Wednesday, December 6, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

ኢትዮጵያን ጨምሮ ሌሎች የአፍሪካ አገሮች ተስፋ ከጣሉባቸው ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሻቱትን እንዳላገኙ ያመላከተው ጥናት

ተዛማጅ ፅሁፎች

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በአፍሪካ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች (ኢንዱስትሪ ፓርኮች) ወደ ሥራ ገብተዋል፣ ቁጥራቸውም ተበራክቷል፡፡ እነዚህ ልዩ ዞኖች የብሔራዊ ኢንዱስትሪ ፖሊሲዎች ነፃ የንግድ ሕጎች የጀርባ አጥንት ተደርገው የሚታሰቡ ናቸው፡፡ ይህ እንዳለ ሆኖ ግን ውጤታማነታቸው ውስን እንደሆነና የአብዛኞቹ እንቅስቃሴም ከሚጠበቅባቸው ወይም ከተለሙት በታች ስለመሆኑ ይሰማል፡፡

በተለይም በአፍሪካ የልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች ቁጥር በከፍተኛ ሁኔታ ቢያብብም የታሰበውን ኢንዱስትሪ ኢኮኖሚና የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት እንዲሁም የሥራ ዕድልን ለማሳካት አልተቻሉም የሚል ሐሳብ ሲሰነዘር ይደመጣል፡፡ 

ለዚህ ሐሳብ ደጋፊ የሚሆነው ከሰሞኑ በኤኮፊን ኤጀንሲ ድረገፅ ይፋ የተደረገው እ.ኤ.አ. በታኅሳስ ወር መጨረሻ በሴኔጋል ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ይፋ የተደረገው የጥናት ውጤት ነው፡፡

በሪፖርቱ እንደተመላከተው በአፍሪካ ውስጥ በ37 የተለያዩ አገሮች 237 የሚደርሱ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች (ኢንዱስትሪ ቀጣናዎች) ይገኛሉ፡፡ ከእነዚህም ውስጥ 61 የሚሆኑት በኬንያ፣ 38 በናይጄሪያ፣ 18 በኢትዮጵያ፣ አሥር የሚሆኑት በግብፅ፣ ዘጠኝ በካሜሮንና በሌሎች የአፍሪካ አገሮች በመገንባት ሒደት ላይ የሚገኙ ናቸው።

በአገራቱ ከሚገኙት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ውስጥ 89 በመቶ የሚሆኑት የቅይጥ ዘርፍ ዞኖች ሲሆኑ፣ እነዚህም የግብርና ምርት ማቀነባበሪያ (የአግሮ ቢዝነስ)፣ የመገልገያ መሣሪያዎችና ዕቃዎች፣ ፋርማሲዩቱካልስና ሌሎችን ያካተቱ ናቸው፡፡ 

ይህም ሆኖ በኢትዮጵያ የሚገኘው የሐዋሳ ጨርቃ ጨርቅ ኢንዱስትሪ ፓርክ፣ በጋቦን የንኮክ እንጨት ኢንዱስትሪ ፓርክ እንዲሁም በሞሮኮ ታንግየር ሜድና ኬንትራ የሚገኘው የአውቶሞቢልንና ኤሮኖቲካል ኢንዱስትሪ ፓርክ ለወጭ የኢንዱስትሪ ዘርፍ/አገልግሎት ተነድፈው ትኩረታቸውን እዚያ ላይ አድርገው የሚንቀሳቀሱ መሆናቸው ተመላክቷል፡፡

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከሚገነቡበት አካባቢያዊ አቀማመጥ አንስቶ ብዙውን ጊዜ በድንበር አካባቢ የሚገነቡ፣ ለአልሚው የታክስ ማበረታቻ የሚቀርብባቸው፣ አሊያም ታክስ የሚቀንስባቸውና አለፍ ሲልም ከታክስ ነፃ ዕድል የሚፈቀድላቸው ናቸው፡፡ በሌላ በኩልም ቀለል ያለ የአስተዳደራዊ አገልግሎቶች የተመቻቸላቸው ሥፍራዎች መሆናቸው በጥናቱ ተመላክቷል። በተለይም በቻይና፣ ደቡብ ኮሪያ፣ ሆንግኮንግና ሲንጋፖር ያሉ ግዙፍ ኩባንያዎች ወደ እነዚህ የአፍሪካ ኢንደስትሪ ፓርኮች በመትመም አገራቱ በኢኮኖሚ እንዲመነጠቁ በማድረግ ረገድ አስተዋጽኦዋቸው በጉልህ የሚጠቀስ ነው፡፡ 

ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች እ.ኤ.አ. በ1980ዎቹ የቻይና የወደብ ከተሞች በሆኑት ዣንግዡና ሼንዢያን እንደተጀመረ፣ ይህ መሆኑ ደግሞ የአገሪቱን መካከለኛ ሥርወ መንግሥት መዋቅራዊ በሆነ መንገድ የተለያየ የኢኮኖሚ ስብጥር እንዲኖረው፣ ለኤክስፖርት የሚመረት ሸቀጦችን እንዲጨምር ስለማድረጉ ይነገርለታል፡፡ 

እንደ ዓለም ባንክ መረጃ ከሆነ ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በቻይና ውስጥ የሚገኙት ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ከአገሪቱ ጥቅል ምርት 22 በመቶ የሚሆነውን፣ ከውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንት 46 በመቶ የሚደርሰውን እንዲሁም ከኤክስፖርት ድርሻ 60 በመቶ የሚሆነውን ይሸፍናሉ፡፡ በተጨማሪም ከ30 ሚሊዮን በላይ የሥራ ዕድል በመፍጠር የአገሪቱን የኢንዱስትሪያዊነት ጉዞ፣ ዘመናዊ የግብርና ሥርዓት፣ ከተማን ከማስፋፋት ባሻገር የቴክኖሎጂ ሽግግር እንዲሰርፅ በማድረግ የቴክኒክ ዕውቀትን ብሎም የአመራር ክህሎትን እንዲፋፋም ስለማድረጋቸው በስፋት ይነሳል፡፡ 

ነገር ግን በአፍሪካ አገሮች፣ በተለይም እ.ኤ.አ. ከ2015 እስከ 2020 ባለው ጊዜ ውስጥ የተገነቡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የኢንዱስትሪ ኢኮኖሚውን ከማሳደግ አንጻር በብዙ ርቀት ላይ እንደሚገኙ ጥናቱ ያሳያል፡፡ 

ከላይ የተገለጸው እንደተጠበቀ ሆኖ በአፍሪካ እንደ ሞሮኮ፣ ኢትዮጵያ፣ ሞሪሽየስና ጂቡቲ ባሉ አገሮች አበረታች ውጤቶች ስለመገኘታቸው ይጠቀሳል፡፡ እነዚህን የጥቂት አገሮች ውጤት ወደ ጎን በመተው የአኅጉሪቱን ልዩ ኢኮኖሚ ዞኖች አፈጻጸም ከሌሎች እስያና የላቲን አሜሪካ ጋር ሲመሳከር ዝግመታዊ (ዝቅተኛ) ደረጃ ላይ አንደሚገኝ ጥናቱ ያመለክታል። በእስያና ላቲን አሜሪካ የሚገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ፣ የሥራ ዕድል በመፍጠርና ኢንዱስትሪን በማሳደግ ረገድ ቁልፍ ሚና የተጫወቱ ናቸው፡፡ 

በጂቡቲ 48 በመቶ ለሚሆነው ዜጋ የሥራ ዕድል ከመፍጠር ውጪ በሌሎች የአፍሪካ አገሮች የሥራ ዕድል በመፍጠር ረገድ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖቹ(በተለይም ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ) ያላቸው አስተዋጽኦ ዝቅተኛ የሚባልና በአማካይ ሲታይም ከአምስት በመቶ በታች መሆኑን ያስረዳል፡፡ 

በተመረጡ 12 የአፍሪካ አገሮች ማለትም በአንጎላ፣ ጂቡቲ፣ ግብፅ፣ ኢትዮጵያ፣ ጋና፣ ኬንያ፣ ሞሮኮ፣ ሩዋንዳ፣ ሴኔጋል፣ ደቡብ አፍሪካ፣ ታንዛኒያና ቶጎ ላይ በተደረገ ጥናት፣ በአንድ የኢንዱስትሪ ፓርክ በአማካይ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ቁጥር ከ1,000 እስከ 10,000 የሚደርስ ነው፡፡ 

ከዚህም በመነሳት በአንድ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ውስጥ የሚፈጠረው የሥራ ዕድል ውስን መሆኑን ያመለከተው ጥናቱ፣ በዚህ ዙሪያ በንፅፅር በርካታ የሥራ ዕድል ፈጥረዋል ተብለው የሚጠቀሱት በሞሮኮ የሚገኘው ታንማኖር ሜድ (ለ80,000 ሺሕ) ዜጎች እንዲሁም የግብፁ መንግሥታዊ ልዩ ነፃ ቀጣና የሆነው (ለ74,000 ሺሕ) መሆናቸውን ያሳያል፡፡ 

