Monday, December 11, 2023
- Advertisement -
- Advertisement -

‹‹ንግድም ሆነ ኢንዱስትሪ የሚጠቅሙት አገርን እንደሆነ እየታወቀ ኢንዱስትሪን ያገለለ ረቂቅ አዋጅ በመዘጋጀቱ በእጅጉ አዝነናል›› አቶ አበባየሁ ግርማ፣ የአገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት

አወዛጋቢው የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ለ20 ዓመታት ሥራ ላይ ቆይቷል፡፡ ይህ በተለያዩ ወገኖች ቅሬታ ሲቀርብበት የነበረው አዋጅ እንዲሻሻል በቀረበው ሐሳብ መሠረት ለዓመታት ጥረቶች ሲደረጉ እንደነበርም ይታወሳል፡፡ በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት አዋጁን ለማሻሻል በንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከዚያም በግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በኩል ኮሚቴ ተቋቁሞ የተለያዩ ረቂቆች ቢቀርቡም ረቂቆቹን ለማፅደቅ አልተቻለም፡፡ ከዚህ ቀደም የመጨረሻ ነው የተባለው ረቂቅ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት ‹‹የንግድ ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ›› ተብሎ ተሰናድቶ ብዙዎች ተስማምተውበት ነበር፡፡ በቅርቡ የወጣው ረቂቅ አዋጅ ግን ከቀደመው ስምምነት ውጪ የንግድ ዘርፉን ብቻ ይዞ ‹‹የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ›› በሚል ተዘጋጅቷል፡፡ ይህም የኢንዱስትሪ ዘርፉን ያገለለና በነባሩ አዋጅ ‹‹ዘርፍ›› በሚል መጠሪያ የሚጠሩ ተቋማትን በዚህ አዋጅ እንዳይካተቱ አድርጓል በሚል ተቃውሞ እየቀረበበት ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ አሁን ባለው ይዘቱ መፅደቅ የለበትም በሚል ጠንከር ያለ ተቃውሞ እያቀረቡ ያሉት፣ በየደረጃው ያሉ የዘርፍ ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ ረቂቁ በከተማ ንግድ ምክር ቤቶችም ቅሬታ እየቀረበበት ነው፡፡ ረቂቅ አዋጁ መፅደቅ የለበትም በሚል እየሞገተ ያለውን የአገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ አበባየሁ ግርማን ዳዊት ታዬ አነጋግሯቸዋል፡፡ አቶ አበባየሁ ከአገር አቀፍ የዘርፍ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትነት ባሻገር፣ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ናቸው፡፡ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የቦርድ አባል ሆነው እያገለገሉ ሲሆን፣ ከእሳቸው ጋር የተደረገው ቃለ ምልልስ እንደሚከተለው ቀርቧል፡፡

ሪፖርተር፡- የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት የ20 ዓመታት እንቅስቃሴውን ቢገልጹልኝ፡፡ እንወክለዋለን የምትሉትን የአምራች ዘርፍ ምን ያህል አገልግለነዋል ብላችሁ ታምናላችሁ?

አቶ አበባየሁ፡- የዘርፉ ምክር ቤት በአዋጅ 341/95 ከተቋቋመ ጀምሮ በርካታ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል፡፡ እስከ 2000 ዓ.ም. ድረስ ብዙም አባል አልነበረውም፡፡ ስለዚህ በመጀመርያዎቹ አምስት ዓመታት ትልቁ ችግሩ የገንዘብ እጥረት ነበር፡፡ ይህንን ችግር ለመቅረፍ አባላቱን በማሰባሰብ ያደረገው ጥረት ተሳክቶለት የተቋቋመለትን ዓላማ ለማሳካት እየተራመደ ነው፡፡ ከዚያ በኋላ ዘርፍ የምንለው ወይም የኢንዱስትሪውን ዘርፍ እንደ ቀኝ እጅ ሆኖ ሲያገለግል የቆየ ነው፡፡ አደረጃጀቱ እየተጠናከረ ሲመጣ በተለይ መንግሥት ባደራጀው መዋቅር ውስጥ አነስተኛና ጥቃቅን አምራቾችን በማሰባሰብና አባል በማድረግ፣ አቅም እንዲያገኙ ከሥልጠና ጀምሮ የተለያዩ ገበያ የማፈላለግ ሥራዎች ተሠርተዋል፡፡ ላኪዎችን ውጭ አገር ድረስ በመውሰድ ከውጭ ባለሀብቶች ጋር በማገናኘት ገበያ የሚያገኙበትን ዕድል ለመፍጠር ተችሏል፡፡ ከውጭ ገዥዎችን በመጋበዝ ከእኛ አገር አምራቾች ጋር በማገናኘት የገበያ ትስስር እንዲፈጠር ማደረግ ተችሏል፡፡ በዓለም አቀፍ ደረጃ በሚዘጋጁት የንግድ ትርዒቶች ላይ የኢትዮጵያን ምርቶች እናስተዋውቃለን፡፡ በጥቅል ሲታይ ምክር ቤታችን ለአምራች ኃይሉ በተለይ አምራች ለሆኑት አባሎቻችን ከፍተኛ ድጋፍ ሲያደርግ ቆይቷል፡፡

