ስለ አገር አንድነት፣ ነፃነትና እኩልነት በአፋን ኦሮሞ በማዜም የሚታወቀው ድምፃዊ ዘሪሁን ወዳጆ ሥርዓተ ቀብር ዛሬ ሚያዝያ 18 ቀን 2015 ዓ.ም. በመንበረ ጸባዖት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ይፈጸማል፡፡
ድምፃዊው ዘሪሁን ሕክምናውን ይከታተልበት በነበረው ህንድ አገር ያረፈ ሲሆን፣ አስክሬኑ ሚያዝያ 17 ቀን አዲስ አበባ ቦሌ ዓለም አቀፍ ኤርፖርት ንጋት ላይ ሲደርስ፣ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳን ጨምሮ የክልልና የፌዴራል መንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣኖች አቀባበል አድርገውለታል፡፡
የድምፃዊውን የሽኝት መርሐ ግብር ለማስፈጸም የተቋቋመው ኮሚቴ በሰጠው መግለጫ፣ ድምፃዊ ዘሪሁን በኢትዮጵያ ውስጥ ፍትሕ እንዲኖርና ሁሉም ብሔረሰቦች በእኩልነት እንዲኖሩ በዘመኑ ሁሉ በሙያው ሲታገል እንደነበር ገልጿል፡፡
‹‹ኢትዮጵያ ካፈራቻቸው ዕንቁ አርቲስቶች መካከል አንዱ ነው፤›› ያለው የድምፃዊው የሙያ ባልደረባ ድምፃዊ ሰዮ ደንደና፣ ድምፃዊ ዘሪሁን ወዳጆ ስለ አገር አንድነት፣ ነፃነትና እኩልነት ሲያዜም ኖሯል ብሏል፡፡
የድምፃዊውን ኅልፈት ተከትሎ የኦሮሚያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ ሽመልስ አብዲሳ ባስተላለፉት የሐዘን መልዕክት፣ በሙዚቃ ሥራዎቹ ለኦሮሞ ሕዝብ ትግል ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከቱን አስታውሰው፣ በሞት ቢለይም ከትውልድ ትውልድ ተሻጋሪ ሥራዎቹ ሲታወስ ይኖራል ብለዋል፡፡
በአፋን ኦሮሞ በርካታ ሥራዎችን ለሕዝብ በማድረስ አድናቆትና ተወዳጅነትን ያተረፈው ድምፃዊ ዘሪሁን፣ ለስኬቱ ከተቀበላቸው ሽልማቶች መካከል የሀጫሉ ሁንዴሳ ፋውንዴሽን ያበረከተለት ሽልማት ይጠቀሳል፡፡