Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ዜናየመከላከያ የትጥቅ ግዥ ሚስጥራዊነት ላይ የፓርላማ አባላት ጥያቄ አነሱ

የመከላከያ የትጥቅ ግዥ ሚስጥራዊነት ላይ የፓርላማ አባላት ጥያቄ አነሱ

ቀን:

በአምስት ዓመታት ውስጥ ለሦስተኛ ጊዜ ማሻሻያ የተደረገበትን የመከላከያ አዋጅ ለማፅደቅ ትናንት ማክሰኞ ሚያዝያ 17 ቀን 2015 ዓ.ም. የተሰባሰቡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላት በአዋጁ መሠረታዊ ጉዳዮች ላይ ክርክር አንስተዋል፡፡

ነባሩ አዋጅ ‹‹መከላከያ ”የፌዴራል መንግሥት የግዥ ሕግጋትን ሳይከተል” ግዥ መፈጸም ይችላል›› የሚለው ሐረግ አሁን እንደ አዲስ ተሻሽሎ በቀረበው አዋጅ ተሸሯል፡፡ በአዲሱ አዋጅ መከላከያ ‹‹የአገር ደኅንነትና ወታደራዊ ሚስጥርን በማያጋልጥ አኳኃን የፌዴራል መንግሥት የግዥ ሕግጋትን ተከትሎ ግዥዎችን ሊፈጽም ይችላል›› ተብሎ ተስተካክሏል፡፡

ይሁን እንጂ የፓርላማ አባላቱ ‹‹እንዴት የመከላከያ ትጥቅ በመደበኛው የግዥ ሕግ መሠረት ሊከናወን ይችላል›› የሚል ጥያቄ አንስተዋል፡፡

‹‹የመንግሥት ግዥ ሕግጋት ‹በግልፅ ጨረታ›› ይላል፡፡ መከላከያ የደኅንነት ዕቃዎችና ትጥቆች እንዴት በግልጽ ጨረታ ሊገዙ ይችላሉ?›› በማለት ልዩ ዘዴ እንደሚያስፈልገው አቶ ኤሳ ቦሩና ሌሎች የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ አንስተዋል፡፡

አባላቱ የመከላከያ ግዥ ለሁለት ተከፍሎ፣ የሲቪል ግዥ በግልጽ ጨረታ እንዲሆንና ወታደራዊ ትጥቆች ግን በልዩ ግዥ ዘዴ እንዲስተናገዱ ሐሳብ አቅርበዋል፡፡

የመከላከያ ሚኒስትር ዴኤታና የምክር ቤቱ አባል ወ/ሮ ማርታ ሎዊጂ ግን ሕጉ ቢሻሻልም፣ በተጨባጭ አሠራሩ ላይ ለውጥ እንደማያመጣ አብራርተዋል፡፡

‹‹ነባሩን የግዥ ሕግ ሳይከተል›› የሚለው መቀየር ያስፈለገው ሕገወጥ ስለሚመስል ነው፡፡ ስለዚህ ከቀጥታ ግዥ ጀምሮ ያለውን አማራጭ ሁሉ እንጠቀማለን፡፡ ግን በግልጽ ጨረታ ብናወጣም ትጥቅ በዚያ ዘዴ መግዛት አንችልም፡፡ ብዙ ጊዜ ወታደራዊ ትጥቅ በቀጥታ ግዥ ነው የሚገኘው፡፡ አወዳድረህም አታገኝም፡፡ ብናወዳድርም ሁሉም አገሮች ወታደራዊ ትጥቅ እንድንታጠቅ አይፈልጉም፣ አይሰጡንም፡፡ በተለያዩ ሎቢና ዲፕሎማሲ፣ በተለያየ መንገድ ወዳጅነት ካላቸውና ትብበር ከፈጠርንባቸው ኢትዮጵያ ራሷን እንድትችል ከሚፈልጉ አገሮች ጋር ብቻ ነው ግዥ የምናደርው፡፡ ጨረታ ስላወጣን አናገኝም፡፡ ስለዚህ ለሲቪልና ወታደራዊ ትጥቅ እንደ ባህሪው የተለያየ ዘዴ መጠቀም የተሻለ ይሆናል፤›› ሲሉ ሚኒስትር ዴኤታዋ መልሰዋል፡፡

