Monday, May 27, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበደቡብ ክልል የሠሩበትን የትርፍ ሰዓት ክፍያ የጠየቁ የጤና ባለሙያዎች ዛቻ እየደረሰብን ነው...

በደቡብ ክልል የሠሩበትን የትርፍ ሰዓት ክፍያ የጠየቁ የጤና ባለሙያዎች ዛቻ እየደረሰብን ነው አሉ

ቀን:

ለአሥር ወራት በትርፍ ሰዓት የሠሩበትን ክፍያ ባለማግኘታቸው ምክንያት የሚመለከተው አካል እንዲከፍላቸው የጠየቁ በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል በጌዴኦ ዞን ዲላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጣቢያ የሚገኙ ከ38 በላይ የጤና ባለሙያዎች፣ ‹‹ደመወዝ በመጠየቃችን እስርና ዛቻ እየተፈጸመብን ነው›› ሲሉ ለሪፖርተር ተናገሩ፡፡

ከጤና ባለሙያዎቹ መካከል ቅሬታቸውን ለሪፖርተር ያስረዱት አምስት ባለሙያዎች፣ ከመደበኛ የሥራ ሰዓት ውጪ ለሠሩበት ሊከፈላቸው ሲገባ፣ ለአሥር ወራት እንዳልተከፈላቸው፣ በዚህም ሳቢያ ከሥራ እንደታገዱ፣ የሚመለከተው አካል እንዲከፍላቸው ጥያቄ ሲያቀርቡ በፖሊስ ተይዘው እንደታሰሩ፣ ከዚህም በተጨማሪ የሁለት ወራት መደበኛ ደመወዛቸውም መታገዱን ገልጸዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎቹ እስከ 12 ወራት የቆየ የትርፍ ሰዓት ክፍያ እንዲከፈላቸው የዲላ ዙሪያ ወረዳን መጠየቃቸውን፣ ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ምላሽ ካልተሰጣቸው ከመጋቢት 1 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ ሥራ የማቆም አድማ እንደሚያደርጉ አስታውቀው እንደነበር ተናግረው፣ እስከ መጋቢት ወር ድረስ የትርፍ ጊዜ ክፍያ እንዳልተሰጣቸው፣ ይህን ተከትሎም በዲላ ወረዳ ዙሪያ በሚገኙ ጤና ጣቢያዎች የሚያገለግሉ የጤና ባለሙያዎች፣ የትርፍ ጊዜ ክፍያቸውን በማግኘት ፋንታ የመደበኛ ደመወዝ ክልከላ፣ እስርና ዛቻ እየተፈጸመባቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

- Advertisement -

የጤና ባለሙያዎቹ ያቀረቡትን ቅሬታ በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ ሪፖርተር በስልክ ያነጋገራቸው የዲላ ወረዳ ዙሪያ ጤና ጽሕፈት ቤት ቢሮ ኃላፊ አቶ ታሪኩ አስፋው፣ ‹‹የጤና ባለሙያዎቹ እየከሰሱ ናቸው፡፡ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ወደ ክልሉ ገብቷል፡፡ እንዴት ነው ፍርድ ቤት ምላሽ ሳይሰጥ ማብራሪያ የምሰጠው? ሕጉ አይፈቅድም፤›› ብለዋል፡፡

የፍርድ ቤት ሒደትን ሳይሆን የጤና ባለሙያዎች ለምን የአንድ ዓመት የትርፍ ጊዜ ሥራ ክፍያ እንዳልተከፈላቸው፣ ለምን እንደታሰሩ፣ ለምን በፖሊስ እየታደኑ እንደሆነ ማብራሪያ እንዲሰጡ በድጋሚ የተጠየቁት የጤና ቢሮ ጽሕፈት ቤት ኃላፊው ማብራሪያ ከመስጠት ተቆጥበዋል፡፡

የጤና ባለሙያዎቹ የትርፍ ጊዜ ክፍያቸው እንዲከፈላቸው የጊዜ ገደብ ሰጥተው ቢጠይቁም፣ ስላልተከፈላቸው ሥራ የማቆም አድማ እንዳደረጉ፣ በዚህም የ24 የጤና ባለሙያዎች ወርኃዊ ደመወዝ መታገዱንና በፖሊስ እየተሳደዱ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡

እስራቱን በተመለከተ ማብራሪያ እንዲሰጡ የተጠየቁት የጤና ባለሙያዎቹ፣ የትርፍ ጊዜ ደመወዝ ይሰጠን በማለታቸው ከሥራ ከታገዱት 24 የጤና ባለሙያዎች ውጪ ያሉና ከሥራ ያልታገዱ ባለሙያዎች ለወረዳ ጥያቄ አቅርበዋል ብለዋል፡፡ ጥያቄው በተነሳበት ወቅት ግን ተጠርጣሪ ናቸው ተብለው ከ30 በላይ የጤና ባለሙያዎች በፖሊስ እንዲታሰሩ ተደርገዋል ሲሉ አስረድተዋል፡፡

