Monday, December 11, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ብሔራዊ ሎተሪ በቲክ ቶክ የዕድል ጨዋታ የሚያካሂዱ ግለሰቦችን አስጠነቀቀ

ተዛማጅ ፅሁፎች

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር በአሁኑ ወቅት ቲክ ቶክን ጨምሮ በሌሎች የማኅበራዊ ትስስሮች ሕገወጥ የዕድል ጨዋታ ለሚያጫወቱ ግለሰቦች የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታወቀ፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በተለያዩ የማኅበራዊ ትስስሮች፣ በተለይም ቲክ ቶክ በሚባለው የማኅበራዊ ሚዲያ አንዳንድ ግለሰቦች የተለያዩ የዕድል ጨዋታዎችን በሕገወጥ መንገድ በቀጥታ ሥርጭት እያወራረዱ መሆኑን ያስታወቀው ብሔራዊ ሎተሪ፣ ግለሰቦቹ ኅብረተሰቡን ያላግባብ እየበዘበዙ ከመሆኑም በተጨማሪ በሕግ የተከለከለውን ሕገወጥ የዕድል ጨዋታ በከፍተኛ ሁኔታ እያስፋፉት ነው ብሏል፡፡

 የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ቴዎድሮስ ንዋይ ለሪፖርተር እንደተናገሩት፣ ቲክ ቶክ በተባለው የማኅበራዊ ትስስር የሎተሪ ጨዋታ የሚደረግ ሲሆን፣ አጫዋቾች ቁጥሮችን በመስጠት ሰዎች ለውርርድ በገንዘብ መላኪያ አፕሊኬሽኖች ገንዘብ እንዲጠቀሙ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል፡፡

ግለሰቦቹ የሚያደርጉት ጨዋታ ዕጣና ሽልማት ያለው ክፍያ የሚፈጸምበት በመሆኑ የሎተሪ ጨዋታ ተብሎ የሚገለጽ እንደሆነ ያስረዱት አቶ ቴዎድሮስ፣ ይህም ድርጊት ብሔራዊ ሎተሪ ከሚሰጠው አገልግሎት ጋር የሚፃረር ነው ብለዋል፡፡

ሕገወጥ የሎተሪ ጨዋታው በስፋት የሚደረገው በአገር ውስጥ እንደሆነና ቴሌ ብርን ጨምሮ በሌሎች የገንዘብ ማስተላለፊያ አፕሊኬሽኖች ክፍያዎች እንደሚፈጸሙ የተገለጸ ሲሆን፣ ይህንን መሠረት በማድረግ የአጫዋቾችን ማንነት ለማወቅ እንደተቻለና የመጨረሻ ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው አቶ ቴዎድሮስ ገልጸዋል፡፡

ሕገወጥ የዕድል ጨዋታ እያጫወቱ የሚገኙ አሥር ግለሰቦች ተለይተው ማስጠንቀቂያ እንደተሰጣቸው፣ ከእነዚህም መካከል ቡም ኢትዮጵያ፣ ላኪ ካሲኖ፣ ቸስ ቸስ፣ ኦፓል ቱርቦ፣ ኢትዮጵያ አርቢቢ (በዕቁብ ስም የተከፈተ ሕገወጥ የዕድል ሙከራ) በሚል የተከፈቱ የቲክ ቶክ አካውንቶች ይገኙበታል ተብሏል፡፡

ግለሰቦቹ የግንዛቤ ችግር ይኖርባቸዋል በሚል የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የመጀመሪያ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን አስታውቆ፣ ነገር ግን ከዚህ ድርጊት ባልተቆጠቡት ላይ ክስ በመመሥረት ጉዳዩን ወደ ፍርድ ቤት እንደሚወስደው አስተዳደሩ ገልጿል፡፡

በብሔራዊ ሎተሪ ደንብ ማቋቋሚያ መሠረት ሕገወጥ የዕድል ጨዋታ ማድረግ ከሦስት እስከ አምስት ዓመት እስራት፣ እንዲሁም ከ50 ሺሕ አስከ መቶ ሺሕ ብር የገንዘብ መቀጫ እንደሚያስቀጣ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተሩ አስታውሰዋል፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የማቋቋሚያ ደንብ ቁጥር 160/2001 የገንዘብ ሎተሪ የማካሄድ ብቸኛ መብት ለተቋሙ ከመስጠቱ በተጨማሪ፣ የዕድል ጨዋታዎችን የመቆጣጠርና ሕገወጥ ዕድለኞችን የመቆጣጠር ኃላፊነቶችን እንደተሰጠው ተገልጿል፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የዓይነትና የሽልማት አማራጫቸው የሰፋ ውድድሮች ሲደረጉ የሚስተዋል መሆኑን፣ ለእንዲህ ዓይነት ጨዋታዎች መበራከት ምክንያት ከሆኑት ውስጥ ብሔራዊ ሎተሪ የወቅቱን የዕድል ጨዋታዎች በየጊዜው አለማቅረቡን በምክንያትነት የሚያነሱ በርካቶች ናቸው፡፡

ከዘመናዊ አገልግሎት ጋር በተገናኘ ብሔራዊ ሎተሪ ከዘመኑ ጋር የሚሄድ ዲጂታል ሎተሪ ማቅረብ እንደጀመረ ያስታወሱት አቶ ቴዎድሮስ፣ ነገር ግን ብሔራዊ ሎተሪ ስላልጀመረው ተብሎ የሚጀመር የዕድል ጨዋታ ሊኖር እንደማይገባና በሌሎች አገሮችም ሎተሪ መንግሥት የሚያስተዳድረው ሥራ አንጂ ለግለሰብ የሚሰጥ አገልግሎት አለመሆኑን አስረድተዋል፡፡

የብሔራዊ ሎተሪ አስተዳደር የዲጂታል ሎተሪ ከማምጣት በተጨማሪ ተቋሙን በአዲስ መልክ ለመቀየር የቢዝነስ ጥናት እየተደረገ እንደሚገኝ የተገለጸ ሲሆን፣ በዓለም አቀፍ ተቋም የሚደረገውን ጥናት መሠረት በማድረግ አገልግሎት የማስፋት ተግባራት እየተከናወነ ይገኛል ተብሏል፡፡

ለግል ዘርፉ ከማይሰጠው የሎተሪ ጨዋታ ውጪ ማንኛውም ተቋም አራት መመርያዎችን መሠረት በማድረግ የዕድል ጨዋታ ማድረግ እንደሚቻል ያስታወቀው የብሔራዊ ሎተሪ፣ እነዚህም የስፖርት ውርርድ ጨዋታ (ቤቲንግ)፣ የልማት ማኅበራት ቶምቦላ ሎተሪዎች፣ በመዝናኛ አካባቢ የሚዘወተሩ የቢንጎ ጨዋታ፣ እንዲሁም አዳዲስ ምርቶችንና አገልግሎቶችን ለማስተዋወቅ የሚቀርቡ ሎተሪዎች መሆናቸውን አክሏል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች