Monday, May 20, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ማኅበራዊያላባራው ወደ ዓረብ አገሮች የሚደረግ ሕገወጥ ስደት

ያላባራው ወደ ዓረብ አገሮች የሚደረግ ሕገወጥ ስደት

ቀን:

ክስተቱ ወደ አሥር ዓመታት አስቆጥሯል፡፡ ተወልዳ ካደገችበት ከአዲስ አበባ ወደ አቡዳቢ ያቀናችው ቀድማት በሄደችው ዘመድዋ ውትወታ ነበር፡፡ ‹‹አካሄዴ ሕጋዊ ነበር›› የምትለው ሃና (ስሟ ተቀይሯል)፣ ዱባይ ከገባች በኋላ በርካታ ኢትዮጵያውያንና የሌሎች አገር ዜጎች ከነበሩበት አንድ ክፍል ውስጥ ለአንድ ቀን ማደሯን ታስታውሳለች፡፡

በቤቱ ውስጥ ንፅህናቸው ያልተጠበቀ፣ ምንም የከተማ ሕይወት የማያውቁ አጋጥመዋት እንደነበር፣ በቤቱ የነበሩ ተቀባዮችም ንፅህና ያልጠበቁትን እየመረጡ በዱቄት ሳሙና ሲያጥቡ እንደነበርም ትናገራለች፡፡

በቤት ውስጥ ከነበሩት ኢትዮጵያውያን በሕገወጥ መንገድ የገቡ እንደነበሩ፣ እሷ ግን በዘመዷ አማካይነት ስለነበር የሄደችው ብዙም ሳትቆይ ወደ አቡዳቢ አቅንታ ከአንዲት መልካም አሠሪ ቤት መቀጠሯን ትገልጻለች፡፡

- Advertisement -

‹‹ኑሮው፣ አካባቢው፣ ሥራው፣ ሁሉ በጣም ደስ የሚል ነበር›› የምትለው ይህች ወጣት፣ በአቡዳቢ ሠርታ፣ ገንዘብ አጠራቅማ ለራሷና ለቤተሰቧ ለመትረፍ ያቀደችው አለመሳካቱን እንዲህ ታስታውሰዋለች፡፡

ከዚህ ስትሄድ ሃያ ዓመት ሊሞላት አካባቢ ነው፡፡ ውጭ ሄዶ የመሥራት ጉጉት ቢኖራትም፣ ይበልጥ ወደዓረብ አገር ሄዳ እንድትሠራ ያነሳሳቻት ዘመድዋ ናት፡፡

በዘመድዋ በኩል የሚላኩ ልብሶች፣ ለቤተሰብ የሚላክ የገንዘብ ድጎማ እሷንም እንድትነሳሳ ተጨማሪ ምክንያት ሆኗል፡፡

አቡዳቢ ደርሳ በጣም ደስተኛ ነበረች፡፡ ከአሠሪዋ ጋር ተስማምታ ብትሠራም፣ የጤናዋ ሁኔታ ከስድስት ወራት በላይ በአቡዳቢ እንድትቀመጥ ዕድል አልሰጠም፡፡ እዛው ለመታከም (ቀዶ ሕክምና) ዕድሉ የነበረ ቢሆንም፣ አሠሪዋ ኃላፊነቱን ወስዳ ለመፈረም ባለመፍቀዷ ወደ አዲስ አበባ ተመልሳለች፡፡

‹‹ዓመታት የወሰደ ሕክምና ተከታትዬና ፀበል ተጠምቄ ጤናዬ ተመልሶ በአንድ ድርጅት ውስጥ በፀኃፊነት ተቀጥሬ እየሠራሁ ነው፤›› የምትለው ሃና፣ ዛሬም ግን ልቧ አቡዳቢ ለመግባት እንደሚሻ ትናገራለች፡፡

ከተሳካላት ተመልሶ ለመሄድ እየሞከረች መሆኑን የምትገልጸው ሃና፣ ‹‹እዛ ትንሽ ጊዜ ከኖርሽ ኢትዮጵያ ተመልሶ መኖር ይከብዳል፡፡ ዕድል አጋጥሞ መልካም ሰዎች ቤት ለተቀጠረ ሰው ኑሮው፣ ክፍያው ሆነ ሁሉ ነገር የተመቸ ነው፤›› ትላለች፡፡

የዓረብ አገርን አኗኗር ባልተመቸ ሁኔታ እየኖረ ተጠርንፎ ኢትዮጵያ የመጣም ቢሆን ደግሞ በሕገወጥ መንገድ የሚሰደደው እዚህ ሥራ በቀላሉ የማያገኝ በመሆኑና ያኛውን አኗኗር ለምዶ እዚህ ያለው ስለማይመቸው እንደሆነም ትናገራለች፡፡

‹‹አኗኗሩ ምን ይገናኛል›› የምትለው ሃና፣ ተሳክቶላቸው በሕጋዊ መንገድ ለሚሄዱ በተሻለ ሁኔታ እየኖሩ ለቤተሰባቸውና ለአገራቸው መጥቀም ይችላሉ ትላለች፡፡

ብዙዎች ዓረብ አገር ሄዶ መሥራትና መለወጥን ሲያስቡ ሕጋዊ ጉዞን ይከተላሉ ወይ? ሲባል ግን፣ የማይከተሉ መሆኑ በተለያዩ ጊዜያት በመንግሥትም ሆነ መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች የቀረቡ ጥናቶች ያሳያሉ፡፡ በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ከዓረብ አገራት ተጠርንፈው ለመመለሳቸው መሠረታዊ ምክንያቱም ይኸው ሕገወጥ ጉዞ ነው፡፡

