Sunday, December 10, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ኪንና ባህልየተቀደሰውን ወር ተከትሎ የመጣው ዒድ አልፈጥር

የተቀደሰውን ወር ተከትሎ የመጣው ዒድ አልፈጥር

ቀን:

  • ተከታዩ ሸዋል ዒድ

በሙስሊሙ ኅብረተሰብ የረመዳን ወር በዓመተ ሒጅራ ካሉት ወሮች መካከል ዘጠነኛው ሲሆን ‹‹የተቀደሰ ወር›› የሚያሰኘው ሙሉውን የጾም ወር መሆኑ ነው፡፡ ቀጣዩ 10ኛ ወር ሸዋል በሚብትበት ዕለት ዒድ አልፈጥር ይውላል። ይህ በጨረቃ የ354 ቀን ዑደት ላይ የተመሠረተው ዓመተ ሒጅራ፣ ዘንድሮ ጾሙ ‹ረመዳን 1 ቀን 1444 ዓመተ ሒጅራ› (መጋቢት 14 ቀን 2015) ላይ ተጀምሮ፣ ሚያዝያ 12 ላይ ረመዳን 29 ቀን ሆኗል፡፡ በማግስቱ 30 ሆኖ ‹ሸዋል 1 ቀን› (ሚያዝያ 14) ዒዱ በዓለም ዙርያ በተከታዮቹ ዘንድ ተከብሯል፡፡

የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ጠቅላይ ምክር ቤት ዒድ አልፈጥርን አስመልክቶ በሰጠው መግለጫ፣ በዓሉ የሰላምና የደስታ፣ የመተዛዘንና የመረዳዳት እንዲሆን መልካም ምኞቱን በምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ሸህ ሐጂ ኢብራሂም ቱፋ አማካይነት አስተላልፏል፡፡ ፕሬዚዳንቱ የረመዳን ወርን አስመልክቶ በተለያዩ ከተሞች የተካሄዱ የጎዳና የኢፍጣር መርሐ ግብሮች ሰላማዊ ሆነው እንዲጠናቀቁ አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላትም ምስጋና አቅርበዋል።

የተቀደሰውን ወር ተከትሎ የመጣው ዒድ አልፈጥር | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
ከዚህ ቀደም ዒድ አልፈጥር በአዲስ አበባ
ስታዲየም በተከበረበት ወቅት
ፎቶ ዢንዋ

ዒድ አልፈጥር ሲገለጽ

ዒድ አልፈጥር፣ የረመዳን ጾም መጠናቀቁን የሚያመላክት ነው፡፡ ዒድ አልፈጥር ረመዳን ካበቃ በኋላ በማግሥቱ ይጀመራል፡፡ ዒስራ አራሁ የተባሉ ጸሐፊ በስታንዳርድ ዩኬ ድረ ገጽ እንደገለጹት፣ ‹‹ይህ ዒድ ሙስሊሞች የረመዳንን ጾም እንዲያልፉ የሚያስችል የአላህ የብርታትና የፅናት ስጦታ መንፈሳዊ በዓል ሆኖ ይታያል፡፡›› ወቅቱ ዘካት አል ፈጥር በመባል የሚታወቀው የችሮታ ጊዜ በመሆኑ ነው፡፡ ሰዎች ለድሆች ምግብም ሆነ ገንዘብ እንዲለግሱ ይጠበቃል፡፡

የዒድ አከባበር የሚጀምረው ጎሕ ሲቀድ ነው፡፡ እሱም ብዙውን ጊዜ በመስጊድ ውስጥ ይከናወናል፡፡ ከሶላት በኋላ ሙስሊሞች በተለያዩ መንገዶች ያከብራሉ፡፡ ማኅበረሰቡ በአንድነት ሆኖ ጣፋጭ ምግብን ይቋደሳል፡፡ ሁሉም እንደ ባህሉ በምርት ልብሶቻቸው ይዋባሉ፡፡ በዓሉ ለልጆች በተለይ አስደሳች ጊዜ ነው፡፡  ወላጆቻቸውና ዘመዶቻቸው በስጦታ (ዒድያ) ያንበሸብሿቸዋል፡፡

የረመዳን ጾም ካለቀ በኋላ የሚከበረው ዒድ አልፈጥር ቀኑ ከጨረቃ ጋር ተያይዞ ከተወሰነ በኋላ እናቶች በዓሉን ለመቀበል የሚያደርጉት ደፋ ቀና ይቀጥላል፡፡ ጨረቃ እስክትወጣ ድረስ ግን ሁኔታቸው በጥርጣሬ የተሞላ መሆኑ ነው፡፡

የሃይማኖቱ ሊቆች እንደሚናገሩት ምንም እንኳ ረመዳን ለአንድ ወር ያህል የሚቆይ ቢሆንም አንዳንድ ወራት 30 ቀናት አይኖራቸውም፡፡ 29 ይሆናሉ፡፡ ስለዚህም የጾም ጊዜ ማብቃቱንና ቀጣዩ ቀን ዒድ መሆኑ የሚበሰረው ምሽት ላይ በምትወጣው ጨረቃ ይሆናል፡፡ ጨረቃን አይቶ የማፍጠር ሱና የተጀመረው ነቢዩ መሐመድ የጨረቃን ገጽታ አይተው በማፍጠራቸው እንደሆነ ይናገራሉ፡፡

ጨረቃም በወጣች ጊዜ ወትሮው ከሚሰገደው የሰላት ዓይነቶች በተጨማሪ በረመዳን ወር ከምሽቱ አራት ሰዓት ጀምሮ እስከ ሌሊቱ አሥር ሰዓት የሚሰገደው የአተራዊ ስግደት አይኖርም፡፡ በዚህ መሠረትም በዓሉ በማግስቱ እንደሆነ በማረጋገጥ ለበዓሉ የሚውል ምግብ የማዘጋጀት ሒደቱ ተጠናክሮ ይቀጥላል፡፡

መንዙማና የዒድ ዝግጅት

‹‹መንዙማ ምስጋና (ማወደስ) ማለት ነው፡፡ መንዙማ በይዘቱ በዋነኛነት ከሃይማኖታዊ ዝማሬዎች ይመደብ እንጂ በውስጡ የተለያዩ ማኅበራዊና ፖለቲካ መልዕክቶችንም ያቀፈ ነው፡፡ ሃይማኖታዊ ይዘቱም አላህ የሚመሰገንበት፣ ነቢዩ መሐመድ የሚሞገሱበት፣ የእስልምና ትምህርት የሚሰጥበት፣ ታላላቅ ሰዎች (አወሊያዎች) እና መላዕክት የሚወደሱበት፣ ገድላቸውና ተአምራቸው የሚነገርበት፣ ችግር (ድርቅ፣ ረሃብና በሽታ) የመሳሰሉት ሲያጋጥሙ የተማፅኖ ጸሎት የሚደረግበት ነው፤›› ይላል በቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን የተዘጋጀ አንድ የጥናት መድበል፡፡

እንደ መድበሉ፣ አብዛኛውን የመንዙማ ግጥሞች የሚጀምሩት አላህና ነቢዩ መሐመድን በማወደስ ሲሆን፣ የሚጨርሱት ደግሞ አላህን ለማመስገንና ለነቢዩ መሐመድ ሰላምና እዝነትን አላህ እንዲሰጣቸው ነው፡፡ የመንዙማው አቀንቃኝ በተሳታፊዎች ፊት ሲያቀነቅን ሲወርድ ሲዋረድ የመጣውን የአከዋወን ስልት በመከተል የተለያዩ አካላዊ እንቅስቃሴዎችን ያሳያል፡፡ ከግራ ወደ ቀኝ ከቀኝ ወደ ግራ ሰውነቱን ያወዛውዛል፣ ታዳሚዎችም አስፈላጊውን አጸፋና ምላሽ በድምፅና በጭብጨባ ይገልጻሉ፡፡ የመንዙማ አጨፋፈር እንደ ዜማዎቹ ዓይነት ይለያያል፡፡ ዝግ ያለ የድቤ መምቻ ያላቸው መንዙማዎች የአጨፋፈር ስልት ምቱን ተከትለው እየዘለሉና እጅን ከአናት በላይ እያሳለፉ ማጨብጨብ ሲሆን፣ ፈጣን የድቤ ምት ያላቸው መንዙማዎች ደግሞ እያጨበጨቡ ከወገብ በላይ አካላቸውን ወደ ግራና ወደ ቀኝ ማወዛወዝ ናቸው፡፡

