Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

የተመረጡ ፅሑፎች

ቃጠሎው!

ሰላም! ሰላም! ሰላም ለአገራችን ሰላም ለሕዝባችን፣ ሰላም ለአፍሪካችን ሰላም ለዓለማችን ይሆን ዘንድ ልባዊ ምኞቴ ነው፡፡ ምሁሩ ወዳጄ የባሻዬ ልጅ፣ ‹‹ወንድም አንበርብር ምኞትህ መልካም ነው፣ ነገር ግን ሰላምህ ከቤትህ ሲጀምር ደግሞ ተከትሎህ የትም ድረስ ይዘልቃል፡፡ እኔና አንተ፣ ሌሎች ወገኖቻችን፣ እንዲሁም አገር የሚመሩና አገር ለመምራት የሚፈልጉ በሙሉ ሰላምን ከቤታቸው ጀምሮ ቢያስቡ ሁሉም ነገር ቀና ይሆን ነበር…›› ሲለኝ፣ እኔና ውድ ባለቤቴ ማንጠግቦሽ ከቤታችን ያልጀመርነውን ሰላም የት እንደምናገኘው ወይም የት እንደምናደርሰው ማሰላሰል ጀመርኩ፡፡ እስላም ክርስቲያኑ ከረጅም ፆም በኋላ በዓላቶቻቸውን ፈጣሪያቸውን እያሰቡ ሲያከብሩ፣ ከምንም ነገር በላይ አጥብቀው የሚመኙት ሰላም መሆኑን ሳስብ ልቤ ሰበር አለ፡፡ ዋጋው ስንት እንደሆነ ሊተመን የማይችለው ሰላም ብቻ ነው፡፡ አልማዝ፣ ወርቅ፣ ብር፣ ነዳጅ፣ መሬት፣ ሕንፃ፣ መኪና፣ ባቡር፣ አውሮፕላን፣ መርከብ፣ ወዘተ ዋጋ ተቆርጦላቸው ይህንን ያህል ገንዘብ ያወጣሉ ተብለው ገበያ ሲቀርቡ የሰላም ዋጋ ግን አይታወቅም፡፡ ልክ እንደ አየር፣ ፀሐይና ዝናብ የሰላም ዋጋው አልተቆረጠለትም፡፡ የሰላም ነገር እያንገበገበኝ ያለው ወድጄ አይደለም፡፡ አያያዙን አናውቅ ያልንበት አኳኋናችን በበርካታ ጉዳዮቻችን ውስጥ ሰላማችንን ሲነሳን ከመጠን በላይ ስታዘብ፣ እኔ ደላላው አንበርብር ምንተስኖት በማይም አዕምሮዬ የሰላም ያለህ እያልኩ ብጮህ ሳይሻል አይቀርም ብዬ ነው፡፡ ሰሚ ካለ አትሉም!

በትንሳዔ በዓል ማግሥት ወጣ ብዬ ከተማውን ዞር ዞር ብልበት ጆሮን ጭው የሚያደርግ ዓይነት ፀጥታ ሰፍኖበታል፡፡ እግረኛውም ሆነ ባለተሽከርካሪ መንገዱ ላይ ዝር ለማለት የፈለጉ አይመስሉም ነበር፡፡ ሰው ሁሉ በሩን ዘግቶ ያረደውን ፍየል፣ በግና ዶሮ ወይም ያስገባውን የበሬ ሥጋ እየከተከተ ነው እንዴ የጠፋው እያልኩ ከራሴ ጋር ስነጋገር፣ ‹‹አቶ አንበርብር በበዓል ማግሥት ሰው አረፍ ብሎ አንተ ድለላ አይጠፋም ብለህ ነው እንዴ የምትንጎራደደው?›› ብሎ አንድ ተንኮለኛ ደላላ ከጀርባዬ እየሳቀ ወደ እኔ መጣ፡፡ ዘንድሮ መቼም ተንኮለኛው በዝቶ በሳቅ እያዋዛ አይደል እንዴ ጉድ የሚሠራን፡፡ ‹‹ምነው ወንድሜ መጀመሪያ እንኳን አደረሰህ ማለት አይቀድምም ወይ?›› ብዬ ወደ ሰላማዊው ድባብ ልመልሰው ጥረት ሳደርግ፣ ‹‹ወዴት… ወዴት… የእንኳን አደረሳችሁ መልካም ምኞቱማ በሃይማኖት አባቶችና በፖለቲከኞች በየተራ ከአንገት በላይ ደርሶናል፡፡ እኔና አንተ ከእነሱ የተረፈውን አንጠልጥለን የመዞር ግዴታ የለብንም አይደል? ይልቁንስ ምን ደስ የሚያሰኝ ነገር አለና ነው ሌላው ቀርቶ ሰላም የምንባባለው…›› እያለ ከየትም የቃረመውን የነገር ታምቡሩን ጆሮዬ ላይ ሊያጮህብኝ ሲል፣ ‹‹ወንድሜ በል በበዓል ክፉ አታናግረኝ፣ አንተም ቤተሰብህም ሰላም ሁኑ…›› ብዬ በቆመበት ጥዬው ሄድኩ፡፡ እንዲያ የሚሻል መሰለኝ!

