Tuesday, July 23, 2024
- Advertisement -
- Advertisement -
ዓለምበሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ያመራ ይሆን?

በሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ያመራ ይሆን?

ቀን:

ሱዳንን ለ30 ዓመታት የመሯት የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር እ.ኤ.አ. በሚያዝያ 2019 በመፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ከተወገዱ በኋላ ሱዳናውያን በፈለጉት መሪ የመተዳደርም ሆነ ሰላም የማግኘት ዕድል አላገኙም፡፡

በሽር ከሥልጣን እንዲወርዱ ምሁራንን ጨምሮ የተለያዩ የሲቪል ማኅበረሰብ አባላት፣ የዴሞክራሲ አቀንቃኞችና ፖለቲከኞች እንዲሁም መከላከያው የተሳተፉበት አብዮት ቢካሄድም፣ ዛሬም ሱዳናውያን በሲቪል መንግሥት እንተዳደር የሚለው ጥያቄያቸው አልተመለሰም፡፡

በሽር ከሥልጣን ከተነሱ ማግሥት ጀምሮ በሱዳን መከላከያና በሲቪሎች  በኩል የነበረው ሽኩቻ፣ ሱዳን በሁለቱ ጥምረት እንድትመራ፣ ጥምር የሽግግር መንግሥቱም አጠቃላይ ምርጫ አድርጎ በሱዳን የሲቪል መንግሥት ሥልጣን እንዲቆጣጠር እንዲያደርግ ከስምምነት ተደርሶ የነበረ ቢሆንም አልተሳካም፡፡

በሱዳን የተቀሰቀሰው ግጭት ወደ እርስ በርስ ጦርነት ያመራ ይሆን? | Ethiopian Reporter | ሪፖርተር
የፈጥኖ ደራሽ ኃይል ሊቀመንበር ጄነራል ሃምዳን ዳጋሎ በ2019 ለደጋፊዎቻቸው ሰላምታ ሲሰጡ (ሮይተርስ)

የሽግግር መንግሥቱ ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት አብደላ ሃምዶክ በሱዳን ለውጥ ለማምጣት ጥረት ቢያደርጉም፣ አብሯቸው ከሚሠራው የሱዳን መከላከያ ጋር ስምምነት ባለመፈጠሩ፣ እሳቸውም በመከላከያውና በሱዳን ፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ትብብር እ.ኤ.አ. በጥቅምት 2021 መፈንቅለ መንግሥት እንደተደረገባቸው ይታወሳል፡፡

የሱዳን ፖለቲከኛ፣ የሱዳን ጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥና በሽግግር መንግሥቱ የመከላከያ ካውንስሉ ሊቀመንበር አብዱል ፈታህ አል ቡርሃን መፈንቅለ መንግሥቱን መርተው ሱዳንን በወታደራዊ አገዛዝ ሥር ማድረጋቸው ከርሟል፡፡ ካደረጉ በኋላ ሱዳንን በርካታ መለስተኛ ተቃውሞዎችን አስተናግዳለች፡፡

በነበሩ ሕዝባዊ ተቃውሞዎችም ቡርሃን ከሥልጣን ይውረዱ፣ ሲቪል የሽግግር መንግሥት ይቋቋም እንዲሁም በሱዳን በምርጫ የሚያሸንፍ ሲቪል ፓርቲ አገሪቱን ይግዛ የሚሉ አጀንዳዎችም ተነስተዋል፡፡

በአል ቡርሃን መፈንቅለ መንግሥት ከሥልጣን ተሰናብተው በሕዝቡ ተቃውሞ ወደ ሥልጣን የተመለሱትና በኋላም ‹‹በፈቃዴ ሥልጣን ለቅቄያለሁ›› ባሉት የቀድሞ የሱዳን ሽግግር መንግሥት ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሃምዶክ ጊዜም፣ መከላከያው ከጥምር የሽግግር መንግሥቱ እንዲወጣ የብዙ ፓርቲዎች ጥያቄም ነበር፡፡

‹‹የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት አልበሽርን ለመገርሰስ የተጀመረው አብዮታችን ግቡን እስኪመታ ድረስ ተቃውሟችን ይቀጥላል፤›› የሚሉት ሲቪሎች፣ ነፃነት፣ ሰላም፣ ፍትሕ፣ ሲቪል አገዛዝ እንዲሰፍንና መከላከያው ወደ ካምፑ እንዲገባ እንደሚፈልጉም ሲወተውቱ ከርመዋል፡፡ ሆኖም ለጥያቄያቸው የተሰጣቸው መልስ የደኅንነት አካላትና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች ሰለባ መሆን ነበር፡፡