የዘርፉ ምክር ቤት አደረጃጀት በአዋጁ በቀጥታ አባልነትን ስለማይፈቅድ፣ ከሥር ጀምሮ ተደራጅቶ የሚመጣ በመሆኑ ብዙዎችን ለመድረስ የቻለም ነው፡፡ በቀበሌ፣ በወረዳ፣ በክፍለ ከተማ እያለ ወደ ላይ የሚወጣ በመሆኑ ታች ያለውን ትንንሽ አምራች ሁሉ ተደራሽ የማድረግ አቅም ፈጥሮልናል፡፡ ከዚያ በዘለለ ትልልቅ አምራች የሚባሉ እንደ ቆዳ ኢንዱስትሪ፣ ብረት ነክ ያልሆኑ የማዕድናት ውጤቶችን የሚያመርቱ የአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤት አባል እንደሆኑ የሚፈቅድ በመሆኑ፣ ለአገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤት አቅም መሆን ችለዋል፡፡ የኤክስፖርትና የኢንፖርት ሥልጠና እንሰጣለን፡፡ አባላት ለሥራቸው የሚሆን እንዲህ ያለ ማሽን እንፈልጋለን ቢሉ እንኳን አፈላልገን ከውጭ ኩባንያዎች ጋር እናገኛለን፡፡ ስለዚህ በርካታ ሥራዎች ሠርተናል፡፡ እኔም በንግድ፣ በአገልግሎትና በማምረት ሥራዎች ላይ የተሰማራሁ ስለሆነ ወደ አመራር ከመምጣቴ በፊት እንደ አንድ አባል እንዲህ ያሉ አገልግሎቶችን አግኝቻለሁ፡፡ ዓለም አቀፍ ንግድ ላይ የሚጎሉንን ነገሮች ከዚህ ተቋም ነው ስናገኝ የቆየነው፡፡ ስለዚህ ምክር ቤታችን በተለይ ለአምራች ዘርፉ የቀኝ እጁ ነው፡፡ አምራች ደግሞ ሁሉም ነገር ነው፡፡ ዛሬ ዓለምን የሚያንቀጠቅጡ አገሮች አምራች ስለሆኑ ነው፡፡ እንዲህ ያሉ አምራች አገሮች ሌሎች አገሮች ተፅዕኖ ቢያሳድሩባቸው እንኳን አምራች ስለሆኑ አይጎዱም፡፡

ሪፖርተር፡- ወደ ዋና ጉዳያችን እንግባና እናንተን በአባልነት ያቀፈውና ከሥር ጀምሮ አደረጃጀት የፈጠረላችሁ ሥራ ላይ ያለው የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ከወጣበት ጊዜ ጀምሮ ተቃውሞ ሲቀርብበት ነበር፡፡ አዋጁ የሚያሠራ አይደለም በሚል ሲተችም ቆይቷል፡፡ በመሆኑም ይህ አዋጅ መሻሻል እንዳለበት ታምኖ ለዓመታት ዝግጅት ሲደረግ ነበር፡፡ በቅርቡም ይህንን አዋጅ የሚተካ አዲስ ረቂቅ ተሰናድቶ ይፋ ሆኗል፡፡ በዚህ ረቂቅ ላይ ያላችሁ አስተያየት ምንድነው? በረቂቅ አዋጁ በግልጽ የሚታየው ኢንዱስትሪውን ይወክላል የተባለው ዘርፍ ማኅበራት ያላካተተ እንደሆነ ነውና በዚህ ረቂቅ ላይ የተቋማችሁ አመለካከት ምንድነው?

አቶ አበባየሁ፡- ነባሩ አዋጅ በእኛም በኩል ሊስተካከሉ የሚገባቸው ጉዳዮች አሉት፡፡ እንዲቀየር የምንፈልጋቸው አንቀጾች ነበሩ፡፡ ከጊዜው ጋር የሚራመድ አሠራርና ሕግ መኖር እንዳለበት እናምናለን፡፡ የዘመነ ሲስተም መኖር አለበት፡፡ እኛም ሲስተሞቻችንን እያዳበርን እንሄዳለን፡፡ አዋጆቻችን ጊዜውን መስለው መስተካከል አለባቸው፡፡ በቋሚነት በየተወሰነ ዓመት እየተፈተሹ ማሻሻያ ሊደረግባቸው ይገባል፡፡ በተለይ ንግድ ፈጣን ለውጥ ስለሚያሳይ ከዚሁ ጋር የተናበቡ ማሻሻያዎች ያስፈልጋሉ፡፡ ስለዚህ እኔም ሆንኩ ተቋማችን የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ማሻሻያ ያስፈልጋል ብለን እየሠራንበት ቆይተናል፡፡ በተለይ እንደ ዘርፍ ከስም ስያሜው አንስቶ ችግሮች ያሉበት ነው፡፡ የማሻሻያው ዕርምጃ ሲወሰድ የአዋጁን ስያሜ በመለወጥ መሆን አለበት ብለን እናምናለን፡፡ ይህንን የምንለው በምክንያት ነው፡፡ ለምሳሌ ከዓለም አቀፍ ግንኙነቶች መረዳት የሚቻለው ዘርፍ የሚል ስያሜ የለም፡፡ አሁን ዘርፍ የሚለው ስያሜ ትልቅ ችግር አለው፡፡