በነጋታው እንዲያው ጎዳናው ላይ ውርውር የሚል ቢኖር ብዬ ብቅ ለማለት፣ ውዴ ማንጠግቦሽ ለቁርስ ያዘጋጀችልኝን የዶሮ ፍርፍር ስቀማምስ ባለውለታዬ ስልኬ ጮኸ፡፡ ደዋዩ ከቀዳማዊ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት እስካሁን ድረስ በንግድ ሥራ የሚተዳደሩ የ80 ዓመት አዛውንት ናቸው፡፡ እኝህ አዛውንት መንፈሰ ጠንካራ፣ አዕምሮአቸው ብሩህ፣ ከብዙዎቹ ጎልማሶች ያልተናነሰ ቁመና ያላቸው፣ ሁሉንም ልጆቻቸውን በአገርም ሆነ በውጭ ዩኒቨርሲቲዎች አስተምረው ለወግ ማዕረግ ያበቁና እስቲ ልረፍ ሳይሉ በከፍተኛ ፍቅር ሥራቸውን የሚያከናውኑ አስገራሚ ሰው ናቸው፡፡ ከእሳቸው ጋራ ጉዳይ ሲኖረኝ እንደ ዘመኑ ክልፍልፍ ባለሀብት ተብዬዎች በዋዛ የሚያልቅ አይሆንም፡፡ ሲገዙም ሆነ ሲሸጡ በከፍተኛ ጥንቃቄና በሕጋዊ መንገድ ብቻ ነው፡፡ ማምታታትም ሆነ ማደናበር እሳቸው ዘንድ አይሠራም፡፡ የፈለጉኝ ቦሌ አትላስ አካባቢ የሚሸጥ ከአሥር ፎቅ የማይበልጥ ሕንፃ እንዳፈላልግ ነው፡፡ ከዚህ ቀደም ያስገነቡዋቸውም ሆነ የገዟቸው ሕንፃዎች እንዳሉዋቸው አውቃለሁ፡፡ ተገናኝተን ለምን እንደፈለጉት በአካል እስኪነግሩኝ ድረስ በስልክ ማሰልቸት አልፈለግኩም፡፡ እሳቸውም በስልክ ብዙ ማውራት አይወዱም፡፡ ውጭ ከሚማሩ ልጆቻቸው ጋር ከሁለት ደቂቃ በላይ ለመነጋገር ትዕግሥት እንደሌላቸው ሲወራ ሰምቻለሁ፡፡ የሥራ ሰው እንዲህ ነው!

