Friday, June 14, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -

ልናገርብልፅግና ዋነኛ ፈተናው የሆነውን የገዛ ራሱን ችግር ይታገል!

ብልፅግና ዋነኛ ፈተናው የሆነውን የገዛ ራሱን ችግር ይታገል!

ቀን:

በገለታ ገብረ ወልድ

አንባብያን እንኳን ለትንሳዔና ለኢድ አልፈጥር በዓል አደረሳችሁ በማለት ወደ ጉዳዬ ልግባ፡፡ በዚህ ጽሑፍ “ኦሊጋርኪ/Oligarchy” የሚለውን ቃል ተጠቅሚያለሁ፡፡ “A form of government in which all power is vested in a few persons or in a dominant class or clique; government by the few.” የሚለውን የመዝገበ ቃላት ብያኔ መሠረት አድርጌ እንደሆነ ለአንባቢያን ስገልጽ፣ አንባቢያን ነገሮችን መሬት ላይ ካለው ሀቅ አኳያ እንዲመረምሩት ለማነሳሳትም ነው፡፡

እውነት ለመናገር ብልፅግና በታሪክ አጋጣሚ አገራችንን እየመራ ስላለ ከችግሩ እንዲወጣና አካሄዱን እንዲያርም ከመጎትጎት አልቦዝንም፡፡ ነገር ግን ብልፅግና የተስፋ ዳቦ እየሆነ ነው ያስቸገረው፡፡ ሲጀምር በአገር አንድነትና ሉዓላዊነት ላይ የማይደራደር፣ በሕዝቦች ብዝኃነትና ጠንካራ መስተጋብር መፍጠር ላይ የማያወላዳ፣ ብሎም ለልማትና ለዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ የማይተኛ እንደሆነ በብዙዎች ቢታመንም፣ እንደ ቃሉ ሆኖ እየተገኘ አይመስልም፡፡ ከፈተናና ከቀውስ ወጥቶ ራሱንም አገርንም ዕፎይታ እንዳልሰጠም እየታየ ነው፡፡

- Advertisement -

የብልፅግና ትልቁ ፈተና ደግሞ በውስጡ ካለው አድርባይነትና አፈንጋጭነት የሚመነጭ ነው፡፡ በመሠረቱ ምንጊዜም ለውጥ ሲመጣ ዋነኞቹ እንቅፋቶች የሚደቀኑት፣ ከውጫዊ ሁኔታ ይልቅ በውስጥ ጥንካሬ ማጣት ላይ የሚጠነሰሱት ችግሮች ናቸው የሚባለውም ለዚሁ ነው፡፡ እናም በረጋ መንፈስና ኃላፊነት በተሞላበት መንገድ ውስጡን ይፈትሽ ዘንድ እንደ ዜጋ የመሰለኝን ለመጠቆም እወዳለሁ፡፡

 ሰላም፣ ዴሞክራሲና ብልፅግና ዕውን የሚሆኑት ሕግ አውጪው፣ ሕግ ተርጓሚውና አስፈጻሚው በሚገባ እየተናበቡ ሥራቸውን ሲያከናውኑና የቁጥጥር ሥርዓቱ ጠበቅ ያለ ሲሆን ነው፡፡ ዜጎች በሕግ ፊት እኩል መሆናቸውና በሁሉም አካባቢዎች ደኅንነታቸው በተግባር ሲረጋገጥ ጭምር ነው፡፡ ይህን ቁልፍ ተግባር አጠናክሮ መተግበር ደግሞ የመንግሥት አልፋና ኦሜጋ መሆን አለበት፡፡

አሁን በተያዘው አካሄድ ግን ፌዴራል መንግሥቱና ክልሎች፣ ክልሎች እርስ በርሳቸው የማይተማመኑ፣ ቃላቸው የሚጣረስ፣ የመንግሥት አካሄድም የማይታወቅና ግልጽነት የሌለው እየሆነ ነው፡፡ በሥርዓቱ ውስጥ ያሉ ትልልቅ ሰዎች ሳይቀሩ አፍ ከልብ ሆነውና ተደማምጠው ከመሥራት ይልቅ አስመሳይነትና አፈንጋጭነት ሥርዓቱን እንደጥንጣን እየበላው ለመሆኑም ማሳያዎች አሉ፡፡

ከለውጥ ወዲህ ተፎካካሪው ፖለቲከኛ ብቻ ሳይሆን ራሱ የብልፅግና ኃይል በሚያራምደው የተምታታና ግብታዊ ውሳኔና አለመግባባት ሁሉ፣ የፀጥታ መዋቅሩና መከላከያው ላይ ታች ሲል የሚኖረውስ እስከ መቼ ነው ብሎ መጠየቅ ግድ የሚልበት ወቅት መጥቷል፡፡ በቅርቡ እንዳጋጠመው ያለ የልዩ ኃይል ትጥቅ መፍታት መርሐ ግብርን ያህል ውሳኔ ሲወሰን ሕዝብና ራሱ ባለጉዳዩን ማሳመን ማንን ገደለ?