ሪፖርተር፡- በዚህ ጉዳይ ላይ ትንሽ ማብራሪያ ቢሰጡን? ነባሩ አዋጅ ስያሜውን በተመለከተ ያለበት ችግር ምንድነው

አቶ አበባየሁ፡- ለምሳሌ ዘርፍ ማለት እንዲህ ነው ብለን ለመግለጽ ብዙ እንቸገር ነበር፡፡ ከተለያዩ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ስንጻጻፍ ዘርፍ ማለት ምን ማለት ነው ይሉናል፡፡ አጥርታችሁ ንገሩን እስከማለት ሲደርሱ የተቋቀምንበትን አዋጅ እስከመላክ እንገደዳለን፡፡ ምክንያቱም ዘርፍ ማለት ኢንዱስትሪ ነው ብለን ለመግለጽ አዋጁን መላክ ስለበረብን ነው፡፡ ስለዚህ በነባሩ አዋጅ በትንሹ የስም ስያሜው እንኳን ችግር ያለበት ስለሆነ ይህ እንዲሻሻል ጭምር ነበር ስንጥር የነበረው፡፡ ወደ ውስጥ ከገባን አዋጁ ሌሎች ችግሮች ያሉበት ሊሆን ይችላል፡፡ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ማለት ይህንን አዋጅ ላወጣው አካል የዘርፍ ምክር ቤት ማለት ኢንዱስትሪውን የሚወክል ተቋም መሆኑ ይታወቃል፡፡ በሌላ አገር ግን ዘርፍ ግልጽ አይደለም፡፡ ስለዚህ አዋጁ ሲሻሻል ቢያንስ ስያሜው የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ሊባል ይገባል የሚል አቋም ይዘን ነበር ስንንቀሳቀስ የቆየነው፡፡ የመጀመርያ ጥያቄያችንም ይህ ነበር፡፡ በነባሩ አዋጅ ሌላው ጥያቄያችን በካፒታል ደረጃቸው ትልልቅ የሆኑ ቀደም ብዬ የገለጽኩልህ የቆዳ ኢንዱስትሪና ብረት ነክ ውጪ ያሉ ማዕድን አምራቾችና የመሳሰሉት በቀጥታ የአገር አቀፉ ምክር ቤቱ አባል ይሆናሉ፡፡ ከዚህ ውጪ ያሉትን ግን በወረዳ ወይም በክፍለ ከተማ እንዲደራጁ ይፈቅዳል፡፡ ንግዱ ላይ ግን ይህንን አደረጃጀት አይፈቅድም፡፡ ቀጥታ ሰዎች አባል እንዲሆኑ ይፈቅዳል፡፡ በዚህም ምክንያት የከተማ ንግድ ምክር ቤቶችም ሆኑ አገር አቀፍ ንግድ ምክር ቤት ላይ ስንመጣ እነሱ አቅም እንዲያገኙ ያደርጋሉ፡፡ ምክንያቱም ባለሀብቱ ቀጥታ መጥቶ ይመዘገባል፡፡ በእኛ በኩል ግን ወረዳና ክፍለ ከተማ ላይ ተደራጅቶ ነው የሚመጣው፡፡ የ500 ሚሊዮን ብር ኢንቨስትመንት ያለው ኢንቨስተር ወረዳ ሊደራጅ አይችልም፡፡ ስለዚህ በካፒታሉ መጠን ወይም በሌላ መመዘኛ አገር አቀፍ ላይ በቀጥታ አባል የሚሆንበት መመቻቸት አለበት የሚል እምነት አለን፡፡ ይህ አደረጃጀት ለንግድ ዘርፍ ስለሚፈቀድ ለኢንዱስትሪውም ዘርፍ መፈቀድ አለበት በሚል አዋጅ ሲሻሻል፣ እንዲህ ያሉ ነገሮች እንዳይካተቱ ስንሞግት ቆይተናል፡፡ ሌሎች ሊካተቱ የምንፈልጋቸው ነጥቦች ነበሩ፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ሲወጣ ግን እንዲህ ያሉ ሐሳቦቻችሁ ቀርተው ኢንዱስትሪውን የሚመለከት አንቀጽ እንኳን እንዳይካተት ተደርጓል በማለት፣ ረቂቅ አዋጁ በዚህ ሁኔታ መውጣት የለበትም የሚል አቋም ይዛችኋል፡፡ ረቂቁ አሁን ባለው ይዘት የሚፀድቅ ከሆነ የእናንተ ህልውና አብሮ እንደሚያከትም እየገለጻችሁም ነውና ይህ ከሆነ ቀጣይ ዕርምጃችሁ ምን ይሆናል?

አቶ አበባየሁ፡- ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ በአዋጁ መሻሻል አስፈላጊነት ላይ የዘርፍ ምክር ቤታችን ተቃውሞ የለውም፡፡ በጀት መድቦ ሲሠራ የቆየው ለዚህ ነው፡፡ አዋጁን ለማሻሻል በተቋቋመው ኮሚቴ ውስጥም ነበርን፡፡ ባለፉት ስድስት ዓመታት አዋጁን ለማሻሻል ንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር አንድ ላይ በነበሩበት ወቅት፣ የባለሙያዎች ዕውቀት ፈሶበት ሲጠና የነበረ ረቂቅ ነበር፡፡ በዚህ ክፍት መነሻነት ስምምነት ላይ የተደረሰበትን ረቂቅ ከሦስትና ከአራት ሚኒስትሮች በላይ ያፀደቁት፣ ‹‹የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ›› የሚለውን ነበር፡፡ አዲሱ አዋጅ ግን ከዚህ ሐሳብ ውጪ ሆኖ መረቀቁ ነው እኛን ለተቃውሞ ያነሳሳን፡፡ የሚገርመው ደግሞ ስድስት ዓመታት ተጠንቶ የመጣው ረቂቅ ላይ ተስማምተን ከጨረስን በኋላ፣ አዲሱ ረቂቅ በስድስት ወር ውስጥ ተቀይሮ መምጣቱ ነው፡፡ ይህንን ረቂቅ አሳፋሪ የሚያደርገው በዓለም ላይ አገርን የሚቀይር ኢንዱስትሪ መሆኑ እየታወቀ፣ በረቂቁ አንድም ቦታ ኢንዱስትሪን የሚጠቅስ ቃል አለመስፈሩ ነው፡፡ ዛሬ ሬዲዮ ከተከፈተ ‹‹ኢትዮጵያ ታምርት›› ይባላል፡፡ እንዲህ እየተባለ በሚነገርበት አገር አምራቾች ተደራጅተው ድምፃቸውን የሚያሰሙበት ተቋም አያስፈልግም ተብሎ የወጣ ረቂቅ አድርጌ ነው የምወስደው፡፡

እንዲሁም ይህ ረቂቅ አዋጅ በመውጣቱ የሁለት ሚኒስትሮች ጥል እንዳለ እየተሰማኝ ነው፡፡ አንደኛው አይመለከተኝም፣ ሌላኛው ደግሞ ሕግ ማውጣት የእኔ ሥልጣን ነው የሚል ይመስላል፡፡ አንዱ እኔ የሚመለከተኝ ንግድ ነው ይላል፣ የሚወጣውም ሕግ ንግዱን የሚመለከት ነው የሚልም ይመስላል፡፡ ነገር ግን ንግድም ሆነ ኢንዱስትሪ የሚጠቅሙት አገርን እንደሆነ እየታወቀ ኢንዱስትሪን ያገለለ ረቂቅ አዋጅ በመዘጋጀቱ በእጅጉ ያሳዝናል፡፡ እዚህ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ የምትመለከተው እኔ ንግዱን ስለምመራ ያወጣሁት አዋጅ ለንግዱ ወደሚል አመለካከት ያዘነበለ ነው፡፡ ረቂቁ ኢንዱስትሪውን በመዘንጋቱ አዝነናል፡፡ የበለጠ መደገፍ የነበረበት ግን ኢንዱስትሪው ነበር፡፡ ለምሳሌ ንግድ ለመነገድ ሰኞ ፈልገህ በተከታዩ ማክሰኞ ፈቃድ ወስደህ ሥራህን ልትጀምር ትችላለህ፡፡ ኢንዱስትሪው ግን ወደ ሥራ ለመግባት ብዙ ፈተና አለበት፡፡ ኢንዱስትሪውን ወደ ሥራ ለማስገባት በጣም ልምድ ካለህ ሁለት ሦስት ዓመት ሊፈጅ ይችላል፡፡ እንዲህ ያለ ችግር ያለበትን ዘርፍ ተደራጅታችሁ የፖሊሲ ጉዳዮች ላይ ሐሳብ አቅርቡ፣ ተቃወሙ ወይም ዕርዱ ነው ማለት የሚሻለው ወይስ እንዲሁ መበተን ነው የሚሻለው? በበኩሌ እንዲህ ያለውን ነገር ሁሉ ለሚኒስትሩ አቅርቤያለሁ፡፡ ለምን እንዲህ ዓይነት አዋጅ እንደወጣ እንኳን ግራ ገብቶናል እስከ ማለት ደርሻለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንደገሩኝ እንዲህ ያሉ ሐሳቦቻችሁን በተለያዩ መድረኮች አቅርባችኋል፡፡ በጽሑፍም አቋማችሁን አሳውቃችኋል፡፡ ለእነዚህ ጥያቄዎቻችሁ የተሰጣችሁ ምላሽ ምንድነው? መጀመርያ ‹‹የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ማቋቋሚያ አዋጅ›› የሚለውና የተስማማችሁበት ረቂቅ ቀርቶ ንግድ ምክር ቤት ብቻ ብሎ ረቂቁ መዘጋጀቱን በመቃወም ላቀረባችሁት አቤቱታ ምን ዓይነት ምላሽ እየተሰጣችሁ ነው?