በተሰጠኝ ቀጭን ትዕዛዝ መሠረት አካባቢውን እያሰስኩ መረጃ ማሰባሰብ ጀምሬያለሁ፡፡ በዚህ መሀል ታዲያ የምሳ ሰዓት ደርሶ አንዱ ዘመናዊ ምግብ ቤት ጎራ ስል፣ ከፊት ለፊት የተቅለጠለጠ ጮማና የወዛ ብሩንዶ በሰፊው የተንጣለለበት ኪዮስክ መሳይ ይታያል፡፡ ወደ ውስጥ እየዘለቅኩ ውጭውንና ውስጡን የሞሉትን ተመጋቢዎች ለአፍታ ገርመም ሳደርግ፣ የገባሁበት ዘመናዊ ምግብ ቤት እኔ የምገኝበትን ሊግ እንደማይመጥን ወዲያውኑ ገባኝ፡፡ ያሸበረቀ የመስተንግዶ ልብስ የለበሰ ወዛ ያለ አስተናጋጅ በፍጥነት ቦታ ሰጥቶኝ፣ ‹‹ምን ልታዘዝ?›› ሲለኝ ሰፊው የብረት ወሳንሳ ላይ የተንጣለለውን ጮማና ብሩንዶ በዓይኖቼ እየማተርኩ ምንተፍረቴን ግማሽ ኪሎ ቁርጥ አዘዝኩ፡፡ ‹‹ግፋ ቢል አዶላ አንሳ ቢል ዶማ›› የሚባለውን የድሮ አባባል እያስታወስኩ ፈገግ ስል አስተናጋጁም ፈገግ እያለ፣ ‹‹የሚጠጣስ?›› ከማለቱ፣ ‹‹ወዳጄ አምቦ ውኃ…›› እያልኩ ማግሳት ጀመርኩ፡፡ ከተፎው አስተናጋጅ ወደ ላቦራቶሪ ለምርመራ ለናሙና የምትላክ የምታክል ፊቴ ላይ አስቀምጦ እብስ ሲል፣ አቤቱታ ለማሰማት እንኳን ዕድል ሳይሰጠኝ እንደነበረ ስገልጽላችሁ የምለው ይገባችኋል፡፡ ያቺን ምርቃት የምታክል ነገር ቀማምሼና አምቦዬን ማወራረጃ አድርጌ ሒሳብ ስከፍል አልደነገጥኩም፡፡ ምክንያቱም ከእነ ቲፑ አንድ ሺሕ ብር ብቻ ነበር፡፡ ጉድ ነው!

እናንተ ይኼ እንዴት አያስደነግጥም ማለታችሁ እኮ አይቀርም፡፡ በቀደም በበዓል ዋዜማ በግ ተራ ሄጄ ነበር፡፡ ከዚያ በፊት ግን ያ የፈረደበት ፌስቡክ ላይ ፍየል 20 ሺሕ ብር፣ በግ 15 ሺሕ ብር፣ ዶሮ 1‚600 ብር ሲባል ሰምቼ ስለነበር በግ ተራ ስደርስ የዋጋው ነገር አላስደነገጠኝም፡፡ አንዱን በግ ሻጭ ጠጋ ብዬ፣ ‹‹ምነው ዘንድሮ እንዲህ ዓይነቱ ዋጋ እንደ ቀልድ ተጠራ?›› ስለው፣ ‹‹አይ ጋሼ መንገዱ ሁሉ ተዘጋግቶ እኮ ከብት አልገባም…›› አለኝ፡፡ ‹‹አንተ ወይድ እባክህ፣ ይኸው መንገድ ተከፋፍቶ ከብትና እህል በገፍ እየገባ ነው ብሎ ቴሌቪዥኑ ነገረን እኮ…›› ብዬ ሙግት ስጀምረው፣ ‹‹አሂሂ… በገፍ ከገባ ታዲያ ለምን እነሱ ለሕዝቡ በቅናሽ አያቀርቡለትም…›› ብሎኝ ሳቀብኝ፡፡ ከአይሱዙ መኪና ላይ በአንድ ሺሕ ብር የገዛሁትን ወደላ ዶሮ እያስታወስኩ፣ ከጥርስ ውስጥ በስቴኪኒ ተጎርጉሮ ለማይገኝ በግማሽ ኪሎ ስም በላሁት ለተባልኩት ምራቂ ሥጋ አንድ ሺሕ ብር ማውጣቴን ከእናንተ በስተቀር ለማንጠግቦሽ አለመናገሬን በትህትና እገልጻለሁ፡፡ የዋጋ ነገር ሲነሳ ሁሉም ነገር ሲጨምር የሰው ልጅ ብቻ ነው እያደር ቁልቁል እየወረደ ነው ብል ያጋነንኩ አይመስለኝም፡፡ ያኔ ድሮ በግ ቆዳ መልስ በሁለት ብር፣ የበሬ ብልት በአምስት ብር ገዝተው በበሉት ታሪክ ስንደመም፣ እኛም ባለተራ ሆነን ጣባ ክትፎ በሦስት ብር የበላንበት ጊዜ አልፎ ለዚህ ደርሰን ወግ እንጠርቃለን፡፡ ምን ይደረግ!

ከወራት በፊት ከሆላንድ የመጣ የድሮ ደንበኛዬ ቤት መሥሪያ ይዞታ ፈልጎ ከተማውን ስናስስ፣ ‹‹ሆላንድ የሚባል ሀብታም አገር እየኖርክ መቼም ደህና ጥሪት ይዘሃል…›› እያልኩ የኑሮውን ሁኔታ ላውጣጣ ወሬ ስጀምርለት፣ ‹‹አንበርብር ይገርምሃል እኔ ያኔ ከዚህ ለመሄድ ስዘጋጅ እንዳንተ ነበር የማስበው፡፡ በእርግጥ በፊት በጣም ጥሩ ነበር፡፡ መጀመሪያ የዛሬ አሥራ አምስት ዓመት ትዝ ይልህ እንደሆነ የዓለም የፋይናንስ ቀውስ ሲፈጠር ብዙ ነገሮች ተናጉ፡፡ ከዚያ ቀውስ ውስጥ ለመውጣት ብዙ ጥረት ተደርጎ ሻል ያለ ነገር ሊፈጠር ነው ሲባል ኮቪድ ድንገት መጥቶ ትርምስምሱን አወጣው፡፡ ከኮቪድ ገና ለማገገም መንፏቀቅ ስንጀምር የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት የነበረውን እንዳልነበረ እያደረገብን ነው…›› ብሎ ሲተክዝ፣ ‹‹ቆይ… ቆይ… የሩሲያና የዩክሬን ጦርነት ከእናንተ ኢኮኖሚ ጋር ምን ያገናኘዋል…›› ከማለቴ በመገረም አፈጠጠብኝ፡፡ ‹‹እንዴ ምን ማለትህ ነው? እንኳንስ እኛ እዚያ አጠገባቸው ያለነውን አይደለም የእነሱ ጦርነት ዓለምን አይደለም እንዴ ቀውስ ውስጥ እየከተተ ያለው፡፡ ሌላውን ተወውና እኛ ጋዝ የምናገኘው ከሩሲያ ነው፡፡ እኔና ባለቤቴ ከአንድ ዓመት በፊት የወር የጋዝ ፍጆታችን ሦስት መቶ ዩሮ ብቻ ነበር፡፡ ጦርነቱ ሲነሳ አምስት መቶ ዩሮ፣ ሲቀጥል ሰባት መቶ ዩሮ፣ እያለ እያለ ይኸው ከአንድ ሺሕ ዩሮ በላይ ለመክፈል ተገደናል፡፡ የምግብና የሌላው ቁሳቁስ ዋጋ ማሻቀብማ አይነገርም፡፡ እዚህም እኮ የበለጠ የባሰ እየሆነ መሆኑን አላውቅም ብትለኝ ይገርማል…›› ብሎኝ አላዋቂነቴን በስላቅ ተዛበተበት፡፡ እንኳን የእሱ ስላቅ ኑሮ ራሱ መጫወቻ አድርጎን የለ!

