- ቅዱስ ጊዮርጊስና ኢትዮጵያ ቡና የ50 ሺሕ ብር ቅጣት ተላልፎባቸዋል
የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር አመራርና ሥነ ሥርዓት ኮሚቴ በ39 ተጫዋቾችና ሦስት ክለቦች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔ ማስተላለፉን የኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ አክሲዮን ማኅበር አስታወቀ፡፡
አክሲዮን ማኅበሩ የ20ኛ ሳምንት ጨዋታዎች ከተከናወኑ በኋላ በሳምንቱ 39 ተጫዋቾችና የቡድን አመራሮች በቢጫ ካርድ መገሰጻቸውን ያሳወቀ ሲሆን፣ አንድ የቡድን አመራር ቀይ ካርድ መመልከቱ አስታውቋል፡፡
የክለብ ቡድን መሪ ሆነው የዳኛን ውሳኔ በመቃወምና ቁሳቁስ በመወርወር ከጨዋታ ሜዳ ስለመወገዳቸው የሚያስረዳው የዲሲፕሊን ኮሚቴ፣ ለፈጸሙት ጥፋት በኢትዮጵያ ፕሪሚየር ሊግ የውድድር ደንብ መሠረት ሦስት ጨዋታ የታገዱ ሲሆን 10,000 ብር የገንዘብ ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር አምስት ቢጫ ካርድ የተመለከተ ተጫዋች አንድ ጨዋታ እንዲታገድና በተጨማሪም 1,500 ብር የገንዘብ ቅጣት እንዲከፍል መወሰኑን አክሲዮን ማኅበሩ በድረ ገጹ ላይ አስታውቋል፡፡ በሌላ በኩል በሦስት ክለቦች ላይ የዲሲፕሊን ውሳኔን መተላለፉ የተገለጸ ሲሆን፣ አርባ ምንጭ ከተማ በሳምንቱ ጨዋታ የክለቡ ስድስት ተጫዋቾች ካርድ መመልከታቸውን ተከትሎ የአምስት ሺሕ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡
በሌላ በኩል የቅዱስ ጊዮርጊስና የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች በፈጸሙት ጥፋት ቅጣት ተላልፎባቸዋል፡፡ በዚህም መሠረት ቅዱስ ጊዮርጊስ በተጫወተበት ዕለት የክለቡ ደጋፊዎች በአዳማ ሳይንስና ቴክኖሎጂ ስታዲየም ጥላ ፎቅ የሚገኙትን 22 የፕላስቲክ ወንበሮችን ሰብረዋል የሚል የክስ ሪፖርት ቀርቦባቸው 50 ሺሕ ብር ቅጣት ተጥሎባቸዋል፡፡ የኢትዮጵያ ቡና ደጋፊዎች የዕለቱን ዳኛ አፀያፊ ስድብ ስለመሳደባቸው ሪፖርት በመቅረቡ የክለቡ ደጋፊዎች ለፈጸሙት ጥፋት 50 ሺሕ ብር እንዲከፍል ወይም የዩኒቨርሲቲው አስተዳደር የሚያቀርበውን የንብረት ዋጋ እንዲከፍል ተወስኗል፡፡
በአንፃሩ በዕለቱ በደጋፊዎች እንዳልተሰበረና ቀድሞውኑ የስታዲየሙ ወንበር የተነቃቀለ ነው የሚል ቅሬታ ተነስቷል፡፡ በዚህም ክለቡ ተጠያቂ ሊያደርገው እንደማይችል ቅሬታ ሲደመጥ ነበር፡፡