረከሩ ለመኖር ሲፍጨረጨሩ ብናይ ለምን አጀብ እንላለን? የፀሐይን ግለት የበገረ የድካም ደመና በወገን ትከሻ ላይ ከብዶ ይታያል። ነገ ስለምትባለዋ ቀን ስንል ግን ማንኛችንም ደክሞንም ቢሆን እንራመዳለን፣ ዝለን እንበረታለን። ሲያቅተን እየተነሳን!

‹‹ኧረ ተው ይኼን መነጽርህን አውልቀው፣ ከሰው ጋር እንዴት ልትተያይ ነው?›› ይለዋል ወያላችንን የሙያ ባልደረባው። ወያላው ጥቁር ግዙፍ መነጽር ዓይኑ ላይ ሰክቶ ጆሮውን በ‘ኢርፎን’ ግጥም አድርጎ ደፍኖ ‹‹ቦሌ… ቦሌ…›› እያለ ይጣራል። ‹‹መነጽሩን አውልቄ ምን ለማየት? በጆሮዬስ ምንስ ለመስማት? እዚህ አገር ሁሉም ነገር ትናንት እንዳስቀመጥከው ነው። ግፋ ቢል የከረመው ጠብ ቢጠብቅህ ነው…›› እያለ ሁሉን የናቀ ወኔውን ለማሳየት ቃላት ያነበንባል። ‹‹እና አላይም አልሰማም ነው የያዘከው?›› ብሎ ይጠይቀዋል። ነገረ ሥራው ሊያስቀውም ሊያበሽቀውም እየቃጣው። ‹‹በእውነት ሊታይና ሊሰማ የሚችል ነገር እስኪመጣ አላይም፣ አልሰማም። ሕገ መንግሥታዊ መብቴ መሰለኝ?›› ብሎ ‘ኢርፎኑን’ ጆሮው ላይ ዓይኑ ላይ ደግሞ መነጽሩን ያጠባብቃል። ይኼን ከምንታዘበው ተሳፋሪዎች መካከል አንድ ጎልማሳ ሽሙጥ አዘሉን የወያሎቹን ጨዋታ በንቃት አዳምጦ ሲያበቃ፣ ‹‹ለመሆኑ እየሰሙ አልሰማም፣ እያዩ አላይም ማለት ይቻላል?›› ሲል፣ ‹‹ቲዮሪውን ከጠየቅከን ጊዜው የመፈክር ስለሆነ ምን የማይቻል ነገር አለ? ይቻላል ነው መልሱ። እንዲያው ማን ይሙት በቫት የምናወራርደውን ሩብ የሚሆነውን ያህል የቻልነውን ካልቻልነው ብናወራርድ ስንት ጉዳችንን አውቀን በነበረ?›› አለና ትንሽ ተንፈስ አለ፡፡ በመቀጠልም፣ ‹‹ከአገር ተሸሽቶ የት ሊደረስ? በበኩሌ ወያላው ሲያደርግ የምናየው የመጨረሻውን አማራጭ መስሎኛል። ምናልባት እያንዳንዳችን ነገ የሚጠብቀን ይኼ ይሆን?›› ብሎ ዝም አለ። በገዛ አገራችን ሰምቶ እንዳልሰማ ዓይቶ እንዳለየ ስለመሆን በስፋት ያወያየን ጀመር። የቻለው ባህር ማዶ ያልቻለው አገር ውስጥ ሁሉንም ነገር በመርሳት ለመሰደድ ሲሞክር እየታዘብን። ትዝብትና እኛ አብረን የተፈጠርን ይመስል!

