Tuesday, October 3, 2023
- ማስታወቂያ -
- ማስታወቂያ -

የዓለም ባንክና የአይኤምኤፍ ድጋፍ ባይኖርም የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራሙ እንደሚቀጥል ተገለጸ

ተዛማጅ ፅሁፎች

ኢትዮጵያ ለምታካሂደው የኢኮኖሚ ማሻሻያ ፕሮግራም የዓለም ባንክና የዓለም ገንዘብ ድርጅት (አይኤምኤፍ) ድጋፍ ባይኖርም፣ መንግሥት በማሻሻያ ፕሮግራሙ እንደሚገፋበት የብሔራዊ ባንክ ገዥ አቶ ማሞ ምሕረቱ አስታወቁ፡፡

በአሜሪካ የሀርቫርድ ዩኒቨርሲቲ አካል የሆነው ኬኔዲ ስኩል ሚያዚያ 9 ቀን 2015 ዓ.ም. ባዘጋጀው መድረክ ላይ ተገኝተው በኢኮኖሚ ማሻሻያዎችና ፖሊሲ ለውጦች ላይ ንግግር ያደረጉት አቶ ማሞ፣ በኢትዮጵያ እየተካሄዱ ስላሉት የኢኮኖሚ ለውጦችና ዕቅዶች ሰፋ ያለ ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡

ከገለጻው በኋላ የዩኒቨርሲቲው ተማሪዎችና ማኅበረሰብ ላነሷቸው የተለያዩ ጥያቄዎች ማብራሪያ የሰጡት ገዥው፣ በዚህ ሳምንት መጀመርያ ላይ ስለተጠናቀቀው የዓለም ባንክና የዓለም የገንዘብ ድርጅት (International Monetary Fund – IMF) ፀደይ ስብሰባ (Spring Meeting)፣ እንዲሁም ተቋማቱ ኢትዮጵያ ለምታቅዳቸው የማሻሻያ ፕሮግራሞች በሚሰጡት ድጋፍ ላይም ጥያቄዎች ተነስተውላቸዋል፡፡

አቶ ማሞ ለጥያቄዎቹ በሰጡት ምላሽ፣ ወደ እነዚህ ተቋማት የሚኬደው የእነሱን ፕሮግራም ለመቀበል እንዳልሆነ፣ ነገር ግን አገሮች የራሳቸውን የኢኮኖሚ ማሻሻያ ተግባራዊ ለማድረግ እንዲያግዙ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

‹‹የኢኮኖሚ ማሻሻያው ፕሮግራም አገር በቀል ነው፣ እኛም የራሳችን ፕሮግራም ምን እንደሆነ እናውቃለን፤›› ሲሉ ስለኢትዮጵያ ሁኔታ የገለጹ ሲሆን፣ ኢትዮጵያ ስላሰበችው የማሻሻያ ፕሮግራም በዝርዝር አስረድተዋል፡፡ ማሻሻያ ከሚደረግባቸው ጉዳዮች መካከል ከፍተኛ የዕዳ ጫና፣ የኑሮ ውድነት፣ ያልተመጣጠነ የውጭ ምንዛሪ፣ እንዲሁም የብድርና የፋይናንስ ጉዳዮች ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ባዘጋጀቻቸው የማሻሻያ ፕሮግራሞች ማዕቀፍ ውስጥ ከእነዚህ ጉዳዮች ላይ ከሁለቱ ተቋማት ጋር እንደሚነጋገሩ፣ ማሻሻያዎቹን ተግባራዊ ለማድረግም የውጭ ፋይናንስ ድጋፍ እንደሚያስፈልግ አቶ ማሞ አስረድተዋል፡፡

ሆኖም ከተቋማቱ ድጋፍ ባይኖር እንኳን በፕሮግራሞቹ ላይ ‹‹መሥራታችንን እንቀጥላለን›› ያሉ ሲሆን፣ አክለውም ማሻሻያው ‹‹የእኛ የለውጥ ፕሮግራም ነው›› ብለዋል፡፡ በተጨማሪም በኢትዮጵያ ዕድገት የሚያስቀጥሉ ስትራቴጂዎችና ፖሊሲዎች ተፈላጊ መሆናቸውን፣ ለኢትዮጵያ የኢኮኖሚ ዕድገት ጠቃሚ ማሻሻያዎች እንደሚወጡ ገልጸዋል፡፡

መንግሥት ሁለተኛውን የአገር በቀል ኢኮኖሚ ማሻሻያ አጀንዳ አዘጋጅቶ በቅርቡ ይፋ ለማድረግ እየሠራ እንደሆነ የሚታወቅ ነው፡፡ ለዚሁ አጀንዳና ሌሎች ድጋፎችን ለማግኘት አቶ ማሞን ጨምሮ የገንዘብ ሚኒስትሩ አቶ አህመድ ሽዴና የጠቅላይ ሚኒስትሩ የፋይናንስ ዘርፍ አማካሪ አቶ ተክለ ወልድ አጥናፉን የያዘ የልዑካን ቡድን በሁለቱ ዓለም አቀፍ ተቋማት የሚዘጋጀው የፀደይ ስብሰባ ላይ ባለፈው ሳምንት ተካፍለዋል፡፡

ሚያዚያ 3 ቀን 2015 ዓ.ም. የስብሰባው አካል በነበረውና የዓለም ባንክ ባካሄደው የፓናል ውይይት ላይ ተሳታፊ የነበሩት አቶ አህመድ ሽዴ በውይይቱ ላይ፣ ከሁለቱ ተቋማት ጋር የማክሮ ኢኮኖሚ አለመጣጣምን ማስተካከል በተመለከተ አብረው እየሠሩ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡ ‹‹በራሳችን አገር በቀል ማሻሻያ ፕሮግራም አማካይነት ነው እየሠራን ያለነው፤›› ነበር ያሉት፡፡

spot_img
- Advertisement -spot_img

የ ጋዜጠኛው ሌሎች ፅሁፎች

- ማስታወቂያ -

በብዛት ከተነበቡ ፅሁፎች