Monday, December 11, 2023

የሚዲያ ነፃነት ፈተናዎች በኢትዮጵያ

- Advertisement -spot_img

በብዛት የተነበቡ

ጊዜው አሜሪካና ስፔን በኩባ ለጦርነት የተፋጠጡበት ነው፡፡ እ.ኤ.አ. በ1898 የአሜሪካና የስፓኒሽ ጦርነት በኩባ ከመፈንዳቱ በፊት የኒውዮርክ ጆርናል ጋዜጣ ኤዲተር ዊሊያም ራንዶልፍ ኸርስት፣ ከማንም ቀድሞ የጦርነቱን ሁኔታ ለመዘገብ ወደ ቦታው ሠዓሊ (ካርቶኒስት) ይልካል፡፡ የተላከው ሰው ታዋቂው የሥዕል ባለሙያ ፍሬድሪክ ሬሚንግተን ነበር፡፡

ሬሚንግተን ኩባ ገብቶ ጦርነቱን መጠባበቅ ጀመረ፡፡ ነገር ግን ግጭቱ ሳይጀመር ቆየ፡፡ በዚህ የተሰላቸው ሬሚንግተን ወደ አለቃው መልዕክት ሰደደ፡፡ ‹‹ግጭትም ሆነ ጦርነት የለምና ወደ አገር ቤት ልመለስ?›› ሲልም ጠየቀ፡፡ በዚህ ጊዜ ከአለቃው ኸርስት ያገኘው ምላሽ አስገራሚ ነበር፡፡ ‹‹እዚያው ቆይ፣ አንተ ሥዕልህን አሳምር፡፡ እኔ ጦርነቱን ከዚህ እልክልሃለሁ፤›› ሲል ነበር የመለሰለት፡፡ ይህ የኸርስት ንግግር በጋዜጠኝነት ሙያ እንደ አንድ ጉዳይ (ኬዝ ስተዲ) የሚታይ፣ የሚዲያን ጉልበትና ኃይል ለመግለጽ ጥቅም ላይ የሚውል ሆኖ እስከ ዛሬም የዘለቀ ነው፡፡

ኸርስት እንደተናገረውም ሚዲያን ለአሉታዊ ነገር ለማዋል ከተፈለገ ግጭትና ጦርነት ለመቀስቀስ የማይሳነው መሣሪያ የመሆኑን ያህል፣ ለአዎንታዊ ነገር ከዋለም በርካታ በጎ ሥራዎችን ለማከናወኛነት የሚውል ተፅዕኖ ፈጣሪ መሆኑን  አመላካች ነው፡፡

ሚዲያ ለአንድ አገር (ማኅበረሰብ) የሚጠበቅበትን በጎ ሚና ይወጣ ዘንድ ደግሞ የዘርፉ መኖር ለአገር ግንባታ ገንቢ ሚና እንዲወጣ የሚያስችል ፖሊሲ፣ ሕግና አሠራር መዘርጋት አስፈላጊ እንደሆነ በሰፊው ይወሳል፡፡

በኢትዮጵያ ያለው የሚዲያ ነፃነት ምኅዳር ከዚህ አንፃር መታየት እንዳለበት ብዙዎች ይሞግታሉ፡፡ ሚዲያ በአገር ግንባታ ሒደት እንደ አንዱ ባለድርሻ መሆኑ በቅጡ መታየት ጀምሯል ወይ ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡

ሚዲያ በአገር ግንባታ ሒደት እንደ አንድ ባለድርሻ አካል እየታየ ነው/አይደለም ከሚለው ክርክር ጎን ለጎን ደግሞ፣ በኢትዮጵያ የሚዲያ ምኅዳሩ እየሰፋ/እየጠበበ ነው የሚለው ሙግትም ጋብ ብሎ አያውቅም፡፡ በተለይ ከሰሞኑ በመንግሥት እየተወሰዱ ባሉ ጋዜጠኞችን በቁጥጥር ሥር የማዋል ዕርምጃዎች፣ መንግሥት የሚዲያ ባለሙያዎችን በማሰር የዘርፉን ምኅዳር እያጠበበው መጥቷል የሚል ስሞታ እየቀረበ ነው፡፡

