ለዓመታት ሲያወዛግብ የቆየው የንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች አዋጅን ለማሻሻል የተረቀቀው አዲስ አዋጅ ሌላ ውዝግብ ማስነሳቱ ተሰማ፡፡ በ1995 ዓ.ም. የወጣው አዋጅ ቁጥር 341/1995 ሥራ ላይ ከዋለበት ማግሥት ጀምሮ አዋጁ ብዙ ችግሮች ያሉበት ነው በሚል የተለያዩ ትችቶች ሲሰነዘሩበት ቆይቷል፡፡
በአዋጁ ላይ ያሉትን ችግሮች ለማረምና ክፍተቶችን ለመድፈን ታስቦ አዋጁን የማሻሻል ጥረት ከተጀመረ ከአሥር ዓመታት በላይ አስቆጥሯል፡፡ በተለይ ባለፉት ስድስት ዓመታት አዋጁን ለማሻሻል የተለያዩ ረቂቆች ተሰናድተው ከዛሬ ነገ ይፀድቃሉ ተብሎ ቢጠበቅም ሳይሳካ መቆየቱም ይታወሳል፡፡
በረቂቅ አዋጁ የማሰናዳት ሒደት ውስጥ ቀደም ብሎ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር፣ ከዚያም ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የሚመራውና የንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አመራሮች የተሳተፉበት ኮሚቴ ከአንድ ዓመት ተኩል በፊት የመጨረሻ የተባለውን ረቂቅ ይፋ ማድረግ ችሎ ነበር፡፡
የመጨረሻ የተባለው ረቂቅ አዋጅ የንግድና የኢንዱስትሪውን ዘርፍ በማጣመር፣ ‹‹የንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት አዋጅ›› የሚል ስያሜ አግኝቶ የነበረ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረትም ይፀድቃል ተብሎ ይጠበቅ ነበር፡፡
ሆኖም ግን ባለፈው ዓመት ይፅድቃል ተብሎ ስምምነት ተደርሶበት የነበረውን ረቂቅ አዋጅ ወደ ጎን ተገፍቶ ሌላ አዲስ አዋጅ በቅርቡ ተረቆ መቅረቡ፣ በተለያዩ ንግድ ምክር ቤቶችና የዘርፍ ምክር ቤቶች በኩል ተቃውሞ አስነስቷል፡፡ ይህንን ረቂቅ በብርቱ ከተቃወሙትና በዚህ መልኩ አዋጁ መውጣት የለበትም ብለው ከሚሟገቱት ውስጥ በዋናነት የሚጠቀሰው የኢትዮጵያ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትና የዚህ ምክር ቤት አባል የሆኑ የክልል ምክር ቤቶች ናቸው፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ረቁቁ የከተማውን ምክር ቤቶች ያቀጭጫል በማለት አቤቱታውን እያሰማ ነው።
የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንትና የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤት የቦርድ አባል አቶ አበባየሁ ግርማ፣ በተለይ ኢንዱስትሪውን ወይም ዘርፉን ነጥሎ የተረቀቀውና የንግድ ምክር ቤቶች ማቋቋሚያ አዋጅ ተብሎ የተዘጋጀውን ረቂቅ ያልገመቱት እንደሆነባቸው ለሪፖርተር ገልጸዋል፡፡ ዋነኛው ምክንያትም ኢንዱስትሪ ዘርፉን አግልሎ የተዘጋጀ ረቂቅ አዋጅ በመሆኑ ነው፡፡
‹‹ይህ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ኢንዱስትሪውን አግልሎና ጨፍልቆ የተዘጋጀ ነው፡፡ እስከዛሬ ድረስ ሲደከም የነበረው ንግድና ዘርፍ (ኢንዱስትሪ) በአንድ አዋጅ ሥር ሆነው በጋራ እንዲሠሩ ለማስቻል ቢሆንም፣ አዲሱ ረቂቅ ግን ከዚህ ውጪ ሆኖ ንግድ ዘርፉን ብቻ ይዞ አዋጁ መረቀቁ እኛን በእጅጉ አስደንግጧል፤›› የሚሉት አቶ አበባየሁ፣ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ከአገር አቀፍ ጀምሮ ታች ወረዳና ከተማ ድረስ ያለውን የዘርፍ አደረጃጀት በሙሉ የሚያፈርስ መሆኑን አብራርተዋል።
