Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -
ማኅበራዊአቤት  ሆስፒታል በግማሽ  ቢሊዮን ብር ባለ 15 ፎቅ ሕንፃ ሊያሠራ ነው

አቤት  ሆስፒታል በግማሽ  ቢሊዮን ብር ባለ 15 ፎቅ ሕንፃ ሊያሠራ ነው

ቀን:

በቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሕክምና ኮሌጅ የአዲስ አበባ በርን፣ ኢመርጀንሲ ኤንድ ትራዋማ (አቤት) ሆስፒታል ከሊዝ ነፃ ባገኘው 8926 ሜትር ካሬ ቦታ ላይ በ500 ሚሊዮን ብር ወጪ ባለ አሥራ አምስት ወለል ሕንፃ ለማሠራት የሚያስችለውን እንቅስቃሴ በማከናወን ላይ ነው፡፡

ከመንግሥት በተመደበው በዚሁ በጀት እስካሁን ባካሄደው እንቅስቃሴ የዲዛይን ሥራ አጠናቆ አማካሪ ድርጅት ቅጥር ያከናወነ ሲሆን፣ ጉዳይ በይበልጥ ከሚመለከተው መንግሥታዊ አካል የግንባታ ፈቃዱ አግኝቷል፡፡ ሕንፃውም የሚሠራው በጉለሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት አዲሱ ገበያ እየተባለ በሚጠራው አካባቢ ነው፡፡

የሕክምና ኮሌጁ የምሕንድስናና ግንባታ ዳይሬክተር አማኑኤል ሕይወት (ኢንጂነር) ለሪፖርተር እንደገለጹት፣ ቦታውን በሊዝ የፈቀደው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ ጽሕፈት ቤት ሲሆን ሕንፃውም ደረጃውን የጠበቀና ዘመናዊነትን የሚላበስ ው፡፡

ሕንፃው ከሚይዛቸው ወለሎች መካከል አራቱ ከምድር በታች ሲሆኑ የቀሩት አሥራ አንዱ ደግሞ ከምድር በላይ የተያያዙ ናቸው፡፡ የሕንፃው መጨረሻ ፎቅ ላይ ለሄሊኮብተር ማሳረፊያ የሚውል ቦታ እንደመቻቸለት፣ ለአስተዳደርና ለልዩ ልዩ ሥራዎች ማከናወኛ የሚውሉ ረቂቅ በርካታ ክፍሎች ያሏቸው ሁለት ብሎኮች ከሕንፃው ጋር ተያይዘው እንደሚገነቡ ነው የተናገሩት፡፡

 ሕንፃው ሲጠናቀቅ ደረጃቸውን የጠበቁ 18 የቀዶ ሕክምናና 40 የማገገሚያ ክፍሎች፣ እንዲሁም ከ700 በላይ አልጋዎች እንደሚኖሩት የገለጹት ዳይሬክተሩ፣ ከዚህም ሌላ ከምድር በታች ከሚገኙት ወለሎች መካከል ሁለቱ ለየት ያሉ አገልግሎቶች እንዲሰጡ ታስቦ መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል፡፡

ከምድር በታች የሚገኙት ወለሎች ለተሽከርካሪዎች ማቆሚያ የሚውሉ ሲሆን፣ በሌላ በኩል በአገሪቱ እንደ ኮቪድ-19 የመሳሰሉ አደገኛ ወረርሽኞች ድንገት ቢከሰቱ ወደ ሕክምና ክፍልነት ያለምንም ችግርና ወጪ በቀላሉ ሊቀየሩ በሚያስችል መልኩ የሚዘጋጁ ይሆናል፡፡ ይህ ዓይነቱም ሁኔታ በኮቪድ-19 ወረርሽኝ ጊዜ ከወረርሽኙ ጋር የተያያዙ ሕክምናዎችን መስጠት የሚቻልባቸውን አዳራሾችና ሕንፃዎች ለመፈለግ የታየው ውጣ ውረድ ወደፊት እንዳይደገም ከወዲሁ ለመከላከል ታስቦ የተደረገ ነው፡፡