የአራት ኪሎ ዩቲዩብ ሚዲያ መሥራቹ ዳዊት በጋሻው፣ የአማራ ሚዲያ ማዕከል አዘጋጅ ዓባይ ዘውዱ፣ የኢትዮ ሰላም አዘጋጅ ቴዎድሮስ አስፋው፣ የየኛ ሚዲያ ሪፖርተር ገነት አስማማው፣ የነገረ ወልቃይት ሚዲያ አዘጋጅ አሰፋ አዳነ፣ የኢትዮ ንቃት ሚዲያ መሥራችና አዘጋጅ መስከረም አበራን ጨምሮ ሌሎችም የሚዲያ ባለሙያዎች ከሰሞኑ በቁጥጥር ሥር ውለዋል መባሉን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ ነፃነት ምኅዳር አሳሳቢ ደረጃ ላይ ይገኛል የሚል ስሞታ እየቀረበበት ነው፡፡

የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች ማኅበር፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን (ኢሰመኮ) ጨምሮ በርካታ ዓለም አቀፍ ተቋማት በኢትዮጵያ በጋዜጠኞች ላይ ተገቢ ያልሆነ ዕርምጃ እየተወሰደ ነው በማለት ስሞታ እያሰሙ ነው፡፡ ሒዩማን ራይትስ ዎች፣ አምነስቲ ኢንተርናሽናል፣ እንዲሁም ሲፒጄ የመሳሰሉ ተቋማት በሚዲያ ወንጀል መከላከል ስም በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኃንና በጋዜጠኞች ላይ አፈና እየተፈጸመ ነው ሲሉ ወቀሳ እያቀረቡ ነው፡፡ ሌሎች ወገኖችም ከሰሞኑ እየተወሰዱ ያሉ ዕርምጃዎችን ተከትሎ፣ የኢትዮጵያ ሚዲያ ነፃነት ምኅዳር ከዕለት ወደ ዕለት እየጠበበና ካለፈው አገዛዝም እየባሰበት ነው የሚሉ ውግዘቶች እያቀረቡ ነው፡፡

ይህን በሚመለከት የተጠየቁት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የጋዜጠኝነትና ተግባቦት ትምህርት ክፍል መምህሩ ጌታቸው ድንቁ (ዶ/ር)፣ ጉዳዩ አሳሳቢ ነው ይላሉ፡፡ ‹‹የሚዲያ ምኅዳሩ ካለፈውም የባሰ ሆኗል ወደሚል ድምዳሜ ላይ ለመድረስ መቸኮል ተገቢ አይደለም፡፡ ይሁን እንጂ እየተወሰዱ ባሉ ዕርምጃዎች ሲሆኑ የሚታዩ አንዳንድ ነገሮች፣ የሚዲያ ምኅዳሩን መጥበብ አመላካች ሊሆኑ ይችላሉ፤›› ሲሉ ያስረዳሉ፡፡

ለዚህ ማሳያ ሊሆኑ ይችላሉ የሚሏቸውን ነጥቦች ሲያሳዩም፣ ‹‹አንደኛው እስሮቹ አሻሚ መሆናቸው፣ ሁለተኛው ለሕዝቡ ግልጽ አለመሆናቸው፣ በአጠቃላይ የታሰሩት ሰዎች የታሰሩባቸው ጉዳዮችም ሆነ የታሰሩባቸው መንገዶች ግልጽ አለመሆኑ ያሳስባል፡፡ የእስር ሁኔታው የሕግ አግባብን (Due Process of Law) የተከተለ ሲሆን አለመታየቱም፣ በዘርፉ የተሰማሩትን በአገር ቤትም ሆነ በውጭ ያሉትን የሚያሳስብ ነው፤›› በማለት ያክላሉ፡፡