መቼ ዕለት ነው የሚፈለገውን ሕንፃ ዓይነት የሚሸጥ አለ የሚለው መረጃ ደርሶኝ ሻጩን አፈላልጌ አገኘሁት፡፡ ዕድሜዎቹ በአርባዎቹ ውስጥ ያለ ነገር ግን በተለየ እንክብካቤ ነው መሰል በሃያዎቹ አጋማሽ የሚገኝ የሚመስል ሰው ቢሮ ደረስኩ፡፡ የመጣሁበትን ጉዳይ አስረድቼው ዋጋ ስጠይቀው ሳቅ እያለ፣ ‹‹ዋጋውን እንኳ ከገዥው ጋር እንጂ ከደላላ ጋር አልነጋገርም…›› ብሎ፣ ‹‹በነገራችን ላይ እኔ እንደ ማንኛውም ሻጭ ከዚህ ዋጋ ተነስቼ በዚህ ዋጋ ለመሸጥ አልፈልግም፡፡ ታውቃለህ ከገዥ ጋር ቁርጥ ያለ ዋጋ እነጋገራለሁ እዚያው ያልቃል…›› በማለት አሰናበተኝ፡፡ በድለላ ዘመኔ እንዲህ ዓይነት የመሸጫም ሆነ የመነሻ ዋጋ የማይነገርበት ድለላ ገጥሞኝ አያውቅም፡፡ ከሰውዬው ቢሮ እንደወጣሁ ለደንበኛዬ የተነገረኝን ስነግራቸው፣ ‹‹አየህ እኔም ከእንዲህ ዓይነቱ ጋር ነው ተገናኝቼ መገበያየት የምፈልገው…›› ብለውን ቀጠሮ አመቻቸሁ፡፡ ጎበዝ አንዳንዴ እኮ ከወትሮው ልምዳችን ቀየርና ቀየርየር ማለት ያስፈልጋል ማለት ነው፡፡ እውነትም ወጣት መሳዩ ጎልማሳና አዛውንቱ በተደጋጋሚ በር ዘግተው ተነጋግረው ዋጋ ለመቁረጥ ሲስማሙልኝ፣ እኔም ምክራችሁ ይስመርና ኮሚሽኔን በሰላም የማገኝበት ዕድል ይፈጠርልኝ ብዬ ወደ ፈጣሪ ተማፅኖ ይዣለሁ፡፡ ሥራ በአግባቡ ሲሠራና አገርም የምትፈልገውን ጥቅም በሥርዓት ስታገኝ ነው ሰላማችን ዕውን የሚሆነው፡፡ እንዲያ መሰለኝ!

እስቲ እንሰነባበት፡፡ አዛውንቱ ባሻዬ ከሁለት የፆም ወራት በኋላ እስከ ዳግማዊ ትንሳዔ ማረፍ ስላለባቸው፣ ከምሁሩ ወዳጄ ጋር የባጥ የቆጡን እየቀባጠርን ውለን አመሻሽ ላይ ወደ ተለመደችው ግሮሰሪያችን ጎራ ብለናል፡፡ የግሮሰሪያችን ደንበኞች ከአድቃቂው ነሮ እስከ አገሪቱ የፖለቲካ ውጥንቅጥ ድረስ፣ የቀረበላቸውን እየቀማመሱ በየፈርጁ ያወጋሉ፡፡ በለሆሳስ ከሚነጋገሩት በሞቅታ ፈረስ ላይ ሆነው ድምፃቸው ገመገም እስከሚደርሰው ድረስ፣ በመሰላቸው ጉዳይ ላይ ማለት አለብን የሚሉትን ይሰልቁታል፡፡ ምሁሩ የባሻዬ ልጅ ቀስ ብሎ፣ ‹‹የእኛ ሰው ስሜቱ ተቀያያሪ ሆኖ ወጥ የሆነ አቋም ባይኖረውም፣ የሚሰማውን ነገር ሁሉ በቁጣ ለመዘርገፍ ግን አሁንም የሰነፈ አይመስልም…›› ሲለኝ ለጊዜው ደንገርገር ቢለኝም እየነገረኝ የነበረው ስለትውልዱ ስለሆነ ብዙም አልተቃወምኩትም፡፡ ነገር ግን በድንገት አንድ ነገር ጭንቅላቴን ጠቅ አደረገኝ፡፡ ይህም ከወራት በፊት ይመስለኛል አንድ የመረረው ሰው፣ ‹‹ፆምና ፀሎቱ ኢትዮጵያ፣ በረከቱና ሰላሙ አሜሪካ›› ነበር ያለው፡፡ ለመሆኑ እኛ መቼ ነው ከዘመናት መከራችንና ሰቆቃችን ውስጥ የምንወጣው የሚለው ደግሞ የእኔ ሐሳብ ነው፡፡ ‹‹ወንድሜ አንበርብር አየህ እኛ ውስጣችን ያለው እሳት ነው፡፡ እሳት በአግባቡ ከያዝከው እያዳፈንከው ትጠቀምበታለህ፣ ካልሆነ ግን አጥፍተኸው ትገላገለዋለህ እንጂ ቤትህን አቃጥሎ እስኪያጠፋው አብረኸው አትኖርም…›› እያለኝ መሽቶ ወደ ቤታችን ስንመለስ፣ ቃጠሎው ውስጤ ድረስ ይሰማኝ ነበር፡፡ መልካም ሳምንት!

Latest Posts

- Advertisement -

ወቅታዊ ፅሑፎች

ትኩስ ዜናዎች ለማግኘት