በ2014 ዓ.ም. መገባደጃ ሰሞን በሱዳን የተቀሰቀሰውን ተቃውሞ ለመቀልበስ በአል ቡርሃን የሚመራው ወታደራዊ አገዛዝ ‹‹ማንኛውም የፖለቲካ ውይይት ውስጥ አንገባም፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተወያይተው ሲቪል የሽግግር መንግሥት ያቋቁሙ፤›› ብለው የነበረ ቢሆንም፣ ዛሬ ነገሮች ተቀይረዋል፡፡

ሲቪሎች አልበሽር ከሥልጣን ከተወገዱ ጊዜ ጀምሮ ሲጠይቁ የከረሙት ‹‹ዴሞክራሲያዊ ምርጫና ሲቪል አስተዳደር ይኑር›› የሚለው አጀንዳ ወደጎን ተትቶ፣ ሽኩቻው በጋራ ሲሠሩ በነበሩት ወታደራዊ ክፍሎች መካከል ሆኗል፡፡

የሱዳን መከላከያን በሚመሩት የሱዳን ሉዓላዊ ምክር ቤት ሊቀመንበር ጀነራል አብዱል ፈታህ አል ቡርሃንና ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን በሚመሩትና ሄሜቲ በሚል ስማቸው በሚታወቁት ጀነራል መሐመድ ሃምዳን ዳጋሎ መካከል ሚያዝያ 7 ቀን 2015 ዓ.ም. የተጀመረው ግጭት ሱዳንን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ሊያመራት ይችላል ተብሏል፡፡

በዳርፉር ግጭት በጦርነት በመሳተፍ የሚተዋወቁት ወታደራዊ አመራሮቹ፣ የሚመሩትን የወታደር ኃይል ይዘው ወደ ጦርነት ከመግባታቸው በፊት የሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት፣ 100 ሺሕ ያህል አባላት ያሉት ፈጥኖ ደራሽ ኃያሉ ከመከላከያ ጋር እንዲዋሃድ ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ ይህ ዕውን ሳይሆን ወደግጭት ማምራታቸው ተዋጊዎቹን ብቻ ሳይሆን ንፁኃንንም ሰለባ አድርጓል፡፡ ግጭቱ ከተጀመረ ወዲህ ከ200 በላይ ሲቪሎች የተገደሉ ሲሆን፣ ተዋጊዎቹን ጨምሮ ከ1‚800 በላይ ሰዎች መገኘታቸውንም አይኒውስ ዘግቧል፡፡

የመከላከያና የፈጥኖ ደራሽ ኃይሎች የሚፋለሙበት ሥፍራ በሱዳን ዋና ከተማ ካርቱም ጭምር መሆኑ ግጭቱን አሳስቦታል፡፡ በካርቱም በተለይ በፕሬዚዳንታዊ ቤተ መንግሥት አቅራቢያ፣ በአገሪቱ ቴሌቪዥን ሕንፃ፣ በካርቱም ዓለም አቀፍ አየር ማረፊያ፣ በኦምዱራማን፣ በሰሜን ምዕራብ ካርቱም፣ በካርቱም ሰሜናዊ ክፍል በምትገኘው ባህሪ ከተማ በሁለቱ አካላት መካከል ውጊያ እየተካሄደ ነው፡፡

በቀይ ባህር ከተማዋ ፖርት ሱዳን በመጀመርያው ቀን ተኩስ ያልተሰማ ቢሆንም፣ ከሚያዝያ 8 ቀን 2015 ዓ.ም. ጀምሮ የተኩስ ልውውጥ መኖሩን አልጀዚራ ዘግቧል፡፡

እንደዘገባው ከሆነ፣ የአገሪቱ አየር ኃይል ነዋሪዎች በቤታቸው እንዲቀመጡ ያዘዘ ሲሆን፣ የፈጥኖ ደራሽ ኃይል እንቅስቃሴንም ይከታተላል፡፡ ሁለቱ የጦር አበጋዞች ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉን ከመከላከያው ለመቀላቀልና የሲቪል አስተዳደር እንዲመሠረት ተስማምተው የነበረ ቢሆንም፣ በመካከላቸው በተፈጠረ አለመግባባት በሱዳን የሲቪል አስተዳደር ለመመሥረት ተስፋ ሰጥቶ የነበረውንና ዓለም አቀፍ ድጋፍ የተቸረውን ስምምነት አስተጓጉሎታል፡፡