በኢትዮጵያ በመገናኛ ብዙኃን ተቋማት ላይ እየተወሰደ ያለው ዕርምጃ አሳሳቢ ነው የሚሉት ዓለም አቀፍ ተቋማትና የተለያዩ ምሁራን ብቻ ሳይሆኑ፣ እንደ ኢሰመኮ ያሉ የመንግሥት ተቋማትም ጭምር ናቸው፡፡ ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. መግለጫ ያወጣው ኢሰመኮ፣ ‹‹በሚዲያ ጥፋት የተጠረጠሩ ታሳሪዎች በሙሉ ያለ ምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስር ሊለቀቁ ይገባል፤›› ሲል ጠይቋል፡፡

ተቋሙ በዚህ መግለጫው፣ ‹‹መንግሥት ወንጀልን የመከላከል፣ የመመርመር፣ ተጠያቂነትን የማረጋገጥ ኃላፊነት ያለበት ቢሆንም ነገር ግን በፖለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና አባላት፣ በሚዲያ አባላትና በማኅበረሰብ አንቂዎች ላይ የሚያተኩር እስር ከማካሄድ ሊቆጠብ ይገባል፤›› ሲል ነው የጠየቀው፡፡

የተለያዩ ወገኖች የሚዲያ ባለሙያዎች እስራት፣ እንዲሁም በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚካሄድ ጫናን በአሳሳቢነት ቢያነሱትም መንግሥት ግን ለዚህ ጉዳይ ፍፁም የሚቃረን ምላሽ ነው የሚሰጠው፡፡ በዚህ ጉዳይ የተጠየቁ ስማቸው እንዳይጠቀስ የፈለጉ አንድ የመገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን የሥራ ኃላፊ፣ ‹‹በኢትዮጵያ ከሚዲያ ሙያ ጋር በተያያዘ የታሰረ ሰው የለም፤›› ብለዋል፡፡

‹‹መንግሥት በማያውቃቸውና ሕጋዊ ዕውቅናም በሌላቸው ዩቲዩቦችና ማኅበራዊ ሚዲያዎች የሚሠሩ ግለሰቦች በጋዜጠኝነት ነው የታሰሩት ሊባል አይችልም፤›› ሲሉም ይከራከራሉ፡፡ ኃላፊነት በሚሰማቸውና ሕጋዊ ፈቃድ ባላቸው ሚዲያዎች ላይ የሚሠራ ጋዜጠኛ አልታሰረም በማለት ነው ኃላፊው የተከራከሩት፡፡

ኃላፊው ከዚህ በተጨማሪም፣ ‹‹አክቲቭዝምና ጋዜጠኝነትን ቀላቅለው የፖለቲካ ዓላማቸውን በሚዲያ ሙያ ለማስፈጸም የሚንቀሳቀሱ አሉ፤›› በማለት ነው የተናገሩት፡፡ ከዚህ ቀደም በኢሳትና ፋና ቴሌቪዥን ጋዜጠኞች ላይ የሕግ ጥሰት ሲፈጸም፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን መብታቸውን ለማስከበር ጥረት አድርጓል፡፡ ከሰሞኑ ደግሞ የኢሳት ቴሌቭዥን የሕግ ጥሰት እየፈጸመ ነው ብሉ በማመኑ የመጨረሻ የጽሑፍ ማስጠንቀቂያ ጽፏል ሲሉ የተናገሩት የሥራ ኃላፊው፣ ሕጋዊ ከሆኑና ኃላፊነት ከሚሰማቸው ሚዲያዎች ጋር ባለሥልጣኑ መልካም ግንኙነት እንዳለው አክለዋል፡፡

