Wednesday, December 6, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየፌዴራል መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሰላም ንግግር በዛንዚባር ተጀመረ

የፌዴራል መንግሥትና የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት የሰላም ንግግር በዛንዚባር ተጀመረ

ቀን:

የኢትዮጵያ መንግሥትና ራሱን የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በማለት የሚጠራው ታጣቂ ቡድን፣ በታንዛኒያ በምትገኘው ዛንዚባር ደሴት ውስጥ ንግግር መጀመራቸው ተገለጸ፡፡ የሰላም ድርድሩ Modality፣ ቅድመ ሁኔታዎችና የሦስተኛ ወገን አደራዳሪ ማንነትን በተመለከተ ሁለቱም ወገኖች ይፋ ከማድረግ ተቆጥበዋል፡፡ ይሁን እንጂ የምሥራቅ አፍሪካ ልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ዋና ፀሐፊ ወርቅነህ ገበየሁ (ዶ/ር) ‹‹ማንኛውንም ድጋፍ›› ለማድረግ ፈቃደኝነታቸውን መግለጻቸውን ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉ የኢጋድ ባለሥልጣን ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› እያለ የሚጠራውና ፓርላማው ከሁለት ዓመት በፊት በአሸባሪነት የሰየመው ታጣቂ ቡድን በኦሮሚያ ክልል በተለይ በወለጋ በተለያዩ አካባቢዎች እንደሚንቀሳስ ይታወቃል፡፡

 ከሁሉት ቀናት በፊት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር) ጦርነት ይብቃ ‹‹ሰላምን እናፅና›› በሚል መሪ ቃል፣ በሰሜን ኢትዮጵያ የነበረው ግጭት በሰላም እንዲጠናቀቅ በማድረግ ሒደት ላይ ቁልፍ ሚና ለነበራቸው አካላት በተዘጋጀ የዕውቅና ፕሮግራም ላይ ከታጣቂ ቡድኑ ጋር የሚደረገው ድርድር በታንዛኒያ እንደሚጀመር ገልጸው ነበር፡፡

በተለይ ባለፉት አምስት ዓመታት በኦሮሚያ የተፈጠረው ደም አፋሳሽ ግጭት ልክ እንደ ሰሜን ኢትዮጵያ ግጭት በድርድር እንዲፈታ የአሜሪካ፣ ኖርዌይ፣ ስዊድን፣ ኬንያና የተለያዩ የአውሮፓ አገሮች በሁለቱም ወገኖች ላይ ግፊት ሲያደርጉ እንደቆዩ ምንጮች ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትሩ በንግግራቸው ድርድሩን ‹‹የኢትዮጵያ መንግሥትና ሕዝብ አብዝቶ ይፈልገዋል፤ በዚህ ድርድር የሚሳተፉ ወገኖች ሁሉ የዛሬዋን ቀን እያሰቡ በግጭትና በጦርነት እንደማያተርፉ አውቀው፣ ሕግና ሥርዓት ተከትለን፣ ይቅር ተባብለን፣ አገራችንን በጋራ መገንባት እንድንችል የወለጋ ሕዝብ አሁን ካለበት ስቃይ እፎይ ማለት እንዲችል፣ ሁሉም ወገን የበኩላቸውን እንዲያደርጉ ከወዲሁ ጥሪ አቀርባለሁ፤›› ብለው ነበር፡፡

በመድረኩ ንግግር ያደረጉት የቀድሞ የናይጄሪያ ፕሬዚዳንትና የአፍሪካ ኅብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ ኦሊሴጉን ኦባሳንጆ፣ የፖለቲካ ችግሮችን ላይ አፋጣኝ የሆነ የፖለቲካ ምክክር መደረግ እንዳለበት በማሳሰብ፣ በዚህም ኢትዮጵያውያን የወደፊት ሕይወታቸውን በጋራ እንዲወስኑና በድጋሜ አንዳቸው በሌላኛቸው ላይ ጦርነት እንዳይከፍቱ መክረዋል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ሰራዊት (ኦነግ ሸኔ) የጠቅላይ ሚኒስትሩን ንግግር ተከትሎ በድረ ገጹ ባወጣው መግለጫ፣ የኢትዮጵያ መንግሥት ለድርድር ጥሪ ሲያቀርብ ሠራዊቱ ለመደራደር ያቀረባቸውን ‹‹ገለልተኛ የሦስተኛ ወገን አደራዳሪ›› እና ድርድሩን ግልጽ በሆነ ሒደት እንዲካሄድ የቀረቡትን ቅድመ ሁኔታዎች መንግሥት መቀበሉን ዕውቅና እሰጣለሁ ብሏል፡፡

ይሁን እንጂ በመንግሥት ‹‹ኦነግ ሸኔ›› የሚል ስያሜ መሰጠቱ ሠራዊቱን የማይወክልና አሳሳች መሆኑን ገልጾ፣ የሠራዊቱን ዓላማና ማንነት የሚያሳስት መረጃዎችን ከማሰራጨት እንዲያቆሙ ጥሪ አቅርቧል፡፡

የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት በመግለጫው ከጅምሩ ጀምሮ ሰላማዊ ድርድር ብቻ አማራጭ መሆኑን ሲወተውት እንደነበር ጠቅሶ፣ ጦርነት መፍትሔ እንደማይሆንና የተፈለገውን ውጤት እንደማያመጣ በመግለጽ መንግሥት በመጨረሻም ወደዚህ ውሳኔ ለመምጣት ማሰቡ ተሰፋ ሰጪ ነው ብሎታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...