አቶ አበባየሁ፡- እንዲህ ያለ ፍጹም የተለየ ነገር ስለመዘጋጀቱ ምንም የተባልነው ነገር የለም፡፡ የሚገርመውና ነገሩን በጣም አሳዛኝ የሚያደርገው ጉዳይ እኛ የሚመለከተን ንግዱ ብቻ ነው መባሉ ነው፡፡ በሌላም ዓለም አዋጅ የማውጣት ሥልጣን ንግዱ ዘንድ ስለሆነ የኢንዱስትሪውም ጉዳይ በዚህ አዋጅ የሚፈታ ነው የሚል አመለካከት አለ፡፡ ኢንዱስተሪው ያመርታል፣ ይነግዳል የሚልም ነው፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡ ለመነገድ እኮ መሠረተ ልማት አያስፈልግም፡፡ የለማ ቦታ ፈልገህ ትነግዳለህ፡፡ ኢንዱስትሪዎች ጫካ ነው ያሉት፡፡ ቀድሞም ችግር ያለባቸው ናቸው፡፡ የሚያጋጥሙንን ችግሮች በጋራ ሆነን ነው ስንፈታው የነበረው፡፡ አሁን ደግሞ ተደራጅቶ ችግሮችን እንዳይፈታና እንዳይሠራ እየተደረገ ነው፡፡ ሌላው አሁንም ንግዱ ላይ ባለው አቋም ኢንዱስትሪውን እንደ ጠላት የማየት አዝማሚያ አይቼበታለሁ፡፡

ሪፖርተር፡- እንዲህ ለማለት የደፈሩበት እንዴት እንደሆነ ግልጽ ቢያደርጉልኝ?

አቶ አበባየሁ፡- ግድ የለሽ መሆንና ኢንዱስትሪው አይመለከተንም ዓይነት ነገር ታያለህ፡፡ ነገር ግን ማሰሪያው አገር መሆን አለበት፡፡ ስለዚህ እኔ የራሴን ብቻ ነው የምሠራው የሚለው ነገር ይጎዳናል፡፡ ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴርም የሠራው ይህንን ነው፡፡ ይህ ትክክል አይደለም፡፡

ሪፖርተር፡- አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የሁለቱም ንግድ ምክር ቤቶች ንብረት አዲስ በሚቋቋመው ንግድ ምክር ቤት ይዛወራል ይላል፡፡ ይህ እንዴት ተፈጻሚ ይሆናል?

አቶ አበባየሁ፡- ይህም ግራ የሚያጋባ ነገር ነው፡፡ ስድስት ዓመት የተጠናን ጥናት ትተህ በስድስት ወር አዋጅ ስታዘጋጅ አደገኛ ሊሆን እንደሚችል ይገመታል፡፡ አንተ የምትለው የሀብት መወራረስን ነው፡፡ ከፌዴራል እስከ ክልል ያሉ ሲደመሩ በሺሕ የሚቆጠሩ ሠራተኞች እኮ አሉ፡፡ እነዚህ ሠራተኞች ምን ይሆናሉ የሚለው ሁሉ ግልጽ አይደለም፡፡ በነገራችን ላይ ይህ አዋጅ ማሻሻያ አይደለም፣ አዲስ አዋጅ ነው፡፡ ይህ አዋጅ ከፀደቀ በነጋታው ነባሩ አዋጅ ይሻራል፡፡ ይህ ሲሆን ደግሞ ንብረቱን እንዴት ነው የምናስተዳድረው የሚል ጉዳይ ጥያቄ ያስነሳል፡፡ ስለዚህ ብዙ ችግሮች አሉ፡፡ ኢንዱስትሪውን ማን ነው መጥቶ የሚያነጋግረው? ኢንዱስትሪው ውስጥ ያሉ ችግሮች በጣም ብዙ መሆናቸው እየታወቀ ይህንን ዘርፍ ለማዳከም ለምን እንደተፈለገ ሁሉ ብዙ ሊያነጋግር ይችላል፡፡

ሪፖርተር፡- ተቃውሞ እያቀረባችሁበት ያለው ረቂቅ አዋጅ አሁን ባለው ይዘቱ ከፀደቀ እናንተ በመጨረሻ ዕርምጃችሁ ምንድነው? እስካሁንስ ምን እያደረጋችሁ ነው?

አቶ አበባየሁ፡- ይህ ረቂቅ እጃችን ከገባ በኋላ ለሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አቋማችንን ገልጸናል፡፡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤትና ለፓርላማ ጭምር ይህንኑ አቋማችንን የሚያንፀባርቅ ደብዳቤ በግልባጭም አሳውቀናል፡፡ ንግዱ አቅም አለው፡፡ ነጋዴ አቅም ኖሮት ብዙ ነገር እንደሚያስቀይር ከዚህ አዋጅ መማሬንም ጭምር ተናግሬያለሁ፡፡ ምክንያቱም በስድስት ወር ተዘጋጅቶ የወጣ ነው፡፡ ለማንኛውም ግን ረቂቁን ካፀደቁት ጎን ለጎን የኢንዱስትሪ ምክር ቤት አዋጅ ሊወጣልን ይገባል በማለት አመልክተናል፡፡ በራሳችን ባለሙያዎች ረቂቅ አዋጅ አዘጋጅተንም ልከናል፡፡ ይህ እየታየ ነው፡፡ ቢቻል ግን የአገር ሀብት ከምናባክንና የእኛንም ጊዜ ከምንገል በዚሁ ላይ የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ተብሎ ቢወጣ የተሻለ ነው፡፡ ምክንያቱም ብዙ ነገሮችን ስለምንጋራ ማለት ነው፡፡ ከዚህ በዘለለ አይሆንም የሚባልና በዚህ ይዘቱ የሚፀድቅ ከሆነ ውሳኔው ኢንዱስትሪውንም አገርንም የሚጎዳ ስለሆነ፣ ቢያንስ ኢንዱስትሪውን ለመታደግ በእኛ በኩል ግን ሁለኛው መፍትሔ ብለን የያዝነው የኢንዱስትሪ ምክር ቤት አዋጅ እንዲዘጋጅ እናደርጋለን፡፡ ነገር ግን ይህ ረቂቅ አዋጅ እንዳይፀድቅ አቋማችንን በተቃውሞ ሠልፍ ጭምር ለመግለጽ እየተዘጋጀን ነው፡፡ ምክንያቱም ኢንዱስትሪው ዘርፍ እንዲህ ገሸሽ ማለት የለበትም፡፡ የኢንዱስትሪ  ምክር ቤቱ እንዲቋቋም የራሳችንን ጥረት እናደርጋለን፡፡

ሪፖርተር፡- ይህ ሐሳብ ተቀባይነት ይኖረዋል? አንድን አዋጅ ለማሻሻል ስድስት ዓመት ከወሰደ አዲስ አዋጅ አሰናድቶ በቀላሉ ማውጣት እንዴት ይቻላል?

አቶ አበባየሁ፡- ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ይጠና ብለው መርተውበታል፡፡ ይወጣል ብለን እናስባለን፡፡ ነገር ግን ይህ የኢንዱስትሪ ምክር ቤት መቋቋም ያለበት የንግድ ምክር ቤት አዋጅ ከመፅደቁ በፊት ነው፡፡ ይህንንም አሳውቀናል፡፡ አንዱ የአደባባይ ተቃውማችን ይህንንም የሚመለከት ነው፡፡

ሪፖርተር፡- በአዲሱ ረቂቅ ሕግ ውስጥ በርካታ አዳዲስ አንቀጾች ተካተዋል፡፡ ለምሳሌ አባልነት አስገዳጅ እንዲሆን ይሻል፣ ይህን እንዴት ያዩታል?

አቶ አበባየሁ፡- የቀጥታ አባልነት አስገዳጅ ይሁን የሚለውን ጉዳይ በግሌ እንደ አንድ ኢንቨስተር አልደግፈውም፡፡ ይህ የግል አቋሜ ነው፡፡

ሪፖርተር፡- ምክንያትዎ ምንድነው?

አቶ አበባየሁ፡- በግል ይህንን የማልደግፍበት አንዱ ምክንያቴ ብዙዎች የአገራችን ተቋማት ደካማ ከመሆናቸው አኳያ ሠርተው ገቢ ማግኘት ሲገባቸው፣ ሳይሠሩ የሚያገኙት ገንዘብ የበለጠ ያዳክማቸዋል ብዬ ስለምሠጋ ነው፡፡ ስለዚህ ተቋማት አባላትን በግዴታ ካገኙ ሳይሠሩ ብር እንዲያገኙ ያደርጋል፡፡ አገልግሎት ሳይሰጡ የንግድ ፈቃድ ለማደስ የንግድ ምክር ቤት አባልነት ክፍያ መክፈል አለበት ከተባለ አስቸጋሪ ነው፡፡ ነጋዴው ፈቅዶ ሳይሆን ፈቃዱን ለማግኘት ከንግድ ምክር ቤቶች ወረቀት ማግኘት ስለሚኖርበት የአባልነት ይከፍላል ማለት ነው፡፡ ሳይሠሩ ብር አገኙ ማለት ነው፡፡ ስለዚህ ይህ ዓይነቱ አሠራር ተቋማቱን አገልግሎት እንዳይሰጡ የሚያደርግ ነው የሚሆነው፡፡ ሌላው ችግር ደግሞ በረቂቁ በአስገዳጅነት አባል ይሁኑ የሚላቸው የተወሰኑ አካላትን ነው፡፡ ይህም የሚደገፍ አይደለም፡፡ ለምሳሌ በአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባል በነበርኩበት ጊዜ እንደ አሠራር ሲራመድ የነበረው አባላትን በፈቃደኝነት ላይ ተመሥርቶ ማሰባሰብን ነው፡፡ ምክር ቤቱ አስገድዶ አባል አያደርግም፡፡ እኔም አባል የሆንኩት ጥሩ አገልግሎት ስለሚሰጥ በፈቃደኝነት ነው፣ ያስገደደኝ የለም፡፡ የምፈልገው አገልግሎት ስላለ ይህንኑ አገልግሎት ለማግኘት አባል ሆንኩ፡፡ አባልነቱን ፈልጌ ነው ሄድኩት፡፡ ስለዚህ አባልነት በግዴታ ይሁን ሲባል ተቋማት ሳይሠሩ ዝም ብሎ ገቢ ማግኘታቸው ተገቢ ነው ብዬ አላምንም፡፡

