የነዳጅ ግብይትን በዲጂታል የክፍያ ዘዴ ለማስፈጸም ከትናንት በስቲያ ጀምሮ መተግበር የጀመረው አሠራር፣ የአዲስ አበባ ከተማ ማደያዎችን እያጨናነቀና ለነዳጅ እጥረት መንስዔ እንደሆነ ተገለጸ፡፡
መንግሥት በአስገዳጅነት እንዲተገበር ያደረገው የታለመለት የነዳጅ ድጎማ ተግባራዊ ከተደረገ ወዲህ፣ በታክሲዎች ላይ ተፈጻሚ ሆኖ የቆየ ሲሆን፣ አሁን ግን በሁሉም ተሽከርካሪዎች ላይ ተፈጻሚ እንዲሆን ተወስኖ፣ ሥራው በአዲስ አበባ ከተማ ተጀምራል፡፡ ይሁን እንጂ አሠራሩን ከመተግበር ጋር በተያያዘ፣ ተገልጋዮች ከመጠን በላይ የነዳጅ ግዥ እየፈጸሙ በመሆኑ፣ በአንዳንድ ማደያዎች የነዳጅ እጥረት እየተፈጠረ መሆኑ ታውቋል፡፡ የዲጂታል ክፍያ መተግበሪያውን ለመጠቀም የተፈጠረው ብዥታ በብዙ ማደያዎች ረዣዥም ሠልፎች እንዲታዩ ከማድረጉም በላይ፣ ቶሎ ነዳጅ ቀድቶ ለመሄድ አዳጋች እንዲሆን አድርጎታል፡፡ የዲጂታል ክፍያ መፈጸሚያ መተግበሪያው በዋናነት በቴሌብር እየተተገበረ ሲሆን፣ በተጨማሪ አማራጭነት የኢትዮጵያ ንግድ ባንክም ሁለት መተግበሪያዎችን ይፋ አድርጓል፡፡
የኢትዮጵያ ነዳጅ አዳዮች ማኅበር እንደገለጸው፣ አሁን ያለው መጨናነቅ የተፈጠረው አገልግሎቱን ለማስጀመር በቂ ጊዜ ባለመሰጠቱና አሽከርካሪዎች አገልግሎቱ ከመጀመሩ በፊት እንዲዘጋጁ ባለመደረጉ ነው፡፡
ሥጋታቸውን ቀደም ብለው በማኅበራቸው በኩል አሳውቀው እንደነበር የገለጹት የማኅበሩ የሥራ አመራር አባል አቶ ኤፍሬም ተስፋዬ፣ አሁን ብዙዎች ወደ ሲስተሙ እየገቡ ቢሆንም ከሥጋት አንጻር የተሽከርካሪዎቻቸውን የነዳጅ ታንከር በመሙላት፣ ግዥ የሚፈጸሙ አሽከርካሪዎች ለነዳጅ እጥረት መንስዔ እየሆኑ መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡ ድርጊቱ የነዳጅ እጥረት ሊያስከትል ይችላል ተብሎ እንደሚሠጋ የሚገልጹት አቶ ኤፍሬም፣ አሁንም ቢሆን ወደ ዲጂታል የግብይት ሥርዓቱ የማስገባቱ ሥራ እንደተጠበቀ ሆኖ፣ ከዚህ ጋር በተያያዘ ሊፈጠር የሚችለውን የነዳጅ እጥረት ለመቅረፍ ተጨማሪ የነዳጅ አቅርቦት ያስፈልጋል ብለዋል፡፡
አሁን የሚታየው መጨናነቅ የተወሰኑ ቀናት ሊቀጥል የሚችል ቢሆን እንኳን መጨናነቁን ለማስቀረት የግድ መንግሥት በቂ ነዳጅ ወደ ከተማው እንዲገባ ማድረግ እንዳይገባውና ይህንን ካላደረገ ዕድሉን አግኝተው ነዳጅ የሚቀዱ ተገልጋዮች፣ ከፍላጎታቸው በላይ እየቀዱ የሚቀጥሉ ስለሚሆን የነዳጅ አቅርቦቱ ላይ ተፅዕኖ ሊያሳድር እንደሚችል ጠቁመዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ኢትዮ ቴሌኮም አሠራሩን ከመተግበር አንጻር ያለውን መጨናነቅ ለማስቀረት በሁሉም የአዲስ አበባ ከተማ ማደያዎች ባለሙያዎችን በማሰማራት ለተገልጋዮች ድጋፍ እየሰጠ መሆኑን አስታውቋል፡፡
የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ የዲጂታል የነዳጅ ግብይት መተግበሪያዎቹን ይፋ ባደረገበት ፕሮግራም ላይ የተገኙት የትራንስፖርትና ሎጂስቲክ ሚኒስትር ደኤታው አቶ ኦዴኦ ሐሰን እንደገለጹት፣ ይህንን አገልግሎት ለመተግበር መንገራገጮች ቢኖሩም፣ በአዲስ አበባ ከተማ የተጀመረው አዲስ አሠራር ከግንቦት 1 ቀን 2015 ጀምሮ በመላ አገሪቱ ሙሉ በሙሉ ተግባራዊ እንደሚሆን አረጋጋጠዋል፡፡
የአገልግሎቱ መጀመር ግን ዘመናዊ ግብይትን ከማሳለጥ ባለፈ ከነዳጅ ሥርጭት ጋር በተያያዘ ሲፈጠሩ የነበሩ ብልሹ አሠራሮችንና ብክነትን ከማስቀረት አኳያ፣ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው ሚኒስትር ዴኤታው ገልጸዋል፡፡