የውጭ ቀጥተኛ ኢንቨስትመንት በመሳብ ረገድ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች መጠነኛ/መካከለኛ አፈጻጸም ያላቸው እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡ ከእነዚህም ውስጥ ሞሮኮና ኢትዮጵያ የተሻለ አፈጻጸም የታየባቸው መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል፡፡ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች በመገንባታቸው ወደ ኢትዮጵያ የሚገባው ኢንቨስትመንት እ.ኤ.አ ከ2010 ጀምሮ በየዓመቱ የ50 በመቶ ዕድገት እያስመዘገበ በ2017 አራት ቢሊዮን ዶላር መድረሱን ጥናቱ አወንታዊ ብሎታል። 

በሞሮኮ የሚገኘው ታንግኖር ሜድ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን በመሳብ ረገድ እንዲሁም ሀብት እንዲፈጠር በማስቻል ስሙ በግንባር ቀደምትነት የተነሳ ሲሆን፣ በቅፅር ግቢው በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ ኩባንያዎች መያዙም ተጠቅሷል። ይህ የግል ኢንቨስትመንት ስድስት ነጥብ ሁለት ቢሊዮን ዶላር ኢንቨስትመንትን የያዘ ሲሆን፣ ዓመታዊ ሽያጩም 8.7 ቢሊዮን ዶላር እንደሆነ ይነገርለታል፡፡ 

በዓመት ጊዜ ውስጥ አምርቶ ለገበያ የሚያቀርባቸው መኪኖች ከአንድ ቢሊዮን ዶላር በላይ ገቢ የሚያስገኙ እንደሆነ የሚነገርለት የሞሮኮው ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ከአገሪቱ የወጪ ንግድ 30 ከመቶ የሚሆነውን የሚሸፍን ነው፡፡ 

በጥናቱ ከተለዩ ጉዳዮች ውስጥ በአፍሪካ ውስጥ የሚገኙ የኢኮኖሚ ዞኖች ለባህር ቅርብ ባለመሆናቸው በባህር ትራንስፖርት አማካይነት የሚደረግን የግብይት አቅርቦት ትስስር መፍጠር እንዳልቻሉ እንዲሁም በከፍተኛ የኃይል (ኢነርጂ) ወጪ እና ሌሎች የአስተዳደር ችግሮች ሳቢያ ውጥናቸው እንዳይሳካ ሆኗል፡፡  

እነዚህ ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖችና ኢንደስትሪ ፓርኮች የተለያዩ ማበረታቻዎችን አግኝተው የሚያመርቷቸው ምርቶች ዋጋ በመደበኛ ኢንዱስትሪዎች ተመርተው ከሚቀርቡ ተመሳሳይ ምርቶች ዋጋ ጋር ተቀራራቢ በመሆኑ እንደ ኤኮዋስ (ECOWAS)፣ የዓረብ ነፃ የንግድ ቀጣና፣ ዋኤሙ (WAEMU) ከመሰሉ የአኅጉሪቱ ቀጣናዊ ገበያዎች ዕድል እየነፈጓቸው መሆኑን ጥናቱ ያስረዳል።

ጥናቱ በማጠቃለያው ካመላከታቸው ጉዳዮች ውስጥ በእነዚህ ዞኖች ውስጥ የሚመረቱ ምርቶች በአፍሪካ ነፃ የንግድ ቀጣና (AFCTA) ተጨማሪ የመገለል ዕገዳ ሳይጣልባቸው ምርቶቻቸው እንደሚያስገቡ በሚሰጠው ማረጋገጫ ላይ ጥልቀት ያለው ውይይት ሊደረግ እንደሚገባ ይገኝበታል፡፡

የኢትዮጵያ መንግሥት ለመጀመርያ ጊዜ በዓለም ገበያ (በዩሮ ቦንድ) አንድ ቢሊዮን ዶላር የዕዳ ሰነድ ለሽያጭ በማቅረብ የሰበሰበውን የውጭ ምንዛሪ ካፒታል እንዲሁም ከዓለም ባንክ ያገኛቸውን ብድሮች በመጠቀም በተለያዩ የአገሪቱ አካባቢዎች ኢንዱስትሪ ፓርኮችን በመገንባት ጥቅም ላይ እንዲውሉ ማድረጉ ይታወቃል።  ነገር ግን ኢንደስትሪ ፓርኮቹ ያስገኙት ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ውስን ወይም ከታሰበው በእጅጉ የወረደ በመሆኑ መንግሥት ለኢንዱስትሪ ፓርኮች ግንባታ በዩሮ ቦንድ የተበደረውን አንድ ቢሊዮን ዶላር ተዝናንቶ ለመመለስ እንኳን አላስቻሉትም። በመሆኑም መንግሥት በቀጣዩ ዓመት ሙሉ በሙሉ መከፈል ያለበት ይህ ብድር የመክፈያ ጊዜው እንዲራዘምለት በመደራደር ላይ ይገኛል።

