የወታደራዊ የመንግሥት ግልበጣና ሕዝባዊ አመፅ በማይለያት ሱዳን እ.ኤ.አ. በ1989 በወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት ሥልጣን የተቆናጠጡትን የቀድሞው ፕሬዚዳት ኦማር አልበሽር የ30 ዓመት አገዛዝ፣ እ.ኤ.አ. በ2019 በሰፊ ሕዝባዊ አመፅ ከተወገደ በኋላ፣ በወታደራዊ ጀኔራሎች እጅ ወድቃ አሁንም ሌላ ጦርነት ውስጥ ገብታለች፡፡
በርካታ ተዋናዮችና እጆች በበዙበት የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና በሱዳን በሁለት ጀኔራሎች በሚመሩ ተዋጊ ኃይሎች መካካከል የተፈጠረው ሰሞነኛ ጦርነት፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ዜጎች ሕይወታቸውን ሲያጡ በርካቶች ቆስለዋል፡፡ የካርቱም አውሮፕላን ማረፊያን ጨምሮ ከፍተኛ ውድመት ከማስከተሉም በላይ ጦርነቱ የዓለምን ትኩረት ስቧል፡፡
የኦማር አልበሽር ከሥልጣን መወገድን ተከትሎ በሁለቱ የጦር ጄኔራሎች ማለትም የአገሪቱ ጦር አዛዥ ሌተና ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃንና ምክትላቸው የፈጥኖ ደራሽ ኃይል አዛዥ ሌተና ጄኔራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ ስትመራ የቆየችው ሱዳን፣ በሁለቱ መካከል በተፈጠረ ‹‹የሥልጣን ሽሚያ›› እ.ኤ.አ. ሚያዝያ 15 ቀን 2023 ዓ.ም. በዋና ከተማዋ ካርቱም የጀመረው ግጭት፣ ወደ በርካታ ከተሞች መስፋፋቱን ከቦታው የሚወጡ መረጃዎች ያስረዳሉ፡፡
የጦርነቱ ዋነኛ መነሻ ሌተና ጄኔራል ደጋሎ ሥር ያሉ ታጣቂዎች፣ በአገሪቱ ጦር ሥር ውስጥ እንዲካተቱ የቀረበውን ጥያቄ ለመፈጸም ፈቃደኛ አልሆኑም፡፡ ሁለቱ ጄኔራሎች ከዓመታት በፊት የቀድሞውን ፕሬዚዳንት ከሥልጣን ያስወገደው ሕዝባዊ አመፅ የሚመኘውን ዴሞክራሲዊ ሥርዓት ከመትከል ይልቅ፣ የገቡበት የእርስ በርስ መወነጃጀልና የሥልጣን ፉክክር ስለመሆኑ በርካቶች ይናገራሉ፡፡
አምስተኛ ቀኑን በያዘው በዚህ ጦርነት የቦይንግና የኤርባስ የመንገደኛ አወሮፕላኖች፣ ወታደራዊ አውሮፕላን አንቶኖቭና የጦር ጀቶች፣ እንዲሁም በርካታ ሕንፃዎች በእሳት ሲጋዩ የተስተዋለ ሲሆን፣ የሉዓላዊ ምክር ቤት ፕሬዚዳንትና ምክትል ፕሬዚዳንት የሆኑት ሁለቱ ጄኔራሎች እርስ በርስ ከመወነጃጀል ባላፈ ጦርነቱ ሊቆም አልቻልም፡፡
ካርቱምን ጨምሮ በበርካታ የሱዳን ከተሞች በአገሪቱ ዋና ጦርና ከ100 ሺሕ በላይ የልዩ ኃይል አባላት አሉት በሚባለው የፈጥኖ ደራሽ አባላት መካከል የሚደረገው ውጊያ፣ ሁለቱ ጀኔራሎች እርስ በርስ በገቡበት አታካራ አገሪቱን ወደ ዴሞክራሲያዊ የሲቪል አስተዳደር ለማስተላለፍ የሚደረገውን ጥረት ተስፋቢስ አድርጎታል፡፡
ወታደራዊ መፈንቅለ መንግሥት በተጠናወታት ሱዳን በሕዝባዊ አመፅ ከሥልጣን የተወገዱትን ኦማር አልበሸር በመተካት ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመመለስ በሚቆየው የሦስት ዓመት የሽግግር ጊዜ፣ የጊዜያዊ አስተዳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው ተሾመው የነበሩት አብደላ ሃምዶክ እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2021 አጋማሽ ሠራዊቱ መፈንቅለ መንግሥት አካሂዶ የሲቪል አስተዳደሩን አመራሮች መበተኑ የሚታወስ ነው፡፡
በዚህ ሁሉ ውጣ ውረድና ጦርነት የተነሳ በተያዘው እ.ኤ.አ. 2023 ምርጫ ተደርጎ ወታደራዊ ሥርዓቱን ወደ ሲቪል አስተዳደር ለመቀየር የነበረው ዕቅድ፣ አሁን በተከሰተው ግጭት ምክንያት ጥላ አጥልቶበታል፡፡
በቀይ ባህር፣ በሳህል አዋሳኝ ቀጣናዎችና በአፍሪካ ቀንድ አገሮች መካከል የምትገኘው ሱዳን ባላት የመልከዓ ምድራዊ አቀማመጥና የተፈጥሮ ሀብት አሜሪካ፣ ቻይና፣ ሩሲያ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችና የአፍሪካ አኅጉርን ጨምሮ ትኩረት የማይነፍጓት አገር ናት፡፡
አሜሪካና ምዕራባውያን በሳዑዲ ዓረቢያና በተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ላይ ግፊት በመፍጠር፣ በሱዳን ያለው ወታደራዊ አገዛዝ ወደ ሲቪል አስተዳደር እንዲቀየር ጥረት ሲያደርጉ ቆይተዋል፡፡
ለጄኔራል አብዱልፈታህ አል ቡርሃን ጠንካራ ወዳጅ የሚባሉት የግብፅ ፕሬዚዳነት አብዱልፈታህ አልሲሲ ደግሞ በሱዳን ያለውን ወታደራዊ ሥርዓት፣ በተለይም ግብፅ በኢትዮጵያ እየተገነባ ካለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ ጋር በተያያዘ ጠንካራና አስተማማኝ የወታደራዊ አጋር ለመፍጠር፣ በሱዳን ያለው የወታደራዊ አገዛዝ እንዲቆይ ጠንካራ ፍላጎት ያላት በመሆኑ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አገሮች ላይ ጫና በማሳደር ላይ ናት፡፡
በሁለቱ አገሮች መካከል ላለው ጠንካራ ግንኙነት፣ በጋራ የሚያደርጓቸው ወታደራዊ ልምምዶችና በሱዳን መሬት እየሠለጠኑ የሚገኙት የግብፅ ወታደሮች ይጠቀሳሉ፡፡ ሰሞነኛው ጦርነት መቀስቀሱን ተክትሎ በሱዳን እየሠለጠኑ ያሉ የግብፅ ወታደሮች በዳጋሎ ልዩ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር መዋላቸው ተገልጿል፡፡
በሱዳን ካሉ የውጭ ተዋናዮች ውስጥ የቅጥረኛ ተዋጊ ቡድን በመባል የሚታወቀው ‘ዋግነር ግሩፕ’ ከሱዳን ልዩ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ዳጋሎ ጋር ጠንከራ ግንኙነት እንዳላቸው ይነገራል፡፡ የሁለቱ ቡድኖች ግንኙነት የሚገለጸው በዋነኛነት በሱዳን በሕገወጥ መንገድ ወርቅ በመነገድ ቢሊየነር እንደሆኑ በሚነገርላቸው የልዩ ኃይል አዛዥ ጋር ባላቸው ቁርኝት ነው፡፡
ከአንድ ዓመት በፊት በሩሲያና በዩክሬን መካከል ጦርነት መጀመሩን ተከትሎ፣ ጄኔራል ዳጋሎ ወደ ሞስኮ ያደረጉት ጉብኝት፣ ጀኔራሉ ከሩሲያ ጋር የፈጠሩት ጠንካራ ግንኙነት ማሳያም ተደርጎም ይጠቀሳል፡፡ ከዚህም ጋር በማገናኘት አንዳንድ ምዕራባውያን ተንታኞች በሰሞነኛው ግጭት የሩሲያ ‹ዋግነር ግሩፕ› በጦርነቱ ተሳትፎ ሊሆን እንደሚችል ይጠረጥራሉ፡፡
ሩሲያ ከቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አልበሽር ጋር በነበራት ጠንካራ ግንኙነት፣ በቀይ ባህር በምትገኘው ፖርት ሱዳን የባህር ኃይል የጦር ሠፈር ለማቋቋም ስምምነት ላይ ደርሳ ነበር፡፡
በተቃራኒው አሜሪካ ለረዥም ዘመናት የቆየው የኦማር አልበሽር አገዛዝ መወገድን ተከትሎ የሲቪል አስተዳደሩ ጠቅላይ ሚኒስትር በመሆን ሥልጣን ይዘው የነበሩት አብደላ ሃምዶክ፣ ቀጥሎም አሁን አገሪቱን በበላይነት እየመሩ ካሉት ወታደራዊ አዛዡ ጄኔራል አብዱልፈታህ አልቡርሃን ጋር የተሻለ ግንኙነት እንዳለቸው ቢነገርም፣ ከልዩ ኃይል መሪው ጄኔራል ዳጋሎ ጋር ግን ጥሩ ግንኙነት እንደሌላቸው ይነገራል፡፡
ሱዳን ባላት ጂኦ ፖለቲካዊ አቀማመጥና በታደለችው የተፈጥሮ ሀብት የተነሳ የተለያየ ፍላጎትን ያዘለና ዒላማቸውን ባነጣጠሩ የውጭ ኃይሎች ምክንያት፣ በሱዳን የሚታሰበውን የሲቪል አስተዳደር ለመመሥረት አስቸጋሪ ሊሆን እንደሚችል ተንታኞች ያስረዳሉ፡፡
ሰሞኑን በሁለቱ ጄኔራሎች መካከል የተጀመረው ጦርነት የፈጥኖ ደራሹ (RSF) ልዩ ኃይል አዛዥ ጄኔራል ዳጋሎ በጦርነቱ የበላይነትን አግኝተው አገሪቱን ቢቆጣጠሩ፣ ዕይታቸውን ካነጣጠሩባቸው ኃይሎች መካከል የመጀመሪያው ተጎጂ ሊሆን የሚችሉት ከአገሪቱ የጦር ኃይል አዛዥ ጋር የጠነከረ ግንኙነት እንዳላቸው የሚነገርላቸውና ወታደሮቻቸውን ሱዳን ልከው እያሠለጠኑ የሚገኙት የግብፅ ፕሬዚዳንት አብዱልፈታህ አልሲሲ ናቸው ሲል፣ አንድ መቀመጫውን በጣሊያን ሮም ያደረገ ሚዲያ የሠራው ሰፋ ያለ ትንታኔ ያስረዳል፡፡
ኤልሲሲ ኢትዮጵያ እየገነባችው ካለው የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር በተገናኘ አገራቸው ኢትዮጵያ ላይ ማሳደር የምትፈልጋቸውን ጫናዎች፣ ሱዳንን እንደ ቀኝ እጅ በመጠቀም በተለይም በወታደራዊ አማራጮች ጭምር ፍላጎት እንዳላቸው ይነገራል፡፡
በዚህም የግብፅ የሰላ ፍላጎት ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከሱዳኑ ጄኔራል አል ቡርሃን ጋር ባለቸው ጠንካራ ግንኙነት፣ አገሮቹ የጋራ ወታደራዊ ልምምድም ሲያደርጉም ተስተውሏል፡፡
በተቃራኒው የልዩ ኃይል አዛዡ ጄኔራል ዳጋሎ ከኢትዮጵያ መንግሥት በኩል የተሻለ ዲፕሎማሲዊ ድጋፍን ለማግኘት ለግድቡ መገንባት መልካም ዕይታ እንዳላቸው፣ ከኢትዮጵያ በርካሽ ዋጋ የኤሌክትሪክ ኃይል ለማግኘት ፍላጎት ማሳየታቸው ይነገራል፡፡ በኢትዮጵያ ሁለት ጊዜ ጉብኝት ማድረጋቸው የሚታወስ ነው፡፡
ባለፉት ሁለት ዓመታት በተለይም የሰሜን ኢትዮጵያ ጦርነት በተከሰተበት ወቅት የሱዳን ወታደሮች ኢትዮጵያና ሱዳን የሚዋሰኑበትን የአልፋሽጋ የጋራ ድንበር ጥሰው ወደ ኢትዮጵያ መግባታቸውና ጠቅላይ ሚኒስትር ዓብይ (ዶ/ር) በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥት መካከል የተፈጠረውን ጦርነት ለማሸማገል ከሱዳን የመጣውን ጥያቄ ውድቅ በማድረጋቸው፣ የሁለቱን አገሮች ግንኙነት ወደ አለመተማመን እንዲገባ እንዳደረገው ቻታም ሃውስ የተሰኘ መቀመጫውን በእንግሊዝ አገር ያደረገ የፖሊሲ ጥናት ማዕከል ባወጣው ጹሑፍ አመላክቷል፡፡
