- የሱዳን የጦር ኃይሎች በከተማ ውስጥ እርስ በርስ ፍልሚያ መጀመራቸውን ሰማህ?
- አዎ። ወንድም የሆነውን ሕዝብ ለመከራ ዳረጉት።
- እኔ እንኳን እሱን ለማለት አልነበረም።
- እና ምን ልትይ ነበር?
- ነገሩ ከሰሞኑ ውሳኔያችሁ ጋር መገጣጠሙ ገርሞኝ ነው።
- የቱ ውሳኔ?
- የክልል ልዩ ኃይሎችን አስመልክቶ የወሰናችሁት።
- ምን አገናኘው?
- የሱዳኑ ክስተት እናንተ ካስረዳችሁት በተሻለ ሁኔታ ስለ ውሳኔያችሁ ምክንያትና አስፈላጊነት ግንዛቤ ይፈጥራል ማለቴ ነው።
- እንዴት? የእኛ ምክንያት ምንድነው?
- ፍርኃት ነዋ!
- የምን ፍርኃት?
- የሱዳኑ እንዳይከሰት።
- ፍርኃት እንኳን አይደለም። ቢሆንም ሌላውም በዚህ መልኩ ቢረዳው ጥሩ ነበር።
- ምን ያድርጉ ብለህ ነው?
- እንዴት?
- እነሱም ፈርተው ነዋ።
- ለምን ይፈራሉ?
- ሌላ ኃይል ይወረኛል፣ መሬቴን ይወስዳል ብለው ይሆናላ።
- እነሱ እንኳ ገና ከግጭት እየወጣን ስለሆነ ቢሰጉ አይገርምም፣ የሕዝቡ ግን ግራ ያጋባል።
- የሕዝቡ ምን?
- ለተቃውሞ አደባባይ ወጥቶ መንገድ መዝጋቱ?
- ምን ያድርግ ብለህ ነው?
- እንዴት?
- ፈርቶ ነዋ!
- ለምን ይፈራል?
- ያፈናቅሉኛል፣ ጥቃት ይደርስበኛል ብሎ ነዋ?
- መንግሥት ባለበት አገር?
- መንግሥት ያነጻጽር ይሆናል እንጂ አይጠብቀኝም ብሎ ይሆናላ?
- የምን ንጽጽር? ከምን?
- አሜሪካ ላይ ከደረሰ ጥቃት፡፡
- ካንቺ ቁም ነገር መጠበቄ ነው ስህተቱ፡፡
- አትሳሳት! ቁም ነገር ነው ያወራሁት!
- ምኑ ነው ቁም ነገሩ?
- የዚህ አገር ችግር ምን እንደሆነ እየነገርኩህ እኮ ነው?
- ምንድነው የዚህ አገር ችግር?
- ፍርኃት!
- የምን ፍርኃት?
- አለመተማመን የወለደው ፍርኃት፡፡
[ክቡር ሚኒስትሩ ዋና ጸሐፊው ጉብኝት እንዳያደርጉ መከልከላቸውን በተመለከተ ስለወጣው መረጃ ከአማካሪያቸው ጋር እየተወያዩ ነው]
- ክቡር ሚኒስትር ባዘዙኝ መሠረት ዋና ጸሐፊው ጉብኝት እንዳያደርጉ የከለከለው ማን እንደሆነ የሚመለከታቸውን ተቋማት መረጃ ጠይቄያለሁ።
- እሺ፣ ምን ምላሽ አገኘህ?
- አንዳንዶቹ ጨርሶ መረጃውን አልሰሙም።
- እነሱን ተዋቸውና የሌላውን ንገረኝ።
- የውጭ ግንኙነት ሰዎች በዚህ ጉዳይ ኦፊሳላዊ ምላሽ እንደማይሰጥ ነው የነገሩኝ።
- እንዴ? አጋሮቻችን ኦኮ እየጠየቁን ነው? ምላሽ የለንም ልንላቸው ነው?
- እኔም ይህንኑ ጥያቄ አንስቼ ነበር።
- እሺ ምን አሉህ?
- የግድ ምላሽ ለሚፈልጉት ብቻ ማለት ያለብንን ነግረውኛል።
- ምን በሏቸው አሉ?
- እኛ አልከለከልንም፣ የመንግሥት አቋም አይደለም!
- ምን ማለት ነው? ማነው የወሰነው ብለው መጠየቃቸው ይቀራል እንዴ?
- አኔም ይህንኑ አንስቼ ነበር።
- እሺ፣ ማን አሉ?
- በግላቸው!