የዓለም ዕድሜ ጠገቡን የማራቶን ውድድር የአሜሪካዋ ከተማ ለማዘጋጀት ሽር ጉዱ ተጧጡፎ ነበር፡፡
ከተማዋ ለ127 ዓመታት የማራቶን ውድድር ስታሰናዳ ብትቆይም፣ ዘንድሮ ግን ድግሱ የከበዳት ይመስል ነበር፡፡ በርካታ ዕውቅ አትሌቶቹ በውድድሩ መካፈላቸው ከተረጋገጠ በኋላ፣ ከተማዋ በተመልካች እንዲሁም በተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች ተጨናንቃ ነበር፡፡ በተለይ የዓለም የማራቶን የፈጣን ሰዓት ባለቤቱ ኬንያዊው ኤሊዩድ ሉድ ኪፕቾጌ እንደሚሳተፍ ከተረጋገጠ በኋላ በከተማ ጥቁር እንግዳ የመጣ ይመስል ደምቆ ነበር፡፡
እ.ኤ.አ. 2013 117ኛውን የማራቶን ውድድር ያስተናገደችው ቦስተን፣ በውድድሩ መጠናቀቂያ የቦምብ ፍንዳታ ተሰማ፡፡ በአገር ውስጥ አሸባሪዎች በቤት ውስጥ የተሠራው ቦምብ መወርወሩን ተከትሎ ሦስት ሰዎች ሲሞቱ በመቶዎች ቆስለዋል፡፡
አሥረኛ ዓመቱን የደፈነው ክስተቱ ዘንድሮ ተዘክሯል፡፡ ከተማዋ የዓለም ክብረ ወሰን ባለቤቱን ኪፕቾጌና ለመጀመርያ ጊዜ ለማስተናገድ መቻሏና የፍንዳታው አሥረኛ ዓመት የማስታወሻ መርሐ ግብር መከናወኑ፣ የማራቶን ውድድሩን ከምንጊዜውም በላይ ደማቅ አድርጎት ነበር፡፡
በመወዳደሪያው ሥፍራው በርካታ የከተማዋ ነዋሪ እንዲሁም በአሜሪካ የተለያዩ ከተሞች የሚኖሩ እንዲሁም ከተለያዩ አገሮች የታደሙ ተመልካቾች ቦስተን ከትመዋል፡፡ ውድድሩ ከመጀመሩ አንድ ሳምንት አስቀድሞ ተሳታፊ አትሌቶች ወደ ሥፍራው ማቅናታቸው ታውቋል፡፡ ከውድድሩ አስቀድሞ በርካታ መርሐ ግብሮች የተሰናዱ ሲሆን፣ አትሌቶች በተለያዩ አልባሳት አጊጠው ታይተዋል፡፡ ለአትሌቲክስ ትልቅ ሥፍራ እንደሚሰጡ የሚነገርላቸው የቦስተን ከተማ ነዋሪዎች የዓለም የማራቶን ፈርጦችን ማየት መቻላቸውን ያመኑ አይመስሉም፡፡
አትሌቶቹም በአድናቂዎቻቸው ተከበውና የፎቶ ሥነ ሥርዓት ላይ ሲታደሙ አምሽተዋል፡፡
የከተሞቹ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች የማሸነፍ ግምቱን ሙሉ በሙሉ ለዓለም የፈጣን ሰዓት ባለቤቱ ኬኒያዊ ኪፕቾጌ ሰጥተዋል፡፡
የአብዛኛው ሚዲያ አስተያየትና ትንተና ‹‹አትሌቱ የራሱን ሰዓት በስንት ደቂቃ ያሻሽላል?›› የሚለው ላይ ያዘነበለ ነበር፡፡