በቀደመው አዋጅ የዘርፍ ምክር ቤቶች በየደረጃው ያላቸውን ውክልና የሚያሳይ ዘርፉን ወይም ኢንዱስትሪውን በመወከል ለአባሎቻቸው ሲያበረክቱ የነበረውን አገልግሎት በሙሉ የሚያቋርጥ በመሆኑ፣ ረቂቅ አዋጁ በየደረጃው በተቋቋሙ ዘርፍ ምክር ቤቶች ሁሉ ተቀባይነት እንደሌለው አመልክተዋል፡፡
በአዲሱ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ አንድ ቦታ ስለዘርፍ ምክር ቤቶችም ሆነ ስለኢንዱትሪው ዘርፍ የሚጠቀስ ቃል አለመካተቱን የገለጹት አቶ አበባየሁ፣ ‹‹እዚህ ድምዳሜ ላይ የተደረሰው ምን ታስቦ እንደሆነ እንኳን ማወቅ አለመቻላቸውን ያመለክታሉ፡፡ የረቂቅ አዋጁ አጠቃላይ ይዘት ሲታይ የንግድ ዘርፉን በሚወክሉ አካላት የተሰናዳ የሚመስል ነው፤›› ሲሉ ግምታቸውን ገልጸዋል።
‹‹በየትኛው አገር ኢንዱስትሪውን ያገለለ የንግድ ምክር ቤት የለም፤›› የሚሉት አቶ አበባየሁ፣ በአብዛኞቹ አገሮች የተቋቋሙ ምክር ቤቶች የንግዱን ማኅብረሰብ በግልጽ የሚወክሉና ስያሜያቸውም ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት መሆኑን ያስረዳሉ። በመሆኑም እንደ አዲስ የተረቀቀው አዋጅ በዚሁ አግባብ መዘጋጀት ነበረበት ሲሉ ቅሬታቸውን ገልጸዋል፡፡
ረቂቅ አዋጁን የማዘጋጀት ሒደት በዚሁ መንፈስ ረቂቁ ሲካሄድ እንደነበር የሚያስታውሱት ምክትል ፕሬዚዳንቱ፣ ምክንያቱን በማያውቁት ግልጽ ያልሆነ መንገድ ቀደም ሲል ተጠናቆ የነበረው ረቂቅ አዋጅ ተገፍቶ የኢንዱስትሪ ዘርፉን የማይወክል ‹‹የንግድ ምክር ቤት›› የሚል ስያሜ ብቻ የተሰጠው አዲስ ረቂቅ አዋጅ፣ በድንገት ለውይይት መቅረቡን ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ዘርፉን ያገለለ ረቂቅ አዋጅ እንዴት ሊዘጋጅ እንደቻለ መረጃ እንኳን እንደሌላቸው የጠቀሱት አቶ አበባየሁ፣ ረቂቅ አዋጁ ኢንዱስትሪውን በማግለል መዘጋጀቱ አግባብ እንዳልሆነ ጠቅሰዋል፡፡
የኢትዮጵያ አገር አቀፍ የዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ይህንኑ ጉዳይ ለሚመለከታቸው መንግሥታዊ አካላት ያሳወቀ ሲሆን፣ አባሎቻቸውም ህልውናችንን የሚያሳጣና ያልተጠበቀ ክስተት እንደገጠማቸው በማሳወቅ ላይ እንደሚገኙ ጠቁመዋል፡፡
በዚሁ ጉዳይ ዙሪያ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር የጻፉት ደብዳቤም፣ ‹‹በንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ተዘጋጅቶ የቀረበው ረቂቅ ሕግ ከወረዳ እስከ አገር አቀፍ ድረስ ያሉትን አምራች ማኅበራት በሙሉ የሚያጠፋ ሆኖ በማግኘታችን እጅግ በጣም አዝነናል፡፡›› ይላል፡፡
በሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ የተሰናዳው ረቂቅ ሕግ፣ የኢትዮጵያ አምራች ማኅበረሰብ ሙሉ በሙሉ የማይቀበለው መሆኑ እንዲታወቅላቸውና ረቂቁ በዚህ ይዘቱ ሊፀድቅ እንደማይገባ በዚሁ በደብዳቤያቸው አመልክተዋል፡፡
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤትም ሆነ፣ በተለያዩ ደረጃዎች በተቋቋመው የንግድና ዘርፍ ምክር ቤታችን ውስጥ ብልጫ ያለው የአባላት ቁጥር የያዘው የዘርፉ ምክር ቤቶች አባላት በመሆናቸው፣ ይህ ረቂቅ በብዙ ሺዎች የሚቆጠሩ አባላት ጥቅም የሚጎዳ መሆኑን ከአቶ አበባየሁ ማብራሪያ ለመረዳት ተችሏል፡፡ ረቂቁን በማዘጋጀት ሒደት ላይ ከዘርፍ ምክር ቤቶች የተወከሉ አባላትን ገለል የማድረግ አሠራር ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስተዋለ መሆኑን በመጥቀስ፣ እንዲህ ያለ አግላይ ሒደትን መከተል በራሱ ትልቅ ግድፈት መሆኑን አቶ አበባየሁ ገልጸዋል፡፡
ከዘርፍ ምክር ቤት የተወከሉ አባላትን በማግለል፣ አዲስ በተዋቀረ ኮሚቴ አዋጁን የማርቀቅ አካሄድ በራሱ አምራች ኢንዱስትሪው ላይ ጫና ለማድረግ የታሰበ መሆኑን እንደሚያሳይም ጠቅሰዋል፡፡ በአጠቃላይ ሲታይ ረቂቁ የተወሰኑ የንግድ ዘርፍ ተወካዮችን ይዞ የተሰናዳ ስለመሆኑ የሚናጉሩት አቶ አበባየሁ፣ ‹‹ይህ መሆን ያልነበረበት ተግባር ነው፤›› ብለዋል፡፡
ችግሩ የኢትዮጵያ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አሰናድቶት የነበረውን ረቂቅ አዋጅና ያለበትን ሁኔታ ደብቆ መቆየቱም ለዚህ ረቂቅ መውጣት የራሱ አስተዋጽኦ እንደነበረው በመግለጽ፣ መንግሥት ሁሉንም ወገን የሚያስማማ ሕግ ማውጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል፡፡
ይህ ጉዳይ በቀላሉ መታለፍ የሌለበት፣ የበለጠ ትኩረት ሊሰጠው የሚገባውን የኢንዱስትሪ ዘርፍ ውክልና የሚያሳሳ በመሆኑ፣ አሁንም በረቂቅ ዝግጅቱ ዋነኛ ባለድርሻ ለሆነው የንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር በደብዳቤና በአካል አቋማቸውን እያሳወቁ መሆኑን ጠቁመዋል።
ይህ አቤቱታቸው የማይሰማ ከሆነ ግን ኢንዱስትሪ ወይም ዘርፉ ራሱን ችሎ የራሱን ምክር ቤት እንዲያቋቁም የሚገደድ መሆኑን ተናግረዋል። የኢንዱስትሪ ምክር ቤቱ እንዲቋቋም የኢትዮጵያ አገር አቀፍ ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ውሳኔ የሰጠበት መሆኑን የገለጹት አቶ አበባየሁ፣ ይህ ምክር ቤት የሚቋቋምበትን ረቂቅ አዋጅ በማሰናዳት ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር እንዲደርሰው ይደረጋልም ብለዋል፡፡ ይህ ተፈጻሚ እንዲሆንም ጉዳዩ በቀጥታ ለሚመለከተው የኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ማሳወቃቸውን ጠቁመዋል፡፡
በመሆኑም ንግድና ዘርፉ የሚለያዩ ከሆነ፣ አሁን የተሰናዳው ረቂቅ አዋጅ ከመፅደቁ በፊት፣ የኢንዱስትሪ ምክር ቤት በአዋጅ እንዲቋቋም መፈቀድ እንዳለበት የኢትዮጵያ ዘርፍ ምክር ቤት ፅኑ አቋም መሆኑን ተናግረዋል።
የዘርፍ ምክር ቤቶችን ህልውና ለማስጠበቅ በየደረጃው የሚያደረጉት ጥረት ካልተሳካ ግን፣ በአገር አቀፍ ደረጃ ድምፃቸውን ለማሰማት አንድ ወር ባልበለጠ ጊዜ ውስጥ ለተቃውሞ አደባባይ ለመውጣት ማቀዳቸውን አቶ አበባየሁ ለሪፖርተር ገልጸዋል።
በአዋጅ ቁጥር 341/1995 በወጣው አዋጅ መሠረት ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች የጋራ ሀብት ማፍራታቸውን በማስታወስ፣ አዲስ የተዘጋጀው ረቂቅ አዋጅ ከዚህ አኳያም ብዙ አወዛጋቢ ጉዳዮች እንደሚፈጥር ሥጋታቸውን ገልጸዋል።
በየደረጃው ያሉ የዘርፍ ምክር ቤቶቹ ሠራተኞች ጉዳይም የሚያሳስባቸው መሆኑን የገለጹት አቶ አበባየሁ፣ ረቂቅ አዋጁ በተለይም የዘርፍ ምክር ቤት ለአባላቶቹ የሚሰጣቸውን አገልግሎቶች በሙሉ እንዲቋረጡ የሚያደርግ በመሆኑ፣ አሁን ባለው ይዘት ፈጽሞ መፅደቅ እንደሌለበት ጉዳዩ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ አጽንኦት እንዲሰጡ አሳስበዋል፡፡