ሪፖርተር፡- አባልነት በግዴታ ይሁን የሚሉ ወገኖች ግን የተለየ ምክንያት አላቸው፡፡ ንግድ ምክር ቤቶች አትራፊ ድርጅቶች አይደሉም፣ ዋነኛ የገቢ ምንጫቸው ከአባላት መዋጮ ከሆነ የፋይናንስ አቅማቸውን ለማዳበርና የተሻለ አገልግሎት ለመስጠት አባልነትን በግዴታ መሆኑ ጠቃሚ ነው ይላሉ፡፡ ምክንያቱም ለምሳሌ አዲስ አበባ ከተማ ውስጥ ወደ ግማሽ ሚሊዮን የሚገመቱ ነጋዴዎች አሉ እየተባለ፣ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ግን አባላቱ አሥር ሺሕ እንኳን አይሞሉም፡፡ ስለዚህ ለተሻለ አገልግሎት አባልነትን አስገዳጅ አድርጎ ገቢውን ማሳደግ ያስፈልጋል ይላሉ፡፡ እርስዎስ ምን ይላሉ?

አቶ አበባየሁ፡- በሐሳብ ደረጃ ትክክል ይመስላል፡፡ ንግድ ምክር ቤቶች ግን ገቢያቸው ከአባላት ብቻ የሚሰበሰብ አይደለም፡፡ ለጋሽ ድርጅቶች የሚሰጡት ገንዘብ አለ፡፡ እርግጥ ነው ለትርፍ የተቋቋመሙ አይደሉም፡፡ አገልግሎት ፈልገው የሚመጡ ሰዎች አሉ፡፡ ለቢዝነስ ግንኙነቶች ወደ ውጭ ለመሄድ ለሚፈልጉ ሰዎች አባልነት ይጠየቃል፡፡ አገልግሎቱን የሚሰጡት ለከፈላቸው ነው፡፡ ስለዚህ የገቢ አማራጮች አሏቸው፡፡ እነዚህ ተቋማት ችግር ቢኖርባቸው እኮ የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አካውንቱ ውስጥ አይኖረውም፡፡ የአገር አቀፍ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቱም በሚሊዮን የሚቆጠር ገንዘብ አለው፡፡ ዘርፉም እንዲሁ፡፡ ይህንን ያገኙት ከአባላት አይደለም፡፡ ሠርተው ያመጡት ነው፡፡ ስለዚህ አባልነት ያውም የተወሰነውን ዘርፍ አስገዳጅ እንዲሆን ማድረጉ ብዙ ጉዳይ ይኖረዋል፡፡

ሪፖርተር፡- አባልነት አስገዳጅ መሆን አለበት የሚለው አመለካከት ጠቃሚ ነው የሚባልበት ሌላም መከራከሪያ ይቀርባል፡፡ ለምሳሌ የንግድ ኅብረተሰቡን ችግር ላይ የጣለ አንድ ሕግ ቢወጣ፣ ይህንን ሕግ ለማሻሻል ንግድ ምክር ቤቶች በመንግሥት ላይ ጫና ፈጥረው ወይም መሆን ያለበት ይህ ነው ብለው የተጠና ነገር አቅርበው ያ ሕግ ቢቀለበስና ቢስተካከል የሚጠቅመው አባል የሆኑትን ብቻ ሳይሆን አባል ላልሆኑትም ነው፡፡ ውጤቱ የተገኘው ግን አባላት በከፈሉት መዋጮ ጭምር ስለሆነ ንገድ ምክር ቤቶች የሚሠሩት ሥራ ወይም የሚያስገኙት ውጤት ለአባሎቻቸው ብቻ ሳይሆን፣ ለሁሉም በመሆኑ አባልነት አስገዳጅ መሆኑ ተገቢ ነው ብለው ይሞግታሉና እርስዎ ምን ይላሉ?

አቶ አበባየሁ፡- በአዲሱ ረቂቅ አስገዳጅ የሚሆንባቸው ተብለው በደፈናው ነው የተገለጸው፡፡ ስለዚህ አስገዳጅ የሆኑ ነገሮችን ባላምንበትም አስገዳጅ ከሆነ በሁሉም ላይ ተፈጻሚ መሆን አለበት፡፡ አንዱን ልጅ፣ አንዱን ደግሞ የእንጀራ ልጅ የሚያደርግ አዋጅ ሊኖር ይገባል ብዬ በግሌ አላምንም፡፡ ይህ መቼም የማልቀይረው አቋሜ ነው፡፡ በአዋጅ የተወሰኑ ዘርፎችን በግዴታ አባል ካደረግክ በኋላ በመመርያ ልታስተካክለው አትችልም፡፡ መጀመርያ መስተካከል አለበት፡፡ የሚገርመው ነገር በረቂቁ አባልነት ግዴታ የሚሆንባቸው የተወሰኑ ዘርፎች አሉ ይላል እንጂ፣ እነማን የሚለውን እንኳን አይመልስም፡፡ ቀደም ብዬ እንደገለጽኩልህ በዚያ ዘርፍ ውስጥ ላሉ በሙሉ ነው፡፡ ነባሩ አዋጅ አባል ከአባል አይለያይም፡፡ ስለዚህ እኩል አገልግሎት የሚያገኝ ከሆነ አንዱ ግዴታ ይሆንበታል፣ ሌላው አይገደድም ከተባለ አገልግሎቱን ግን እኩል ያገኛል ሲባል ብዥታ መፍጠሩ አይቀርም፡፡ ይኼ ማለት የሠራው ላልሠራው ይከፍለዋል እንደ ማለት ነው፡፡ ይህ ፍትሐዊ አይደለም፡፡ ደግሞስ አስገዳጅ የሚሆነው እንዴት ነው? የአባልነት ካልከፈልክ ንግድ ፈቃድህ አይታደስም ነው የምንለው? ይኼ ደግሞ በሚሊዮንና በቢሊዮን የሚቆጠር ኢንቨስት ያደረገ አንድ መቶና ሁለት መቶ ሠራተኛ ያለው ባለሀብት አባል መሆን አልፈልግም በማለቱ ብቻ የንግድ ፈቃዱ አይታደስም ማለት ነው? ይህ ማለት ከኢንቨስትመንቱ ወጣ ማለት ነው፡፡ እንዲህ ያለ አዋጅ በማውጣት አገር አትራፊ አትሆንም፡፡ ስለዚህ አስግዳጅ ይሁን መባሉን ጠለቅ ብለህ በዝርዝር ስታየው ጉዳቱ የበዛ ይሆናል፡፡ ይሁን ከተባለም ሁሉም ላይ ተፈጻሚ መሆን አለበት፡፡

ተዛማጅ ፅሁፎች

- Advertisment -

ትኩስ ፅሁፎች ለማግኘት

በብዛት የተነበቡ ፅሁፎች

ተዛማጅ ፅሁፎች

‹‹ምሁራንም ሆኑ የሲቪል ማኅበረሰቦች በፖሊሲ ቀረፃና መሰል እንቅስቃሴዎች ለመንግሥት ያስፈልጋሉ›› አድማሱ ገበየሁ (ፕሮፌሰር)፣ የቀድሞ ፖለቲከኛና የውኃ ሀብት ተመራማሪ

በምርጫ 97 ጊዜ በእጅጉ ከሚታውሱት ውስጥ ቅንጅት ለአንድነትና ለዴሞክራሲ የነበረው ሚና ሲሆን፣ በጊዜው የታሪክ አሻራ አኑሮ ያለፈ ስብስብ ነበር፡፡ ቅንጅትን ከመሠረቱት አራት የፖለቲካ ድርጅቶች...

‹‹መንግሥት ለአገር ውስጥ የኅትመት ኢንዱስትሪ ገበያ ከመፍጠር ጀምሮ ሥራ የመስጠት ኃላፊነት አለበት›› አቶ ዘውዱ ጥላሁን፣ የኢትዮጵያ አሳታሚዎችና አታሚዎች ማኅበር ዋና ሥራ አስኪያጅ

የኅትመት መሣሪያ በጉተምበርግ ከተፈበረከ ከ400 ዓመታት በኋላ በኢትዮጵያ በ1863 ዓ.ም. በምፅዋ የተጀመረው የኅትመት ኢንዱስትሪ ከአፍሪካ ቀዳሚ ቢሆንም፣ ዕድገቱ ውስን መሆኑ ይነገራል፡፡ ከኢትዮጵያ በኋላ የኅትመት...

‹‹ከጨረታ በስተጀርባ ያሉ ድርድሮችን ለማስቀረት ጥረት እያደረግን ነው›› ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር)፣ የኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ (የቀድሞ ሜቴክ) ዋና ሥራ አስፈጻሚ

ሱሌማን ደደፎ (አምባሳደር) በተባበሩት ዓረብ ኤሜሬትስ የኢትዮጵያ ባለሙሉ ሥልጣን አምባሳደር ሆነው ሲያገለግሉ ከቆዩ በኋላ፣ ከጥር 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ በኢትዮ ኢንጂነሪንግ ግሩፕ የቦርድ...