 ታክሲያችን ሞልታለች። ሆኖም ትርፍ ሰው ለመጫን ሲል ወያላችን መጣራቱን ቀጥሏል። ‹‹ኧረ እባክህ ግባ እንሂድ? ገና ተራቸውን የሚጠብቁ ሌሎች ታክሲዎች አሉ አይደል?›› ትላለች አንዲት ወይዘሮ እየተቁነጠነጠ የሚያስቸግራት ልጇ ላይ የቁጣ ቃላት ጭምር እየወረወረች። ወያላው መልስ የለውም፣ መጣራቱን ቀጥሏል። ‹‹ማን ሰምቶሽ እናቴ? እሱን እንደሆነ ትዕቢት አሳብጦ ሊገድለው ደርሷል…›› ትላለች ከኋላዋ የተቀመጠች ሌላ ወይዘሮ። ሁለቱም ተቀራራቢ ዕድሜ ላይ መገኘታቸውን ማጤን ይቻላል። ‹‹በስንቱ ደርቀን እንችለዋለን ግን?›› ትጠይቃታለች ልጅ የያዘችው። ‹‹ኧረ ተይኝ፣ ገበያው ውስጥ ሽንኩርት እየገዛሁ አንዱ ይመጣልሻል። እኔም የሽንኩርቱን ዓይነት ስላልወደድኩት ትቼው ልሄድ ስል ሊለቀኝ መሰለሽ?›› ስትላት ሌላኛዋ፣ ‹‹ምን ብሎ?›› መልሳ ጠየቀች። ‹‹‘ና ብለሽ ጠርተሽ አስቁመሽኝ እንዴት ዝም ብለሽኝ ትሄጃለሽ?’ አይለኝ መሰለሽ፡፡ እውነት እልሻለሁ እኔ ግን አልጠራሁትም። አሁን ይኼን ምን ይሉታል?›› ስትላት፣ ‹‹ለነገሩ ‘ባለቤቱ ያቀለለውን አሞሌ ባለዕዳ አይቀበለውም’ ነው የሚባለው። ሕግ አስከባሪውና የሕግ የበላይነት ደብዛቸው የጠፋበት ጊዜ ስለሆነ፣ አይደለም የታችኛዎቹና የላይኞቹ ቢፈነጩብን ምን ይገርማል? ይኼንንም እኛ ሆነን ነው…›› ትላታለች። በምትሰማውና በወያላው ላይ የምታየው ነገር እያበሳጫት ልጁን ክፉኛ ትጮህበታለች። ጩኸት ብቻ!

እንደ ልቡ የሆነው ወያላ እስኪበቃው አጠጋግቶ ጠቅጥቆ ጭኖን ሲያበቃ ‹‹ሳበው!›› አለ በሩን እንደ ምንም ዘግቶ። ‹‹አደራ ብስምሽ ‘ያለ ፈቃዴ ሳመኝ’ ብለሽ ሴቶች ጉዳይ እንዳትከሽኝ…›› ይላታል ወጣት አፈ ቅቤ ተሳፋሪ አንዷን ቀዘባ። እሷም እየሳቀች አፏን በከፊል ‘ብራስሌት’ ባጠለቀችበት የቀኝ እጇ ክንድ ትጋርዳለች። ታክሲያችን መንገዷን ይዛ ጉዞዋን እየጀመረች ነው። አብራኝ የተቀመጠው ወይዘሮ (ባለልጇ አይደለችም)፣ ‹‹የዘመኑ ወጣቶች አባባሉን ስትችሉበት?›› እያለች በንፅፅሮሽ ትደነቃለች። ‹‹ወይ ስምንተኛው ሺሕ? በየመንገዱ ጠበሳ…›› ይላል ለድምፁ ምንም የማይጨነቀው ወያላ ያለ መጠን ጮሆ። ወያላው ሰውን ማክበር ከተወ የሰነባበተ ይመስላል። ምን እሱ ብቻ? ‹‹እንተዋወቅ?›› ወንድየው ሲላት ያለ ምንም ኃፍረት ስሟን ስትነግረው ሰማን። ቆየት ብለው ደግሞ የስልካቸውንም ቁጥር ተቀያየሩ። ድንገት ወንድየው፣ ‹‹በዓሉ እንዴት አለፈ?›› አላት ምላሿን ለመስማት ጉጉት በሚሰብቅ የድምፅ ቃና። ‹‹ምን እባክህ ቦይ ፍሬንዴ ይገርምሃል ለበዓል ጎልድ ይሰጠኛል ብዬ ስጠብቅ (እንዳስለመደኝ ብላለች ቆይታ) የአገር አበባ ታቅፎ አይመጣ መሰለህ? ከዚያማ ይኼው ካየሁት ሳምንቴ…›› ስትለው፣ ‹‹እስኪ ሙት በይኝ?