አዲሱ ረቂቅ አዋጅ የዘርፉ ንግድ ምክር ቤቶቻቸውን ህልውና ከማሳጣቱ ባሻገር፣ አንዳንድ ድንጋጌዎቹ ከነባሩም ሆነ ይፅድቃል ተብሎ ይጠበቅ ከነበረው ረቂቅ አዋጅ የተለየ ይዘት ያለው ስለመሆኑ ለማወቅ ተችሏል፡፡ ረቂቁ ዘርፍ ምክር ቤቱን ብቻ ሳይሆን፣ እንደ አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ያሉ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶችን ጭምር ያሳሰበ ነው፡፡
በተለይ ከዚህ ቀደም የክልል፣ የወረዳ፣ የከተማ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም አገር አቀፉ ዘርፍ ምክር ቤት በቀጥታ ይሰጣቸው የነበረውን ሥልጣን ለኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት የሰጠ መሆኑ እንደ ክፍተት ታይቷል፡፡ የአገር አቀፉ የክልልና የከተማ ዘርፉ ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም ንግድ ዘርፍ ምክር ቤቶች በቀጥታ ከውጭ አቻ ምክር ቤቶችና ሌሎች ንግድና ኢንቨስትመንትን ከሚመለከቱ የውጭ ተቋማት ጋር ያደርጉ የነበረው ግንኙነትን አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ያሳጣቸዋል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ከዓለም አቀፍና ከተለያዩ አገሮች የንግድ ምክር ቤቶች፣ እንዲሁም በዓለም አቀፍ ደረጃ ከሚገኙ የንግድና የኢንቨስትመንትን ከሚያስፋፋ አካላት ጋር ግንኙነት መፍጠር የሚችለው የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት እንደሆነ ተመላክቷል፡፡
ይህም እንደ አዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤት ያሉ የከተማና የወረዳ፣ እንዲሁም የክልል ንግድ ምክር ቤቶች በቀጥታ ዓለም አቀፍ ተቋማት ጋር ግንኙነት መፍጠር እንደማይችሉ ያመለክታል፡፡ በዚህ ረቂቅ አዋጅ ንግድና ኢንቨስትመትን ለማስፋፋት የክልል፣ የወረዳና የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች የተሰጣቸው ሥልጣን በአገር ውስጥ የተገደበ ብቻ መሆኑ ተቃውሞ ያስነሳ ሲሆን፣ ጠንካራ ምክር ቤቶችን የሚያቀጭጭ ይሆናል ተብሏል፡፡
ከአገር ውጭ የንግድ ግንኙነት ለማድረግና የንግድ ትርዒትና ተያያዥ ሥራዎችን ለመሥራት የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትና ንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር አውቀውት መሆን እንዳለበት መደንገጉ፣ ሌላው በረቂቅ አዋጁ ላይ የሚቀርብ ተቃውሞ ነው። ይህ ድንጋጌ እንደ አዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ምክር ቤትና ሌሎች መሰል ምክር ቤቶች እስካሁን የፈጠሩትን ዓለም አቀፋዊ ግንኙነቶች የሚቀለብስ፣ የውጭ ጉዞዎችንም በራሳቸው መንገድ እንዳያከናውኑ የሚገድብ ስለመሆኑ፣ በጉዳዩ ዙሪያ ያነጋገርናቸው የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት አባላት ገልጸዋል፡፡
በዚህ ረቂቅ አዋጅ ዙሪያ ያነጋገርናቸው አዲስ አበበ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ዋና ጸሐፊ አቶ ሺበሺ ቤተ ማርያም በበኩላቸው፣ አዲሱ ረቂቅ አዋጅ ለንግድና አገልግሎት ዘርፍ ዕውቅና መስጠቱ መልካም ነው ይላሉ፡፡ ሥራ ላይ ባለው አዋጅ የንግድና አገልግሎት ዘርፉ በአግባቡ አለመወከላቸውን አስታውሰው፣ አሁን ይህንን ስህተት አርሞ በተለይ ለንግድ ዘርፉ የሰጠው ዕውቅና በመልካም የሚታይ መሆኑንም አመልክተዋል፡፡
