- ‹‹ታሪኩን፣ አመጣጡንና ባህሉን የማያውቅ ሕዝብ ሥር እንደሌለው ዛፍ ነው››
ማርከስ ጋርቬይ
- ‹‹ኑ ባህላችንን እናወድስ፣ ኑ ስለ ቅርሶቻችን እናውራ፣ ኑ ማንነታችንን እንጠብቅ››
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለአደራ ማኅበር
በየዓመቱ ሚያዝያ 10 ቀን (ኤፕሪል 18) የሚከበረው የዓለም ቅርስ ቀን ትናንትና በዓለም ዙርያ ተከብሮ ውሏል፡፡ ዕለቱ የመታሰቢያ ሐውልቶችና የቅርስ ቦታዎች ቀን በመባልም ይታወቃል። የ2023 መሪ ቃል ‘የቅርሶች ለውጥ’ ሆኖ የአካባቢ ማኅበረሰቦችን ለመደገፍ፣ ባህላዊ ዕውቀትን ለማክበር፣ የቅርስና የአየር ንብረት ለውጥ መስተጋብር ላይ ያተኮረ ነው።
ያለፈውን ታሪክ ለመረዳትና መጻዒውን ሕይወት መልክ ለማስያዝ ቅርሶችን መጠበቅ አስፈላጊ ነው። በዓለም ቅርስ ቀን፣ ምድራችንን ፀንታ እንድትቆም ያደረጉትን የበለፀጉ ብዝኃ ባህሎች፣ ታሪኮችና ልማዶችንም እናከብራለን ይላል ዓለም አቀፉ ተቋም።
ዩኔስኮ እ.ኤ.አ. ከ1983 ጀምሮ ኤፕሪል 18 (ሚያዝያ 10 ቀን) የዓለም ቅርስ ቀን ብሎ በአባል አገሮቹ እያከበረው ይገኛል፡፡ የታሪክና የባህል አካል ስለሆኑት ሐውልቶችና ሌሎች ቦታዎች እንዲሁም ጥንታዊ ቤቶችን በተመለከተ ለሕዝብ ስለ ቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ግንዛቤ ማስጨበጫ መሰናዶዎች፣ ጉብኝቶችና ተያያዥ ሥራዎች ይከናወንበታል፡፡
የዘንድሮው “የቅርሶች ለውጥ” መሪ ቃል፡ በምንቀየርበት በምንለወጥበት ጊዜ ቅርሶቻችንም ነባራዊ ሁኔታዎችን የሚያንፀባርቁ መሆን እንዳለባቸው ያስታውሰናል። የጋራ ቅርሶቻችንን ለመጪው ትውልድ የመጠበቅን አስፈላጊነት ለመገንዘብ እንድንሰባሰብ ያደርገናል። ስለ ልዩ ልዩ ባህላዊ ውርሶቻችን በማወቅና ዋጋ በመስጠት፣ እርስ በርሳችን የበለጠ ግንዛቤን በማግኘትና አድናቆትን ማዳበር እንችላለን።
የህንድ የቅርስ ተቋም የትናንትናውን የዓለም ቅርስ ቀን ምክንያት አድርጎ፣ መልዕክቱን ያስተላለፈው ዕውቁ ጃማይካዊ የፓን አፍሪካን አቀንቃኝ ማርከስ ጋርቬይ የተናገረውን ‹‹ታሪኩን፣ አመጣጡንና ባህሉን የማያውቅ ሕዝብ ሥር እንደሌለው ዛፍ ነው፤›› በማለት ነበር፡፡
በዘንድሮው የዓለም ቅርስ ቀን በመሪ ቃሉ መሠረት ከቀደምት የወረስናቸውን ቅርሶቻችን ለመጠበቅና ለመንከባከብ ቃል እንግባ ሲል ያከለው ተቋሙ፣ የሕንድን የበለፀገ ባህልና ብዝኃነት የሚገልጹ፣ በዩኔስኮ ጥላ ሥር ያሉ የዓለም ቅርስ ይዞታዎችን ጨምሮ ከ3691 በላይ ጥብቅ ሥፍራዎችና ቦታዎች አሏት ብሏል። ‹‹ባህላችንን ለመንከባከብና ለመጠበቅ በራሳችን እንወስን፣ ለትውልድም በኩራት እናስተላልፍ፤›› በማለትም አንፀባርቋል።
ኢትዮጵያ የዘለለችው የዓለም ቅርስ ቀን
በምሕፃሩ ዩኔስኮ ተብሎ የሚጠራው ዓለም አቀፉ የባህል ተቋም፣ በየአገሩ የሚገኙትን ጥንታዊ ቅርሶች ተገቢው ክብካቤ እንዲያገኙ፣ ይበልጥም እንዲጠበቁ የሚያነቃቃ የኅብረተሰቡ ግንዛቤ እንዲሰፋ ለማድረግ በየዓመቱ ሚያዝያ 10 የዓለም ቅርስ ቀን ተብሎ በአባል አገሮቹ እንዲከበር ደንግጓል፡፡