አዲስ የተሻሸለው የመከላከያ አዋጅ የመከላከያ የሒሳብ መዛግብትና ገንዘብ ነክ ሰነዶች በውስጥና በፌዴራል ዋና ኦዲተር እንዲመረመር ያዛል፡፡ ይሁን እንጂ ‹‹በመከላከያ ሚኒስትሩና በጠቅላይ ኤታ ማዦር ሹሙ አቅራቢነት ጠቅላይ ሚኒስትሩ አገራዊ ጥቅምና ደኅንነትን ለመጠበቅ ሲባል ‹‹እጅግ ጥብቅ ሚስጥር››› ብሎ የሚሰይማቸውን የጦር መሣሪያና የውጊያ ቁሳቁስ የግዥ ሒሳብ መዛግብትና ሰነዶች፣ ለመረጃ የወጡ የክፍያ ማስረጃዎች፣ እንዲሁም የሠራዊት ፕሮፋይል ወይም መገለጫ እንዳይገለጽ ሊያደርግ ይችላል፤›› በማለት አዲሱ አዋጅ ደንግጓል፡፡

የመከላከያን ገለልተኝነት በተመለከተ አዲሱ አዋጅ እንዴት አድርጎ መከላከያ ከአንድ ፓርቲ ወይም መንግሥት ጋር እንዳይጠበቅ ሊያደርግ ይችላል ተብሎ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ አንስተዋል፡፡

‹‹ከለውጥ በኋላ እየገነባን ያለነው ገለልተኛ መከላከያ ነው፡፡ በፊት በነበረው ግንባታ ለአንድ ፓርቲ ያደላ ሊሆን ይችላል፤›› ሲሉ ወ/ሮ ማርታ ምላሽ ሰጥተዋል፡፡

መከላከያ ከተለያዩ ምንጮች የሚያገኘውን ገቢም ጠቅላይ ሚኒስትሩን እያስፈቀደ ለመከላከያ አቅም ግንባታ እንዲጠቀም አዋጁ ፈቅዷል፡፡ ይሁን እንጂ የመከላከያ በጀት የሚወሰነው በፓርላማ ሆኖ እያለ፣ በጎን ሌላ የበጀት ሥልጣን ለጠቅላይ ሚኒስትሩ መስጠቱ ትክክል አይደለም ሲሉ የፓርላማ አባላቱ ሞግተዋል፡፡

የፓርላማ አባል የሆኑት ደሳለኝ ጫኔ (ዶ/ር) የተሻሻለው አዋጅ አሁንም ቶሎ ማሻሻያ እንዳይቀርብበት ጊዜ ተወስዶ እንዲጠና የጠየቁ ቢሆንም፣ አዋጁ በስድስት ድምፀ ተዓቅቦና በአብላጫ ድምፅ ፀድቋል፡፡

አዲሱ አዋጅ የመከላከያ መሥሪያ ቤት ‹‹ዕድሜያቸው 18 የሞላቸው የከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ወይም ዩኒቨርሲቲ ትምህርታቸውን ያጠናቀቁ ተማሪዎችን በፈቃዳቸው ወታደራዊ ሥልጠና ወስደው ለሁለት ዓመታት ብሔራዊ አገልግሎት እንዲሰጡ ሊያደርግ ይችላል፤›› በማለት ሥልጣን ሰጥቶታል፡፡

‹‹ተማሪዎች በፈቃዳቸው በመደበኛ የመከላከያ ሠራዊት ወይም የብሔራዊ  ተጠባባቂ ኃይል አባላት የሚሆኑ ከሆነ፣ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ተያያዥ መብቶችንና ጥቅሞችን እንዲጠበቅላቸው ያደርጋሉ፤›› ሲሉ ዲማ ነገዎ (ዶ/ር) የውጭ ግንኙነትና የሰላም ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ ገልጸዋል፡፡

ሌላው መሠረታዊ ለውጥ የተደረገበት አዲሱ አዋጅ ይዘት የመከላከያ አባላት የአገልግሎት ወረታን በተመለከተ ነው፡፡ ለሰላሳ ዓመታትና ከዚያ በላይ ያገለገሉ የሠራዊት አባላት የግል መኖሪያ ቤት ወይም የመሥሪያ ቦታ ይሰጣቸዋል፡፡ በሌላ በኩል ግን ሃያ ዓመትና ከዚያ በላይ ያገለገሉት ‹‹አቅም በፈቀደ›› መጠን ተመሳሳይ ጥቅም እንደሚያገኙ አዋጁ ይደነግጋል፡፡

‹‹የመጀመርያው ግዴታ ሲሆን ሁለተኛው ግን አቅም ሲፈቅድና ሲቻል ነው፡፡ አጭር ዕድሜ ያገለገሉትም የሠራዊት አባላት በመከላከያ ፋውንዴሽን በኩል ቆጥበው የኮንዶሚኒየምና ሌሎች የቤት ዓይነቶች ባለቤት እንዲሆኑ ዕድል ተመቻችቷል፤›› ሲሉ ሚኒስትር ደኤታ ወ/ሮ ማርታ ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...