በመሠረቱ በየትኛውም መለኪያ የመጨረሻው የሥልጣን ባለቤት ሕዝቡ ነው፡፡ በመሆኑም በሕዝቡ ይሁንታ የፀደቁትን ሕጎች፣ ደንቦችና መመርያዎች ተግባራዊ የማድረግ፣ ሰላምና መረጋጋት እንዲፈጠር፣ በጥቅሉ የሕግ የበላይነት የነገሠባት ዴሞክራሲያዊት ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ ከሕዝብና ከወኪሎቹ ጋር እየመከሩና እየተደማመጡ ከመሥራት ውጪ መንገድ የለም፣ ሊኖርም አይገባም፡፡

እነዚህን ሥርዓታዊ አካሄዶች ግን አንዳንድ አመራር ተብዬዎችና ኦሊጋርኪዎች እየናዷቸው ሲሆን፣ ብልፅግና እንደ ተቋምም ሲያስተካክላቸው አልታየም፡፡ እንዲያውም ከመሻሻል ይልቅ በችግሮች ውስጥ እየደጋገሙ መመላለስ እየታየ መሆኑ በአገር ላይ ሥጋት እየደቀነ ነው፡፡ ስለሆነም የውስጥ መተማመንንና ተመጋጋቢነትን ማሳደግ ትኩረት ሊሰጠው ይገባል፡፡

ዛሬም ሆነ ነገ መንግሥት በውስጡ የተሰገሰጉ መርህ አልባዎችን ማፅዳት ካልቻለ፣ ችግሩ ይቀጥላል እንጂ ሊታረም አይችልም፡፡ የበላይ አለቆቹን ሲመለከት እንደ ውሻ ጭራውን እየቆላና በአድርባይነት እየተሸነጋገለ፣ ሕዝቡ ጋ ሲወርድ ግን ሌላ ትብትብ ሲተረትር የሚውለው የብልፅግና ሰው መብዛቱን አለመጠርጠር ከታሪክ አለመማር ነው፡፡

 አሁን በሚታየው ሁኔታ በብልፅግና ቤት ሕዝበኝነት፣ ብሔርተኝነትና መርህ አልባነት ክንፍ አውጥተው መብረር ይዘዋል፡፡ ዴሞክራሲያዊ ማዕከላዊነትን እንደ መርህ አለመቁጠርና በየራስ ፈረስ መጋለቡም ተባብሶ ቀጥሏል፡፡ ይኼ ደግሞ አገርን ወደ ቀውስ ይወስድ እንደሆን እንጂ ለማንም አይጠቅምም፡፡ እናም ለቀውስ ሁሉ መፍቻ መንገዱ ከራሱ ከገዥው ፓርቲ የውስጠ ዴሞክራሲ ትግል ሊጀምር የገባል፡፡

መንግሥትና ገዥው ፓርቲ ብልፅግና በብዙ ፈተና ውስጥ በሚገኙበት በዚህ ወሳኝ ወቅት እንኳን፣ ከራሳቸውና ከቢጤዎቻቸው ጥቅም በላይ የአገር ጉዳይ ግድ የማይሰጣቸው ደካሞች በየመዋቅሩ ውስጥ እየታዩ ነው፡፡ ያላመኑበትን ለማስፈጸም ተማምለው የሚንሸራተቱ ድንክዬዎችም በዝተዋል፡፡ ከጎን ያለው የዩቲዩብ አጫፋሪና ለሕዝብ ጥቅም ደንታ የሌለው እየበዛ የሄደውም በዚህ ክፍተት ላይ ተመሥርቶ ነው፡፡

ከአገር አጠቃላይ ብሔራዊ ጥቅም ይልቅ የራሳቸውንና የቢጤዎቻቸውን ምቾት ብቻ ስለሚያስቀድሙ፣ ለእነሱ ሕዝብ ማለት ምንም አይደለም፡፡ ሕዝብን በከፍተኛ የአገር ፍቅር ስሜት፣ በዳበረ ዕውቀትና ክህሎት ለማገልገል አሁንም ብቃቱ ያላቸው በርካታ ዜጎች እያሉ፣ እንዲህ ዓይነቶቹ የኦሊጋርኪዎች ስብስብ መንግሥትን መፈናፈኛ እያሳጡት መሆኑን ማወቅና ማስተካከል ይጠበቅበታል፡፡

ኦሊጋርኪዎቹ ለዜጎች ሰብዓዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶችም ሆነ ለአገር አንድነት ደንታ የላቸውም፡፡ ብቻ በብሔር እየማሉና እየተገዘቱ ጥቅማቸውን ማሳደድ፣ ካልበላሁት ጭሬ ልድፋው ማለት ነው የሚቀናቸው፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግ ኃላፊነታቸው የሆኑ ተቋማት ውስጥ ሳይቀር ተሰግስገው እየመዘመዙን መሆኑንም እያየን ነው።

በየአካባቢው የሕዝብን አቤቱታና እሮሮ በማፈን፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በማድበስበስና ያልተሠራውን ሁሉ በወሬ በመሙላት መንግሥት በሕዝብ ዘንድ እንዳይታመን ከማድረግም አይቦዝኑም፡፡ እናም እንደ መንግሥትም (በሦስቱም መንግሥታዊ ክንፎችና በየደረጃው) ሆነ ብልፅግና እነዚህን አካላት ሳያስተካክሉና ሳያጠሩ ሥርዓታዊ ለውጥ ለማምጣት እንደምን ይቻላል?

በተለይ የመንግሥት አስፈጻሚ አካላት በክልልም ሆነ በቦታ የተቀመጡበት ሥፍራ ይለያይ እንጂ፣ ዓላማቸው ለሕዝብ አገልግሎት መስጠት ነው፡፡ መሬት ላይ ያለው እውነት እንደሚያሳየው ግን በተለያየ አገር እንደሚሠሩ ሁሉ ውህደትና መናበብ የጎደለው አፈጻጸም ነው ያለው፡፡ በአንዳንዱ አካባቢ በግል ጥቅምና ሌብነት ላይ ሲርመጠመጥ የሚውለውም ትንሽ አይደለም፡፡

በመላ አገሪቱ በመንግሥታዊ ተቋማት፣ በትምህርት ተቋማት፣ በጤና ተቋማት፣ በማዘጋጃ ቤታዊ አገልግሎቶች፣ በመሬት አስተዳደር፣ በግንባታ ፈቃድ፣ በገቢዎችና ጉምሩክ፣ በወረዳና በክፍላተ ከተሞች፣ በንግድ ፈቃድና ምዝገባ፣ በትራንስፖርት፣ በግዥና ጨረታ፣ በፋይናንስ ተቋማት፣ በፍትሕ አካላት፣ ወዘተ. ውስጥ አሁንም ቀላል የማይባል የመልካም አስተዳደር ጉድለት ይስተዋላል፡፡ ይህ አካሄድ ደግሞ በኦሊጋርኪዎች መፈጸሙ ብቻ ሳይሆን ሕዝብንም እያመረረና እየቆሰለ ነው፡፡

ለሙስና መስፋፋት አሉታዊ ሚና የሚጫወቱትን ነጣቂዎች ከተነጠቀውና እየተነጠቀ ከሚገኘው ሕዝብ በላይ ማንም የሚያውቃቸው የለም፡፡ ሥርዓቱ ደግሞ ሕዝቡን እያዳመጠ ውግንናውን ለብዙኃኑ ማረጋገጥ ካልቻለ ሥርዓታዊ ሙስና ወደ መምሰል ነው የሚሄደው፡፡ ስለሆነም በእያንዳንዱ ተግባርም ሆነ አፈጻጸም ላይ ሕዝብን እያሳተፉ ከመታገል ውጪ አማራጭ የለም።

እውነት ለመናገር ኦሊጋርኪዎች አቋምና ዓላማ ብቻ አይደለም ያላቸው፡፡ መንገዳቸውም የጥፋትና የአደናቃፊነት ነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ የጥፋት ኃይሎች ሀቀኛ ሠራተኞችን ጭምር እያሸማቀቁ የተጀመሩ የለውጥና የብልፅግና ሐሳቦችንም ለማክሸፍ አይቦዝኑም፡፡ አጥፊዎች የሐሰት ሪፖርቶችን በመፈብረክ ያልተሠራውን እንደተሠራ ማቅረባቸውም ሕዝብና መንግሥትን ክፉኛ የሚለያይ ነው፡፡