ሰሞነኛው የሱዳን ግጭት ታዲያ በቀጣናው ላይ የሚያማትሩ ዓለም አቀፍ ኃይሎችን ለሁለት ከመክፈሉ ባለፈ፣ ስምምነት ተደርጎ በቀጣይ ምርጫ ካልተደረገና ጄኔራሎቹ በጦርነት አሸናፊ ለመሆን የሚያደርጉት ደም አፋሳሽ ትንቅንቃቸው የቀጣናውን የፖለቲካ አሠላለፍ የመቀየር አቅም ይኖረዋል እየተባለ ነው፡፡
የኦማር አል በሽር አገዛዝ በሕዝባዊ አመፅ ከመወገዱ በፊት ሩሲያ በሱዳን ፖለቲካ ትልቅ ሚና የነበራት ቢሆንም፣ አል በሽር መወገዳቸውን ተከትሎ ግን አሜሪካንን ጨምሮ ሌሎች የምዕራባውያን አገሮች፣ እንዲሁም ሩሲያና ቻይና በሱዳን ፖለቲካ ውስጥ በተለያያ ጎራ ተሠልፈዋል፡፡ ሱዳናውያን ወደ ዴሞክራሲዊ የሲቪል መንግሥት የሚያርጉትን የሽግግር ጊዜ ጥረት አደጋ ውስጥ እንደከተተው ምዕራባውያኑ ወቀሳ ያቀርባሉ፡፡
አሜሪካ፣ እንግሊዝ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስና ሳዑዲ ዓረቢያ ከተባበሩት መንግሥታት ድርጅት፣ ከአፍሪካ ኅብረት፣ እንዲሁም ከምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት ድርጅት (ኢጋድ) ጋር በመሆን በሱዳን የሲቪል መንግሥት እንዲመሠረት ጥረት እያደረጉ ሲሆን፣ ከዚህ በተቃራኒው ደግሞ ሩሲያ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ድጋፍ ታደርጋለች በሚል ወቀሳ ይቀርብባታል፡፡
ዘ ቴሌግራፍ የተሰኘው ሚዲያ ማክሰኞ ይዞት የወጣው መረጃ እንደሚያሳው ደግሞ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ ለሱዳን ፈጥኖ ደራሸ (RSF) ልዩ ኃይል በሚስጥር መሣሪያ ስታቀብል እንደነበር የሚያመላክት መረጃ መገኘቱን አስታውቋል፡፡
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አንቶኒዮ ብሊንከን ሁለቱ ኃይሎች የቀሰቀሱት ጦርነነት ቆሞ ወደ ስምምነት እንዲያመሩ በተደጋጋሚ በሚያወጧቸው መግለጫዎች እየወተወቱ ነው፡፡
በሌላ በኩል የግብፅ ፕሬዚዳንት አልሲሲ ከጄኔራል አል ቡርሃን ጋር በመሠረቱት ወዳጅነትና ካላቸው ሰፊ የድንበር አዋሳኝ፣ የንግድ እንቅስቃሴና በወታደራዊ ሕይወት ታሪክ ቁርኝታቸው በሱዳን ወታደራዊ ሥርዓቱ እንዲቆይ ያላቸው ፍላጎት የተጀመረው ጦርነት በቶሎ እንዳይቋጭ እንቅፋት እንዳይፈጥር ተሰግቷል፡፡
በሱዳን ጦርነቱ መቀስቀሱን ተከትሎ የአፍሪካ ኅብረት የሰላምና ፀጥታ ምክር ቤት እ.ኤ.አ. እሑድ ሚያዝያ 16 ቀን በአዲስ አበባ ባደረገው ድንገተኛ ስብሰባ፣ ጦርነቱን ለማባባስ የሚደረገውን የውጭ ኃይሎች ጣልቃ ገብነት አጥብቆ እንደሚቃወም አስታውቋል፡፡
ጦርነቱ እየተባባሰ በመሆኑ አሁን ካለበት ወደ ባሰ አደገኛ ሁኔታ ውስጥ እንዳይገባ ሥጋት የገባቸው አካላት፣ ሐሳባቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች እያስደመጡ ናቸው፡፡
በተመሳሳይ ጦርነቱ እንዲቆም ሁሉም አገሮችና ኃይሎች ጥረት ካላደረጉ ሱዳን ከምታዋስናቸው የጎረቤት አገሮች ጋር ያላት ግንኙነት አደጋ ውስጥ እንደሚጥለው፣ በከፍተኛ የስደተኛ ቁጥር የሚታወቀውን የምሥራቅ አፍሪካ ቀጣና የፍልሰት መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንደሚጨምረው በሥጋት እየተነገረ ነው፡፡