በዓለም አቀፍ ደረጃ የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ሰዎች ቁጥር ከፍተኛ ነው፡፡ የሕመሙ ተጠቂዎች በወላጆቻቸውም ሆነ በተለያዩ ችግሮች ከማኅበረሰቡ ሲገለሉ ይታያል፡፡ በተለይ የኦቲዝም ተጠቂዎች በሕክምና መዳን ስለማይችሉ ችግሩን ይበልጥ ያወሳስበዋል፡፡ ሆኖም በርካታ ሰዎችም የኦቲዝም እክል ኖሮባቸው በሙያቸው አንቱታን ማትረፍ ችለዋል፡፡ በአሁኑ ወቅት በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር ለመቅረፍና የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ሕፃናትን ከመደበኛ ተማሪ ጋር ተቀላቅለው እንዲማሩ ለማድረግ ሻምፒዮንስ አካዴሚ ትምህርት ቤት እየሠራ ይገኛል፡፡ ወ/ሮ መዓዛ መንክር የተቋሙ መሥራችና የአዕምሮ ሕክምና ባለሙያ ናቸው፡፡ የተቋሙን ሥራ በተመለከተ ተመስገን ተጋፋው አነጋግሯቸዋል፡፡
ሪፖርተር፡- ሻምፒዮንስ አካዴሚ ትምህርት ቤት እንዴት ተመሠረተ?
ወ/ሮ መዓዛ፡- ሻምፒዮንስ አካዴሚ የተመሠረተው የዛሬ አሥራ አምስት ዓመታት አካባቢ ነው፡፡ ተቋሙ ከተመሠረተ ጊዜ ጀምሮ ሕፃናት ልጆችና ወላጆች ላይ በመሥራት ውጤታማ እየሆነ ነው፡፡ በተለይ የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር በመቀላቀል የአካቶ ትምህርት እንዲወስዱ እያደረገ ይገኛል፡፡ የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ሕፃናት በትምህርት ቤቱ ውስጥ የተሻለ ትምህርት እንዲያገኙ ለበርካታ አስተማሪዎች ሥልጠና እየሰጠን እንገኛለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ ከወላጆች ጋር በየጊዜው በመገናኘት ግንዛቤ እንዲያገኙ እያደረግን ነው፡፡ የኦቲዝም ተጠቂ የሆኑ ሕፃናት ልጆችንም ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ከመቀላቀላቸው በፊት ለብቻቸው ትምህርት ይሰጣቸዋል፡፡ በሒደትም በባህሪያቸው ላይ ለውጥ ሲታይ ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር እንዲቀላቀሉ ይደረጋል፡፡ ኢትዮጵያ ውስጥ አብዛኛውን ጊዜ የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት የትምህርት ዕድል ባለማግኘታቸው የተነሳ ሜዳ ላይ ቀርተዋል፡፡ እነዚህንም ልጆች ለመታደግና በዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ተቋሙ እየሠራ ነው፡፡ በአሁኑ ወቅት በርካታ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ በማድረግ፣ ተስፋ ሰጪ ነገሮችን እያየን ነው፡፡ ተቋሙ የአዕምሮ እክል ያለባቸው ተማሪዎች ጤናማ ከሆኑት ጋር ተቀላቅለው መማር እንደሚችሉ ለማሳወቅ ምቹ ዕድሎችን እየፈጠረ ነው ማለት ይቻላል፡፡ በኢትዮጵያ እንዲህ ዓይነት ሥራዎችን መሥራት ከተቻለ፣ የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ልጆችን በቀላሉ መታደግ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- ተቋሙ ከተመሠረተ አሥራ አምስት ዓመታትን አስቆጥሯል፡፡ እስካሁን ምን ዓይነት አገልግሎቶችን ሰጥታችኋል?
ወ/ሮ መዓዛ፡- በኢትዮጵያ ልዩ ፍላጎት ወይም የአዕምሮ እክል ችግር ያለባቸው ልጆች እንደ መጥፎ፣ አሊያም ደግም ትልቅ ችግር ሆነው መታየታቸው ሥራችን ላይ እንቅፋት ሆኖብናል፡፡ ተቋሙም እነዚህን ሁሉ ችግሮች በማስቀረት ተስፋ የሚታይበት ሥራ እየሠራ ይገኛል፡፡ እስካሁንም ከፍተኛ ቁጥር ያላቸውን የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት በመቀበል የትምህርት አገልግሎት እንዲያገኙ ማድረግ ችለናል፡፡ የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ባህሪያቸው የተለየ ስለሆነ፣ እነሱን ለመንከባከብ በርካታ ወላጆች ሲቸገሩ ይታያል፡፡ ወላጆች ያሉባቸውን ችግሮ ለማቃለል ተቋሙ ውጤታማ ሥራዎችን መሥራት ችሏል፡፡ መደበኛ ተማሪዎችን የኦቲዝም ተጠቂ ከሆኑ ሕፃናት ልጆች ቀላቅሎ ለማስተማር ትንሽ ከበድ ይላል፡፡ ይሁን እንጂ ያሉትን ችግሮች ለመቅረፍ ተቋሙ ለረዥም ጊዜ ያህል ለብቻቸው እንዲማሩ በማድረግና ለውጥ ሲያሳዩ ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር እየቀላቀለ በማስተማር ላይ ይገኛል፡፡ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆች መማር እንደሚችሉ እንዲያውቁ ለበርካታ ወላጆች ግንዛቤ እየሰጠን ነው፡፡
ሪፖርተር፡- በሥራችሁ ላይ ምን ዓይነት ችግር ገጥሟችኋል?