ከሰሞኑ በመንግሥት መገናኛ ብዙኃኖች በተደጋጋሚ አስተያየቶች ሲሰጡ የሰነበቱት የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ዋና ዳይሬክተር አቶ መሐመድ ኢድሪስ በኢትዮጵያ ሚዛናዊነት የጎደላቸው፣ ሕዝብን ከሕዝብ ለማጋጨት የሚሠሩና አሉታዊ ግንዛቤን የሚፈጥሩ የሚዲያ ሰዎችና ተቋማት መኖራቸውን ተናግረው ነበር፡፡

አቶ መሐመድ በሚዲያ ነፃነት ስም የሚደረግ ከተጠያቂነት የማፈንገጥ እንቅስቃሴ መኖሩን የገለጹ ሲሆን፣ ‹‹ሚዲያ ኃላፊነት ነው፣ ትክክለኛው ነፃነት የሚወለደው ኃላፊነትን በመወጣት ነው፡፡ ነፃነት ያለ ተጠያቂነት ትርጉም የለውም፤›› በማለት መናገራቸው ተዘግቦ ነበር፡፡

አቶ መሐመድ ይህን ሲሉም መንግሥት የሚዲያ ነፃነት እንዲጠበቅ ቁርጠኛ መሆኑን አውስተዋል፡፡ ይሁን እንጂ ከዚሁ ጎን ለጎን ሚዲያዎችም የራሳቸውን ግዴታ መወጣት አለባቸው ብለዋል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከኤዲቶሪያል ፖሊሲ በተጨማሪ ራሳቸውን በራሳቸው መቆጣጠሪያ መንገድ ሚዲያዎች መፍጠር እንዳለባቸው ተናግረው ነበር፡፡

የባለሥልጣኑ ዋና ዳይሬክተር ይህን ይበሉ እንጂ በኢትዮጵያ የሚዲያ ዘርፍ ራሱን በራሱ ተቆጣጣሪ (Self Governed) እንዲሆን የተደረጉ ጥረቶች በሙሉ እንዳልተሳኩ ነው የሚነገረው፡፡ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤትን በኢትዮጵያ መፍጠር ቢቻልም አቅም አለመገንባቱን መንግሥት ይናገራል፡፡

የግሉ መገናኛ ብዙኃን ምክር ቤት አቅም እስኪያደራጅ ተብሎ በመንግሥት በኩል፣ የኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ባለሥልጣን ቦርድ ተመሥርቶ ነበር፡፡ ቦርዱ ሲመሠረት የመንግሥት ባለሥልጣናትና የፖለቲካ ሰዎች በአባልነት እንዲገቡ መደረጉ ሕግን የጣሰና የቦርዱን ገለልተኝነትም ጥያቄ ውስጥ የከተተ በሚል ብዙ ቢተችም የተወሰደ ማሻሻያ አልነበረም፡፡ ቦርዱ በሒደት እንደታየው ከሆነ ይሸፍናል የተባለውን ክፍተት አለመሙላቱ፣ እንዲሁም እስካሁን የሠራው ሥራ አለመታወቁ ነው የሚነገረው፡፡ ይህ ሁኔታ ደግሞ በኢትዮጵያ መገናኛ ብዙኃን ራሳቸውን የሚቆጣጠሩበትን ተቋማዊ አሠራር ለመገንባት የተደረገው ሙከራ ፍሬ አለማፍራቱን አመላካች መሆኑ ይነገራል፡፡

አሁን በኢትዮጵያ ለመገናኛ ብዙኃንና ለጋዜጠኞች ነፃነት ከለላ ከማድረግ ይልቅ፣ ዘርፉ ባለቤትና ጠባቂ የሌለው ሆኗል የሚለው ወቀሳ ጎልቶ እየተሰማ ነው፡፡