›› እያለ አጋግሎ በመዳፉና በእሱ እየማለች እንድትቀርበው እጁን ይዘረጋል። ‹‹ኧረ ጠላትህ፣ እናም በዚህ ዓይነት ዞሬ የማየው ይመስልሃል?›› ካለችው በኋላ ጆሮአችን እየሰማቸው ዓይናችን እያያቸው፣ ‘ቦይ ፍሬንድ’ የተባለውን ሰውዬ ዘንግተው ግለ ታሪካቸውን በደንብ መፈታተሽ ቀጠሉ። ‹‹ወይ ፍቅርና ጎልድ? ደግሞ በወርቅ ስጦታ ተጀመረልኝ?›› ሲል አንዱ ጎልማሳ ሌላው ተቀብሎ፣ ‹‹ኧረ ይኼን ጆሮዬን የት አባቴ ላስቀምጠው? መቼም በደፈነው አልል ነገር በአፍ ይሄዳል…›› ይላል። ስጦታ ያፈረሰውን ፍቅር የትራንስፖርት ዕጦት ሲክሰው ለምናይ ደግሞ መደነቃችን ጨምሯል። ዕጦትና ግሽበት ዛሬም እንደ ቀጠሉ ናቸው!

ታክሲያችን ሽምጥ ስትጋልብ የምታልፋቸው እንጂ የሚያልፏት መኪኖች አልነበሩም። ታዲያ አንዱ እንዲህ ብሎ ራሱንም እኛንም ይጠይቅ ጀመር። ‹‹መኪና እንዲህ እንደሚከንፈው መብረር ቢችል ኖሮ ምን ነበረበት? በዚሁ ላጥ ነበር ያለ ቪዛ፣ ያለ ፓስፖርት…›› ካለ በኋላ መልሶ፣ ‹‹ምን ነበረበት የትም መኖር ቢቻል?›› ሲል ተናገረ። መኪና መብረር ቢችልና ባህር ቢያቋርጥ ኖሮ ሰው አገር ውስጥ የሚቀር አይመስልም። ምሬት ደስታውን ደጋግሞ ድባቅ እንደመታው ኮስታራ ፊቱ ላይ ማንበብ ይቻላል። በሌላው የታክሲያችን ግድግዳ ደግሞ አስቸጋሪው ሕፃን ከእናቱ አጠገብ የተቀመጠችው ተሳፋሪ ጫማዬን ረገጠችብኝ ብሎ መነጫነጭ ጀምሯል። ጥፋተኛ ነች የተባለችዋ ተሳፋሪ ሳቅ እያሸነፋት በይቅርታ ታባብለዋለች። ድንገት ሕፃኑ፣ ‹‹ከአሜሪካ እኮ ነው የመጣልኝ፣ እዚህ የተገዛልኝ መሰለሽ?›› እያለ ጫማውን ለመጠቆም እየሞከረ። ይኼኔ የታክሲዋ ተሳፋሪ በሙሉ ክው ብሎ ያየው ጀመር። ልጁ ዕድሜው ከአራት የሚበልጥ ዓይነት አይደለም። ‹‹አይ! አይ! እማማ አገሬ? ከዚህ በኋላማ ምን ቀረሽ? እንዲያው… እንዲያው ነው…›› ሲል አንዱ ሌላው ደግሞ፣ ‹‹ዛሬስ በጫማ ነው፣ ነገ አድገው አገሪቱ ኢትዮጵያ፣ ሕዝቧ ደግሞ ታሪካዊ መሆኑን ሲያውቁ ምን ይሉን ይሆን? እንጃ እኔስ በዚህ አስተዳደግ የሚያስኖሩንም አይመስለኝ…›› ይላል ከወዲያ አንዱ። እናቱ አፍራ በዝምታ ዓይኗን ከወዲያ ወዲህ ተንከባልላለች። ‹‹አንድ ጥያቄ አለኝ…›› አለ አንድ ወጣት ከኋላ። ‹‹ምን?›› ቢሉት አጠገቡ ያሉት፣ ‹‹ኢትዮጵያ ወደ እግዚአብሔር ነው ወይስ ወደ አሜሪካ እጆቿን የምትዘረጋው?›› ቢል ገሚሱ እየሳቀ ገሚሱ እያዘነ ‘ዝም’ን መለሰለት። አቤት መልስ የሚሹ ጥያቄዎቻችን ብዛታቸው!