ከዜማ ቅብብሎሹ/ከዝማሬው ለአብነት የሚከተለውን መጥቀስ ይቻላል፡፡

‹‹አሏሁም መሶሌ አላሙሀመዴ(2x)

ሙሐመድ፣ ሙሐመድ የዓለሙ ዘውድ፣

ተቆጥሮ የማያልቀው የሱማ ገለታ፣

ለሙሐመድ ኡመት ያደረገን ጌታ፣

መሻሪያ ሰጥቶናል ከወንጀል በሽታ፣

ሰላምና ሶላት ይጉረፉ ጠዋት ማታ፣

በአህመድ በኛ ጌታ በአዘሉውድ፡፡››

ዚያራ

በዒድ ዚያራ ትልቅ ቦታ ይሰጠዋል፡፡ ስለዚህም ከቅርብ ቤተሰብ በመጀመር ሌሎች ቤተሰቦቻቸውን ይዘይራሉ፡፡ ‹‹ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትና ክዋኔዎች›› በሚለው የሀረሪ ድርሳን እንደተገለጸው፣ ዚያራ በቀጥተኛ ትርጉሙ ጉብኝት ማለት ሲሆን ለበዓላት እና ለተለያዩ ምክንያቶች ቤተሰብንም ሆነ የጀመዓ አባላትን መጎብኘትን ያካትታል፡፡

ይሁንና በሀረር ዚያራ ሲባል በስፋት የሚታወቀው ለጸሎት፣ በዓላትና ተያያዥ ጉዳዮች ወደ አዋቾች የሚደረግ ጉዞ ነው፡፡ አዋቾች የተቀደሱ ቦታዎች እንደመሆናቸው በነዚህ ቦታዎች ዚያራ የሚደረገው በአብዛኛው በበዓላት ወቅት ሲሆን አልፎ አልፎ ለተለየ ጉዳይ አላህን የሚለምንላቸው የሚፈልጉ ሰዎች አዘቦት ቀናት ዚያራ ሊያደርጉ ይችላሉ፡፡

ሸዋል ዒድ

በሀረሪዎች ዘንድ በዋናነት ከሚከበሩት በዓላት መካከል አንዱ ሸዋል ዒድ ነው፡፡ ሸዋል ዒድ በእስልምና የዘመን አቆጣጠር በሸዋል ወር፣ የረመዳን ጾም ተጠናቆ ዒድ አልፈጥር በዋለበት በስምንተኛው ቀን የሚከበር በዓል ነው፡፡ ይህም ዒድ አልፈጥር ከተከበረ በኋላ ስድስት ተከታታይ ቀን ተጹሞ በቀጣዩ ቀን የሚከበርበት ምክንያቱ በእስልምና አስተምህሮ ሴቶች በረመዳን ጾም ወቅት የወር አበባ በሚያዩባቸው ቀናት ጾሙን ስለሚያቋርጡ ያጎድሉትን የጾም ቀናት ለማካካስ እንዲችሉ ለማድረግ ሲባል ነው፡፡ ከዚሁ ጋር ተያይዞ ወንዶች ተጨማሪ እጅሪ (ምንዳ) ለማግኘት ጾሙን የሚጾሙ በመሆናቸው በዓሉ ዒድ አልፈጥር በተከበረ በስምንተኛው ቀን ይውላል፡፡

‹‹ሃይማኖታዊ ክብረ በዓላትና ክዋኔዎች›› በሚባለው የሀረሪ ድርሳን አገላለጽ፣ ዚክሪ በምስጋና መዝሙሮች የተሞላ አላህ፣ ነቢዩ መሀመድና ቅዱሳን የሚመሰገኑበት ሥርዓተ ጸሎት ሲሆን፣ ቃሉ የምስጋና መዝሙሩ (መንዙማ) መጠሪያ ሆኖም ያገለግላል፡፡ የዚክሪ ክዋኔ ግጥም በዜማ የሚያወጡ ሸኽ እና ዚክሪውን በሚቀበሉ ታዳሚዎች እየተመራ በድቤ (ከረቡ) እና ከእንጨት የተሠሩ ማጨብጨቢያዎች (ከበል) የሚታጀብ ሲሆን፣ ተሳታፊዎች እየተነሱ ክብ ሠርተው በመወዛወዝ (በመጨፈር) ያደምቁታል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...