የጋዜጠኝነት መምህሩ ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ‹‹የዘርፉ ህልውና በአስፈጻሚው አካል ፍላጎት ላይ የተመሠረተ እንዳይሆን ሥጋት አለኝ፤›› ሲሉ ነው የሚናገሩት፡፡ የሚዲያ ነፃነት ጉዳይ የፖለቲካ ሥርዓቱ ሲፈልግ ብቻ ለቀቅ የሚያደርገው ሳይፈልግ ደግሞ ሸብቦ የሚያስረው ጉዳይ መሆን እንደሌለበት የሚያነሱት ምሁሩ፣ ይህ ከሆነ ደግሞ አገሪቱ በዓለም አቀፍ ደረጃ ዋጋ እንደሚያስከፍላት ሥጋታቸውን ያስረዳሉ፡፡

በለውጡ ማግሥት በነበሩት ሁለት ዓመታት፣ ‹‹በፖሊሲም ሆነ በሕግ የሚዲያ ነፃነት ምኅዳሩን ለማስፋፋት እጅግ አበረታች እንቅስቃሴዎች ታይተዋል፤›› ሲሉ ይናገራሉ፡፡ በሒደት ግን ይህ እንቅስቃሴ ቀዝቅዞ አሁን የሚዲያ ምኅዳሩ አሳሳቢ ወደሆነ ደረጃ መውረዱን ይጠቅሳሉ፡፡

‹‹ለዚህ የመንግሥት ተቋማት የታሰሩት ጋዜጠኞች በደረቅ ወንጀል የተያዙ ናቸው፣ ጋዜጠኞች አይደሉም እንዲሁም በጋዜጠኝነት ስም የአክቲቪዝም ሥራ ይሠራሉ የሚሉ የመከላከያ አመክንዮዎች ይሰማሉ፤›› የሚሉት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ይህ ግን መንግሥትን ከመጠየቅ እንደማያድነው ያመለክታል ሲሉ ያክላሉ፡፡

‹‹መንግሥት እንደሚለው ቢሆን እንኳ ሰዎቹ የእስር አያያዛቸውም ሆነ የፍርድ ሒደታቸው ሕግን የተከተለ ሲሆን ቢታይ የተሻለ ነው፤›› በማለትም ያስረዳሉ፡፡

ኢትዮጵያ በሚዲያ ነፃነት ምኅዳር መሻሻል በዓለም አቀፍ ደረጃ ስትደነቅና ዕውቅና ተሰጥቷት፣ የፕሬስ ቀንን እንድታስተናግድ ዕድል ሲሰጣት የታየበት አጋጣሚ የቅርብ ጊዜ ትዝታ እንደነበር ያስታውሳሉ፡፡

አሁን ደግሞ ነገሮች ተለውጠው በሚዲያ ነፃነት ምኅዳር መጥበብ ተወቃሽ እየሆነች መምጣቷን ያስረዳሉ፡፡ ‹‹እነዚህ ዓለም አቀፍ ሪፖርቶች የታሪክ አካል ሆነው ከመቀመጣቸው ባለፈ በየወቅቱ አገሪቱ ለሚኖራት ዓለም አቀፍ ዲፕሎማሲ መሠረት ሆነው ያገለግላሉና ሪፖርቶቹን አቃሎ መመለከቱ የዋህነት ነው፤›› ሲሉ ያስገነዝባሉ፡፡

በቅርቡ በፓርላማ ማብራሪያ የሰጡት ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ አህመድ (ዶ/ር)፣ በሕገወጥ ድርጊቶች ላይ ተሰማርተዋል ባሏቸው የመገናኛ ብዙኃን ላይ ባለሥልጣኑ ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰዱን እንዲያጠናክር ማሳሰባቸውን ያስታወሱት ጌታቸው (ዶ/ር)፣ ይህ አስፈጻሚው አካል ተመጣጣኝ ያልሆነ ጫና በሚዲያዎች ላይ እንዲያሳድር የሚጋብዝ መሆኑን ገልጸዋል፡፡  

spot_img
- Advertisement -

ትኩስ ጽሑፎች

ተዛማጅ ጽሑፎች

- Advertisement -
- Advertisement -