በአዲስ አበበ ከተማ አስተዳደር ቂርቆስ ክፍለ ከተማ ወረዳ አራት ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት የሆኑት የዳቦ ፋብሪካና የቂርቆስ ፓርክ የበርካታ ዜጎችን ችግር የሚቀርፉ መሆናቸው ተገለጸ፡፡
ፕሮጀክቶቹ የተገነቡት በደቡብ ግሎባል ባንክና አቶ አየለ አርፍጮ በተባሉ በጎ ፈቃደኛ ባለሀብት ሲሆን፣ ፕሮጀክቶቹም በ90 ቀናት ውስጥ ተገንብተው ለአገልግሎት ክፍት መሆናቸውን ሚያዝያ 10 ቀን 2015 ዓ.ም. ተገልጿል፡፡
በቀን ከ300 ሺሕ እስከ 400 ሺሕ ዳቦና ኬክ የማምረት አቅም አለው የተባለው በረከት የዳቦና የኬክ ማምረቻ ፋበሪካ ለ120 ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥራልም ተብሏል፡፡
በተመሳሳይ በክፍለ ከተማው ቄራ አደባባይ አካባቢ የተገነባው የቂርቆስ ፓርክ በነዋሪዎች፣ በባለሀብቶችና በተቋማት ተሳትፎ መሆኑን የክፍለ ከተማው ሥራ አስፈጻሚ ብሩክ ከድር (ዶ/ር) ተናግረዋል፡፡
በሦስት ሺሕ ካሬ ሜትር ላይ ያረፈው ፓርኩ፣ ለከተማዋ ውበት ከመስጠቱም ባለፈ ለ100 ሰዎች የሥራ ዕድል የሚፈጥር መሆኑን አክለዋል፡፡