ወደ መዳረሻችን ተቃርበናል። ‹‹ይኼ የቀለበት መንገድ በደህና ቀን ባይሠራ ኖሮ ምን ይውጠን ነበር?›› ይጠይቃል ጎልማሳው። ‹‹በደህና ቀን ያልተሠሩ ሥራዎች አሁን እየተጀመሩ መከራችንን እያሳዩን እንዳሉት ይኼም አሳራችንን ያስቆጥረን ነበራ…›› ትላለች ከኋላ ያለችው ወይዘሮ። ‹‹ተኝቶ መነሳትም አንድ ነገር ነው…›› ትላለች ከኋላ የተቀመጠች ወይዘሮ። ‹‹መሥራቱስ ባልከፋ እየሠሩ ማፍረስ የሚባል አባዜ ግን መቼ ነው የሚለቀን?›› ይላል ወጣቱ። ‹‹እሱን ጠይቁልኝ…›› ሲል ለመጀመርያ ጊዜ አንዱ ቃል ተነፈሰ። ‹‹አሁን ደግሞ ሁሉም በአንድ የሚሉት አሠራር በተራው ያሰቃየን ጀምሯል። እኛ እኮ በኤሌክትሪክ መጥፋት እንጂ በአከፋፈል ላይ ቅሬታ አልነበረንም። የለመድነውን ለምደነዋል። በውኃ መቋረጥና መጥፋት እንጂ በአከፋፈሉ መቼ ተማረርን? የ‘ኔትወርክ’ ችግር እንጂ የስልክ ቢል አከፋፈል መቼ አንገበገበን? የምንጠይቀው ሌላ የሚመለስልን ሌላ…›› ሲል ጎልማሳው አጠገቡ ያለ ተሳፋሪ ተቀብሎ ‹‹እኔምለው የተፍታታውን ማወሳሰብ ነው የተያዘው? ወይስ የተወሳሰቡትን ማፍታታት?›› ብሎ ይጠይቅ ጀመር። ቦሌ ደርሰን ታክሲያችን ገብታ ስትቆም ወያላው በሩን ከፍቶ፣ ‹‹‘ከድጡ ወደ ማጡ…’ መጨረሻ…›› ብሎ ውረዱ አለን። እኛም ተግተልትለን ወርደን ስንክሳሩ የሰፈነበት ጎዳና ላይ ጉዟችንን ቀጠልነው። ‹‹ኑሯችን በተረት ታጅቦ ተወሳሰበብን…›› እያለ አንዱ ሲያጉተመትም የሚቀጥለው ጉዳያችን በጣም አንገብጋቢ ስለነበር ነው መሰል ውስብስቡ ምን እንደሆነ በቅጡ አልሰማነውም፡፡ በደመነፍስ ግን እናውቀዋለን፡፡ መልካም ጉዞ!     

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት