Wednesday, December 6, 2023
- Advertisment -
- Advertisment -

ጦርነት ቆሞ ሰላም የሚፀናው የጦረኝነት ባህሪ ሲገራ ነው!

በሰሜን ኢትዮጵያ ለሁለት ዓመታት ያህል የተካሄደውን አውዳሚ ጦርነት ምዕራፍ ለመዝጋት፣ ‹‹ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና›› የሚል መርሐ ግብር ሰሞኑን ተካሂዷል፡፡ ቀደም ሲል ያ ሁሉ ዕልቂትና ውድመት ከመከሰቱ በፊት በዕንባ ጭምር ተማፅኖ ያሰሙ ወገኖች ድምፅ ችላ ተብሎ፣ ኢትዮጵያ በታሪኳ ዓይታው የማታውቀው መከራ ውስጥ ገብታ የደረሰው ሰቆቃ መቼም ቢሆን አይረሳም፡፡ ጦርነትን አስቁሞ ሰላምን ለማፅናት የሚቻለው የኢትዮጵያን ሕዝብ በማክበርና በማዳመጥ ነው፡፡ በሁለቱ ዓመት ጦርነትም ሆነ በተለያዩ ጊዜ በተከሰቱ ጥቃቶችና ግጭቶች በሕዝብ መካከል ምንም ዓይነት ችግር አልነበረም፡፡ ፖለቲከኞች ሲስማሙና ልዩነቶቻቸውን አደብ ሲያስገዙ አገር ሰላም ትሆናለች፡፡ ችግሮቻቸውን በሠለጠነ መንገድ መፍታት አቅቷቸው ትከሻ መለካከት ሲጀምሩ ግን ዳፋው የሚተርፈው ለምስኪኑ ሕዝብ ነው፡፡ የሰሜኑ ጦርነት እንደተባለው ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ ቆሞ ሰላም የሚሰፍን ከሆነ ለሕዝባችን ትልቅ ዕፎይታ ነው፡፡ ነገር ግን ለሕዝባችን ዘለቄታዊ ሰላም ሲባል የጦረኝነት ባህሪን መግራት የግድ ነው፡፡ በፖለቲከኞች አጉል ባህሪ ምክንያት የፈሰሰው የንፁኃን ደም ለጊዜው በሕግ ባያስጠይቅም የታሪክ ተጠያቂ እንደሚያደርግ መታወቅ አለበት፡፡

በሌላ በኩል ደግሞ በፌዴራል መንግሥትና በኦነግ ሸኔ ወይም የኦሮሞ ነፃነት ሠራዊት ነኝ በሚለው አካል መካከል፣ የሰላም ስምምነት ሒደት መጀመሩ ተሰምቷል፡፡ የሰላም ማስፈኑ ሒደት  ዕውን ሊሆን የሚችለው፣ በኢትዮጵያ አንድነትና ሉዓላዊነት ጥላ ሥር ሲሆን ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪ በሌሎች አካባቢዎች ጥያቄ ካላቸውም ሆኑ ትጥቅ ካነገቡ አካላት ጋር ዘለቄታዊ ሰላም የሚያሰፍን ስምምነት ሊኖር ይገባል፡፡ እንደ እሳተ ገሞራ የሚንተከተከተው የአፍሪካ ቀንድ ውስጥ ካለው ውጥረት በተጨማሪ፣ ሱዳን ውስጥ የውጭ ኃይሎችን ፍላጎት ተሸክመው በሚፋለሙት የሁለቱ ጄኔራሎች ተዋጊዎች የተፈጠረው አደገኛ ጦርነት ይዞት የመጣው ሥጋት አለ፡፡ የአሁኑ የኢትዮጵያ ነባራዊ ሁኔታ ከሰላም ውጪ ሌላ አማራጭ እንደማይኖር ቁልጭ አድርጎ ያሳያል፡፡ የኢትዮጵያ ሁሉም የፖለቲካ ኃይሎች ለሕዝብ እናስባለን የሚሉ ከሆነ፣ መጀመሪያ ሕዝቡ የሚወዳትን እናት አገሩን ሰላም መንሳት ማቆም አለባቸው፡፡ በእነሱ ምክንያት የፈሰሰውን የንፁኃን ደምና የወደመውን የአገር ውድመት በፀፀት እያስታወሱ፣ ከጦረኝት ባህሪ ራሳቸውን ማላቀቅ ይጠበቅባቸዋል፡፡

ፖለቲከኞች ራሳቸውን ከአገርና ከሕዝብ ፍላጎት በታች ሲያውሉ ሰላም በጣም ቅርብ ነው፡፡ ነገር ግን በግትርነት፣ በቂም፣ በጥላቻና በእኔ እበልጥ ፉክክር ውስጥ ገብተው ሕጋዊውንና ሰላማዊውን መንገድ ሲስቱ የመከራው ዶፍ የሚዘንበው በምስኪኑ ሕዝብ ላይ ነው፡፡ በፕሪቶሪያው የሰላም ስምምነት መሠረት እዚህ ደረጃ ላይ ተደርሶ ይቃረኑ በነበሩ አመራሮች አማካይነት ስለሰላም ሰበካ መስማት መልካም ቢመስልም፣ የመተማመን ምልክቶች በስፋት ካልታዩ ሥጋት ያጭራል፡፡ ከእዚህ ጎን ለጎን ደግሞ ለተፈጠረው ችግር ሁሉ በሽግግር ፍትሕ ፖሊሲ አማካይነት ሊደረግ የሚችለው ታሳቢ ሆኖ፣ በጦርነቱ ከፍተኛ በደል የደረሰባቸውን ወገኖች ይቅርታ መጠየቅ የፖለቲከኞች ድርሻ ነው፡፡ ለሰላም እየተገባ ያለው ቃል ተዓማኒነት ማግኘት የሚችለው በትግራይ፣ በአማራና በአፋር ክልሎች ውስጥ ወገኖቻቸውን ያጡና የሥቃይ ሰለባ የሆኑ ተጎጂዎች በይፋ ይቅርታ ሲጠየቁ ነው፡፡ ለሰላም ስምምነቱ አስተዋፅኦ በማድረግ የተገኘው ሽልማት የሚያኮራው ይቅርታ ለማለት ድፍረት ሲኖር ጭምር ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በፍጥነት ለማስቀጠል ቀና ባህሪ ያስፈልጋል፡፡

ከተለያዩ አቅጣጫዎች ከሚሰሙ የሕዝቡ ፍላጎቶች አኳያ ከምንም ነገር በፊት ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባው ተግባር ሰላም ማስፈን ነው፡፡ ፖለቲከኞች ሆይ ልዩነቶቻችሁን በድርድር ፈታችሁ ሰላም አስፍኑ እየተባላችሁ ነው፡፡ ከሰላም አፈንግጦ በጉልበት የሚሳካ ትግል እንደሌለ የቅርቡ የሰሜን ኢትዮጵያ አውዳሚ ጦርነት ህያው ምስክር ነው፡፡ ይህም ሆኖ ግን የሰላም ድርድር እንደሚኖር ሲሰማ ከየጎሬያቸው እየወጡ መሰናክል የሚደረድሩ የግጭት ጠማቂዎች ይስተዋላሉ፡፡ በግጭት ከሚፈሰው የንፁኃን ደምና ከሚወድመው የአገር አንጡራ ሀብት ይልቅ፣ የራሳቸውና የቢጤዎቻቸው ጥቅም የሚበልጥባቸው ፖለቲከኞችና አጃቢዎቻቸው ማንም ሳይቀድማቸው ሐሰተኛ ዘገባዎችን እየፈበረኩ በስፋት ያሠራጫሉ፡፡ ይህም አልበቃ ብሏቸው በሕዝብ መብትና ነፃነት ስም የተለመደ ቁማራቸውን ይጀምራሉ፡፡ በዚህም ሳቢያ ከመቀራረብ፣ ከመነጋገርና ከመተማመን ሊገኝ የሚችለውን ዘርፈ ብዙ ጥቅም በማሳጣት ለሌላ ዙር ዕልቂትና ውድመት ነጋሪት ይጎስማሉ፡፡ ሕዝባችን በየቤተ ዕምነቱ ለሰላም መስፈን አጥብቶ ፈጣሪውን በሚለምንበትና በሚፀልይበት አገር ውስጥ፣ ለምን የሰላም ድርድር ይካሄዳል የሚሉ ግጭት ጠማቂዎችን ተባብሮ ማስቆም የሚቻለው በሁሉም ዘንድ ከጦረኝነት የተላቀቀ የባህሪ ለውጥ ሲኖር ነው፡፡