ሆኖም የንግድ ምክር ቤቶች አደረጃጀትና ሥልጣንን በተመለከተ በአዲሱ ረቂቅ ውስጥ የተደነገጉ ድንጋጌዎች አስደንጋጭ የሚባሉ መሆናቸውን ጠቅሰዋል፡፡ የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት ይህን በማየት ቦርዱ ከአባላትና ከተለያዩ አካላት ጋር በመወያየት አቋም የያዘ ሲሆን፣ በዚሁ መሠረት በረቂቁ ላይ ያለውን ቅሬታ ለንግድና ቀጣናዊ ትስስር ሚኒስቴር ማቅረቡንም አቶ ሺበሺ ገልጸዋል፡፡
የአዲስ አበባ ንግድና ዘርፍ ማኅበራት ምክር ቤት በአዲሱ ረቂቅ ላይ ተቃውሞ ካቀረበባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ፣ እስካሁን በከተማ ንግድ ምክር ቤት በአባልነት የታቀፉት እንደ ባንክ፣ ኢንሹራንስ፣ አየር መንገድና የመሳሰሉ ትልልቅ ተቋማት በቀጥታ የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤት አባል እንደሚሆኑ የሚገልጸው ድንጋጌ ነው፡፡ ይህ ድንጋጌ አግባብ ያልሆነና መተግበር የሌለበት እንደሆነ ዓለም አቀፋዊ አሠራሮችን በምሳሌነት በማቅረብ ይሞግታሉ፡፡
ከዚህም ሌላ የከተማ ንግድ ምክር ቤቶች የውጭ ግንኙነት የንግድ ትርዒትና የመሳሰሉ ተግባሮችን ለማከናወን የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ማስፈቀድ እንደሚገባቸው የሚገልጽው ድንጋጌ፣ ሌላው ተቃውሞ ከቀረቡባቸው ጉዳዮች መካከል የሚጠቀስ ነው፡፡ በተለይ እንደ አዲስ አበባ ያሉ ንግድ ምክር ቤቶችን ህልውና የሚገፉና አጠቃላይ አሠራሩን ወደ ኋላ የሚጎትቱ ሆኖ በመገኘቱ፣ ረቂቁ በዚህ መልኩ መዘጋጁቱ አግባብ እንዳልሆነ ማሳወቃቸውንም አቶ ሺበሺ ገልጸዋል፡፡
የንግድ ምክር ቤቶቹ አባላትን በሚመለከት በረቂቁ ውስጥ የተደነገገውም ድንጋጌ እንደ ምክር ቤታቸው አግባብ አለመሆኑንም አመልክተዋል፡፡ በረቂቁ አባልነት አስገዳጅ ይሆናል መባሉ ሕገ መንግሥቱን ጭምር የሚፃረር በመሆኑ፣ ንግድ ምክር ቤታቸው የማይቀበለው መሆኑን አመልክተዋል፡፡ አባልነት ግዴታ ከሚሆን በፈቃደኝነት ላይ የተመሠረተ መሆኑ፣ ብዙ ጥቅም ያለው ሲሆን ንግድ ምክር ቤቶች አባላትን በማስገደድ ገቢያቸውን ከማሳደግ ይልቅ፣ በአገልግሎታቸው አባሎቻቸውን ማብዛት የተሻለ በመሆኑም ይጠቅሳሉ፡፡ በመሆኑም ንግድ ምክር ቤታቸው፣ አባልነት አስገዳጅ ይሁን የሚለውን እንደማይስማበት በማሳወቅ ይህ እንዲሻሻል ለሚኒስቴሩ በጽሑፍ ጭምር አሳውቀዋል፡፡
ሌሎች ሊታረሙ ይገባል ያሏቸውንም አንቀጾች ማብራሪያ ችግር በመስጠት አቤት ማለታቸውን ከአቶ ሺበሺ ገለጻ ለመረዳት ተችሏል፡፡ የአባልነት ጉዳይን በተመለከተ አቶ አበባየሁም አስገዳጅ መሆኑ ተገቢ አይደለም በማለት የአቶ ሺበሺን ሐሳብ ተጋርተዋል፡፡
አቶ አበባየሁም፣ አዋጁ እስካሁን ሲታሰብ እንደ ነበረው ንግድና ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ተብሎ ቢወጣ ተቃውሞ እንደማይኖራቸው ገልጸዋል።
‹‹ስለዚህ በጋራ መሥራት ካልተቻለ ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ለማቋቋም የምናደርገውን ጥረት እንገፋበታለን፡፡ ይህም ይሳካልናል ብለን እናምናለን፡፡ ነገር ግን እዚህ ሁሉ ውጣ ውረድ ውስጥ ከምንገባ እኛ ያለንበት ሆኖ ረቂቅ አዋጁ እኛን ባካተተ መልኩ የንግድ ኢንዱስትሪ ምክር ቤት ተብሎ ቢስተካከል መልካም ነው፤›› ብለዋል።