ስብጥር ባህላዊ ገጽታዎችን፣ የባህል ብዝኃነትን ሁሉም እንዲያከብሩ ለማድረግ በተመሠረተው የዓለም ቅርስ ቀን አማካይነት በተለይ ወጣቱ ትውልድ ቅርስና ውርሱን አውቆ እንዲዘልቅ ለማድረግም ታልሞበታል፡፡
ክብረ በዓሉ የታሪክና የባህል አካል ስለሆኑት ሐውልቶችና ሌሎች ቦታዎች እንዲሁም ጥንታዊ ቤቶችን በተመለከተ ለኅብረተሰቡ ስለ ቅርስ ጥበቃና ክብካቤ ግንዛቤ ማስጨበጫ መሰናዶዎች፣ ጉብኝቶችና ተያያዥ ሥራዎች ይከናወንበታል፡፡
ይሁን እንጂ የዩኔስኮ አባል የሆነችው ኢትዮጵያ፣ የሚመለከተው መንግሥታዊ ተቋሟ በየዓመቱ ለምን እንደማይዘክር ጥያቄ የሚያነሱ ቁጥር ቀላል አይደለም፡፡
ከዓመታት በፊት የቅርስ ጥናትና ጥበቃ ባለሥልጣን በማኅበራዊ ትስስር ገጹ፣ ‹‹እንኳን በሚያዝያ 10 ለሚከበረው የዓለም ቅርስ ቀን በሰላም አደረሳችሁ፤ ቅርሶቻችንን በመጠበቅ፣ በማልማትና በማስተዋወቅ ከዘርፉ የሚገኘውን ታሪካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ እናሳድግ›› ከሚል መፈክር ባለፈ የተራመደበት ነገር አልተሰማም፡፡ ከዚህ በፊትም ጭምር፡፡
የኢትዮጵያ ቅርስ ባለሥልጣንን ማኅበራዊ ትስስር ገጽ የቃኘው ሪፖርተር እንደታዘበው፣ በቀዳሚ ልጥፉ ‹‹በ2015 የዘጠኝ ወር የዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ላይ ውይይት ተካሄደ›› ከሚል በስተቀር ስለ ቅርስ ቀን የተነፈሰው የለም፡፡ ሚኒስቴሩም በየዓመቱ የዓለም ቱሪዝም ቀንን እያከበረ፣ እንዴት የቅርስ ቀንን ለማክበርና ለማስከበር ሳይተጋ ቀረ የሚሉ ድምፆች ሚያዝያ በመጣ ቁጥር የሚሰሙ ናቸው፡፡
ሃቻምና ከኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር ጋር የዓለም ቅርስ ቀንን ያከበረው የአዲስ አበባ ባህል ኪነጥበብና ቱሪዝም ቢሮም ድምፁ አልተሰማም፡፡ በከተማዋ የሚገኙ ቅርሶችን በባለቤትነት ከመጠበቅና ከመንከባከብ አንፃር ከመሥራት ባለፈ ኅብረተሰቡ ስለቅርሶች ግንዛቤ እንዲኖረው ለማስቻል በር ከፋች የሆነውን የቅርስ ቀን አለማሰቡ ምነው ተብሎበታል፡፡
ይሁን እንጂ በፎቶግራፍ ዓውደ ርዕይ፣ ታሪካዊ ቅርሶችን በማስጎብኘትና በማስገንዘቢያ መድረኮች የሚያከብረው መንግሥታዊ ያልሆነው የኢትዮጵያ ቅርስ ባለ አደራ ማኅበር፣ ዘንድሮ በማኅበራዊ ትስስር ገጹ የዓለም ቅርስ ቀንን በማስገንዘቢያ መጣጥፉ ዘክሯል፡፡
‹‹ቅርስ ያለው ሁሉም አለው›› የሚለው ባለ አደራ ማኅበሩ፣ ‹‹ኑ ታሪክን እንዘክር፣ ኑ ባህላችንን እናወድስ፣ ኑ ስለ ቅርሶቻችን እናውራ፣ ኑ ማንነታችንን እንጠብቅ፣ ኑ የቀደሙ አባቶቻችንን እናመስግን›› የዓለም ቅርስ ቀን በመጣ ቁጥር የሚያስተጋባው ነው፡፡
የሚያዝያ አሥሩን የዓለም ቅርስ ቀንን በአርምሞ የዘለሉት የአዲስ አበባና የፌዴራሉ ተቋማት፣ ሚያዝያ 27 ቀን (ሜይ 5) የሚከበረውን የአፍሪካ ቅርስ ቀንን ያስቡት ይሆን?!