በዚህ ጽሑፍ ርዕስ ላይ እንደተገለጸው ኦሊጋርኪዎቹ (ከገዥው ፓርቲ በተፃራሪ የቆሙቱ ውስጥ ጣውንቶች) ከባድ ናቸው። የመንግሥትን ሚዲያዎች ሳይቀር ጠልፈው ማደናገር ብቻ ሳይሆን፣ አጠቃላይ ለውጡንም ሆነ አገርን ከሚጠሉ ኃይሎች ጋር እየተሻረኩ ሕዝብ ይበድላሉ፡፡ ከውስጥ ያለው ጥቅምም እንዳይቀርባቸው እየቦጠቦጡ፣ ለውጡ እንዲቀለበስም ይፍጨረጭራሉ፡፡ በተጨባጭ በአንዳንድ ማሻሻያ ዕርምጃዎች (ሰሞኑን የፀጥታ ኃይሎችን አቀናጅቶ ለአገር እንዲሠሩ የማድረግ ጥረት መልካም ቢሆንም፣ ከውስጥ በወጣ መረጃ አፍራሽ መስሎ እንደታየው) ላይ እየታየ ያለው እውነትም ይኼው ነው፡፡

አሁንም ኦሊጋርኪዎቹ ለውጡም ሆነ መጪው ጊዜ ከቀውስ እንዲወጣ አይፈልጉም፡፡ የመንግሥት አሠራር ለሕዝብ ግልጽና ተጠያቂነት እንዲኖረው ማድረግም አይፈልጉም፡፡ በአንድ በኩል ሌብነቱና የሴራ ፖለቲካው እንዳይጋለጥባቸው፣ በሌላ በኩል ሥርዓቱ ዴሞክራሲያዊነትን እንዳይላበስ ይኮትናሉ፡፡ የመንግሥት መገናኛ ብዙኃን ሳይቀሩ ተዓማኒነት የሌላቸውና ልፍስፍስ እንዲሆኑ የሚሠሩ ኦሊጋርኪዎችም አይጠፉም፡፡

በየአካባቢው ሕዝቡ በተደማመረ ምሬት መንግሥትን እንዲያጨናንቅ የሕዝብን አቤቱታና እሮሮ በማፈን፣ መፍትሔ የሚያስፈልጋቸውን ችግሮች በማድበስበስና ያልተሠራውን ተሠራ በማለት ሲያውኩም ይታያሉ፡፡ የሕዝብ አገልጋይነት መንፈስ በመንግሥታዊ ተቋማት ውስጥ እንዲኮሰምንና ጠባብነትና መንደርተኝነት እንዲስፋፋ በማድረግ፣ ሕዝብ በየደረሰበት ቦታ ሁሉ ምሬት እየተፈጠረበት አገሩን እንዲጠላ ሲደረግ መታገል ካልተቻለ ለውጡ ሥር ሊሰድ አይችልም፡፡

በየትኛውም አገር ይሁን መንግሥታት እንቅፋቶች ሊያጋጥሙ ይችላሉ፡፡ አገራችንም በተለያዩ ጊዜያት ፈተና ሲገጥማት ነበር፡፡ ይነስም፣ ይብዛም የሚገጥሟት ፈተናዎችና ችግሮችም የሚያደርሱትን ጉዳት እያደረሱ ታልፈዋል፡፡ አሁን በፖለቲካ ተቸንካሪዎችና አክራሪ ብሔርተኞች ወደ አልተፈለገ ግጭትና ትርምስ ገብታ ዋጋ ስትከፍል ማየት ግን ብልፅግንን ብቻ ሳይሆን ሁላችንንም ሊያስቆጭ ይገባል፡፡

የኢትዮጵያ ልጆች ለዘመናት ተቻችለውና ተከባብረው ከመኖራቸው ባሻገር፣ ወደፊትም ተደጋግፈው ለመኖር በቃል ኪዳን መተሳሰራቸው ትልቅ አስተዋጽኦ ይኖረዋል፡፡ አብሮ ለመኖር የሚያውኩ የሕግ ሆኑ የአስተሳሰብ ተግዳሮቶችን መቅረፍ የሚቻለው ደግሞ በመነጋገርና በመደማመጥ ብቻ ነው፡፡ አንዳቸው ከሌላኛቸው ጋር በጋራ በሚገነቧት አገር በጋራ ተጠቃሚ እንደሚሆኑ ተማምነው የጀመሩት ጉዞ የሚፀናው ደግሞ ብልፅግና የመሰሉ አገር የሚመሩ ኃይሎች ሲጠናከሩ ነው፡፡