ኢንዱስትሪ ፓርኮቹ በአዲስ አበባ፣ አዳማ፣ ሐዋሳ፣ ኮምቦልቻ፣ ባህር ዳር፣ ድሬዳዋ፣ ደብረ ብርሃን፣ ጅማ፣ ሰመራና መቀሌን በመሳሰሉ ከተሞች ተቋቋመው አገልግሎት መስጠት ከጀመሩ ዓመታት ተቆጥረዋል፡፡

በኢትዮጵያ ከኢንዱስትሪ ፓርኮች ባሻገር የልዩ ኢኮኖሚ ዞን በማደራጀት አለማቀፍ የንግድ ትስስርን ለማጠናከር እየተሰራ መሆኑን የሚታወቅ ነው፡፡

የኢንዱስትሪ ፓርኮች የአገርን ኢኮኖሚ ከመደገፍ አኳያ ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከቱ የሚገኙ መሠረተ ልማቶች እንደሆኑ ይጠቀሳል፡፡ መንግሥትም ኢትዮጵያን የኢንዱስትሪ ኮሪደር ለማድረግ ከሰራቸው ተግባራት ውስጥ ከላይ እንደተጠቀሰው በመንግሥት አሥራ ሦስት፣ በግል ስድስት፣ በክልሎች ደግሞ ሦስት በማኑፋክቸሪንግና ላኪነት ዘርፍ የተሰማሩ ኢንዱስትሪ ፓርኮች መገንባታቸው ይገለጻል፡፡

እንደሚታወቀው በኮቪድ-19 ወረርሽኝና በሰሜን ኢትዮጵያ በነበረው ጦርነት በኢትዮ የተገነቡ የኢንዱስትሪ ፓርኮችንና እንዲሁም ወደ ፓርኮቹ የሚደረገውን ኢንቨስትመንት ፍሰት እንዳቀዛቀዘው ሲገለፅ የቆየ ሲሆን፣ ሆኖም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት ለመፍታት ከተደረገው የሰላም ስምምነቱ በኋላ ነገሮች በመሻሻላቸው ወደ ኢንዱስትሪ ፓርኮች የሚገቡ የአገር ውስጥና የውጭ አገር ድርጅቶች ቁጥር እየጨመረ መሆኑን የኢንዱስትሪ ፓርኮች ኮርፖሬሽን አስታውቋል፡፡

የኢንቨስትመንት ኮሚሽን በአገሪቱ ያሉትንና በቀጣይ የሚገነቡትን የኢንደስትሪ ፓርኮች በልዩ ሁኔታ ለማስተዳደር በማለም ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ረቂቅ አዋጅ ያሰናዳ ሲሆን፣ በረቂቁ ላይም ባለፈው ኅዳር ወር አጋማሽ ከተለያዩ የመንግሥት ተቋማት ከተውጣጡ ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት አድርጎ ነበር። በውይይቱ ወቅትም ልዩ የኢኮኖሚ ዞኖች ለኢንቨስትመንት ምቹ ሁኔታ በሚፈጥሩ ፖሊሲዎች፣ ንግድን በሚያሳልጡ አቅርቦቶች፣ መሰረተ ልማቶችና አገልግሎቶች የተደገፈ እንዲሆኑና የአንድ ማዕከል አገልግሎትን ጨምሮ ልዩ ማበረታቻዎች እንደሚቀርብላቸው ተገልጿል። ረቂቅ አዋጁ፣ ልዩ የኢኮኖሚ ዞን ወይም ኢንዱስትሪ ፓርኮች፣ ነፃ የንግድና ሎጂስቲክስ ቀጣናዎች፣ የሳይንስና የአገልግሎት ፓርኮች፣ የግብርናና እንስሳትና ሌሎች ኢንቨስትመንቶችን ሁሉንም ወይም አንዱን ይዞ የሚደራጅ የተለየ አካባቢ መሆኑ ረቂቅ አዋጁ ያትታል ተብሏል።

በመዘጋጀት ላይ ያለው የልዩ ኢኮኖሚ ቀጣና የኢንዱስትሪ ፓርኮችን አሰራር ይበልጥ በማሻሻል ኢትዮጵያ ቀጣናዊና ዓለም አቀፋዊ የንግድና የኢንቨስትመንት ተሳትፎዋ እንዲያድግ ያግዛል እየተባለም ይገኛል፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች