Tuesday, May 21, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ዜናበወላይታ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ሕግ ጥሰዋል የተባሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሙስና ወንጀል ሊጠየቁ...

በወላይታ ሕዝበ ውሳኔ ላይ ሕግ ጥሰዋል የተባሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሙስና ወንጀል ሊጠየቁ ነው

ቀን:

  • ፖሊስ 40 ተጠርጣሪዎችን እያደነ መሆኑ ተገልጿል

በደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልል ከሁለት ወራት በፊት ‹‹የደቡብ ኢትዮጵያ›› የተሰኘ አዲስ ክልል ለመመሥረት በወላይታ ዞን በተካሄደው ሕዝበ ውሳኔ፣ ወንጀል ፈጽመዋል የተባሉ የምርጫ አስፈጻሚዎች በሙስና ወንጀል ክስ ሊመሠረትባቸው መሆኑ ተገለጸ፡፡

ምርጫ ቦርድ ጥር 29 ቀን 2015 ዓ.ም. በደቡብ ክልል በሚገኙ ኮንሶ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ወላይታ፣ ጋሞ፣ ጌዴኦ፣ ጎፋ ዞኖች እና 5 ልዩ ወረዳዎች ማለትም ቡርጂ፣ ባስኬቶ፣ አሌ፣ አማሮና ደራሼ ባካሄደው ሕዝበ ውሳኔ፣ በወላይታ ዞን ተፈጽሟል በተባለ የሕግ ጥሰት፣ የዞኑን አጠቃላይ ምርጫ ውጤት ሙሉ በሙሉ መሰረዙን ገልጾ፣ ምርመራ እንዲጀመር ለፌዴራል ፖሊስ ደብዳቤ መጻፉን አስታውቆ ነበር፡፡

በዚህም መሠረት የፍትሕ ሚኒስቴር ከፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ክፍልና ከደቡብ ክልል ጋር በመሆን ተፈጽሟል የተባለውን ወንጀል ለማጣራት በተደረገ ምርመራ፣ በ136 ተጠርጣሪዎች ላይ ክስ መመሥረቱን፣ የፌዴራል ፖሊስ የወንጀል ምርመራ ቢሮ የምርመራ ኦፕሬሽን መምርያ ኃላፊ አቶ ሙሊሳ አብዲሳ ከፍትሕ ሚኒስትር ደኤታ አቶ ፍቃዱ ፀጋ ጋር በመሆን ሐሙስ ሚያዚያ 12 ቀን 2015 ዓ.ም. ጉዳዩን አስመልክቶ ለጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ አስታውቀዋል፡፡

- Advertisement -

የተፈጸመው ድርጊት በምርጫ አዋጁ፣ በወንጀል ሕጉና በሙስና አዋጅ መሠረት የሚያስጠይቅ መሆኑን የገለጹት ሚኒስትር ደኤታው፣ ‹‹ሕግ የጣሱ የምርጫ አስፈጻሚና የመንግሥት ሠራተኞችን በፀረ ሙስና አዋጁ መሠረት፣ እንዲሁም የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎችን ደግሞ በወንጀል ሕግ ተጠያቂ እናደርጋለን፤›› ብለዋል፡፡

ሁለቱ ተቋማት ባቋቋሙት ሁለት የምርመራ ቡድን በወላይታ ዞን በ350 የምርጫ ጣቢያዎች በተለያዩ መንገዶች የምርጫ አዋጁን የሚቃረኑ የሕግ ጥሰቶች መፈጸማቸውን፣ ቡድኑ ባሰባሰበው መረጃ እንዳረጋገጠ አስታውቋል፡፡  

የምርመራ ቡድኑ ምርጫ ቦርድ ያሰማራቸውን የምርጫ ታዛቢዎች፣ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብቶች ኮሚሽን ታዛቢ ቡድን፣ እንዲሁም የፀጥታ አካላትን በማካተት የተፈጸመውን የሕግ ጥሰት በተመለከተ ከ450 በላይ ሰዎች ቃል መቀበሉንና በተደረገው ምርመራም በዞኑ 136 ተጠርጣሪዎች በወንጀሉ የተሳተፉ መሆናቸው መለየቱን አቶ ሙሊሳ ተናግረዋል፡፡

በወንጀል ተጠርጥረው ከተለዩት መካከል 18 ያህሉ በቀበሌና በወረዳ በሚገኙ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች፣ ምርጫውን እንዲያስፈጽሙ ኃላፊነት የተሰጣቸውን የምርጫ አስፈጻሚዎችን በማስፈራራት፣ በመደለልና በማስገደድ ምርጫው እንዲጭበረበር ማድረገቸው ተገልጿል፡፡ 18ቱ አመራሮች ሁሉም በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተገለጸ ሲሆን፣ በቀጣይ በሕግ ተጠያቂ እንደሚሆኑ አቶ ፍቃዱ ተናግረዋል፡፡

በሌላ በኩል ከ118 ምርጫ አስፈጻሚዎች መካከል 75 ያህሉ በቁጥጥር ሥር መዋላቸው የተጠቆመ ሲሆን፣ ቀሪዎቹን 43 ደግሞ በቁጥጥር ሥር ለማዋል በፖሊስ እየታደኑ ነው ተብሏል፡፡

ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ሕግ ተጣሰ በማለት በቀረበው አቤቱታ በምርመራ ተረጋግጠዋል ከተባሉት ጥፋቶች መካካል መራጮች በአካል ሳይቀርቡ ምርጫ ማካሄድ፣ ኮሮጆን ቀድሞ በመራጮች ካርድ መሙላት፣ የመራጮችን ፊርማ አስመስሎ ካርድ ማስገባት፣ መራጮች ሳይመዘገቡ ለመራጭነት ስማቸው ተመዝግቦ መገኘት፣ ለምሳሌም በመራጮች ምዝገባ ወቅት 1,000 ሰዎች የተመዘገቡበት የምርጫ ጣቢያ፣ በምርጫ ወቅት 1,400 ሰዎች እንዲመርጡ ተደርጎ መዝገብ ላይ መገኘትና የመሳሰሉት ይገኙበታል፡፡ 

በዚህ የመብት ጥሰት የተነሳ ዜጎች በጥቂት ግለሰቦች የማጭበርበር ድርጊት ሕገ መንግሥታዊ መብታቸውን እንዳይጠቀሙ መደረጋቸውን፣ ለዞኑ ምርጫ ማስፈጸሚያ የተመደበው ከ205 ሚሊዮን ብር በላይ ሙሉ በሙሉ በመባከኑ፣ ድርጊቱ በከባድ ወንጀል የሚያስጠይቅ ስለሆነ ጥፋት በመፈጸም ተጠርጥረው በቁጥጥር ሥር የዋሉ አካላት አስተማሪ ዕርምጃ እንደሚወሰድባቸው አቶ ፈቃዱ ተናግረዋል፡፡

የወንጀል ምርመራው አዲስ አበባ ዋናው ቢሮ ያሉ ሥራዎችን የሚመረምር አንድ ቡድን፣ እንዲሁም በወላይታ ዞን የምርጫ ሒደቱን በተመለከተ ምርመራ የሚያደርግ ሌላ ቡድን መደራጀቱን ሚኒስትር ደኤታው ገልጸው፣ የተጀመረው የምርመራ ሥራ በአጭር ጊዜ ውስጥ ይጠናቀቃል ብለዋል፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

በሥጋ ላይ አላግባብ እየተጨመረ ያለውን ዋጋ መንግሥት ሊቆጣጠረው ይገባል

በአገራችን የግብይት ሥርዓት ውስጥ ኢኮኖሚያዊ ያልሆኑ ወይም ያልተገቡ የዋጋ...

ኢትዮጵያን የተባበረ ክንድ እንጂ የተናጠል ጥረት አይታደጋትም!

ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከምትገኝበት ውጥንቅጥ ውስጥ የምትወጣበት ዕድል ማግኘት...

የፖለቲካ ቅኝቱ የሕዝባችንን ታሪካዊ ትስስር ለምን አያከብርም?

በንጉሥ ወዳጅነው የዓብይ አህመድ (ዶ/ር) መራሹ የ2010 ዓ.ም. የለውጥ መንግሥት...

ዛሬም ኧረ በሕግ!

በገነት ዓለሙ በዚህ በያዝነው ሚያዝያ/ግንቦት ወይም ሜይ ወር ውስጥ የተከበረው፣...