ወ/ሮ መዓዛ፡- የመጀመርያውና ዋነኛ ችግር የሆነብን ማኅበረሰቡ ላይ የሚታየው የግንዛቤ እጥረት ነው፡፡ አብዛኛው ሰው ልዩ ድጋፍ የሚፈልጉ ሕፃናት ለብቻቸው ወይም ተለይተው መማር እንዳለባቸው ስለሚያምን፣ በትንሹም ቢሆን ሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ ጤናማ ልጆች ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው የኦቲዝም ተጠቂ ከሆኑ ሕፃናት ጋር እንዲማሩ አለመፈለጋቸው ችግር ሆኖብናል፡፡ ይሁን እንጂ እነዚህን ችግሮች ለማለፍ ተቋሙ ለወላጆቻቸው ግንዛቤ እየሰጠ ይገኛል፡፡ በተለይ ጤናማ ልጆች ያላቸው ወላጆች ልጆቻቸው ከኦቲዝም ተጠቂ ልጆች ጋር ሲማሩ ሕመሙ ይተላለፍባቸዋል ብለው ስለሚያምኑ፣ በዘርፉ ላይ የሚታየውን ችግር አባብሰውብናል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በዘርፍ ላይ የሠለጠነ ባለሙያ ባለመኖሩ የተነሳ የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ለመማር ተቸግረዋል፡፡ ተቋሙ የራሱ የቦታ ይዞታ ስለሌለውም በሥራችን ላይ እንቅፋት ፈጥሮብናል፡፡ በቤት ኪራይ ውስጥ ሆኖ ሥራ ሲሠራ ይከብዳል፡፡ በርካታ የኦቲዝም ተጠቂ ልጆችን ለመድረስ ተቋሙ ቢፈልግም፣ የምንሠራው በቤት ኪራይ ውስጥ በመሆኑ ተፅዕኖ አሳድሮብናል፡፡ ነገር ግን መንግሥት የቦታ ይዞታ ቢያመቻችልን ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ ልጆችን በር በማንኳኳት ተደራሽ መሆን ይቻላል፡፡ ይህንን ማድረግ ልጆቹ ከፍተኛ ቦታ እንዲደርሱ መንገድ ይከፍታል፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በየዓመቱ የተለያዩ መድረኮችን በመፍጠር የግንዛቤ ሥራ የምንሠራ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናትን በምን ዓይነት መልኩ ነው የምትቀበሉት? የዕድሜያቸው ሁኔታስ?
ወ/ሮ መዓዛ፡- የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናትን የምንቀበለው ከወላጆች ጋር ግንኙነት በመፍጠር ነው፡፡ ተቋሙ የሚሠራው ሕፃናት ልጆች ላይ በመሆኑ፣ ዕድሜያቸው ከሁለት እስከ አራት ዓመት የዕድሜ ክልል ላይ ያሉ ሕፃናትን እናስተናግዳለን፡፡ ወላጆች ትዕግሥት ኖሯቸው በትጋት እንዲሠሩ ተቋሙ ክትትል ያደርጋል፡፡ ከዚህ ውጪም ግንዛቤዎችን ይፈጥራል፡፡ ይህም ከሆነ በርካታ የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናትን መታደግ ይቻላል፡፡
ሪፖርተር፡- የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ሲማሩ ያጋጠማችሁ ችግር ካለ ቢነግሩን? በቂ የሆኑ ሙያተኞችስ አሏችሁ?
ወ/ሮ መዓዛ፡- የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር ከመቀላቀላችን በፊት በባለሙያ ለብቻቸው እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ ይህንንም ለማድረግ ረዥም ጊዜ እንፈጃለን፡፡ በሌላ በኩል ደግሞ በአካዴሚው ውስጥ የሚያስተምሩ መምህራንን ሥልጠና በመስጠት የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር እንዲማሩ ምቹ ሁኔታዎችን ፈጥረናል፡፡ ለመምህራንም ሥልጠናውን የምሰጠው ራሴ ነኝ፡፡ ይህንን አድርገን የኦቲዝም ተጠቂዎችም ከመደበኛ ተማሪዎች ጋር በማቆራኘት እንዲማሩ ይደረጋል፡፡ እነዚህም ሕፃናት ልጆች ከመደበኛው ተማሪዎች ጋር መግባባት ሲፈጥሩ ወደ አካቶ ትምህርት ውስጥ በቀላሉ የሚቀላቀሉ ይሆናል፡፡
ሪፖርተር፡- በቀጣይ ምን ለመሥራት አስባችኋል?
ወ/ሮ መዓዛ፡- በቀጣይ የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናትን ችግሮችን በመረዳት ወደ ተሻለ ደረጃ የሚደርሱበትን አጋጣሚ የምንፈጥር ይሆናል፡፡ ከዚሁ ጎን ለጎን ደግሞ ወላጆች ግንዛቤ እንዲያገኙ በማድረግ ልጆቻቸውን አካቶ ትምህርት ወደሚሰጡ ትምህርት ቤቶች እንዲልኩ ለማድረግ ዕቅድ ይዘናል፡፡ ችግሩ ከፍተኛ በመሆኑ ከአርቲስቶችና ከሌሎች ታዋቂ ሰዎች ጋር በመተባበር አገር አቀፍ እንቅስቃሴዎችን ለማድረግ ዝግጅት ጀምረናል፡፡ መንግሥትም ይህንን ችግር በማጤን የኦቲዝም ተጠቂ ሕፃናት ትምህርት የሚማሩበትን ቦታ ማመቻቸት ይኖርበታል፡፡ እነዚህን ሁሉ ሥራዎች መሥራት ከተቻለ ዘርፉ ላይ ያሉትን ችግሮች በተወሰነ መልኩ ማስወገድ ይቻላል፡፡