የኢትዮጵያ ብሔሮች ብሔረሰቦችና ሕዝቦች የተያያዙትን የብልፅግና መንገድም ሆነ አዲስ ዕይታ ለማጠናከር ተሳትፏቸው መጠናከር አለበት፡፡ ከተዛባ ትርክትና ፍጥጫ ወጥተው ለመጭው ትውልድ የሚተርፍ ጉዞ መጀመርም አለባቸው፡፡ ለዚህ ደግሞ መላው የፖለቲካ ኃይሎችና ልሂቃን ደሞክራሲያዊ ባህል ማጎልበት ሰላማዊ ትግልን ማጠናከር ግድ ይላቸዋል፡፡ መንግሥትም ውስጡን ማጥራት ብቻ ሳይሆን አካሄዱን ግልጽ ማድረግና ራዕዩን ለመላው ሕዝብ ማጋራት አለበት፡፡

ብልፅግና የመላው የአገራችን ሕዝቦች ውክልና ያለውና አገር እየመራ ያለ እንደመሆኑ በሆደ ሰፊነትና በኃለፊነት ስሜት አገር መምራት አለበት፡፡ ለዚህ ደግሞ ቅድሚያ የራሱን ኦሊጋርኪዎች ማጥራትና ማስወገድ አለበት፡፡ በኢትዮጵያ የሚገኙ ብሔሮች፣ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ቀድሞ ያጡትን መብትና ጥቅም ራሳቸው በጋራ ባፀደቁት ሕገ መንግሥት አማካይነት ተጎናፅፈውም ሆነ እያሻሻሉ መሄድ የሚችሉት ይህ የፖለቲካ መረጋጋትና ስከንት ሲኖር ነውና።

ሕዝቦች ሁሉ ራሳቸውን በራሳቸው ከማስተዳደርም በተጨማሪ በአገራቸው ሀብት እኩል የመጠቀምና በእኩልነት የመኖር መብታቸው ሊረጋገጥ የሚችለው ቅድሚያ ሰላማቸው ሲጠበቅ ነው፡፡ ልማታቸውን በማፋጠንና ዴሞክራሲያቸውን በማጎልበት ጉዟቸውን መቀጠል የሚችሉትም አንዱ ከሌላው ሳይበላለጡና ሳይገፋፉ በሥርዓቱ ላይ እምነታቸውን ሲያጠናክሩ ነው፡፡

አሁን እየታየ ያለው ሽኩቻና መበላላት ቆሞ፣ በሰከነ መንገድ ኢትዮጵያውያን ኅብረታቸውና አንድነታቸው መጠናከር የሚችሉት ግን አርዓያነቱ ከመሪው ፓርቲ ሲጀምር ነው፡፡ የአገራችን ሕዝቦች በእስከ ዛሬው ትግላቸው ወድቀው እየተነሱ፣ ያበበውን የዴሞክራሲ ጅምር መጠናከር የሚችሉትም በዚሁ መንገድ ነው፡፡ እንደ ዜጋ መንግሥትን አምነውና አደራ ሰጥተውም አገርን መጠበቅና የጋራ ጥቅምን ማስከበር ሲችሉም ነው፡፡ ለሁሉም ነገር ግን ኦሊጋርኪነት ይወገድልን፡፡

ከአዘጋጁ፡-   ጽሑፉ የጸሐፊውን አመለካከት ብቻ የሚያንፀባርቅ መሆኑን እንገልጻለን፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

[ክቡር ሚኒስትሩ በመንግሥት የሚታወጁ ንቅናቄዎችን በተመለከተ ባለቤታቸው ለሚያነሱት ጥያቄ ምላሽ ለመስጠት እየሞከሩ ነው]

እኔ ምልህ? እ... ዛሬ ደግሞ ምን ልትይ ነው? ንቅናቄዎችን አላበዙባችሁም? የምን ንቅናቄ? በመንግሥት...

የመንግሥት የ2017 ዓ.ም በጀትና የሚነሱ ጥያቄዎች

የ2017 ዓመት የመንግሥት ረቂቅ በጀት ባለፈው ሳምንት መገባደጃ ለሚኒስትሮች...

ከፖለቲካ አባልነትና ከባንክ ድርሻ ነፃ የሆኑ ቦርድ ዳይሬክተሮችን ያካተተው ብሔራዊ ባንክ ያዘጋጃቸው ረቂቅ አዋጅና መመርያዎች

የኢትዮጵያ የብሔራዊ ባንክ የፋይናንስ ተቋማትን የተመለከቱት ድንጋጌዎችንና የባንክ ማቋቋሚያ...

የልምድ ልውውጥ!

እነሆ መንገድ ከቦሌ ሜክሲኮ። አንዱ እኮ ነው፣ ‹‹እንደ ሰሞኑ...