የሰሜን ኢትዮጵያን ጦርነት ፈፅሞ ሊያስቆም ይችላል ተብሎ የታመነበት የፕሪቶሪያ የሰላም ስምምነት አንዱ ተግዳሮት፣ በስምምነቱ ፈራሚዎች በፌዴራል መንግሥትና በሕወሓት አመራሮች መካከል መተማመን መፍጠር ነበር፡፡ በተደጋጋሚ በተገኙ መድረኮች ሲገለጽ ለመረዳት እንደተቻለው መተማመኑ በየጊዜው መጠነኛ ለውጦች እየታዩበት፣ እስከ እሑድ ሚያዝያ 15 ቀን 2015 ዓ.ም. ‹‹ጦርነት ይብቃ፣ ሰላምን እናፅና›› በሚል መሪ ቃል የተዘጋጀው ሥነ ሥርዓት ድረስ ዘልቋል፡፡ የአሜሪካ፣ የአውሮፓ ኅብረትና ሌሎች የውጭ የዲፕሎማሲ ሚሽኖች፣ እንዲሁም የአፍሪካ ኅብረት አደራዳሪዎች፣ ሹማምንትና ሌሎች እንግዶች የታደሙበት ሥነ ሥርዓት ላይ የተሰሙ ድምፆች የሰላምን አስፈላጊነት በእጅጉ የሰበኩ ነበሩ፡፡ አሁን የሚነፍሰው አንፃራዊ የሰላም ንፋስ ዕውን እንዲሆን የተደረገው ጥረትና የተገባው ቃል እንዲሰምሩ ግን፣ መተማመኑን የላቀ ደረጃ ላይ ሊያደርስ የሚችለው የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነት ሊታሰብበት ይገባል፡፡ በፖለቲከኞች ጊዜያዊ መስማማት የሚፀና ሰላም ስለማይኖር፣ የሕዝብ ለሕዝብ ግንኙነቱን በፍጥነት እንዲጀመር የጦረኝነት ባህሪን መግራት የግድ ነው፡፡

መንግሥትን የሚመራው ገዥው ፓርቲ ብልፅግናም ሆነ አመራሮቹ፣ እንዲሁም በተለያዩ ጎራዎች ውስጥ ሆነው የሚፎካከሩ ተገዳዳሪዎቹና ተከታዮቻቸው የፖለቲካ ምኅዳሩን ካበለሻሸው መጥፎ ባህሪያቸው ይላቀቁ፡፡ ለዚህም ደግሞ ሁሉም ከእነሱ በላይ አገርና ሕዝብ እንዳሉ ይወቁ፣ ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችን ያክብሩ፣ ልዩነቶችን በድርድር ይፍቱ እንጂ በጉልበት እንሞካከር አይባባሉ፣ ሁሉንም በእኩልነት የሚያቅፍና የሚያሳትፍ ዴሞክራሲያዊ ምኅዳር እንዲፈጠር ዕገዛ ያድርጉ፣ በሕዝብ ስም እየቆመሩ መከራውን አያብዙ፣ ለዘመኑ የሚመጥን የዕውቀት፣ የክህሎትና የአደረጃጀት ቁመና ይኑራቸው፣ ለሥልጣን ሲሉ ብቻ በንፁኃን ደም እጃቸውን እየተለቃለቁ አያደናግሩ፣ ለአገር ልማትና ለሕዝብ ዕድገት የሚበጁ አማራጮን ይዘው ለመፎካከር ይዘጋጁ፣ የመንግሥትና የፓርቲ ሥራዎች እንዳይደበላለቁ የበኩላቸውን ሚና ይጫወቱ፣ ሁሉም የፀጥታ ኃይሎችና የፍትሕ ተቋማት በነፃነት ሥራቸውን እንዲያከናውኑ መደላድሉን ያመቻቹ፣ እንዲሁም የሥልጣን ሉዓላዊ ባለቤት የሆነውን የኢትዮጵያ ሕዝብ አክብረው ሥራቸውን ያከናውኑ፡፡ እንዲህ ዓይነቱ ሥልጡን ባህሪ ሲኖር ግጭት ሥፍራ አይኖረውም፡፡ ጦርነት ቆሞ ሰላም የሚፀናው የጦረኝነት ባህሪ ሲገራ ነውና!

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች

ታዋቂው የኤሌክትሮኒክስ ብራንድ አይቴል የስትራቴጂ ለውጥ አካል የሆነውን አዲስ አርማ እና መለዮ ይፋ አደረገ።

በአለማችን ታዋቂ ከሆኑት የኤሌክትሮኒክስ ብራንዶች መካከል አንዱ የሆነው እና...

የጠቅላላ ጉባኤ ስብሰባ ጥሪ ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ

ለሸገር አነስተኛ የፋይናንስ ተቋም አ.ማ ባለአክሲዮኖች በሙሉ የሸገር አነስተኛ የፋይናንስ...

[የክቡር ሚኒስትሩ ጸሐፊ፣ የሌላ ሚኒስትር ጸሐፊ ከሆነችው የቅርብ ወዳጇ ጋር በስልክ እየተጨዋወቱ ነው]

አንቺ ግን ምን ሆነሽ ነው? ጠፋሁ አይደል? ጠፋሁ ብቻ?! ምን ላድርግ ብለሽ...

በሱዳን ላይ ያጠላው የመከፋፈል ዕጣና ቀጣናዊ ተፅዕኖው

የሱዳን ጦርነት ስምንተኛ ወሩን እያገባደደ ይገኛል፡፡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን...

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ በግሉ ኢንሹራንስ ዘርፍ ሁለተኛውን የገበያ ድርሻ ለመያዝ ያስቻለውን ውጤት ማስመዝገቡን ገለጸ

ኦሮሚያ ኢንሹራንስ ኩባንያ የባንኮች የጥሬ ገንዘብ እጥረት፣ የመለዋወጫ ዕቃዎች...
spot_img

ተዛማጅ ፅሁፎች

ለአገልግሎት ሰጪ ተቋማት የደንብ ልብስ አለባበስ የጌጣጌጥና መዋቢያ አጠቃቀም ደንብን ማውጣት ለምን አስፈለገ?

በዳንኤል ንጉሤ በሆቴልና መሰል አገልግሎት ሰጪ ተቋማት ባለሙያዎች የደንብ ልብስ አለባበስ፣ የጌጣጌጥ አጠቃቀም የገጽታና የውበት አጠባበቅን አስመልክቶ በተዘጋጀው ረቂቅ ደንብ ላይ ውይይት ተካሂዷል፡፡ ረቂቅ ደንቡን ያዘጋጀው...

ትኩረት ለሕዝብና ለአገር ደኅንነት!

ኢትዮጵያ ውስጥም ሆነ በቅርብ ርቀት ባሉ አገሮች፣ እንዲሁም ራቅ ባሉ የአፍሪካና የዓለም አገሮች ውስጥ የሚስተዋሉ ዘርፈ ብዙ ችግሮች የተፅዕኖ አድማሳቸው እየሰፋ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሌላው...

የአስተሳሰብና የአስተዳደር ዘይቤ ለውጥ ያስፈልጋል!

ኢትዮጵያ ውስጥ ሕዝቡን በጋራ አስተሳስረው የሚያኖሩ በጣም በርካታ ማኅበራዊ እሴቶች አሉ፡፡ እነዚህ ለዘመናት ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲሸጋገሩ የኖሩ እሴቶች አገር ለማቆም ትልቅ አስተዋፅኦ ነበራቸው፣...