ዲላ ወረዳ ዙሪያ ፖሊስ ጣቢያ እንዲታሰሩ የተደረጉት የጤና ባለሙያዎቹ እስከ አምስት ቀን ድረስ ማረሚያ ቤት ቆይተው በዋስ ነው የተለቀቁት ያሉት የጤና ባለሙያዎቹ፣ ይህ ሁሉ የሆነው በትርፍ ሰዓት የተሠራው ክፍያ ይከፈለን በሚለው ጉዳይ መሆኑንና አሁንም ከእስራት ያልተፈቱ አሉ ብለዋል፡፡

የዲላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት የወረዳ አስተዳደርና የሚመለከታቸው አካላት የጤና ባለሙያዎቹ እንዲከፈላቸው የጠየቁትና የትርፍ ሰዓት ክፍያ መክፈል እንዳለባቸው ማመናቸውን፣ የጥሬ ገንዘብ እጥረት እንዳለባቸው መግለጻቸውን፣ የጤና ባለሙያዎቹ ሥራቸውን እየሠሩ ጥያቄያቸውን እንዲጠይቁ ማሳሰቢያ መሰጠቱን፣ እንዲሁም አድማ ባደረጉ የጤና ባለሙያዎች ላይ ከመጋቢት 2 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የዲላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጽሕፈት ቤት ከሥራና ከደመወዝ ዕገዳ ማድረጉን ሪፖርተር ያገኘው ደብዳቤ ያሳያል፡፡

ከጤና ጽሕፈት ቤቱ ደብዳቤ በመነሳት ‹‹የጥሬ ገንዘብ ዕጥረት›› ካጋጠመ ሥራ ከማቋረጥ መሥራት ለምን እንዳልቻሉ ጥያቄ የቀረበላቸው የጤና ባለሙያዎቹ፣ ደመወዝ ሳይከፈላቸው ከአሥር ወራት በላይ መታገሳቸውን፣ ይባስ ብሎ ደግሞ የሠሩበት እንዲከፈላቸው ሲጠይቁ ፖሊስ እያሳደዳቸው መሆኑን፣ የታሰሩ የሥራ ባልደረቦች አሉ ብለዋል፡፡

በዲላ ዙሪያ ወረዳ ጤና ጣቢያዎች የሚገኙና ከሥራ ያልታገዱ የጤና ባለሙያዎች ‹ለእነሱ ዕገዳ አያስፈልግም፡፡ ጥያቄው የጋራ ነው፡፡ ሁላችንም በአንድ ቃል ነው የጠየቅነው፡፡ ደብዳቤዎችንም ለዞንና ለወረዳ ያስገባነው በአንድነት ነው፤› ብለው እንደሞገቱ ተናግረዋል፡፡

ከ30 በላይ የጤና ባለሙያዎች ታስረው እንደነበር የገለጹት ቅሬታ አቅራቢዎቹ፣ ስምንት የጤና ባለሙያዎች እየታደኑ ናቸው ብለው፣ ለእስር ተዳርገው የነበሩት የጤና ባለሙያዎችን ‹ስልክ በመደዋወል አመፅ አነሳስተዋል› ተብለው መሆኑን አስረድተዋል፡፡

ከአሥር ወራት በላይ የትርፍ ሰዓት ክፍያ አልተከፈለንም ላሉት የጤና ባለሙያዎች ምን ያህል ገንዘብ እንደሆነ ሲጠየቁ፣ በደመወዝ ስኬል መሠረት ነው የሚከፈለው፡፡ በግለሰብ ከ30 እስከ 50 ሺሕ ብር ይደርሳል ሲሉ አክለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

የፋይናንስ ኢንዱስትሪው ለውጭ ባንኮች መከፈት አገር በቀል ባንኮችን ለምን አስፈራቸው?

የማይረጥቡ ዓሳዎች የፋይናንስ ተቋማት መሪዎች ሙግት ሲሞገት! - በአመሐ...

የምርጫ 97 ትውስታ!

በበቀለ ሹሜ      መሰናዶ ኢሕአዴግ ተሰነጣጥቆ ከመወገድ ከተረፈ በኋላ፣ አገዛዙን ከማሻሻልና...

ሸማቾች የሚሰቃዩት በዋጋ ንረት ብቻ አይደለም!

የሸማች ችግር ብዙ ነው፡፡ ሸማቾች የሚፈተኑት ባልተገባ የዋጋ ጭማሪ...

መንግሥት ከለጋሽ አካላት ሀብት ለማግኘት የጀመረውን ድርድር አጠናክሮ እንዲቀጥል ፓርላማው አሳሰበ

የሦስት ዩኒቨርሲቲዎች ፕሬዚዳንቶች በኦዲት ግኝት ከኃላፊነታቸው መነሳታቸው ተገልጿል አዲስ አበባ...