በውድድሩ ከአራት ጊዜ በላይ መሳተፍ የቻለውን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮናው ሌሊሳ ዴሲሳ፣ የለንደን ማራቶን አሸናፊው ሹራ ኪታታን ጨምሮ በርካታ አትሌቶች በርቀቱ ላይ ትልቅ ግምት አግኝተው ነበር፡፡
በታላላቅ ማራቶኖች ላይ በመሳተፍ ገናና ስም ካላቸው የኬንያ አትሌቶች መካከል ኤቫንስ ቺቤት፣ ቤንሰን ኪፕሪቶ፣ እንዲሁም አልበርት ኮሪር ከተጠባቂዎች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡
ለአትሌቶች እምብዛም አመቺ ያልሆነው ፈታኙ የቦስተን ቁልቁለታማና ዳገታማ የውድድር ርቀት፣ ኢትዮጵያዊቷ የኦሪገን ዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የወርቅ ሜዳሊያ ባለቤቷ ጎተይቶም ገብረ ሥላሴ፣ አባባል የሻነህ፣ ሕይወት ገብረ ማርያም ከፍተኛ ግምት ካገኙ ኢትዮጵውያት አትሌቶች መካከል ነበሩ፡፡
ሆኖም የሁሉም ተመልካቾች ዓይን የሁለት ጊዜ የኦሊምፒክ ሻምፒዮኑ ኪፕቾጌ ላይ ያነጣጠረ ብቻ ነበር፡፡
በአንፃሩ ያለፉትን ታላላቅ ሁለት የማራቶን ውድድሮችን ማሸነፍ የቻለውና የ2022 የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ኢቫንስ ቼቤት ልምዱን ተጠቅሞ ዘንድሮም ለሁለተኛ ጊዜ ማሸነፍ ችሏል፡፡
ኪፕቾጌ 1፡02፡19 ከሌሎች ዘጠኝ አትሌቶች ጋር ሆኖ ሲመራ ቢቆይም፣ በውድድሩ በዝናብ፣ በንፋስ እንዲሁም ሙቀት የታጀበ በመሆኑ ኪፕቾጌ ወደ ኋላ ሲቀር ተስተውሏል፡፡
የውድድሩ ክስተት የነበረውና በአትሌቲክሱ እምብዛም ከማትታወቀው ታንዛንያ የተገኘው ጌይ ጋብሬሄል፣ ከኬንያዊው ኢቫንስ ጋር እግር በእግር ተያይዘው ተነጠሉ፡፡
ዘንድሮ ጥሩ የውድድር ጊዜ ያሳለፈውና የኒውዮርክ ማራቶን እንዲሁም የዓምናው የቦስተን ማራቶን አሸናፊ ኬንያዊው ኢቫንስ 2፡05፡54 በመግባት ለሁለት ተከታታይ ዓመታት የቦስተን ማራቶን አሸነፈ፡፡
ታንዛኒያዊው ጌይ 2፡06፡04 ሁለተኛ ሆኖ ሲያጠናቅቅ፣ ኪፕሪቶ 2፡06፡06 ሦስተኛ ደረጃ በመያዝ አጠናቋል፡፡
ከፍተኛ ግምት ተሰጥቶት የነበረው ኪፕቾጌ 2፡09፡23 ስድስተኛ ደረጃ ይዞ አጠናቋል፡፡ የሚረታ የሚመስል የነበረው ኪፕቾጌ በዕለቱ የነበረው የአየር ንብረት ሁኔታ ሳይፈትነው እንዳልቀረ ተገልጿል፡፡
‹‹ስኖር የሚያጋጥሙኝን ፈተናዎች እስከ መጨረሻው እጋፈጣቸዋለሁ፡፡ ዛሬ ለእኔ ከባዱ ቀን ነበር፡፡ በተቻለኝ መጠን ለመግፋት ሞክሬያለሁ፡፡ ግን አንዳንዴ መግፋት ከሚቻለው በላይ ሲያጋጥም መቀበል ግድ ይላል፤›› በማለት የዓለም የማራቶን የክብረ ወሰን ባለቤቱ ኤሊዩድ ኪፕቾጌ አስተያየቱን ሰጥቷል፡፡
የአትሌቱን ያልተጠበቀ ውጤት ተከትሎ በርካታ ባለሙያዎች የራሳቸውን መላ ምት የሰጡ ሲሆን፣ ኪፕቾጌ በቦስተን የተቻለውን ማድረጉና ውድድሩን ሳያቋርጥ ማጠናቀቅ በራሱ ትልቅ ድል መሆኑን መስክረዋል፡፡
ሦስተኛ ደረጃን ይዞ ያጠናቀቀው ቤንሰን በበኩሉ ውድድሩ ጥሩ እንደሆነ ገልጾ፣ የአየር ንብረቱ ግን አትሌቶችን ሲፈትን እንደነበረ አስታውሷል፡፡
‹‹ሁሉም አትሌት ከአየር ንብረቱ ጋር ትግል ሲያደርግ ነበር፡፡ ሁላችንም የአቅማችንን ሞክረናል፤›› ሲል ቤንሰን ከውድድር በኋላ አስተያየቱን ለሚዲያ ሰጥቷል፡፡ በሌላው ተጠባቂ የሴቶች ማራቶን የትራክ ፈርጥ ኬንያዊቷ ሔለን ኦቢሪ የመጀመርያውን የማራቶን ውድድር ማሸነፍ ችላለች፡፡
ሔለን ለሁለተኛ ጊዜ በተሳተፈችበት የማራቶን ውድድር 2፡21፡38 በመግባት ድል አድርጋለች፡፡
ኢትዮጵያዊቷ አማኔ ቦሪሶ በ2፡21፡50 ሁለተኛ ደረጃ ስትይዝ፣ አባበል የሻነህ በ2፡22፡00 አራተኛ ወጥታለች፡፡
በውድድሩ የማሸነፍ ግምት የተሰጣት ጎተይቶም 2፡24፡34 አሥረኛ ደረጃ አጠናቃለች፡፡
በአንድ ላይ ታጭቀው ሲሮጡ የነበሩ እንስቶቹ ስብስብ ከ25 ኪሎ ሜትር በኋላ እየተበታተኑ ሄደው፣ እስከ 40ኛው ኪሎ ሜትር ድረስ ኦቢሪ፣ አማኔ እንዲሁም አባበል እግር በእግር ተከታትለው ሲያመሩ ነበር፡፡
በማጠናቀቂያ ርቀት ሔለን በ5,000 እና 10 ሺሕ ሜትር ላይ ያዳበረችውን አጨራረስ ተጠቅማ ጥሳቸው ገብታለች፡፡
ሔለን የመጀመርያ የማራቶን ተሳትፎዋን በኒውዮርክ ያደረገች ሲሆን፣ ስድስተኛ ደረጃ ነበር የወጣችው፡፡
ምንም እንኳን ኢትዮጵያዊያን አትሌቶች በተለይ በወንዶች ውጤታማ መሆን ባይቻልም ከዝናብ፣ ሙቀቱ፣ ዳገታማ እንዲሁም ቁልቁለታማ ታጅቦ የተከናወነው የቦስተን ማራቶን ለአትሌቲክስ ደምቆ የታየበት የውድድር ቦታ መሆኑን አረጋጠዋል፡፡
በዓለም በርካታ የማራቶን ውድድሮች ቢከናወኑም እንደ ቦስተን ለአትሌቲክስ የበለጠ ክብር የሰጠ የውድድር ከተማ የለም የሚሉ በርካቶች ናቸው፡፡
የቦስተን ማራቶን ድል የቀናቸው የኬንያ አትሌቶች፣ ይህንን ድል በ2024 የፓሪስ ኦሊምፒክ መድገም ፍላጎት እንዳላቸው ሐሳባቸውን ሰጥተዋል፡፡