የሲቪል ማኀበረሰብ አባላት የተሳተፉበትና ከአራት ወራት በፊት የተደረሰው ይህ ስምምነት መደናቀፉንም አልጀዚራ አሥፍሯል፡፡ እ.ኤ.አ. በ2013 በፕሬዚዳንት ኦማር አል በሽር የሥልጣን ዘመን የተመሠረተው ፈጥኖ ደራሽ ኃይል፣ ከመከላከያው ጋር ፍጥጫ የገባው በ2021 የሽግግር መንግሥቱን በጋራ ካስወገዱ በኋላ ነው፡፡

ሁለቱ ቡድኖች አገሪቱን ለመቆጣጠር ሲፎካከሩም ከርመዋል፡፡ ከቅርብ ወራት ወዲህ በሁለቱ መካከል የተፈጠረው ሽኩቻም፣ ፈጥኖ ደራሽ ኃይሉ ወደመከላከያ በሚቀላቀልበትና ማን ይምራው በሚለው አካሄድ ላይ ስምምነት አለመደረሱ ነው፡፡

በሁለቱ የጦር አበጋዞች አለመስማማት የተፈጠረው ጦርነት፣ ሱዳንን ወደ እርስ በርስ ጦርነት ያመራታል?

ዘ ኮንቨርሴሽን እንዳሰፈረው፣ በአገሪቱ ያሉ የሲቪል ማኅበረሰብ ቡድኖች፣ ዓለም አቀፍ ተቋማትና አገሮች በሱዳን የተቀሰቀሰው ወታደራዊ ግጭት እንዲቆም ጥሪ ቢያቀርቡም፣ በቀላሉና በቅርቡ ሊሆን አይችልም፡፡

ተፋላሚዎች ወታደራዊ አቅም ያፈረጠው መሆናቸው ደግሞ ችግሩን ያጎላዋል፡፡ አሁን የተጀመረው ግጭት መስፋፋቱም ሱዳንን ማመሳቀልና መከራ ውስጥ መክተት ብቻ ሳይሆን፣ የጎረቤት አገሮችንም ያውካል፡፡ ይህንንም ፍራቻ በመዝጋት የመጀመርያዋ ሆናለች፡፡ ከሱዳን የሚያዋስናትን ድንበር ዘግታለች፡፡

በሱዳን አሁን የተከሰተው ግጭት የሚያደርሰው ጉዳት ከጀነራል ቡርሃንም ሆነ ከጀነራል ዳጋሎ የሥልጣን ፍላጎት በላይ ነው፡፡ ሁለቱ ጀነራሎች የሥልጣን እንጂ የርዕዮተ ዓለም አጀንዳ የላቸውም፡፡

ሁለቱ ለሥልጣን ሲዋጉ፣ ሲቪሎች ደግሞ በሲቪል መንግሥት እንዲመሩ ይፈልጋሉ፡፡ ዘ አይሪሽ ታይምስ እንደሚለው፣ ከሁለቱ ወታደራዊ አመራሮች አንዱ ካላሸነፈ ችግሩ የሚፈታ አይመስልም፡፡ ሁለቱም ኃይሎች የአንድ አገር ዜጎች ቢሆኑም፣ በሱዳን በገበሲ የእርስ በርስ ግጭቶች ተሳታፊ ናቸው፡፡ አሁን የገቡበት በጦር መሣሪያ የታገዘ ግጭት ደግሞ የሱዳንን ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ቀጣናውን ጭምር የሚያምስ፣ በሱዳን የከፋ የእርስ በርስ ጦርነት ሊያስነሳ የሚችል ነው፡፡

spot_img
- Advertisement -

ይመዝገቡ

spot_img

ተዛማጅ ጽሑፎች
ተዛማጅ

ኢትዮጵያዊ ማን ነው/ናት? ለምክክሩስ መግባባት አለን?

በደምስ ጫንያለው (ዶ/ር) የጽሑፉ መነሻ ዛሬ በአገራችን ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች ግጭቶችና...

ዴሞክራሲ ጫካ ውስጥ አይደገስም

በገነት ዓለሙ የዛሬ ሳምንት ባነሳሁት የኢሰመኮ ሪፖርት መነሻነትና በዚያም ምክንያት...

ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን የምትችለው መቼ ነው?

መድረኩ ጠንከር ያሉ የፖሊሲ ጉዳዮች የተነሱበት ነበር፡፡ ስለረሃብ፣ ስለምግብ፣...

ደረጃውን የጠበቀ ስታዲየም በሌላት አገር ዘመናዊ ስታዲየም እየገነቡ ያሉ ክልሎች

አዲሱ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ዘመናዊ ስታዲየም ለማስገንባት ከ500 ሚሊዮን...