‹‹የአዲስ አበባ በርን፣ ኢመርጀንሲ ኤንድ ትራዎማ ሆስፒታል በአማርኛ ‹‹አቤት›› በሚል ምኅጻር ቃል ሲሰየም የቻለው በሰው ሠራሽና በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት ለሚደርስበት ወገን አለሁልህ ብሎ ምላሽ የሚሰጥ ተቋም እንፍጠር ከሚል መሠረተ ሐሳብ በመነሳት ነው፤›› ያሉት ደግሞ የአንጎል፣ ህብለ ሰረሰር፣ ነርቭና ተጓዳኝ ሕመሞች ቀዶ ሕክምና ስፔሻሊስትና የአቤት ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ሀነኒያ ጅምባይ (ዶ/ር) ናቸው፡፡

እንደ ዋና ሥራ አስኪያጁ አባባል፣ አቤት ሆስፒታል በአሁኑ ጊዜ አገልግሎት እየሰጠ ያለው ከግለሰብ በየወሩ ከአራት ሚሊዮን ብር በላይ በተከራየው ባለ አራት ወለል ሕንፃ ውስጥ ነው፡፡ የሆስፒታሉ ሕንፃ ከአገልግሎት ፈላጊዎች መብዛት አንጻር ሲቃኝ ከፍተኛ መጨናነቅን ከመፍጠሩም ባሻገር፣ ምቹ የሥራ ቦታም አይደለም፡፡ ለማሳያ ያህል ከተፈለገ የአጥንት ሕክምና ያለው በአቤትና በአለርት ሆስፒታሎች ሲሆን በአቤት ብቻ ይህንኑ ሕክምና ለማግኘት 800 ታካሚዎች ወረፋ ይዘው በመጠባበቅ ላይ ናቸው፡፡ በዚህም ብቻ ሳይወሰን የወገብ አከርካሪ ሕክምናንም በብቸኝነት ይሰጣል፡፡

ሆስፒታሉ አሁን ባለበት ሁኔታ ከድንገተኛ ጋር ተያይዞ የሚከሰቱ አራት ዓይነት በሽታዎች በማከም ላይ መሆኑን ገልጸው፣ እነርሱም አንጎልና ህብለ ሰረሰር፣ የአጥንት፣ የጅማቶችና የፕላስቲክ ሪኮንስትራክሸን ሰርጀሪዎች፣ እንዲሁም የድንገተኛና የጽኑ ሕመሞች መሆናቸውንም አስረድተዋል፡፡

በየዓመቱ በአማካይ ሃምሳ ሺሕ ለሚሆኑ ታካሚዎች ተገቢውን የሕክምና አገልግሎት እንደሚሰጥ፣ አዲሱ ሕንፃ ተጠናቆ ወደ ሥራ በሚገባበት ጊዜ ግን በዓመት የሚሰጠውን አገልግሎት በእጥፍ ከፍ ያደርገዋል ተብሎ ተስፋ እንደተጣለበት ነው ያመለከቱት፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ለሰው ልጅ መብት መከበር ስናወራ 75 ዓመት ሞላን!

በገነት ዓለሙ ዓለም ስለሰብዓዊ መብቶች ሲያወራ፣ ሲምል፣ ሲገዘት፣ ሲፈጠም፣ ቃል...

ካልተማከለ የካፒታል ገበያ ወደ ዘመናዊና የተደራጀ የሰነደ ሙዓለ ንዋዮች ገበያ

በእሱፈቃድ ተረፈ በአገራችን የካፒታል ገበያ አዋጅ መውጣትን ተከትሎ የተማከለ የሰነደ...

ለማይቀረው ምክክርና ድርድር እንዘጋጅ

በያሲን ባህሩ  የዘመናዊት ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውዝግብ በትንሹ የአንድ ምዕተ ዓመት...

ደንብ አስከባሪዎች ደንብ ያክብሩ!

በአዲስ አበባ ከተማ ደንብ አስከባሪዎች፣ ሌሎች የፀጥታ አካላት፣ እንዲሁም...