የማኅበራዊና ሴቶች ጉዳይ ሚኒስቴር እንደሚለውም፣ ዜጎች በሕገ-ወጥ አዘዋዋሪዎች የሐሰት ማማለያ፣ የተሻለ ኑሮና ሥራ ፍለጋ ያላቸውን ጥሪት ሸጠው፣ ተበድረውና ሕይወታቸውን ለአደጋ አጋልጠው ወደ ሳዑዲ ዓረቢያና ሌሎች አገሮች በተለያዩ መንገዶች ዛሬም በሕገወጥ እየተጓዙ ነው፡፡

መንግሥት በሰዎች መነገድ ወንጀልና ሰዎችን በሕገወጥ መንገድ ድንበር ማሻገር ወንጀልን ለመከላከልና የዚህ ወንጀል ሰለባ የሆኑ ዜጎችን መብት ለማስከበርና ተጋላጮችን ለማስተማር የሚያስችሉ የተለያዩ ዕርምጃዎችን ቢወስድም፣ ወንጀሉን ለመግታት የሚያስችሉ እንዲሁም የዜጎችን መብት፣ ደኅንነትና ጥቅም የሚያስከብሩ የሕግ ሥርዓት ቢዘረጋም የሚጠበቀውን ያህል ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለም ሚኒስቴሩ ይገልጻል፡፡

ሕገወጥ ድርጊቱም ከጊዜ ወደ ጊዜ ሥር እየሰደደና መልኩን በመቀየር እየተባባሰ በመምጣቱ ዜጎችን ለአስከፊ የሰብዓዊ መብት ጥሰትና እንግልት እየዳረገ ይገኛል ብሏል።

የተሻለ ሕይወትን በመሻት በሕገወጥ መንገድ ለመሸጋገር በሚደረገው የጉዞ ሒደት በርካታ ዜጎች ለሥቃይ፣ ለእንግልት፣ ለጉልበት ብዝበዛ፣ ለወሲብ ጥቃት፣ እስራት፣ ለአሸባሪና ታጣቂ ቡድኖች መጠቀሚያ፣ ለተለያዩ የአካል ክፍል መሰረቅ፣ ለዘላቂ አካል ጉዳትና ለሞት እየተዳረጉ ሲሆን፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ደግሞ ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ሕፃናትና ሴቶች በብዛት መሰደዳቸውና የዚህ ገፈት ቀማሽ መሆናቸው ሁኔታውን ይበልጥ አስከፊ እንዳደረገውም አክሏል፡፡

በሕገወጥ የሰው ዝውውር መረብና ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ ወደ ሳዑዲ ዓረቢያ የገቡ ዜጎች በገፍ ታስረው፣ በማቆያ ማዕከላት ሥቃይና እንግልት ደርሶባቸዋል ያለው ሚኒስቴሩ፣ በሕጋዊ መንገድ ለረጅም ዓመታት የኖሩና የመኖሪያ ፍቃድ ባለማሳደሳቸው የሚታሰሩ ዜጎችም የዚህ ስቃይ ሰለባ እንደሆኑ አስታውሷል፡፡

እንደ ሚኒስቴሩ፣ ይህን ስቃይ የተረዱ ኢትዮጵያውያን ለወገኖቻቸው ድምፅ ሆነዋል፡፡ መንግሥትም እየተከተለ ካለው ዲፕሎማሲ አኳያ ለጉዳዩ ትኩረት በመስጠት በዜጎች ላይ እየደረሰ ያለውን የመብት ጥሰት ለማስቆም፣ ጉዳዩ ከሚመለከታቸው የሳዑዲ ዓረቢያ ጋር ውይይት በማድረግ ዜጎችን ለአገራቸው እያበቃ ይገኛል፡፡

በሳዑዲ ዓረቢያ እስር ቤቶችና ማቆያ ማዕከላት ከሚገኙ ዜጎች መካከል ከመጋቢት 21 ቀን 2014 ዓ.ም. እስከ መጋቢት 25 ቀን 2015 ዓ.ም. ድረስ ከ130 ሺሕ በላይ ዜጎች መመለሳቸውንና ከቤተሰብ የማቀላቀል ሥራ መከናወኑንም አስታውሷል፡፡

ዜጎችን ወደ አገር የመመለስ ሥራው በሚሠራበት ወቅት ሕገወጥ የሰዎች ዝውውር መቀጠሉን፣ ዛሬም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ኢትዮጵያውያን በኢትዮጵያ ዕርዳታ ወደ አገር በሚመለሱ ወቅት ንብረት ሸጠውና አሽጠው በአሰቃቂው ሕገወጥ የጉዞ መስመር የሚሰደዱ ዜጎች ቁጥር ቀላል እንዳልሆነ ጠቁሟል፡፡

ይንንን አስከፊ ክስተት ለመከላከል መንግሥትና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ከሚሰሩት ሥራ በተጨማሪ ኅብረተሰቡ በመከላከል ሥራ እንዲሳተፍም ሚኒስቴሩ ጥሪ አቅርቧል፡፡

ሕገወጥ ስደትን ለማስቀረትና ግንዛቤ ለመፍጠር የማኅበረሰብ ንቅናቄ መጀመሩ የሚታወስ ሲሆን፣ ከዚህ ጎን ለጎን በአገር ሠርቶ ለመኖር አስቻይ ሁኔታ መፍጠር፣ ራስን ለመለወጥ ጥረት ለሚያደርጉ ሁሉ ዕገዛ ማድረግ፣ ሕጋዊ ጉዞን ማበረታታት፣ ግንዛቤ መፍጠር፣ ብድር ማመቻቸትና ሥልጠና መስጠት፣ ተመላሾችን መደገፍና ወደ ሥራ ማስገባትም ከመንግሥት የሚጠበቁ ናቸው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...